Skip to main content
x
ለከፋ አደጋ የተጋለጡት የአክሱም ሐውልቶችና ቅርሶች

ለከፋ አደጋ የተጋለጡት የአክሱም ሐውልቶችና ቅርሶች

የኢትዮጵያ ጥንታዊ መዲናና መንግሥት የነበረችው አክሱም፣ ተመራማሪዎች እንደሚገልጿት የኃያል መንግሥት ዋና ከተማ፣ ቀጥሎም የሃይማኖት ማዕከል ብሎም የጥንት ሃይማኖታዊ መንግሥት በአፍሪካ ውስጥ የመሠረተች፣ አሁንም በርካታ ምዕመናን የምታስተናግድ የተቀደሰች ከተማ ነች፡፡ በውስጧም እጅግ በጣም የተቀደሰው ጽላትና የክርስትና ሃይማኖት የተለየው መገለጫ ይገኛል፡፡ እንደ ባለታሪኩ ፍራንሲስ አንፍሬ የአክሱም መንግሥትና ከተማ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓለም ከሚገኙት አራት መንግሥታት ከሮም፣ ከፋርስና ከቻይና ቀጥሎ አራተኛው ኃያል መንግሥት ነበረች፡፡ ለኃያልነቷ ምስክር ግዙፍ ሐውልት፣ ግዙፍ የድንጋይ፣ ጠረጴዛ፣ ግዙፍ የዘውድ መሠረታዊ ድንጋይ የተሰባበሩ ትላልቅ ዐምዶች፣ የነገሥታት መቃብር ከተለያዩ የማይዳሰሱ አፈ ታሪኮችና ባህሎች ጋር ከመገኘታቸውም በላይ ጎብኚን የጥንቱ ታሪክ ምን ያህል ታላቅ እንደነበር ያሳያል፡፡ ታሪካዊቷ አክሱም ከአራት አሠርታት በፊት በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ሳይንስና ባህል ድርጅት) የዓለም ቅርስ ሆና ተመዝግባለች፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዩኔስኮን ጭምር ያሳሰበ የአክሱም ሐውልቶችን ጨምሮ በቅርሶቿ ላይ አደጋ እየደረሰ ነው፡፡ ኅብረተሰቡም ሆነ ባለሙያዎች እሮሮ እያሰሙ ነው፡፡ መሰንበቻውን በዓመታዊው የኅዳር ጽዮን ማርያም በዓል አጋጣሚ አክሱም ዩኒቨርሲቲ በአክሱም ቅርሶች ዙርያ ዐውደ ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡ በመድረኩ በጉዳዩ ዙርያ ጥናታዊ ጽሑፍ ካቀረቡት አንዱ የኢትዮጵያ አርኪዮሎጂ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር ተክሌ ሐጎስ ናቸው፡፡ በጥናታቸውና በአክሱም ቅርሶች ላይ እየደረሰ ባለው ነገር ላይ ከሔኖክ ያሬድ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአክሱም ያቀረቡት ጥናትና ውጤቱ ምን ይመስላል?

አቶ ተክሌ፡- የአክሱም ዓለም አቀፍ ቅርስን ከመጠበቅና ከማልማት አኳያ ነው፡፡ አክሱም እ.ኤ.አ 1980 የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በዓለም በሦስተኛው ዙር ከተመዘገቡት ቅርሶች አንዱ አክሱም ነው፡፡ ያኔ ሲገባ ሁለት ዓለም አቀፍ የቅርስ መስፈርትን ማለትም አንደኛ ከፍተኛ የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት፣ ሁለተኛ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍን የሚወክል በመሆኑ ገባ፡፡ የዩኔስኮ አሥር መስፈርቶች ስድስቱ የባህላዊ፣ አራቱ የተፈጥሮ ቅርስ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሲታይ አክሱም ስድስቱንም የባህላዊ ቅርስ መሥፈርቶች ያሟላል፡፡ ግን በወቅቱ ሁለቱ ብቻ ነው የቀረበው፡፡ ስለዚህ የዓለም ኅብረተሰብ ማወቅ ያለበት የአክሱም እሴት አለመታወቁን ነው፡፡ ስድስቱ የማይዳሰሱት ቅርሶች የአክሱም ጽዮን ታሪክ፣ ሥነ ጽሑፉ፣ ብራናው፣ የያሬድ ዜማ፣ የአክሱም ሥልጣኔ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ይጠቀሳሉ፡፡ የሥልጣኔ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ እስከ የመን ሄዷል፡፡ የላሊበላ ሥልጣኔም የአክሱም ተፅዕኖ ውጤት ነው፡፡ ይኼ አልታየም፡፡ እንደገና በዩኔስኮ መሠራት አለበት፡፡ ሁለተኛ የዓለም ወካይ ቅርስነቱ፡፡ በመሬትና በከተማ በአጠቃላይ ለየት ያለ የቅርስ መሠረቱም አልታየም፡፡ አክሱም እስካሁን በዓለም የታወቀው በሁለት መሥፈርት ብቻ ነው፡፡ በስድስቱ መሥፈርት ዩኔስኮ ውስጥ መግባት ይችላል፡፡ ይህን ባደረግን ቁጥር ተቀባይነቱ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ይጨምራል፡፡ ዩኔስኮ ያላወቃቸው አራት መሥፈርቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአክሱም ጽዮን በዓል ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሳይሸራረፍ እስካሁን ለ2000 ዘመን እየተከበረ ነው፡፡ የቅዱስ ያሬድ ሙዚቃ (ዜማ)፣ዝማሬው፣ ፍልስፍናው፣ ፊደላችን፣ ሥነ ጽሑፋችን እዚያ ውስጥ ነው መግባት ይችላል፡፡ ይህ ቀርቷል፡፡ ይህን ሁሉ የምንጠብቀው ለዕውቀቱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ቅርስ በተለያየ ምክንያት አደጋ ላይ ይገኛል፡፡ ዩኔስኮ ለኢትዮጵያ መንግሥት የአክሱም የዓለም ቅርስን ከመጠበቅ አኳያ እ.ኤ.አ. ከ1996 ጀምሮ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ እስካሁን ድረስ አልተመለሱም፡፡

ሪፖርተር፡- በአክሱም ቅርሶች ላይ የተፈጠሩት ችግሮች ምንድናቸው?

አቶ ተክሌ፡- የመጀመርያውና ዋነኛው ችግር የመሠረተ ልማት ግንባታ መካሄድ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. በአሮጌው የአክሱም ከተማ ይኖሩ የነበሩትን የፌዴራል መንግሥት 15 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ አደረገ፡፡ የክልሉ መንግሥትም የውኃ፣ የመንገድና የመሬት ወጪ ሸፈነ፡፡ ሰዉ ከተነሳ በኋላ መካነ ቅርሱ ባዶ በመሆኑ ሌላ አዲስ ግንባታ እየተፈጠረ ነው፡፡ እንዳየሁት ግማሾቹ ካሳ የተከፈላቸው ናቸው፡፡ ታዕካ ማርያም የአክሱም ዘመን ቤተ መንግሥት ነው፡፡ እዚያ የነበሩ ሠፋሪዎች በወቅቱ ተነስተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ሌሎች ሰዎች ሌላ ካሳ ለማግኘት በቦታው ላይ አዲስ ቤት ሠርተዋል፡፡ እንዲያውም ‹‹በከፍተኛ ባለሥልጣኖች›› ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ናቸው ተብሎ በሕዝቡ ይነገራል፡፡ ሌላው እንዳ ሚካኤል የአክሱም ክፍለ ዘመን ቤተ መንግሥት ያለበትም፣ ቅርሱን ለመጠበቅ ሰዎች እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ ከጎኑ አንድ ትልቅ ሕንፃ ተሠርቷል፡፡ ስለዚህ በአሮጌው የአክሱም ከተማ አንደኛ አዲስ ግንባታ እየተካሄደ ነው፤ ካሳ የወሰዱ ሰዎች ድጋሚ ካሳ ለመውሰድ ቅርሱን እያጠፉ ነው፡፡ ሁለተኛ በደጀን ዞን እና በእምብርት ዞን ግንባታ ይካሄዳል፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ያሬድ አደባባይ በሚባለው ዳዕሮ ዒላ አካባቢ ቦታው ጭምር መጠበቅና መከበር ሲገባው የኮካ ኮላ መሸጫ፣ መፀዳጃ ቤትና ከፍተኛ ግንባታ ተካሂዶበታል፡፡ የአካባቢውን ውበት እያሳጣው ነው፡፡

      ሌላው የአክሱም ጽዮን ማርያም ግቢ በንጣፍ ድንጊያ (ኮብልስቶን) መሆን ሲገባው በዘመናዊ የስሚንቶ ንጣፍ (ቴራዞ) እንዲለብስ በመደረጉ ጉዳት አድርሷል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ፣ ከድሮ ታሪኩ፣ ከዙፋን ድንጊያዎቹ ጋር አብሮ የማይሄድ ነገር ተሠርቶበታል፡፡ በዙፋኖቹ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ሌላው በአክሱም ሐውልቶች ላይ የተፈጠረው እክል ነው፡፡ የቆመው ሐውልት ጎን በውስጡ የመሬት መደርመስ በመፈጠሩ ተቦርቡሯል፡፡ ለቆመውም ሆነ ለተንጋደደው ሐውልት አደገኛ ነው፡፡ የታሰረው ሐውልት እስካሁን መፍትሔ አላገኘም፡፡ ከሮም የመጣው ሐውልት በ1999 ዓ.ም. ሲተከል የታሰረ እስካሁን አልተፈታም፡፡ ዓምና (2009 ዓ.ም.) ከዘጠኝ ወር በፊት ይስተካከላል ተብሎ ከጣሊያኖች ጋር ስምምነት ተደርጓል ቢባልም በመሬት የሚታይ የሚጨበጥ ነገር የለም፡፡ ሐውልቱ እንደታሰረ የሚቆይ ከሆነና ካቦው ካፈተለከ፣ ሐውልቱ የመውደቅ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ከሱ ይባስ ብሎ ከጎኑ የመሬት መደርመስ ተፈጠረ፡፡ ቦታው በ1966 ዓ.ም. በእንግሊዛዊው ቺቲክ አማካይነት ተቆፍሯል፡፡ ያኔ የደርግ አብዮት ሲመጣ ችኮላ ስለበረ በደንብ ስላልተደፈነ (ስላልተሞላ) በየጊዜው መደርመስ ያጋጥማል፡፡ ይህንን ነገር የሚያስተካክል አካል የለም፡፡

      በሌላ በኩል ነባሩን ቅርስ የሚሸፍኑ ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ፒያሳ በደጃዝማች ገብረ ሥላሴ ቤተ መንግሥት አካባቢ ከፍተኛ የሆኑ ዘመናዊ የአካባቢውን ውርስ የማይመስሉ ግንባታዎች እየካሄዱ ነው፡፡ አካባቢን በመጠበቅ ረገድ ጥሩ ሥራ እየተሠራ ያለው በላሊበላ ከተማ ነው፡፡ በላሊበላ የአካባቢውን የሕንፃ ጥበብ ባማከለ መልኩ የአማራ ክልል ተግቶ ይሠራል፡፡ በትግራይ ግን የአካባቢውን ባህላዊ የአክሱም ዘመን ሥነ ሕንፃ ውበት በጣሰ መንገድ በቅርሱ ላይ አደጋ እየመጣ ነው፡፡ በግንባታ አካባቢን በማዘባረቅ፡፡ ሌላው ከፍተኛ ችግር በቤተ ክርስቲያን የተሠራው የአክሱም ሙዚየም ነው (ገና ያላለቀ)፡፡ ይህ ሙዚየም የ17ኛው ክፍለ ዘመን አፄ ፋሲል ያሠሩት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ዕይታን እንዲሁም ሐውልቶቹን ጋርዷል፡፡ የሕንፃው አሠራር በጣም አስቀያሚ፣ ባለ አራት ፎቅ በመሆኑም በ1957 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያሠሩትን አዲሱን ሕንፃ ጨምሮ የአካባቢውን ዕይታ ሁሉ ጋርዷል፡፡ ይህንን ገጽታ የተመለከተው ዩኔስኮ ሁለት ጊዜ እ.ኤ.አ. በ2013 እና በ2016 ቡድኖችን ልኳል፡፡ የተደረገው ሕንፃ ግንባታ ትክክል አለመሆኑን ጠቅሶ እንዲስተካከል ቢያሳስብም የሚስተካከል አልሆነም፡፡ ስለዚህም ከፍተኛ አደጋ እየደረሰ ነው፡፡ በዚያ ላይ ሕገወጥ የቅርስ ዝውውርም ይካሄዳል፡፡ የአክሱም ሳንቲም ይሸጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ከየት ነው የሚወጣው?

አቶ ተክሌ፡- ሕገወጥ ቁፋሮ እየተካሄደ፡፡

ሪፖርተር፡- መካነ ቅርሱ የሚጠብቀው የለም?

አቶ ተክሌ፡- የአክሱም መካነ ቅርስን ለመጠበቅ በ2006 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት ያወጣው መመርያ አለ፡፡ መመርያው ለጎንደር፣ ለጢያ፣ ለላሊበላና ለአክሱም የዓለም ቅርሶች ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋምና አካባቢው እንዲጠበቅ የሚያስችል ነው፡፡ አልተተገበረም፡፡ ሌላው አዋጅ 839 የሚባል ነው፡፡ በ2006 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ መሠረት፣ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶች በቀጥታ የፌዴራል ቅርስ ይሆናሉ ይላል፡፡ ያም ነገር አልተተረጎመም፣ አልተተገበረም፣ መመርያም ደምብም የለውም፡፡ ስለዚህ አክሱምን የሚያስተዳድር ባለቤት የለም፡፡ እዚያ ያሉ ሰዎች ስለቅርሱ ተቆርቁረው አዲስ አበባ መጥተው አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ እዚያ ያለው ችግር ለክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተነግሮታል፡፡ ከመንግሥት ምንም የሚሰማ ሰው ጠፍቷል፤ ጆሮ ዳባ፡፡ እኛ እያቀረብን ያለነው ለኅብረተሰቡና ለዓለም አቀፍ ነው እንጂ በባህል ሚኒስቴር ያለው ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ወረዳ በተዋቀረው የባህል ሚኒስቴር መዋቅር ምንም ይሠራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ አንደኛ እነዚህ ሰዎች ባህል ምን እንደሆነ አያውቁም፡፡ ቢያውቁም ኢንታንጀብል ሄሪቴጅ (የማይዳሰስ ቅርስ) ብቻ ነው፡፡ በዓመት ጫምባላላ፣ ኢሬቻ፣ መስቀል፣ ኅዳር ጽዮን፣ ጥምቀት ብቻ ነው፡፡ ለነርሱ ቅርስ ማለት ጭፈራ ነው፡፡ ታንጀብል (ተዳሳሽ) የሚባለው ነገር ተረስቷል፡፡ ሕገ ወጥ ቁፋሮ፣ ሕገ ወጥ ቅርስ ዝውውር ሕገ ወጥ መሠረተ ልማት እየተካሄደ ነው፡፡ በአክሱም መካነ ቅርስ ላይ ቤት እየተገነባ ነው፡፡ የሕንፃው ከፍታ ቅርሶቹን እየሸፈነ ውበቱን እያጣ በመሆኑ የአክሱም ሕዝብ እያለቀሰ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአክሱም የቅርስ ይዞታ አሳሳቢ በመሆኑ ዩኔስኮ ማሳሰቢያ መስጠቱን አንብበናል፡፡ እስካሁን በፌዴራልም ሆነ በክልል ማስተካከያ ሲደረግ አለመታየቱ ምን ሊያስከትል ይችላል?

አቶ ተክሌ፡- አክሱም ወደ አደገኛ ሁኔታ እየሄደ ነው፡፡ ልክ እንደ ስሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ ለአደጋ የተጋለጠ ተብሎ ከፋይል እንዳይወጣ ያሰጋል፡፡ ስሜን ፓርክ ለ20 ዓመት ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ የአክሱም ሁኔታ ከዚህ አይለይም፡፡ ዩኔስኮ ሁለት ጊዜ በተከታታይ በመምጣት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ አንድም የተስተካከለ ነገር የለም፡፡ አሁንም በዚህ ከቀጠለ ወደ አደገኛ መዝገብ ብሎም ከዓለም ቅርስነት ሊሰረዝ ይችላል፡፡ የአክሱም ሐውልት እንደዘመመ ነው፡፡ ከ10 ዓመት በላይ በካቦ ታስሯል፡፡ በሐውልቱ ዙሪያ ያሉ ቅርሶች ችግር ላይ ነው ያሉት፡፡ የሚመለከተው ባለቤት አጥቷል እያልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዩኒቨርሲቲው ዐውደ ጥናት ምን ግብረ መልስ አገኙ?

አቶ ተክሌ፡- የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ይሰበስባል፡፡ የሚመለከታቸው የሥራው ባለቤቶች የመንግሥት አካላት ሥራቸውን ስለሚያውቁ በዐውደ ጥናቱ አይገኙም፡፡ በወቅቱ የትግራይ ባህል ቢሮ የለም፡፡ በዓዲግራት መስቀልም ሆነ በዚህ አይገኙም፡፡ አንደኛ ሥራቸውን አያውቁም፡፡ ለመማርም ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ኅብረተሰቡ ግን ከመጠየቅ አልተቆጠበም፡፡ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ፒያሳ አካባቢ ስለሚገኙት ጥንታውያን ቤቶች ይገኙበታል፡፡

      አክሱም ከማይዳሰስ ቅርስ በስተቀር ሦስት ዓይነት ቅርስ አለ፡፡ እነዚህም የአክሱም ዘመን ቅርስ ሐውልቱና ከተማው፣ ሁለተኛው ባህላዊ ቤቶች (ሕድሞ)፣ ሦስተኛው በጣሊያን ዘመን የተሠሩት ቤቶች ናቸው፡፡ ሕዝቡ በፒያሳ አካባቢ ያሉት እየፈረሱ ነው፣ ጽዳት የላቸውም፣ ቱሪዝሙም እየተበከለ ነው አሉ፡፡ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ተወካይ ‹‹አዎ አይተናል›› ከማለት ውጪ ተገቢው ምላሽ የሚሰጥ አካል የለም፡፡ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አንደኛ ሥራና ሠራተኛ አልተገናኘም፡፡ እኔ የምለው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለቤት አጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት የኢትዮጵያ አርኪዮሎጂ ማኅበር ከዚህ አኳያ ምን ሚና ይኖረዋል?

አቶ ተክሌ፡- የአርኪዮሎጂ ማኅበር እንደ ሙያ ማኅበር ተፅዕኖ በመፍጠር ላይ ነው፡፡ በየጊዜው በባለሙያዎች የግንዛቤ መፍጠሪያ የጥናት መድረኮችን ያዘጋጃል፡፡ መንግሥትንም ይደግፋል፡፡ ክፍተትንም ያሳያል፡፡ በተከታታይ በምናዘጋጃቸው መድረኮችም ኢትዮጵያውያንና የውጭ ምሁራን በሚያቀርቧቸው ጥናቶች አዳዲስ ግኝቶችን ያሳውቃል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ በአርኪዮሎጂው ግኝቶች ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ 1800 ዓመተ ዓለም እየሄደ ነው፡፡ ብዙ ባጠናን ቁጥር ያገራችን ታሪክ ዕድሜው እየረዘመ ይሄዳል፡፡ ግን ይኼን ዕውቀቱን እያጠፋነው፣ እያረስነው፣ ቤት እየሠራንበት፣ ውበቱን እያጠፋነው ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በኋላ እንዳይቆጨን ቁጭት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የሚመለከታቸው አካላት አንድ ይበሉ፡፡ የአክሱም ሕዝብ ተወካዮቹን ልኮ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን አነጋግሯል፡፡ ለክልሉም ተናግረዋል፡፡ ያገኙት ምላሽ የለም፡፡ የሕዝብ ጥያቄ የማይመለስበት ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቅርሱ፣ በሀገሩ፣ በሚስቱ አይደራደርም፡፡ ሕዝቡ ወደ ተስፋ መቁረጥ እየሄደ ነው፡፡ የአክሱም ሕዝብ ለቅርሱ ያለው ፍቅር በጣም የተለየ ነው፡፡ አንዱ የቅርሱ ባለቤት የአክሱም ማዘጋጃ ቤት ነው፡፡ ለመካነ ቅርስ ተብሎ በተለቀቀው ቦታ ቤት ሲሠራበት፣ ከፍተኛ ሕንፃ ሲገነባበት ማዘጋጃ ቤቱ እያየ ዝም ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ማርያም ጽዮንን የከለለው ፎቅ ግንባታው እንደቆመ ነው?

አቶ ተክሌ፡- ዝም ብሎ ተጋርዶ ቆሟል፡፡

ሪፖርተር፡- ውሳኔ አልተሰጠበትም?

አቶ ተክሌ፡- ምንም! ዩኔስኮ እ.ኤ.አ. በ2013 ይስተካከል ቢልም፣ እንዴት እንደሚስተካከልም መፍትሔ አልጠቆመም፡፡ ሕንፃው ከአካባቢው ጋር እንዲመጣጠን መስተካከል አለበት፡፡ ዩኔስኮም በራሱ ችግር አለበት፡፡ የዩኔስኮ ቡድን በ2013 የመጣው አነጋግሮ የሄደው በቅርሱ ላይ ብልሽት የሚያደርሱትን አካላት እንጂ ከዚያ ውጭ አይደለም፡፡ ያነጋገራቸው ቅርሱን መጠበቅና ማስተዳደር ያልቻሉትን ለምሳሌ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን፣ የቤተ ክህነት ሰዎችን ብቻ ነው፡፡ በ2016 የመጣው ቡድን እኔንም አነጋግሯል፡፡ ያ ሙዝየም ሲሠራ በውስጡ የነበረው እስከ ሦስት ሜትር የሚረዝም ሕንፃ ፈርሷል፡፡ የመጀመርያው ቡድን ምንም ቅርስ የለውም ብሎ ነበር የሄደው፡፡ የሙዚየም ግንባታው በ2011 ሲጀመር ዩኔስኮ ይጠና ነበር ያለው፡፡ ግን ሥራው ቀጠለ፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴና አፄ ፋሲል ያሠሯቸውን የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎች በስሚንቶ የተገነባው የማይሆን ሕንፃ ጋረዳቸው፡፡ የመሬት ውስጥ ቅርስ አውድሟል፤ ያካባቢውን ዕይታ አስቀያሚ አድርጎታል፡፡ መምሰል የነበረበት የአካባቢውን የሕንፃ ጥበብ፣ ባህላዊ (ሕድሞ) ቤቶች ባለ አንድ ፎቅ ዓይነት ጥበብ፣ በስሚንቶ ሳይሆን በድንጋይ መሠራት ነበረበት፡፡ ቱሪስት ሲመጣ ምንድነው የሚያየው? የሚመጣው’ኮ የአክሱምን ሥልጣኔ ውበት ለማድነቅ ነው፡፡ በግቢው የሚገኙትን ቀደምት የድንጋይ ዙፋኖች በዘመናዊ ስሚንቶ መርገው በጣም አበላሽተዋቸዋል፡፡ እናም በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቅርሱ ዕጣ ፈንታ ምንድነው?

አቶ ተክሌ፡- መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜ ሳይወስድ አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ዩኔስኮ ለሦስተኛ ጊዜ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ይኼ ከመሆኑ በፊት ሥራቸውን ይሥሩ፡፡ አንደኛ የአክሱም ማዘጋጃ ቤት በዓለም ቅርስ ደጀን ዞን አካባቢ የሚሠሩ ሕንፃዎች ከፍታ ምን መሆን እንዳለበት መመርያ ማውጣትና መቆጣጠር አለበት፡፡ ሁለተኛ ቅርሳችን በፌዴራልና በክልል ደረጃ የሚከፍለው በ2006 ዓ.ም. የወጣውን አዋጅ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ይተግብረው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መመርያ 346 በአክሱም ላይ እንዲፈጸም ያወጣውን ባለሥልጣኑ መተግበር አለበት፡፡ የፌዴራል መንግሥት ዓለም አቀፍ ቅርስ የሚተዳደረው በብሔራዊ ነው፡፡ ምክንያቱም ፈራሚው ዩኔስኮ የሚያውቀው የኢትዮጵያ መንግሥት እንጂ ክልሎችን አይደለም፡፡ ስለዚህ መሠረተ ልማት ግንባታ ሲካሄድ ጥንቃቄና ቁጥጥር ይደረግ፤ ባጠቃላይ መንግሥት ባዋጅ የተሰጠውን ሥራ ይሥራ፡፡ ይኸው ነው፡፡