Skip to main content
x
ቨላድሚር ፑቲን በዶናልድ ትራምፕ ላይ የበላይነት ያስገኘላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ድንገተኛ ጉብኝት
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቱን በሶሪያ ባደረጉት ድንገተኛ ጉብኝት በአንድ የአየር ኃይል የጦር ሠፈር ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ

ቨላድሚር ፑቲን በዶናልድ ትራምፕ ላይ የበላይነት ያስገኘላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ድንገተኛ ጉብኝት

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መሰንበቻውን በመካከለኛው ምሥራቅ ነውጥ የፈጠረ ድርጊት ከፈጸሙ ከቀናት በኋላ፣ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ ያልተጠበቀ ጉብኝት በማድረግ የበላይነቱን ይዘዋል፡፡ ትራምፕ የእስራኤል ዋና ከተማ ኢየሩሳሌም መሆኗን ዕውቅና በመስጠት የአሜሪካ ኤምባሲ ወደዚያ እንደሚዛወር አስደንጋጭ ውሳኔ በማስተላለፋቸው፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ተቃውሞ ተቀስቅሶባቸዋል፡፡ ውሳኔውን የተቃወሙ አገሮችም ትራምፕ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡ በዚህ ውሳኔ ሳቢያ በመካከለኛው ምሥራቅ ትራምፕን በመቃወም በደረሱ ግጭቶች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በዚህ ውጥረት መሀል ነበር ሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ሳይጠበቅ ፑቲን ሶሪያ የደረሱት፡፡ በሶሪያ ተገኝተው ጦራቸው እንደሚወጣ ሲያስታውቁ ለዓለም መገናኛ ብዙኃን ገረሜታን ነበር የፈጠረው፡፡ የብዙዎቹምን ቀልብ ስቦ ነበር፡፡

ከሶሪያ ወደ ግብፅ ካይሮ ያመሩ ፑቲን እ.ኤ.አ. በ2015 የተቋረጠው የንግድ አውሮፕላኖች በረራ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በነበራቸው ቆይታም በ30 ቢሊዮን ዶላር ስለሚገነባው የኑክሌር ኢነርጂ ተቋምና ሩሲያ በግብፅ ወደፊት ስለሚኖራት የአየር ኃይል ጦር ሠፈሮች መነጋገራቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በግብፅ ሻርም አልሼክ ሪዞርት ሲዝናኑ የሰነበቱ የሩሲያ ቱሪስቶችን የጫነ የመንገደኞች አውሮፕላን በሮኬት ተመቶ በመውደቁ በደረሰው ዕልቂት ሳቢያ፣ የሩሲያ ቱሪስቶችም ሆኑ የመንገደኞች አውሮፕላን ወደ ግብፅ መሄድ አቁመው ነበር፡፡ የፑቲን በግብፅ መገኘትና የበረራው መቀጠል መገለጹ በግብፅ ትልቅ ደስታ መፍጠሩ ታውቋል፡፡ በቱሪስት ድርቅ ለተመታችው ግብፅም ዕፎይታ አስገኝቷል ተብሏል፡፡

ቨላድሚር ፑቲን በዶናልድ ትራምፕ ላይ የበላይነት ያስገኘላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ድንገተኛ ጉብኝት
የሶሪያን ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ በጉብኝታቸው ወቅት ያገኙት ፕሬዚዳንት ፑቲን የሩሲያ ጦር አገሪቱን ለቆ እንደሚወጣ አስታውቀዋል

 

ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ደቡብ አውሮፓዊቷ ቱርክ ያመሩት ፑቲን እ.ኤ.አ. በ2017 ከፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ጋር መገናኘታቸው ተዘግቧል፡፡ ሩሲያ በሶሪያ ዘመቻዋ ወቅት በቱርክ አየር መቃወሚያ የጦር አውሮፕላኗ ተመቶ መውደቁ፣ እንዲሁም በቱርክ የሩሲያ አምባሳደር በተፈጸመባቸው ግድያ ምክንያት ሁለቱ አገሮች ተቃቅረው ነበር፡፡ ይሁንና ሁለቱ አገሮች ችግሮቻቸውን በመፍታት የጠበቀ ወዳጅነት በመመሥረታቸው የአሁኑ ግንኙነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል፡፡ ቱርክ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገር እንደ መሆንዋ መጠን፣ ይህ የጦፈ ግንኙነት አሜሪካን እያስኮረፈ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቱርክ በአሜሪካ የተጠለሉት መንፈሳዊ መሪ ፈቱላህ ጉለን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ስላደረጉ ተላልፈው ይሰጡኝ ብትልም የሚሰማት በማጣቷ፣ በአሜሪካ ተስፋ ቆርጣ በሩሲያ ላይ ሙጥኝ ብላለች፡፡ ይህም ለአካባቢው ፖለቲካ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል እየተባለ ነው፡፡  

በዋሽንግተን ፖስት ዘገባ መሠረት ፑቲን በመካከለኛው ምሥራቅና በቱርክ ያደረጉት ድንገተኛ ጉብኝት ትልቅ አንድምታ አለው፡፡ የመጀመርያው በጦርነት በወደመችው ሶሪያ እ.ኤ.አ. በ2015 ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የፈጸመችው ሩሲያ አይኤስን መደምሰሷን አስታውቀዋል፡፡ አይኤስ በሠራዊታቸው ጠንካራ ድጋፍ በመደምሰሱም ሠራዊቱ ከሶሪያ እንደሚወጣ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽብርተኝነትን የደቀነውንና ኃይለኛ ተዋጊ የሆነውን አይኤስ ከሶሪያ ጦር ጋር በመተባበር አሸንፈናል፤›› ካሉ በኋላ፣ በዚህ መሠረት የሠራዊታቸውን ለቆ መውጣት መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ስለሆነም መጠኑ ከፍ ያለ የሩሲያ ጦር ሶሪያን ለቆ ወደ አገሩ ይመለሳል፤›› ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ‹‹መጠኑ ከፍ ያለ›› የሩሲያ ጦር ሶሪያን ለቆ ይወጣል ቢሉም፣ ሩሲያ አሁንም በሶሪያ የመቆየት ዕቅድ እንዳላት ማሳያ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ በሌላ በኩል የዛሬ ሁለት ዓመት ሩሲያ ለሶሪያ መንግሥት ድጋፍ በማድረግ ዘመቻውን ስትቀላቀል የማትወጣው ‹‹አረንቋ›› ውስጥ ገባች ቢባልም፣ አይኤስን በመደምሰስ ትልቅ ሚና መጫወቷ በመካከለኛው ምሥራቅ ጉልህ ሥፍራ እንዳገኘች መጠርጠር አይገባም የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ፡፡ የአሜሪካ ሚና እየቀነሰ የሩሲያ ደግሞ እየጠነከረ መምጣቱ እንደ ማሳያም እየቀረበ ነው፡፡ የአትላንቲክ መጽሔት ዓምደኛና የፖለቲካ ተንታኝ ጁሊያ ጆፍ፣ ‹‹በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ የተለመደ ሚና ተኮማትሯል፤›› ብለው፣ የአሜሪካንና የምዕራቡን ዓለም ግዴለሽነት በሚገባ የተጠቀመችበት ሩሲያ ግን የአይኤስ አሸባሪዎችን በሚገባ በመዋጋት ሚናዋን አስፍታለች ብለዋል፡፡

የሩሲያንና የአሜሪካን መካከለኛው ምሥራቅ ሚና በንፅፅር የሚያዩ የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞችም፣ የአሜሪካ ሁለት አስተዳደሮች በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ የጠራ ፖሊሲ መከተል አልቻሉም ብለዋል፡፡ የባራክ ኦባማ አስተዳደር ቀድሞ የአሜሪካ ወዳጅ በነበሩ የዓረብ ጠንካራ መሪዎች ላይ ፊቱን አዞሮባቸዋል ይላሉ፡፡ የአሜሪካ የቀድሞ ወዳጅና ተባባሪዎች የተባሉት የዓረብ መሪዎች በፀደይ አብዮት ኤ.ኤ.አ.  በ2011 እንዲወገዱ ሲደረግ፣ የሶሪያው በሽር አል አሳድ አብዮቱን ተሻግረው እዚህ መድረስ መቻላቸው ኦባማን የሚያስወግዝ ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ ቱዴይስ ወርልድ ቪው ኢንስቲትዩት የፖለቲካ ተንታኝ፣ ‹‹የባራክ ኦባማ አስተዳደር ከዓረብ መሪዎቹ ጋር መተማመን ባለመፍጠሩ ሳቢያ ዕድሎችን ለሩሲያ አሳልፎ ሰጥቷል፤›› ብለዋል፡፡ የአሁኑ የትራምፕ አስተዳደር ደግሞ የሩሲያ ደጋፊ በመሆኑ ለሩሲያ እየሠራ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

ቨላድሚር ፑቲን በዶናልድ ትራምፕ ላይ የበላይነት ያስገኘላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ድንገተኛ ጉብኝት
ፕሬዚዳንት ፑቲን በግብፅ ባደረጉት ጉብኝት ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ በ30 ቢሊዮን ዶላር የኑክሌር ኢነርጂ ተቋም ግንባታ ኮንትራትና ሩሲያ በግብፅ ወደፊት ስለሚኖራት የአየር ኃይል ሠፈሮች ላይ መነጋገራቸው ተሰምቷል

 

አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ ለማስመሰል ያህል በሶሪያ የአየር ኃይል ሠፈር ላይ በአንድ ወቅት ሚሳይሎች ቢያዘንብም፣ አሁን ደግሞ ሶሪያን ፈጽሞ ረስቷል እየተባለ ነው፡፡ የበሽር አል አሳድ መንግሥት በኬሚካል በርካታ ዜጎቹን እየፈጀ ከቃላት ያለፈ ምንም ዓይነት ዕርምጃ አለመውሰዱ ተወስቷል፡፡ ሌላ ቀርቶ አይኤስን ሲዋጉ የነበሩ አማፂያን የአቅማቸውን ያህል ቢፍጨረጨሩም አሜሪካ ግን ረስታቸዋለች የሚሉ አሉ፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይ በኢራቅ አይኤስን ለማስወገድ አሜሪካ የተጫወተችውን ሚና ሩብ ያህል በሶሪያ ባለመወጣቷ በሩሲያ ብልጫ ተወስዶባታል ሲሉም የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ የዶናልድ ትራምፕ ረብ የለሽ ፖለቲካና የውጭ ፖሊሲ ሩሲያን እያገነናት ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡

ፒው በተሰኘ ተቋም በተሠራ የዘንድሮ የዳሰሳ ጥናት መሠረት ሩሲያ ከአሥር ዓመታት በፊት ከነበራት በጣም ያሻቀበ ውጤት አግኝታለች፡፡ በተወሰኑ የዓለም አገሮችና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት መሠረት፣ ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ ከአሜሪካ ልቃ 64 በመቶ ተቀባይነት አግኝታለች፡፡ ይህ ቁጥር በመጪዎቹ ወራት ሊያሻቅብ እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡ ዴይሊ ሳባህ በተባለ ጋዜጣ ላይ የጻፉት ቱርካዊው ምሁር ታልሃ ኮስ እንደሚሉት፣ ለብዙዎች የመካከለኛው ምሥራቅ ሰዎች የሩሲያ በስፋት በአካባቢው መገኘት ሚዛኑን ለማስተካከል ጠቃሚ ነው፡፡ ‹‹የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ አድርጎ ማወጁ የሚያፋጥነው አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖራትን ተፅዕኖ ማሳጣት ሲሆን፣ በሌላ በኩል የሩሲያን ተፅዕኖ ማግዘፍ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሩሲያ በዚህ ዘመን ቀዝቃዛውን ጦርነት ባትፈልገውም፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ተፅዕኖዋን መጨመር መፈለጓ እንደማይቀር ግን በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ተፅዕኖ በመካከለኛው ምሥራቅ በመንሠራፋት ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኃይል ሆኖ መውጣት ደግሞ የፑቲን ፍላጎት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ለዚህ ደግሞ የጦር መሣሪያዎችን ኤክስፖርት ማድረግ፣ የኑክሌር ኢነርጂ ተቋማትን መገንባት፣ በምሥራቅ ሜዲትራኒያን የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለማልማት ከእነ ሳዑዲ ዓረቢያ ጋር መተባበርና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከአሜሪካ በተቃራኒ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መካከል በተለይ በሳዑዲ ዓረቢያና በኢራን መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ማርገብ፣ ወደ ጦርነት የሚያመሩ ቀውስ ፈጣሪ ድርጊቶችን ማስቆም የሩሲያ አዲሱ ስትራቴጂ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ፑቲንና ሩሲያ ትራምፕንና አሜሪካን በመካከለኛው ምሥራቅ ብልጫ እየወሰዱባቸው እንደሆነ ዘገባዎች እያመለከቱ ነው፡፡ 

ኒውዮርክ ታምይስ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው ዘገባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች አሜሪካ በኢየሩሳሌም ጉዳይ የያዘችውን አቋም አውግዘዋል፡፡ የሲዊድን፣ የግብፅ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሣይ፣ የቦሊቪያ፣ ወዘተ አምባሳደሮች የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ የአካባቢውን ሰላም ያናጋዋል ማለታቸው በዘገባው ተካቷል፡፡ የትራምፕ ውሳኔን በተመለከተም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስቸኳይ ጉባዔ እንዲጠራም ተጠይቋል፡፡ የትራምፕ ውሳኔም ከፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ እነ ጣሊያን፣ ጀርመንና የመሳሰሉ አገሮችም ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡ የአካባቢውን ሰላም አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑን በአፅንኦት ማስታወቃቸው በዘገባው ተመልክቷል፡፡ የአሜሪካና የትራምፕ አካሄድም በሩሲያ እየተበለጠ ስለመምጣቱ ሌላው አመላካች ሆኗል፡፡  

ቨላድሚር ፑቲን በዶናልድ ትራምፕ ላይ የበላይነት ያስገኘላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ድንገተኛ ጉብኝት
እ.ኤ.አ. በ2017 የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃንን ለስምንተኛ ጊዜ እንዳገኙ የተነገረላቸው ፕሬዚዳንት ፑቲን አገራቸው በጣም በተሻለ ሁኔታ ከቱርክ ጋር ግንኙነቷን እያጠበቀች ነው ተብሏል