Skip to main content
x
የየመን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዓሊ አብደላ ሳላህ ግድያ አንድምታ
ለ33 ዓመታት የመንን የመሩት ዓሊ አብደላ ሳላህ ሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ሰነዓ ውስጥ በሁቲ ሚሊሻዎች ተገድለዋል

የየመን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዓሊ አብደላ ሳላህ ግድያ አንድምታ

የመንን ለ33 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመሩትና በአገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2011 በተቀሰቀሰ አብዮት ምክንያት በ2012 ሥልጣን የለቀቁት ዓሊ አብደላ ሳላህ፣ ሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2010 ዓ.ም.   በቀድሞ አበሮቻቸው መገደላቸው ተሰምቷል፡፡

ይህ ደግሞ በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ሳዑዲ ዓረቢያና ኢራን የውክልና ጦርነት በሚያደርጉባት የመን፣ የተንሰራፋውን የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ከፋ ደረጃ ያሸጋግረዋል ተብሏል፡፡

 የዓሊ አብደላ ሳላህ በቀድሞ የጦር ጓዳቸው የሁቲ ሚሊሻዎች እጅ መገደላቸው በአገሪቱ ሰላምን ለማምጣት የነበረውን ጥቂት ተስፋ እንዳጨለመ ይነገራል፡፡

ዓሊ አብደላ ሳላህ ለምን በሁቲ አማፅያን ተገደሉ?

 የፖለቲካ ሴራን ማቀነባበር ይችሉ ነበር የሚባሉት ዓሊ አብደላ ሳላህ ከአምስት ዓመታት በፊት በየመን አብዮት በተቀሰቀሰበት ወቅት፣ በአገሪቱ የከፋ ዕልቂት እንዳይመጣ ሥልጣናቸውን ለቀው ነበር፡፡ ከአገሪቱ መሰደድን ባይመርጡም በአገራቸው ሆነው የፖለቲካ ቁማር ይጫወታሉ ተብለው ይታሙ ነበር፡፡ ይህ እውነት መሆኑ የተገለጠው ደግሞ ከቀናት በፊት ነው፡፡

የየመን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዓሊ አብደላ ሳላህ ግድያ አንድምታ
ፕሬዚዳንት ዓሊ አብደላ ሳላህን የገደሉት የሁቲ ታጣቂዎች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ

 

የ75 ዓመቱ ዓሊ አብደላ ሳላህ እ.ኤ.አ. በ1978 የሰሜን የመን ፕሬዚዳንት፣ በኋላም ደቡብና ሰሜን የመን ሲዋሀዱ እ.ኤ.አ. በ1990 የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ነበር፡፡ ተፅዕኖ አለብን የሚሉት የየመኖቹ ዛዲ ሺዓ (የሁቲ አማፂያን) ደግሞ በተለይ እ.ኤ.አ ከ2004 እስከ 2010 ባለው ጊዜ በተደጋጋሚ ከፕሬዚዳንቱ ጦር ጋር በሽምቅ ተዋግተዋል፡፡

በአገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2011 የተቀሰቀሰውን አብዮት ያነሳሱትም እነዚሁ ሁቲዎች ነበሩ፡፡ ፕሬዚዳንት ሳላህም አገሪቷ ወደ ከፋ ብጥብጥ ሳትገባ ነበር ሥልጣናቸውን ለምክትላቸው ሂዲ ያስረከቡት፡፡

ሆኖም ሁቲዎች ሃዲንም አልፈለጉም፡፡ ተዋግተውም የአገሪቱን ዋና ከተማ ሰነዓ እ.ኤ.አ. በ2014 ተቆጣጠሩ፡፡ በፖለቲካ ቁማር ይጫወታሉ፣ የፖለቲካ ሴራ አቀነባባሪም ናቸው የሚባሉት ዓሊ አብደላ ሳላህ አገሪቱን ከፖለቲካ ቅዠት አወጣለሁ በማለት፣ ከአማፂያኑና በኢራን ከሚደገፉት ሁቲዎች ጋር እ.ኤ.አ. በ2014 ጥምረት ፈጠሩ፡፡ ሥልጣኑን ከዓሊ አብደላ ሳላህ ተረክበው የነበሩትን ሃዲ እ.ኤ.አ. በ2015 ሥልጣናቸውን እንዲለቁና ከአገር እንዲሰደዱ አደረጉ፡፡

ይህ ግን ለየመን መልካም ዜና ይዞ አልመጣም፡፡ ከየመን የተሰደዱትን ሃዲ ወደ ሥልጣን ለመመለስ ሳዑዲ ዓረቢያ መራሹ ጦር በየመን ላይ የጦርነት ዘመቻውን ጀመረ፡፡

በየመን ንፁኃን የቦምብ ጥቃት ሰለባ ሆኑ፡፡ ከስምንት ሺሕ በላይ ተገደሉ፡፡ ከ49 ሺሕ በላይ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ የመናውያን በጦርነት ብቻ ሳይሆን በረሃብ ተገረፉ፡፡ በበሽታ ተመቱ፡፡ ሳዑዲ መራሹ ጦር በየመን ላይ በሚያደርገው የአውሮፕላን ቦምብ ድብደባ ከ20 ሚሊዮን በላይ የመናውያን ከሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጪዎች እንዲመፀወቱ አደረገ፡፡ የመንም በዓለም ከፍተኛ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋት አገር ሆነች፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2017 አጋማሽ በኮሌራ ብቻ ከሁለት ሺሕ በላይ የመናውያንም አለቁ፡፡  

የየመን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዓሊ አብደላ ሳላህ ግድያ አንድምታ
ፕሬዚዳንት ዓሊ አብደላ ሳላህ በዓረብ የፀደይ አብዮት ማዕበል ሥልጣናቸውን ካጡት ስደተኛው ዛይን ቤን ዓሊ (ቱኒዚያ)፣ ከሟቹ ሙአመር ጋዳፊ (ሊቢያ) እና በሕይወት ካሉት ሆስኒ ሙባረክ (ግብፅ) ጋር ይታያሉ

 

ይህ ሁሉ ሲሆን ዓሊ አብደላ ሳላህ ከሁቲዎቹ  የጦር አጋሮቻቸው ጋር ለሦስት ዓመታት ያህል አብረው ሳዑዲን ተቃውመዋል፣ ተዋግተዋል፡፡

ዘ ጋርዲያን እንደሚለው፣ ዓሊ አብደላ ሳላህ ለሦስት ዓመታት ያህል ወዳጅ ካደረጓቸው ከቀድሞ ጠላቶቻቸው ከሁቲ አማፂያን በድንገት አፈነገጡ፡፡ ሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በአማፂያኑ ከመገደላቸው ሁለት ቀናት አስቀድሞ ሁቲዎቹን ያስቆጣ ንግግር አደረጉ፡፡

ሲኤንኤን እንዳሰፈረው፣ ሳላህ በኢራን ከሚደገፉት ሁቲ አማፂያን ጎራ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተናገሩ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ በየመን የአውሮፕላን ድብደባ ከሚያደርገው የሳዑዲ ጥምር ጦር ጋር ለመሥራት ፊታቸውን ማዞራቸውንና ቀድሞ ከነበሩበት ጎራ ወደ ሌላኛው መሸጋገራቸውንም አስታወቁ፡፡

የሳዑዲ መንግሥትም የሳላህን ዕርምጃ በጄ ብሎ ሳላህ አማፂያንን እንዲዋጉ የአየር ድብደባ ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡ ሆኖም ለሳላህ ይህ የሞት ጽዋ መጎናፀፊያቸው ነበር፡፡

 የሁቲ አማፂያን የሳላህን ክህደት በትዕግሥት አልተቀበሉም፡፡ ቀድሞም የፖለቲካ ቁማር ይጫወታሉ የሚባሉትን ሳላህ ‹‹ሸፍጥ ሲሠሩብን ከርመዋል፤›› አሉ፡፡

በሰነዓ የሚገኘውን ቤታቸውን ለ48 ሰዓታት ያህል ከበቡ፡፡ ሳላህ በበኩላቸው በተሽከርካሪ ለማምለጥ ቢሞክሩም፣ በደቡብ ሰነዓ መፈተሻ ጣቢያ ከነከፍተኛ አጋሮቻቸው ተያዙ፡፡ በወቅቱ በተፈጠረ ተኩስ መገደላቸውንም የሩሲያ ቴሌቪዥን (አርቲ) ዘገበ፡፡ በኋላም አልጄዚራ የሁቲን ሬዲዮ ጠቅሶ ስለመገደላቸው አተተ፡፡

የሁቲ ኮማንደርን ጠቅሶ ሲኤንኤን እንዳለው፣ የሳላህ አስከሬን ለፓርቲያቸው ጄኔራል ፒፕልስ ኮንግረስ አመራሮች ተሰጥቷል፡፡ ሁቲዎቹ እንደሚሉት፣ ለሳላህ ሞት ምክንያት የሆነው ክህደታቸው ነው፡፡

በየመን ሰላም የማስፈን ፈተና

የሳላህ መገደል ቀድሞውንም በየመን የውክልና ጦርነት ለሚያደርጉት ኢራንና ሳዑዲ ዓረቢያ እሳት የሚያቀጣጥል ይሆናል ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ በየመን የተፈጠረው የእርስ በርስና የውክልና ጦርነት በውይይት እንዲያከትም የሚፈልጉ ኃይሎችን ተስፋ እያሟጠጠ ነው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የየመን መልዕክተኛ ኢስማኤል ኡልድ አህመድ፣ ‹‹በየመን ለዓመታት የዘለቀው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያገኝ በተደጋጋሚ ተናግረን ነበር፤›› ብለዋል፡፡ በአውሮፓ ካውንስል የውጭ ግንኙነትና የየመን ጉዳይ ተንታኝ አዳም ባሮን ደግሞ፣ ‹‹ሁቲዎቹ ጠንክረው እየተዋጉ ነው፡፡ በየመንም ሙሉ ሥልጣን የመያዝ አቅማቸውን እያሳዩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሰላም ድርድሩን ያደናቅፈዋል፤›› ብለዋል፡፡

የየመን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዓሊ አብደላ ሳላህ ግድያ አንድምታ
የሁቲ ታጣቂዎች ዓሊ አብደላ ሳላህን ከገደሉ በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹ

 

የሁቲ መሪ አብዱልማሊክ አል ሁቲ ግን ምልከታቸው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሳላህ የፈጸሙት ክህደት ሞት እንዳስከፈላቸው ያምናሉ፡፡ ‹‹በየመን ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው ሸፍጥ አበቃ፤›› ሲሉም ለአል ማስራህ ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡ ግድያውንም ‹‹ታሪካዊና ልዩ›› ብለውታል፡፡

ታሪካዊና ልዩ የተባለው አጋጣሚ ግን ለየመን ሰላም ይዞ ይመጣል የሚል ግምት አላሰጠም፡፡ ይልቁንም በሳዑዲና በኢራን መካል ያለውን ቅራኔ ያባብሰዋል ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የ75 ዓመቱ ዓሊ አብደላ ሳላህ መገደል ለሦስት ዓመታት ያህል በከፋ ጦርነት ውስጥ የዘለቀችውን የመን የፖለቲካ ምኅዳሯን ይቀይራል የሚል መላምት አለ፡፡

ሳዑዲና ኢራን በየመን የሚያደርጉትን የውክልና ጦርነት እስካላቆሙ ድረስ በየመን ሰላም የማስፈን ተስፋ የጨለመ ይሆናል የሚሉም አሉ፡፡ ሲኤንኤን ምንጮቹን ጠቅሶ እንደሚለው፣ የሳዑዲ ዓረቢያ አልጋ ወራሽ የሳህላን ልጅ አህመድ ዓሊ አብደላ የሳዑዲ ጥምረት አካል ለማድረግ እየሠሩ ነው፡፡ ከሳላህ ጎሳ ጋርም ስምምነት እያደረጉ ነው፡፡ ይህ በኢራን የሚደገፉትን ሁቲዎች ያገለለ ስምምነት ደግሞ ዋጋ ያስከፍላል  ተብሏል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ አል ኢክባሪያ ቴሌቪዥን ማክሰኞ ከቀትር በኋላ እንዳለው፣ የሳላህ ልጅ አህመድ ዓሊ ሳላህ የአባቱን ገዳዮች ለመበቀል ጥሪ አቅርቧል፡፡ ‹‹ሁቲዎች ከየመን ተባረው እስኪወጡ ድረስ ጦርነቱን እመራለሁ፡፡ የአባቴ ደም እንደ ገሃነም ኢራን ጆሮ ላይ ይጮሃል፤›› ካለ በኋላ፣ የአባቱ ደጋፊዎች የኢራን ሁቲ ሚሊሻዎችን ከየመን ጠራርገው ለማስወጣት እንዲተባበሩት ጠይቋል፡፡ ይህ ደግሞ የመንን የማትወጣው ማጥ ውስጥ ሊከታት ይችላል እየተባለ ነው፡፡

ጥንቅር በምሕረት ሞገስ