Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

አድርባይነትና አስመሳይነት የዘመናችን አሳፋሪ ክስተቶች ከሆኑ ሰነባብቷል ቢባል የተጋነነ አይመስለኝም፡፡ ይህንን ማስታወሻ ለመጻፍ ያነሳሳኝ በጣም ጨዋ በሚባለው ሕዝባችን ውስጥ የመሸጉት አድርባይነትና አስመሳይነት ወዴት እየወሰዱን ነው? የሚለው በጣም አሳሳቢ ስለሆነብኝ ነው፡፡ እኔ በቅርቡ የገጠመኝ ብዙ ቦታ ስለሚስተዋል እስቲ እንዲህ እናውጋው፡፡

ከወራት በፊት የተሰጠንን አንድ ለሥራ ጉዳይ የተዘጋጀ ጥናት አጠናቀን ለበላይ አለቃችን ለማቅረብ ቀጠሮ ይዘናል፡፡ አለቃችን የጥናቱን ክብደትና ቅለት የሚመዝኑት በሚያስገኘው ውጤት ሳይሆን፣ ተሠርቶ በቀረበው የጥራዝ መጠን፣ ማነስና መብዛት ነው፡፡ ከምክንያታዊነት ይልቅ በዘፈቀደ የሚያስቡት አለቃችን፣ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› የሚለውን መርህ አጥብቀው ይወዳሉ፡፡ በምን መመዘኛና ግምገማ ይህንን የመሰለ ተቋም እንደሚመሩ ማወቅ ካልቻሉ ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ፡፡ እንግዲህ እኔና የሥራ ጓደኞቼ ከእንዲህ ዓይነቱ በድንጋይ ካብ ከሚመሰሉ ሰው ጋር ነው ጥናታችንን የምንገመግመው፡፡

የፕሮጀክት ፕሮፖዛሉ ቀርቦ ገና መግቢያው ላይ መነጋገር ስንጀምር አለቃችን የጥራዙ ማነስ ወይም በውስጡ የያዘው ቁም ነገር ከንክኗቸው ይሁን በእጃቸው ላይና ታች እያደረጉ በነገር ይሸነቁጡን ጀመር፡፡ በጣም ተናድጄ፣ ‹‹ጥናቱ መቅረብ ያለበት በፓወር ፖይንት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ወረቀት እያባከንን መጠረዝ የለብንም፡፡ ሁላችንም ጥናቱን በፍላሽ ዲስክ በመውሰድ ላፕቶፓችን ላይ ጭነናል፡፡ እርስዎም እንዲያ ያድርጉና ሥራችንን እንቀጥል፤›› ስል ሰውየው አበዱ፡፡ ‹‹አጉል ቴክኖሎጂ እያልክ ድክመትህን አትሸፋፍን . . . ›› እያሉ ተወራጩ፡፡ እየተልጎመጎሙም ተሳደቡ፡፡ የቴክኖሎጂ ነገር ሲነሳባቸው እንደ ዛር ያንቀጠቅጣቸዋል፡፡ ሦስት ጓደኛሞች በዓይን ጥቅሻ ስንግባባ አንደኛው ግን አፈጠጠብን፡፡ ነገር ተጀመረ፡፡

አለቃችን 30 ገጽ ያለውን ጥራዝ እንደ እሳት ማርገብገቢያ ወዲያና ወዲህ እየወዘወዙ፣ ‹‹ከንቱ የከንቱ ከንቱ . . . ›› እያሉ ሲዘባበቱ አንደኛው አጫፋሪ፣ ‹‹ገና ምን ታይቶ ውስጡ እኮ ገለባ ነው፤›› አለ፡፡ ይኼኔ ሦስታችንም ከመቀመጫችን ተፈናጥረን ተነሳን፡፡ ይህንን በከፍተኛ ጥንቃቄ በርካታ የመረጃ ግብዓቶችን በመጠቀምና በርካታ ቃለ መጠይቆችን በማካሄድ የሠራነውን ሥራ ከንቱው አለቃችንና አድርባዩ አጫፋሪያችን በዜሮ አባዝተው አፈር አበሉት፡፡ ሦስታችንም በንዴት እየተወራጨን ተራ በተራ ለማስረዳት ብንሞክር ማን ሰምቶ? ጭራሽ አለቃችን፣ ‹‹ይህንን ከእርግብ ላባ የቀለለ የማይረባ ጥናት ተብዬ አልቀበለውም፤›› ብለው የፕላስቲክ ቅርጫት ውስጥ ወርውረው ከተቱት፡፡ አድርባዩ የሥራ ባልደረባችንም፣ ‹‹የሚገባው ቦታ ነው የወረወሩት . . . ›› እያለ ተሳለቀብን፡፡ ወይ ጊዜ?

አለቃችን ምን ጠጥተው ወይም አጪሰው እንደሚመጡ ባላውቅም፣ አድርባዩ የሥራ ባልደረባችን ግን አንዴ የፈጣሪን ስም እየጠራ ሲምል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዓለማዊ ፈላስፋ ሆኖ ሲፈላሰፍ፣ ሲያሰኘው ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ሆኖ በማያገባው እየገባ ሲነታረክ እናውቀዋለን፡፡ ይህ ራሱን መሆን ያልቻለ አድርባይ በዚህ ምድር ላይ የሚፈራውና የሚሰግደው ግን ለእኝህ አለቃ ተብዬ ስለሆነ በመሥሪያ ቤታችን ቅፅል ስም ወጥቶለታል፡፡ ሁላችንም በጋራ የምንጠራው፣ ‹‹የገረወይናው ውታፍ›› እያልን ነው፡፡ አለቅየው ቀዳዳ ገረወይና ሲሆኑ እሱ ደግሞ የእሳቸው ውታፍ ነው፡፡ ሁለቱም ከሰብዓዊነት ወርደው እንዲህ ይጠራሉ፡፡

የሁለቱ ግንኙነት ከጥቅም ጋር የተሳሰረ በመሆኑ አበልጆች መሆናቸውን ብዙዎች ያውቃሉ፡፡ በግዥና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ስለሚጎራረሱ አንዱ አንዱን ይጠብቃል፡፡ የሚያጉረመርም ወይም የሚያፈጥ ካለ በሁለቱ ትብብር ይወገዳል፡፡ ከደረጃ ዝቅ ማለት እስከ መሰናበት፡፡ ሁለቱ በአንድ ሳንባ እየተነፈሱ ሌላውን ያጨናንቃሉ፡፡ የእኛ ጥናት የተጠላው ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው በጥራዙ ማነስ ብቻ አይደለም፡፡ የሁለቱን የጥቅም ሰንሰለት የሚበጥስ አዲስ አሠራር ስለሚያስተዋውቅ ነው፡፡ የዋህ መስለው በእጃቸው ጥናቱን የመዘኑት ስለገጹ ማነስ ብቻ ሳይሆን፣ ውስጡ የሠፈረው ሥር ነቀል አብዮት የሚቀሰቅሰው አዲሱ የሥራ አቅጣጫ አስፈርቷቸው ነው፡፡ ስለዚህ አድርባዩና አለቃችን ተባብረው ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ አደረጉት፡፡

የጥናታችን ውጤት መጣሉን የሰሙ የመሥሪያ ቤታችን ሠራተኞች ለሁለት ተከፈሉ፡፡ ለውጥ ፈላጊ ብዙኃንና በነበረው እንዲቀጥል የሚፈልጉ አናሳዎች፡፡ አናሳዎቹ በተለያዩ የጥቅማ ጥቅም ቦታዎች ላይ የተቀመጡ በመሆናቸው ከድምፃቸው ይልቅ ግርማ ሞገሳቸው ያስፈራል፡፡ የሚቃወማቸውን ሠራተኛ ከማስፈራራት ጀምሮ እስከ አሽከርነት ማሠማራት ይችሉበታል፡፡ የሠራነውን ጥናት የደገፉት ፊት ለፊት ወጥተው ማንኛውንም ጥቃት መመከት የማይችሉና ውስጥ ለውስጥ የሚያንሾካሹኩ ሲሆኑ፣ የጥናቱ ተቃዋሚዎች ደግሞ በአደባባይ የፈለጉትን ማለት የሚችሉ ክንደ ብርቱዎች ጭምር ናቸው፡፡ አንደኛው ጓደኛችን ምናለበት በዚህ መዘዘኛ ጥናት ባልተሳተፍን ብሎ ሲቆጭ፣ ሁለታችን ግን የመጣው ይመጣል እንጂ እንጋፈጣለን ብለን ቆረጥን፡፡ ጓደኛችን ግን ሳይታሰብ 360 ዲግሪ ዞሮ ከተቃዋሚዎቹ ወገን ሲቀላቀል አዘንን፡፡ አድርባይነት ምን ያህል እንደተንሰራፋ በዓይናችን አየን፡፡ የገባንበትን ለመወጣት ግን ግንባራችንን አላጠፍንም፡፡ ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ሕገወጥነት የትም አይደርስም ብለን ተነሳን፡፡

አዎ ሕገወጥነት በጣም ከአቅም በላይ ሆነ፡፡ ያንን ሁሉ ጊዜ ወስደን የሠራነው እጅግ በጣም ጠቃሚ ጥናት ተጥሎ ሌላ አዲስ ጥናት እንዲሠራ ተወሰነ፡፡ የጥናቱ አርቃቂዎች በሙሉ ለውጥ ከማይፈልገው ኃይል ተመደቡ፡፡ እኛም በየተራ ከሥራ መደብ ኃላፊነትና ደረጃ ዝቅ እየተደረግን በየስርቻው ተመደብን፡፡ አቤት ስንል ቅሬታ የሚሰሙት በዳዮቻችን ናቸው፡፡ ጓደኛችን የአዲሱ ቡድን አባል ሆኖ ሹመት ሲጨመርለት እኛ ደግሞ አሽቆለቆልን፡፡ እኔና ጓደኛዬ መልቀቂያችንን አቅርበን ከዚያ የሞራልና የሰብዕና ማላሸቂያ ቦታ ለመሸሽ ተዘጋጅተናል፡፡ አስመሳዮችና አድርባዮች ግን በእኛ ሽሽት ፈንጠዝያ ላይ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጉድ በየቦታው ፋሽን መሆኑን ስሰማ ግን ከልቤ አዘንኩ፡፡ ለራሴ ሳይሆን ለአገሬ፡፡ ‹‹አድርባይነት አገር የሚያጠፋ ካንሰር ነው›› የሚል መፈክር አራት ኪሎ አደባባዩ አጠገብ መለጠፍ አማረኝ፡፡

(ማስተዋል ተሻለ፣ ከስድስት ኪሎ)