Skip to main content
x
የቁጠባ ትሩፋት

የቁጠባ ትሩፋት

ወይዘሮ ወርቅነሽ ይማም የአምስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ነዋሪነታቸውም በአማራ ክልል ሀብሩ ወረዳ መርሳ ከተማ ሲሆን፣ እሳቸውና በአጠቃላይ ቤተሰቡ የሚተዳደሩት በባለቤታቸው ወርሃዊ ደመወዝ ብቻ ነበር፡፡ ከቤት እንዲወጡ ባለቤታቸው አይፈቅዱላቸውም ነበር፡፡ በመካከሉ ግን ባለቤታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ በዚህም የተነሳ ቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ ጠፋ ሲሉ ወ/ሮ ወርቅነሽ ያስታውሳሉ፡፡ ከችግሩ ለመላቀቅ በኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ የሆኑ 19 ሴቶች ባቋቋሙት የራስ አገዝ ቡድን (ሰልፍ ኸልፕ) አባል ሆኑ፡፡

በሳምንት ሁለት ብር ይቆጥቡም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከ30 እስከ 100 ብር ለመቆጠብ መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡ ከቡድኑም ለመጀመርያ ጊዜ 2,000 ብር ተበድረው በጠላ ንግድ፣ በኋላም 30 ሺሕ ብር ተበድረው በጥራጥሬ ንግድ በመሠማራት የተበደሩትን ገንዘብ እየከፈሉ እስከ 20 ሺሕ ብር መቆጠብ እንደቻሉ ይገልጻሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ በወር ወደ 10 ሺሕ ብር የሚንቀሳቅስ የተለያዩ የጥራጥሬ ንግድ ሥራ ላይ በመሠማራት እተዳደራለሁ፡፡ ከሸማቾች ማኅበር ዘይት በመውሰድ በአካባቢው ለሚገኙ 23 ሰዎች አከፋፍላለሁ፡፡ ከራስ አገዝ ቡድኔ የመበደር ዕድሉን በመጠቀም ሁለት ልጆቼ የሙያ ሥልጠና ተከታትለው በግል ሥራ እንዲሠማሩ አድርጌአለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ለትልቁ ልጃቸው 25 ሺሕ ብር በመበደር የመንጃ ፈቃድ አውጥቶ በቅጥር ሾፌርነት ላይ እንደተሠማራ፣ ለሴቷ ልጃቸው ደግሞ 10 ሺሕ ብር በመበደር የሞባይል ጥገና ቤት እንደከፈቱላት፣ የመጨረሻ ልጃቸው ዘንድሮ ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ እንደሚመረቅ በአጠቃላይ በራስ አገዝ ቡድን ውስጥ ተሳታፊ በመሆናቸው በሕይወታቸው ለውጥ እንዳመጡ ወ/ሮ ወርቅነሽ ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ አሰቅቅ ጌታሁን የሁለት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ በአማራ ክልል ቡሬ ወረዳ ዋደራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከ19 የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ‹‹ጥሩ ጊዜ›› በሚል በ1999 ዓ.ም. ካቋቋሙት የራስ አገዝ ቡድን መጠቀማቸውን ይናገራሉ፡፡

ቡድኑ ሲመሠረት በየሳምንቱ ሃያ አምስት ሳንቲም ይቆጥቡ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ሳምንታዊ ቁጠባቸውን ወደ አምስት ብር በማሳደግ ጠቅላላ የቁጠባ ሒሳባቸው 1,500 ብር ደርሷል፡፡ ወይዘሮ አሰቅቅ ሥራ የጀመሩት ከቡድናቸው ለመጀመርያ ጊዜ በተበደሩት 300 ብር በቅመማ ቅመም ንግድ ነበር፡፡ ከቡድናቸው ተጨማሪ በመበደር የሳር ክዳን ቤታቸውን በ47 ቆርቆሮ ቤት መቀየራቸውን፣ በ12 ዓመታቸው ጋብቻ በመመሥረታቸው ምክንያት ያጡትን የትምህርት ዕድል፣ የተቀናጀ የጎልማሶች ተግባር ተኮር ትምህርት የመጨረሻ የሆነውን ደረጃ ሦስት  ማጠናቀቃቸውን አውግተውናል፡፡

አቶ ሙሉጌታ ገብሩ በኢትዮጵያ የራስ አገዝ ቡድን አሠራር ድርጅቶች ኅብረት (ኮንሰርቲየም) የቦርድ ስብሳቢ ናቸው፡፡ እንደ ሰብሳቢው፣ በተለያዩ ስድስት ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳድሮች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ 213,000 ሴቶች፣ 11,000 በሚደርሱ የራስ አገዝ ቡድኖች ተደራጅተው በጠቅላላው 125 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማፍራት ኑሯቸውን እያሻሻሉና ከድህነት ለመላቀቅ እየተጣጣሩ ናቸው፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በድሬዳዋ አስተዳደር ካውንስል የሚገኙት እነዚህ ሴቶች ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን ካፒታል ለማፍራት የቻሉት እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ በቡድን ተደራጅተው ከ25 ሳንቲም እስከ 50 ሳንቲም መቆጠብ በመቻላቸው ነው፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ተመሳሳይ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ያላቸውና በራሳቸው ጥረት ኑሯቸውን ለመለወጥ ደፋ ቀና የሚሉት እነዚሁ ሴቶች፣ በፈቃደኝነት ከመሠረቷቸው ቡድኖች ያለምንም መያዣና ውጣ ውረድ እየተበደሩ በንግድ ሥራ አገልግሎት ዘርፍ በከተማ ግብርና እየተሠማሩ ጥቅሞቻቸውን ማጎልበት ችለዋል፡፡ ከድህነት ውስጥም እየወጡ ናቸው፡፡ የተበደሩትንም ገንዘብ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ በመመለስ ካፒታላቸውን ማሳደግ መቻላቸውን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

በአንድ ቡድን ውስጥ የሚደራጁትም እርስ በርሳቸው የሚተዋወቁትና የሚግባቡ፤ ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ ሴቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የመጀመርያው የሴቶች ራስ አገዝ (ሰልፍ ኸልፕ) ቡድን የተመሠረተው በ1994 ዓ.ም. ከደብረ ብርሃን ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ጠባሴ አካባቢ ሲሆን፣ የተቋቋመውም ኪንደርኖትሄልፈ (ኬኤንኤች) በተባለ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት ነው፡፡

ከድህነት አረንቋ ለመውጣት ከሚያስችሉ ሥልቶች አንዱ የሆነው የሴቶች ራስ አገዝ አሠራር ባልተደረሰባቸው ክልሎች እንዲመሠረትና በተለይም የሴቶች ራስ አገዝ ቡድን በተጠነሰሰባት ደብረ ብርሃን ከተማ አገር አቀፍ የራስ አገዝ ቡድን የሥልጠና ልቀት ማዕከል ለማቋቋምም ታቅዷል፡፡

ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ፣ ቡድኖቹ ወደ ኅብረት ሥራ ከዛም ወደ ዩኒየን ለመሸጋገር የሚያስችላቸው አቅጣጫ መቀየስ እንዳለበትና ለዚህም ሚኒስቴሩ ከጎናቸው እንደሚቆም ተናግረዋል፡፡