Skip to main content
x

የኢንዱስትሪ - ዩኒቨርሲቲ ትስስር ለሰው ኃይል ልማት

በዳዊት ወልደ ኢየሱስ

ያደጉ አገሮች ለማደጋቸው ዋናው ምስጢር ኢንዱስትሪያላይዜሽንን በአገራቸው ተግባራዊ በማድረጋቸው እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ለዘርፉ ማደግ ደግሞ አዳዲስ ቴክኖሎጂና በሙያው ብቁ የሆነ የሰው ኃይል መኖር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ አገራችንም ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለመሸጋገር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ትገኛለች፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተስፋፉ፣ የግል ባለሀብቶችም ያለውን መልካም ዕድል በመጠቀም ኢንቨስት እያደረጉ በመሄዳቸው ኢንዱስትሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከቱ መጥተዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የቴክኒክ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትም በሁሉም ክልሎች ተገንብተው ትውልድ እየቀረጹ ይገኛሉ፡፡

ስለሆነም በአገራችን እየተመዘገበ ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ በትምህርትና ሥልጠና፣ በምርምር ተቋማትና በኢንዱስትሪ መካከል የሚፈጠረው ትስስር ወሳኝ ሚና እንዳለው ይታመናል፡፡ ይኼ ደግሞ የልማት ፕሮግራሞችንና የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ከማረጋገጥ አንፃር ያደጉ አገሮችን ቴክኖሎጂዎች በሚመች መልኩ በመምረጥ፣ በመጠቀም፣ በማላመድና በተመሳሳይ ሒደቶች ውስጥ የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ለኢንዱስትሪዎች የማማከር ድጋፍ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ተቋማት ሠልጣኞችንና አሠልጣኞችን በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የተግባር ሥልጠና እንዲያገኙ ከማድረጉም በላይ በተቋማቱ መካከልም የሚፈጠረው ትስስር የትብብር ባህልን ለመፍጠር በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ያለው አደረጃጀት፣ የአመራርና የክትትል ሥርዓት ሊዘረጋለት የሚገባ መሆኑም አስፈላጊነቱ ታምኖበታል፡፡

ይሁንና ቀደም ባሉ ዓመታት ኢንዱስትሪዎች ምሩቃንን ከዩኒቨርሲቲዎች ከመቀበልና ከመቅጠር ባለፈ በትብብርና በትስስር ለመሥራት የጎላ ተሳትፎ አልነበራቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ  ባለሀብቶች ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተናገድፍላጎት አናሳ መሆን፣ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች የነባር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ብቻ መቀበል፣ ተማሪዎችን ከተቀበሉም በኋላ ምንም ዓይነት ማሽን እንዳይነኩ መከልከልና ቴክኒካል ዶክመንቶችን እንዲያዩ አለመፍቀድ ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡

ዩኒቨርሲቲዎችም ከኢንዱስትሪዎች ሳይቀራረቡ በንድፈ ሐሳብ ትምህርት ብቻ በመጠመድ ትኩረታቸውን ከቀለሙ ትምህርት ጋር አድርገውት ቆይተዋል፡፡ ይኼ ደግሞ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተማሪዎች ወደ ኢንዱስትሪው ሲቀላቀሉ እንግድነት እንዲሰማቸው አድርጓል፡፡ በመሆኑም ምሩቃኑ ሥራን ሲጀምሩ ለመልመድ የሚወስድባቸው እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ ክፍተት ይኖረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በኢንተርንሺፕና ኤክስተርንሺፕ አማካይነትዩኒቨርሲቲዎችና የኢንዱስትሪዎች ግንኙነት አዲስ ቅርጽ እየያዘ የመጣ ቢሆንም፣ አሁንም ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመቀራረብና አብሮ በመሥራት የኢንዱስትሪዎችና የዩኒቨርስቲዎችን ትስስር እውን ማድረግ እንደሚገባ ብዙዎችን ባለጉዳዮች እያስማማ መጥቷል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ በመሆናቸው ለያይቶ ማሰብ አስቸጋሪ ነውና፡፡

በመሆኑም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 22(6) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ በመንግሥትና በግል የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማትና በኢንዱስትሪው ዘርፍ መካከል ለምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት እንቅስቃሴ የሚያግዝ ምቹ የርስ በርስ ትስስርና ቅንጅታዊ አሠራር እንዲፈጠር ለማመቻቸት መመሪያ እንዲወጣ አድርጓል፡፡

በዚህ መነሻነት ቀጣናዊ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ፎረም ለየዘርፎቹ ተስማሚ የሆኑ ትስስሮች እንዲካሄዱ በመደረጉም የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በበላይነት የሚያስተባብረው የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ልማት የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስር ፎረምም ከሦስት ዓመታት በፊት ተመሥርቷል፡፡ አገሪቱ የምትፈልገውን ያህል ብዙ ርቀት መጓዝ ባይቻልም!

የፎረሙ አባላትም በኢንጂነሪግ ዘርፍ ትምህርት የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የዘርፉ ኢንዱስትሪዎችና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ተቋማት ሲሆኑ፣ ዋነኛ ትኩረቱም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ መስክ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና ሽግግር ሆኖ የጋራ ምርምር፣ ማማከር፣ ኢንተርንሺፕ፣ የግብይት ክህሎትን መፍጠርና የመሳሰሉትን ተካተዋል፡፡

መንግሥት ለመሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልዩ ስትራቴጂያዊ ትኩረት መስጠቱን ተከትሎ፣ የዘርፉን ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ይህ ፎረም አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡

በተመሳሳይም የዘርፉን ሁለንተናዊ ልማት ለመደገፍ በሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ በምርጥ ተሞክሮ ትግበራ፣ በምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በቴክኒክና ምክር አገልግሎትና በፋሲሊቴሽን ሥራዎች አፈጻጸም መልካም ጅምሮች ቢኖሩም ከሚፈለገው ፈጣንና ቀጣይ ዕድገት አንፃር በሁሉም መስኮች ብዙ ለመሥራት መንገድ እንደሚከፍትም ይጠበቃል፡፡

በዚህ መሠረት የሰው ኃይል ልማት፣ ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስርና በሌሎች የዘርፉ የልማት ፖሊሲ የተለዩ ወሳኝ ጉዳዮች በተቀናጀ መልኩ ወደ መሬት በማውረድ የተሳለጠ ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ ያስችል ዘንድ በተለዩት የኢንዱስትሪ ልማት ኮሪደሮች ላይ ያተኮሩ ንዑስ የቀጣና ዩኒቨርሲቲ- ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረሞች ማቋቋም ወሳኝ በመሆኑ፣ ዘርፉን እንዲያስተባብር ሥልጣን በተሰጠው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዘርፉ በተለዩ ስድስት ንዑስ የልማት ቀጣናዎች አደረጃጀቱን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በእነዚህ ሦስት ዓመታት የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ስድስት ቀጣናዎችን በመለየት፣ በአካባቢው የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰርና ስምምነት እንዲፈጥሩ የጋራ የመግባቢያ ሰነድ በማፈራረም፣ በምሕንድስ ዕጩ ምሩቃንንና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ተቋም ተማሪዎችን በኢንዱስትሪዎች ኢንተርንሺፕ እንዲወጡ በማግባባት፣ በክልሎች የሚገኙ ኢንዱስትሪ ቢሮዎች  ትስስሩን እንዲመሩት በማድረግና የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉ በማድረግ መልካም የሚባል እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡

ትስስሩ የሚከናወነው በስትራቴጂያዊ ጥናት በተለዩ የኢንዱስትሪ ልማት ኮሪደሮች ላይ በማተኮር ሲሆን፣ ለዚህም የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ልማት ዘርፍ የኢንዱስትሪ - ዩኒቨርሲቲና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ትስስር ፎረሞች  ስድስት ንዑሳን ቀጣናዎች አደራጅቷል፡፡

ስድስቱ ንዑሳን ቀጣናዎችም የአዲስ አበባ ቁጥር 1 እና ቁጥር 2፣ የኦሮሚያ፣ የትግራይ፣ የአማራ፣ የድሬዳዋ ከተማ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ልማት ዘርፍ ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረም መሆናቸው ታውቋል፡፡ 

በእነዚህ ንዑሳን ቀጣናዎች የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምገምና በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት የጋራ መግባባት ለመፍጠር የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ምሁራንንና የኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጆችን ባለፈው ጥቅምት ጋብዟል፡፡

በሪፖርቱም በ2009 በጀት ዓመት በትስስሩ መሠረት በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት 811 የኤሌክትሪካል፣ ኮንትሮል፣ ኮሙዩኒኬሽንና ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ኢንተርኒሺፕ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የወጡ ሲሆን፣ በሁለተኛው መንፈቀ ዓመት ደግሞ 636 የመካኒካል ማኑፋክቸሪንግና ኤሌክትሮ መካኒካል  ተማሪዎች ወደ ተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ወጥተው ልምምድ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይም በትስስሩ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን በምርትና ምርታማነት ያለባቸውን ችግሮች ለመለየት በተደረገው እንቅስቃሴ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ስምንት ችግሮች ተለይተው በምርምር ሥራዎች እየተፈቱና በመፈታት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የጂማ ዩኒቨርሲቲም በበኩሉ ከ65 በመቶ በላይ ማገዶ ቆጣቢ ተቋማዊ ምድጃ፣ ለሕክምና መሣሪያዎች የሚውል የውኃ ማጣሪያ አልምቷል፡፡ በቀጣይም ለማልማት ከለያቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል የሰውነት ስብ መጠን መለኪያ፣ የኩላሊትና ስኳር ሕመም መመርመሪያ ተጠቃሾች መሆናቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በአንፃሩም አፓረንትሺፕና ኢንተርንሺፕ ወደ ተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ተመድበው ለሚላኩ ተማሪዎች የክትትል ማነስ መኖሩ፣ ከዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪዎች ለተማሪዎች የሚሰጥ ማበረታቻ በቂ አለመሆንና አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ምንም ዓይነት ማበረታቻ ለተማሪዎች አለመፈጸማቸው፣ ተማሪዎች በኢንዱስትሪው ልምድ ለመቅሰም ተቀራርበው አለመሥራታቸው፣ አብዛኞቹ ተማሪዎች ለኢንዱስትሪው ችግር ፈቺ የሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ  አለማተኮራቸውና ኢንዱስትሪውም ወጪ አለማጋራታቸው የሚሉት በሪፖርቱ እንደዋና ዋና ችግሮች የተጠቀሱ ናቸው፡፡

ስለሆነም ኢንዱስትሪ- ዩኒቨርሲቲና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና  ትስስሩ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ በመሆኑ የሁሉንም አካል ርብርብ ይሻል፡፡ ምክንያቱም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ለኢንዱስትሪዎች የማማከርና የምርምር እንዲሁም ባለሙያዎችን የማስተማር ተግባርን ሲፈጽሙ፣ የዩኒቨርሲቲም ሆነ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ተቋማት ተማሪዎች ደግሞ በኢንተርንሺፕ ከኢንዱስትሪዎች የሙያና የክህሎት ሥልጠና እንዲሁም በሥራ ምደባን ሲያገኙ፣ የኢንዱስትሪ- ዩኒቨርሲቲ ትስስሩ የተጠናከረና ተመጋጋቢ ከመሆኑም በላይ አገሪቱ የምትፈልገውን በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የዳበረ የሰው ኃይል ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ አሁን ያለውን የልማት እንቅስቃሴ የሚያፋጥንላት አስተማማኝ ኃይልንም  ታገኛለች፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡