Skip to main content
x

የአፄ ቴዎድሮስ ጦርነት አልባ ጦርነት

የኢትዮጵያን አንድነት ጠብቆ ለማቆየት ጉጉት የነበራቸው አፄ ቴዎድሮስ ወይም በቅጽል ስማቸው ‹‹መይሳው ካሳ››፣ ፍላጎታቸውንና እምነታቸውን እውን ለማድረግ አልፎ አልፎ የእኩይ ባህሪይ ተላብሰው የጨካኝነት ተግባር ይፈጽሙ እንደነበር እርግጥ ነው፡፡

በሠለጠነው ዓለም ምጡቅ የሥነ አዕምሮ ወይም የሳይኮሎጂ ዕውቀትና ሥልጠና ያላቸው ምሁራን አሉ፡፡ የሰውን ባህሪይ ከልጅነት ዕድገት ጀምሮ የኖረበትን ሕይወት በማጥናትና በመመርመር ለችግሩ መፍትሔ የሚሰጡ ባለሙያዎች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ የዚህ ምርምር ሊቃውንቶች በእኛም አገር ይኖራሉ፡፡ ትምህርቱን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ዘመናይ ባለሙያዎች አሉን፡፡ ሆኖም የአሁኑ መላምት እውነታ ግን ሌላ ነው፡፡

ከላይ የተገለጸው የሥነ አዕምሮ አጥኝዎች ጉዳይ፣ ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ምን  አገናኘው? ብለው የሚጠይቁ የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎች ይኖራሉና የምናቤን ዕይታ እነሆ ከዚህ በታች አቅርቤያለሁ፡፡

አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ በ1868 ዓ.ም. በጀግንነት ከእንግሊዝ አገር ከመጡ 32,000 ወታደሮች ጋር ተዋግተው ከመሞታቸው ስድስት ወር በፊት በአንዱ ቀን እንዲህ ሆነ፡-

አፄ ቴዎድሮስ ጋሻ ጃግሬዎቻቸውን በአስቸኳይ አስጠርተው ከሳቸው ጋር ለዓመታት ቤተ መንግሥት ውስጥ እየኖሩ ይሠሩ የነበሩና በኋላ ጠፍተው ሲኮበልሉ ተይዘው በእስር ያሉትን አምስት እስረኞች እንዲያመጧቸው አዘዙ፡፡ ቦታው መቅደላ አከባቢ፣ ጥልቅ ገደላማ ሥፍራ ነው፡፡ ተውኔቱ በገሃድ የሚታይበት ሰዓት ከቀኑ አምስት ሰዓት ተኩል ነበር፡፡ አፄው ከቆሙበት ቦታ ፊት ለፊት በግምት የአሥር ሜትር ርቀት ላይ፣ ከባህር ማዶ የመጡ 12 ነጮች ቆመዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለሃይማኖት፣ ለፖለቲካና ለስለላ ሥራ ወደ አገራችን ተልከው የመጡ ናቸው፡፡ አሁን ግን የአፄ ቴዎድሮስ እስረኞች ናቸው፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ከቅርብ ርቀት እንደ አንበሳ ተቆጥተው፣ ዓይናቸውን በቁጣ እስረኞቹ ላይ ተክለው፣ በእጃቸው ጎራዴ ይዘው ባማተሩ ቁጥር ላያቸው ያስፈራሉ፣ ያስደነግጣሉ፡፡ በትዕዛዛቸው መሠረትም አምስቱ እስረኞች አፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ቀረቡ፡፡ ንጉሡም ለስለስ ባለ አነጋገር ‹‹ምን በደልኳችሁ፣ ምን አጠፋሁ?›› አሉ፡፡ ወዲያው ግን በሚያስፈራና ድንጋጤ በሚፈጥር ግርማዊ ንግግር ‹‹ወገኖቼ ናችሁ፣ የቤተ መንግሥቴ አገልጋዮች ናችሁ፡፡ አምናችሁ ነበር፡፡ ከጠላቶቼ አብራችሁ በጠፍ በጨረቃ ሌሊት የጠፋችሁት ለምንድነው? እስቲ ንገሩኝ ችግራችሁን ልስማው?›› አሏቸው፡፡

‹‹ጌታዬ›› አለ አንደኛው እስረኛ አንገቱን አቀርቅሮ እጁን ወደ ላይ አደግድጎ እየፈራ፣ እየቸረ፤ ‹‹በወሬ ተፈተን ጃንሆይን በማስቀየማችን ጥፋተኞች ነን፡፡ ይቅርታ ይደረግልን፤›› በማለት ሲለምን ሌሎቹም ወደ ንጉሡ ለይቅርታ አጎነበሱ፡፡

 ‹‹ንሳ ስንቴ ነው ይቅርታ የማደርገው?›› በማለት ‹‹ውሰድልኝ እጅና እግራቸውን ቁረጥና ወደ ገደሉ ወርውርልኝ፤›› በማለት አዘዙ፡፡ በሚያስፈራራ ድምፅ በቆሙት በነጭ እስረኞች ላይ የድንጋጤና የመረበሽ ስሜት ለመፍጠር ያደረጉት ይመስላል፡፡

አምስቱ የንጉሡ አገልጋዮች መጀመርያ ሁለቱን ፍርደኞች ቀጥሎም ሦስቱን እየገፈተሩ ወስደው እጅና እግራቸውን ተራ በተራ በጎራዴ ቆርጠው ወደ ገደሉ ወረወሯቸው፡፡

አፄ ቴዎድሮስ በኩራት ከፊታቸው የቆሙትን የባህር ማዶ እስረኞች ይመለከቱ ነበር፡፡ ዓይናቸውን ያለወትሮው በልጥጠው በመደዳ ወደቆሙት እስረኞች ይመለከቱ ጀመር፡፡ አንገታቸውን ነቅነቅ ሲያደርጉ ወደ ገደሉ ተወርዋሪ ተረኞች እናንተ ናችሁ የሚሏቸው ይመስል ነበር፡፡ እስረኞቹም በተመለከቱት ፍርድና ንጉሡ በሚያሳዩት ሁኔታ በጣም ደንግጠዋል፡፡ ሆኖም የፍርድ ትዕይንቱ እንደተጠናቀቀ፣ እስረኞቹ ወደ ማረፊያቸው እንዲወሰዱ አዘዙ፡፡

ይህ ከተፈጸመ ከአንድ ሳምንት በኋላ የባህር ማዶ እስረኞቹ ለወዳጆቻቸውም ሆነ ለላኳቸው ኤምባሲዎች የተጻጻፏቸው የደብዳቤና የግል መልዕክቶች ‹‹በሰላይነት››  በተጠቆሙት ላይ ምርመራ ተደርጎባቸዋል፡፡ ደብዳቤያቸውና የቃል መልዕክቶቻቸው ተፈትሸዋል፡፡

ከመልዕክቱ ዋናው ግን ‹‹ወደ ኢትዮጵያ የተላኩበትን ግዳጅ ለመፈጸም አገሪቱ አስቸጋሪ መሆኗን ገልጸው፣ ካሁን በኋላ ለመሞት ካልሆነ በቀር ወደ ኢትዮጵያ ማንም ድርሽ እንዳይል፤›› የሚያሳስብ መልዕክት ያስተላልፉ ነበር፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ለፈለጉት ዓላማ መቅደላን ተውኔታዊ በሆነ መንገድ አገራቸውን ከውጭ ወራሪዎች ለመጠበቅ በጦርነት ብቻ ሳይሆን፣ በጥበባዊ እልቅና (Mastery) ባለው ትዕይንት ሒደት ታድገዋል አትሉም?

(ባጫ፣ ከአዲስ አበባ)