Skip to main content
x
አገር የግለሰቦች መፈንጫ አትሁን!

አገር የግለሰቦች መፈንጫ አትሁን!

የሕግ የበላይነት ባለበት ማንም ሰው ከሕግ በላይ መሆን አይችልም፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ሕግ ሲጥሱና ራሳቸውን ከሕግ በላይ ሲያደርጉ ግን አገርን ያመሰቃቅላሉ፡፡ ሕገወጥነት እንዲስፋፋና ሥርዓተ አልበኝነት እንዲነግሥ ያደርጋሉ፡፡ በሕገ መንግሥት አማካይነት የቆመ ሥርዓት ሳይቀር ከማፈራረስ አይመለሱም፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን መንግሥት ሕግና ሥርዓት የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ኃላፊነት በማኅበረሰቡ ላይም የወደቀ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መልካቸውን እየቀያየሩ በሚከሰቱ ነውጦችና ግጭቶች ሳቢያ የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ እያራመዱ፣ የአገርንና የሕዝብን ህልውና የሚፈታተኑ በስፋት እየታዩ ነው፡፡ በዚህች ታሪካዊት አገርና ለዓለም ተምሳሌት በሆነው ሕዝብ ውስጥ ተወሽቀው ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ግጭት የሚቀሰቅሱ፣ አንዱን ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ለማነሳሳት መሰሪ ፕሮፓጋንዳ የሚረጩና አገሪቱን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ ለመክተት ያሰፈሰፉ ግለሰቦች በብዛት እየታዩ ነው፡፡ በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ መሽገው በሚረጩት መርዝ ይህንን የተከበረ ጨዋ ሕዝብ የማያባራ ግጭት ውስጥ እንዲገባ ሌት ተቀን እየቀሰቀሱ ነው፡፡ ሃይ ሊባሉ ይገባል፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ ክልሎች ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታ አለባቸው፡፡ ግለሰቦች ሲፈነጩ ዝም ብሎ ማየት ሕግ አለማስከበር ነው፡፡

ዘወትር እንደምንለው ኩሩውና አስተዋዩ ሕዝባችን ዘመናትን አብሮ የዘለቀው የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህልና የመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገድቡት ነው፡፡ ይልቁንም አብሮነቱን በማፅናት እየተጋባና እየተዋለደ ክፉውንና ደጉን ጊዜ አብሮ አሳልፏል፣ አሁንም አንድ ላይ አለ፡፡ ከምንም ነገር በላይ አገሩን በፍቅር የሚወደው የኢትዮጵያ ሕዝብ መቼም ቢሆን እርስ በርሱ ለጠብ ተፈላልጎ አያውቅም፡፡ በዚህ መንገድ የተመዘገበ ታሪክም የለውም፡፡ አሁን ከራሳቸውና ከቡድኖቻቸው ጥቅም በላይ ማሰብ የተሳናቸው ኃይሎች ይህንን ታሪካዊ ትስስር ለመበጣጠስ እያሴሩ ነው፡፡ የግለሰቦችን ግጭት የብሔር ገጽታ በማላበስ የጥፋት ረመጥ ይቆሰቁሳሉ፡፡ የእከሌ ብሔር የእከሌን ብሔር አጠቃ እያሉ መያዣ መጨበጫ የሌለው መረጃ እየለቀቁ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳ ይማስናሉ፡፡ በሩዋንዳ፣ በብሩንዲና በመሳሰሉ የዘር ፍጅት የተካሄደባቸው አገሮች ዓይነት ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ የሕዝቦችን ጤናማ ግንኙነት የሚደመስስ ኩሬ ውስጥ እየዋኙ ነው፡፡ ይህ በፍፁም ኢትዮጵያዊነትን የማይወክል ስለሆነ መወገዝ አለበት፡፡

ኢትዮጵያዊነት ጨዋነት፣ አስተዋይነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ጀግንነት፣ ተምሳሌታዊነት፣ ወዘተ. ነው፡፡ ይህ የመላው ኢትዮጵያውያን ድምር ውጤት ነው፡፡ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ፣ ከምዕራብ ጫፍ እስከ ምሥራቅ ጫፍ ድረስ በተዘረጋው ምድር ውስጥ የሚኖሩ ተመሳሳይ ሥነ ልቦና ያላቸው አትዮጵያውያን የሚገለጹበት ነው፡፡ አሁን ግን ሕዝብን በጅምላ የሚሳደቡ፣ የሚያዋርዱና ቂምና ጥላቻ የሚዘሩ ከንቱዎች እየተፈለፈሉ ነው፡፡ ከግለሰባዊና ቡድናዊ ጥቅም በላይ የሕዝብና የአገር ደኅንነት ቅንጣት ያህል ደንታ የማይሰጣቸው ከንቱዎች፣ በተቻለ መጠን ሕገወጥነት እንዲሰፍንና አገር እንድትጠፋ የሚጥሩ ይመስላሉ፡፡ በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ ሆነው ለአገር ቅን የሚያስቡ ሰዎችን በማጣጣል፣ አገር የሚያስተዳድሩ ወገኖችን በማዋረድና ክብራቸውን በመንካት አገሪቱን የአውሬ መፈንጫ ለማድረግ እየታገሉ ነው፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ የንፁኃን ደም ይፈሳል፡፡ አካላቸው ይጎድላል፡፡ ከቤት ንብረታቸው ይፈናቀላሉ፡፡ እጅግ በጣም የተከበረ ጨዋ ሕዝብ ውስጥ ይህ ዓይነቱ አስፀያፊ ድርጊት ሲፈጸም ግን ዝምታው በርትቷል፡፡ አሁን ግን በቃ መባል አለበት፡፡

ይህንን ሰቆቃ ማስቆም አለመቻል ነገ ተነገ ወዲያ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉና ለነገ ‹‹የጎበዝ አለቅነት›› እየተዘጋጁ ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ አርበኞች በሕግ መባል አለባቸው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ከለላ በማድረግ የጦርነት ነጋሪት መጎሰምም ሆነ፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት አገር ለማፍረስ የሚደረገው ሽኩቻ ማቆሚያ ያስፈልገዋል፡፡ በየቀኑ የሞት መርዶ በሚሰማበት አገር ውስጥ ‹‹የፈለግኩትን መናገር መብቴ ነው›› ተብሎ መቀለድ አይቻልም፡፡ ማንነታቸውን ደብቀው የጥፋት ቅስቀሳ ከሚያካሂዱት ጀምሮ፣ በአደባባይ ደረታቸውን ገልብጠው የሚንጎራደዱ ወገኖች ወደ ህሊናቸው ሊመለሱ ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን በሕግ አምላክ መባል አለባቸው፡፡ የብሔር ካባ ውስጥ በመደበቅ የጥፋትና የውድመት አጀንዳ እያራገቡ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ነው እያሉ ማሾፍ አይቻልም፡፡ የሕዝብን ሕይወትና የአገርን ህልውና አሳሳቢ ችግር ውስጥ እየከተቱ ማላገጥ ይሆናል፡፡ ወቅቱ አገርን የመታደጊያ እንጂ የማላገጫ አይደለም፡፡ በተቃራኒ ጎራ ጽንፈኛ አስተሳሰብ ውስጥ ተሁኖ ቁልቁለቱን መውረድ ከተጀመረ ወደ ላይ ለመመለስ አዳጋች ነው፡፡ የሚቀድመው የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው እሰጥ አገባ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ፋይዳ የለውም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገጽታውን እየቀያየረ የመጣው የአገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት አስፈሪ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም ሆነ የሚመራው መንግሥት አገር መስቀለኛ መንገድ ላይ ሆና ለሕዝብ በቂ የሆነ መረጃ እያቀረበ አይደለም፡፡ ከግራና ከቀኝ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎች ከሥርዓቱ ውስጥ ሳይቀር እየወጡ ሕዝቡን ግራ እያጋቡት ነው፡፡ በዚህ ላይ ሥርዓቱ ውስጥ ሆነው እርስ በርስ እየተናቆሩ ትርምስ የሚፈጥሩ ኃይሎች አሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው የሥርዓቱን ዝቅጠት ነው፡፡ ሕዝብ እየተደናበርኩ ነው፣ አገሬም አስፈሪ አዘቅት ውስጥ እየገባች ነው፣ መንግሥት ምን እያደረገ ነው፣ ወዘተ. ብሎ ሲጠይቅ ምላሽ የሚሰጥ የለም፡፡ ማዕከላዊ መንግሥቱ ከክልሎች ጋር ሆኖ አገርን አረጋግቶ ሕግ ማስከበር ሲገባው፣ በጠራራ ፀሐይ ዜጎች በነውጠኞች በአደባባይ ይገደላሉ፡፡ አጋጣሚውን ለግል ወይም ለቡድን ፍላጎት ሊጠቀሙበት ያሰፈሰፉ ኃይሎች ደግሞ የብሔር ካርድ ይመዙበታል፡፡ የንፁኃን ሕይወት በከንቱ እየጠፋና ሕዝብ እየተሳቀቀ ደንታ ቢሶች ይቆምሩበታል፡፡ ወጣቱን ትውልድ ስሜቱን እየኮረኮሩ ለሌላ በቀልና ሰቆቃ ያዘጋጁታል፡፡ እየሆነ ያለው ይኼው ነው፡፡ ይኼንን ዝቅጠት ማን ያስቁመው? የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በድፍረት ሊጋፈጡ ይገባል፡፡ በአገር ጉዳይ ቀልድ የለምና፡፡

አገር የሁሉም ዜጎቿ የጋራ ቤት መሆን የምትችለው በሰከነና በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ የገቡ ተቀናቃኝ ኃይሎችና ተከታዮቻቸው የመረጡት መንገድ ትርፉ ውድመት ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም የአገሪቱ ባለቤት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ከሕዝብ ፍላጎት እያፈነገጡ ለራስና ለቡድን ጥቅም ሲባል አገር ማተራመስ በታሪክም በትውልድም ያስጠይቃል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር መተዳደርን የመሰለ ፀጋ እያለ በኮርኳሪ መፈክሮች መተረማመስ ለዚህ ኩሩ ሕዝብ አይገባውም፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለዚህ ዓይነቱ አጥፊ ተግባር ተባባሪ መሆንም አይገባም፡፡ ይልቁንም በዚህች ታሪካዊት አገር እንዴት የሕግ የበላይነት ይስፈን? እንዴትስ በእኩልነትና በነፃነት መኖር የሚቻልበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገንባ? ካሁን በኋላ ወደ ጥፋት የሚወስዱ ብልሹ አሠራሮችና አስተሳሰቦች እንዴት ይስተካከሉ? ወዘተ. በማለት ሰላምና የጋራ መግባባት ያለበት ዓውድ ለመፍጠር መትጋት ይገባል፡፡ አገሪቱንም ሆነ ሕዝቧን እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሱ መሠረታዊ ችግሮች ተነቅሰው ወጥተው ዘላቂ መፍትሔ ማመንጨት ሲገባ፣ ብሔርተኝነትን እያራገቡ ሕዝቡ ውስጥ ጥላቻ መዝራት ታሪክ ይቅር የማይለው ኃጢያት ነው፡፡ ብሔር ላይ ብቻ በመንጠላጠል ሰብዓዊነትን ማጣጣል የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት አይደለም፡፡ በሕዝባችን ደም መነገድ ይቁም፡፡ አገሪቱም የግለሰቦች መፈንጫ አትሁን!