Skip to main content
x
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ማብራሪያ ተሰጠ

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ማብራሪያ ተሰጠ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ፣ ማክሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀ መድረክ ማብራሪያ ሰጡ፡፡

እንዲህ ያለው መድረክ ከዚህ ቀደም የተከናወነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ በነሐሴ ወር አጋማሽ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህኛው መድረክ ሚኒስትሩ  በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የድንበር አካባቢ ስለተከሰተው ግጭት፣ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ተከስቶ ስለነበረው አለመረጋጋት፣ አገሪቷ እያካሄደች ስላለችው የምርጫ ሥርዓት ማሻሻያና በቅርቡ ስለተወሰደው የብር ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህ መሠረት በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ፣ በግጭቱ ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መሞታቸውንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቸ ደግሞ መፈናቀላቸውን ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አስታውቀዋል፡፡

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ የመንግሥት የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ዕርምጃ በመውሰድ ግጭቱን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሥራ ማከናወናቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ በግጭቱ እጃቸው ያለበትን ወደ ሕግ ለማቅረብ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እያከናወነ የሚገኘውን የምርመራ ውጤት መንግሥት እየጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ጥፋተኞችን ለመለየት ምርመራ መጀመሩንም እንዲሁ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ግጭቱን ለመፍታት መንግሥት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን እንዳካሄደ ጠቁመው በተጨማሪም የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና በአጠቃላይ ነዋሪዎች ተሳታፊ የሆኑባቸው ስብሰባዎችና ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቀመዋል፡፡ መንግሥት የአካባቢውን ሰላምና መረጋጋት ወደ ነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ሥራዎች ማከናወኑን አስታውሰው በቅርቡም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ የሚሳተፉበት የሰላም ኮንፈረንስ በድሬዳዋ ከተማ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ሳቢያ በኦሮሚያ ክልል ወደ ስምንት አካባቢዎች ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበር ጠቁመው፣ በዚህም የተቃውሞ እንቅስቃሴ የስምንት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል፡፡

 በዚህ ግጭት ተሳትፈዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ዕርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ገልጸው፣ በዕርምጃውም የፖሊስና የመከላከያ አባላት በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አስታውቀዋል፡፡

የምርጫ ሥርዓቱ በተመለከተ እየተካሄደ ባለው የገዥው ፓርቲና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርድር፣ የአገሪቷ የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ እንዲሆን መስማማታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ውይይትና ድርድር በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ቡድኖችንና ሐሳቦችን አሳታፊ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ በመግለጽ፣ መንግሥት ከተቀዋሚ ፓርቲዎች ጋር የጀመረው ድርድር ቀጣይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የብርን የምንዛሪ መጠን ማሻሻያን በተመለከተ ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት በተደጋጋሚ የሚቀርብ ጥያቄ እንደነበር አስታውሰው፣ መንግሥት በዚህ ጊዜ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው የአገሪቷን የወጪ ንግድ ለማሳደግ በማቀድ እንደሆነ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከገለጻው በኋላ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለሚኒስትሩ አቅርበዋል፡፡ ከጥያቄዎቹ መካከልም የምርጫ ሥርዓቱ ማሻሻያ ተግባራዊ የሚደረገው መቼ ነው? ኢንተርኔት ለመጠቀም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለምን ይኖራሉ? የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ የምርጫ ሥርዓቱ ማሻሻያ አፈጻጸምን በተመለከተ ጉዳዩ በሒደት ላይ ያለ እንደሆነ ጠቁመው፣ ያለው የሕግ ማዕቀፍ ከተስተካከለ በኋላ መንግሥት ማሻሻያውን በተግባር ለማዋል ዝግጁና ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህ ከሕግ ማዕቀፍ ጋር የተያያዙት የአሠራር ሥርዓቶች ከተጠናቀቁ፣ በመጭው አገር አቀፍ ምርጫ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

ኢንተርኔትን በተመለከተ በአሁኑ ጊዜ ምንም ችግር የለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ምናልባት ከአቅም ጋር የተያያዘ ችግር ሊኖር እንደሚችል ጠቁመው አለ የተባለው ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ ለሚመለከተው አካል እንደሚያሳውቁ በመግለጽ፣ ስብሰባው ተጠናቋል፡፡