Skip to main content
x

ይድረስ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መጪው ዕጣ ለሚያስጨንቃቸው ሁሉ

በገነት ዓለሙ

      አገራችን ውስጥ ምሬት ኩፍ ብሏል፡፡ ንብረት እስከ ማጥፋት የተቆጣና ገዢውን ክፍል ውረዱልን እስከማለት የደፈረ ተቃውሞ አስገምግሟል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ለህልውናችን አደጋ ነው ብለው፣ ይህንንም ፖሊሲያቸውን የሕዝባቸው ግንዛቤ ያደረጉ፣ የኢትዮጵያን መጠንከር ከሥጋት የሚቆጥሩና ከዚህ ቀደምም የኤርትራን ትግል በማዳከሚያነት ሲጠቀሙት የኖሩ፣ ስለዚህም የኢትዮጵያ መተራመስ ይጠቅመናል ያሉ የውጭ ጠላቶችም ዕጣን በማጫጫስ ላይ ናቸው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥትም ያልተጠበቀ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕግ አውጇል፡፡ ይህንን ሕግ የተቃወሙ ተቃዋሚዎችም አሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ ሕጋዊነቱን (ሌጅተማሲውን) አጥቷል፣ የመተማመን ምርጫ ያካሂድ ያሉም አሉ፡፡

በሌላ ጎን የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ጉባዔ ተቃዋሚዎችና መንግሥት ተቀራርበው እንዲነጋገሩ አደርጋለሁ የሚል ድምፅ አሰምቷል፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ስብስብ የአገሪቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ጥያቄ ያላቸው ወገኖች፣ ወዘተ የተካተቱበት መወያያ መድረክ እንዲፈጠር አሠራለሁ ማለቱን ሰምተናል፡፡

መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም በተከፈተው የተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ደግሞ፣ ኢሕአዴግ ስላሰባቸው ወይም ስላሰበልን ለውጥ አንዳንድ ጉዳዮች ጠቁመውናል፡፡

‹‹….. አገራችን በምትከተለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት በመመራት ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በድምሩ ለአሥር ጊዜ አገራዊ፣ ክልላዊ፣ ከባቢያዊ ምርጫዎች›› መካሄዳቸውን፣

‹‹በእነዚህ ምርጫዎች የብዙ ፓርቲዎች ተሳትፎ የነበረ ሲሆን በተለይ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች እንደተከሰተው በምክር ቤቶቻችን፣ የገዢው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት ያለበት ሁኔታ …›› መስተዋሉን፡፡

‹‹ይህ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደ ምርጫ የሕዝብ ድምፅ ያስገኘው ውጤት እንደሆነ ባያጠያይቅም ተቃዋሚዎችን የመረጡ የኅብረተሰብ ድምፆች በመኖራቸውና በአብላጫ ድምፅ ወንበር የማግኘት የምርጫ ሥርዓታችን መሠረት በአገራችን ወሳኙ የሥልጣን አካል በሆነው ምክር ቤት የማይወከሉ ድምጾች እንዲኖሩ›› ማድረጉን ገልጸው፣

‹‹ይህን የመሰለው ሁኔታ ሥርዓታችን ተረጋግቶ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትል በመሆኑ በተቻለ መጠን፣ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በማስፋትና በቀጣዩ ምርጫም በሕግ ማዕቀፍ በተደገፈ አኳኃን የሕዝብ ምክር ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰሙባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ በማድረግ መስተካከል ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

      በአጠቃላይ የአብላጫ ድምፅ መመዘኛው የተበለጡትን ከውክልና ውጪ ስለሚያደርግ፣ ይህንን እንከን ለማረም ሕግ ተሻሽሎ በድምፅ የተበለጡም ውክልና የሚያገኙበት ዕድል በመጪው ምርጫ ይኖራል ተብሏል፡፡ ሲቪክ ማኅበራትንም ስለማካተት የታሰበው ነገር ተነግሮናል፡፡ የሕግ አስፈጻሚው አካል ማለትም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም ካቢኔው እንደገና እንደሚደራጅም ተገልጾልናል፡፡ በምርጫ ወደ መወከል በሚያደርሰው ምኅዳርና ተቋማዊ አስተናባሪነት ላይ ስላለው ወሳኝ ችግር ምንም አልተነገረንም፡፡

ምክር ቤታዊ ውክልናን የማስፋት መፍትሔ ዴሞክራሲን ለማጥለቅም ሆነ ገዢውን ፓርቲና ተቃዋሚዎቹን ለማቀራረብ በእርግጥ በቂ ነው ወይ? ቁጣን ወደ እርቅ ለውጦ በዴሞክራሲያዊ ሰላም ወደፊት የመራመድ ተግባር በአሁኑ ጊዜ የደቀነው ዝቅተኛው ወይም መነሻ የጋራ መገናኛ ምንድነው? በእኔ በኩል የሚከተለው ይታየኛል፡፡

የአገሪቱ ፓርቲዎች ተገናኝተው በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን በአግባቡ የማቋቋም ተግባርን የጋራ አደራቸው አድርገው መግባባታቸው፣ ለዚህም የሚሆን መርሐ ግብር መንደፋቸውና አጠቃላይ የእርቅ መንፈስን ማወጃቸው ቁልፍ መነሻ ነው፡፡ እዚህ መነሻ ላይ በመቆም፣

ሀ) • ‹‹የሕዝብ ፀር›› ‹‹የጥፋት መልዕክተኛ››፣ ‹‹ዘረኛ››፣ ወዘተ ከሚሉ መፈራረጅ የመራቅና፣ ፍረጃዎችን ከመገናኛ ብዙኃን መድረክ የማስወገድ ስምምነት ማድረግ፣

 • ከመጠማመድና ከጥላቻ በፀዳ መንፈስ ለአገሪቱና ለሕዝቦችዋ ግስጋሴና ሰላም ሊሠሩ የሚፈልጉ በትጥቅ ትግልም ሆነ ከትጥቅ ትግል ውጪ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች ወደ እርቅ እንዲመጡ መጋበዝ፣
 • በአገር ውስጥም በእስር ላይ ያሉ በፖለቲካ ወንጀል ታስረዋል የሚባሉ ሰዎችን መፍታት፣
 • በአጠቃላይ በፓርቲዎችም ሆነ በማኅበረሰቦች ግንኙነት ውስጥ ያሉ ጥርጣሬን፣ ፍራቻን፣ ሥጋትን፣ መሸካከርን የሚፈረካክሱና የሚያጥቡ በነፃ ተሳትፎ የደመቁ እንቅስቃሴዎች ማካሄድ፣
 • የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሥራ አስፈጻሚዎች የሕዝብ ከበሬታና ተሰሚነት አግኝተው፣ የኢኮኖሚና የዴሞክራሲ መርሐ ግብሮችን ለማሳካት እንዲችሉ ለሕዝብ ጥቆማ ቦታ በሰጠ ሁኔታ በሕዝብ ዘንድ የታመነባቸውን (ከተቃዋሚም ከፓርቲ ፖለቲካ ውጪ ከሆኑም ውስጥ) እንዲያካትት ማድረግ፣
 • ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች የሚገናኙበት በሩ ለአዲስ መጪዎች ያልተዘጋ በዴሞክራሲ የእርቅ መቃናት ላይ የሚሠራ የመገናኛ ብዙኃን የአየር ጊዜም፣ የተሰጠው መድረክ ማቋቋም፣

ለ) • ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና በሰላም የመቃወም መብቶች ላይ ከሕግ ውጪ የሚደረግን የሹም አፈና በፈጣን ተጠያቂነት መከላከል ጥያቄዎችና ቅሬታዎች በውይይት በድርድርና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ከሚስተናገዱ በቀር በወንጀልና በጉልበት እንዳይደፈጠጡ ነቅቶ በመጠበቅና ይህንኑ በደል በመፋረድ ላይ መስማማት፣ ይህንንም የሕዝብ ግንዛቤ ማድረግ፣

 • ከዴሞክራሲ መብቶች ተከባሪነት ጎን፣ የአደባባይ ሠልፎችንና ስብሰባዎችን በሰውና በንብረት ላይ ጥቃት መፈጸሚያ መሣሪያ ማድረግ ነውረኛ ተግባር መሆኑንና በሕግ የመጠየቁን ተገቢነት ሕዝብ ከልብ እንዲቀበለው ማድረግ፣
 • ለዴሞክራሲያዊ የሕዝብ መነቃቃት የማይበጁ ድንጋጌዎችን የመሰረዝ፣ የማሻሻል ወይም አዲስ በማውጣት የመተካት ሥራ ማካሄድ፣ በተለይም ከሁሉም በላይ ደግሞ ዝሆን የማይጥሰው ጫካ የወረሰውንና ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚገኘውን የፀጥታ ኃይሎች የ‹‹ኃይል አጠቃቀም›› ሥርዓት እንደገና መመርመር፣ መልሶ መላልሶ መፈተሽና በዝርዝርና በነቂስ አፍታትቶ መደንገግ (በዚህ ውስጥ በተቃውሞ ትዕይንት ውስጥ የውኃ ግፊት፣ አስለቃሽ ጪስ፣ ቆመጥና አፈሳ ማካሄድን አግባብ የሚያደርጉ ከዚህም አልፎ በሰው ላይ እውነተኛ ጥይት መተኮስን የሚፈቅዱ ፀጥታ የማስከበር ሁኔታዎችን በሕግ አፍታትቶ መወሰን፣ ተጠያቂነትን ማበጀትና ሳይጠየቁ መቅረትን መዋጋት፣
 • በነፃ መደራጀትንና ነፃ ንቁ ተሳትፎን ማነቃቃት፣ እንዲሁም በሚዛናዊነት መከራከርን፣ መተንተንና መዘገብን ማጎልመስ ከዚሁ ጋር የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ከገዢው ፓርቲ ልሳንነት አውጥቶ የኅብረተሰቡ ልሳንና መገልገያ ማድረግ፣
 • አወዛጋቢ የአከላለል ችግሮች በደንብ ተብላልተው፣ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታና አንጀት አግኝተው እንዲፈቱ መሥራት፣
 • የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን፣ የፌዴራል አወቃቀሩንና ሰንደቅ ዓላማውን ጭምር የአንድ ፓርቲ ሥራ አድርጎ እስከመቁጠር የሄደ የመግባባት ችግር ስላለ፣ ይህንን ለመዝጋት አገር (ኅብረተሰቡ) እንዳለም ሆነ አሻሽሎ በቀጥተኛ ድምፁ የራሱ የሚያደርግበትን ተግባር ለወደፊት ቀይሶ ለዚሁ የሚረዱ ግምገማዎችና ጥናቶች እንዲካሄዱ ማድረግ፣
 • የአገሪቷ ሕዝቦች የጋራ ታሪክ ተጣርቶ የሕዝብ ንቃት ለመሆን መቻል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጥበቅ ያለው ጠቀሜታ ከወዲሁ ታውቆ፣ ያለፖለቲካዊ ወገናዊነት የአገሪቱን ሕዝቦች ታሪክ መርምሮና አደራጅቶ የሚያቀርብ ግብረ ኃይል ማቋቋም፣

ሐ) • መራራ ስሜቶች ሟሽሸው፣ እርቃዊ ስሜት እየተቃና በመጣበት ደረጃ ላይ በገለልተኝነታቸውና ለሥራ አደራቸው በመታመን ጥንካሬያቸው በተመረጡ አባላት የተሞላ የምርጫ አስፈጻሚ አውታር ከላይ እስከ ታች ማደራጀትና ሕዝብ አመኔታ የነፈጋቸው የምክር ቤቶች አባላት (በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ) ቢኖሩ የማሟያ ምርጫ ማካሄድ፣

 • የአገሪቱ የመከላከያ፣ የመረጃና ደኅንነት፣ የዳኝነት፣ የፖሊስና የዓቃብያነ ሕግ አውታራት፣ የዋናው ኦዲተር፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በፖለቲካዊ ወገናዊነትም ሆነ በንቅዘት ሳይሰናከሉ ለአደራቸው በመታመን ላይ እንዲተጉ መሥራት፣
 • ምርጫን ነፃና ፍትሐዊ ለማድረግ በሚደረግ ዝግጅት ውስጥ ምርጫ የሞት ሽረትና የዝርፊያ ግብግብ ወደ መሆን ወርዶ ገና ያልጠናውን (ይልቁንም ያልለየለትን) የዴሞክራሲ ግንባታ እንዳይጎዳ የመጠበቅና የማጎልመስ ተግባር፣ አጠቃላይ ኅብረተሰቡንና ሁሉንም አካባቢዎች ያደረሰ ልማትን የማፋጠኑ ተልእኮ ገና የሁሉንም ፓርቲዎች ርብርብ የሚሻ መሆኑን ያስተዋለ የጋራ መርሐ ግብር መንደፍ፣
 • የሰብዓዊ መብት ተቋማት በየትም ሥፍራ ተንቀሳቅሰውና ቅርንጫፋቸውን አስፋፍተው የገመና መስታወት እንዲሆኑ ክልከላዎችን፣ ገደቦችንና መሰናክሎችን ማንሳትና ነፃነታቸውን ማስፋት፣
 • የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው የተቃውሞም ሆነ ሥልጣን ላይ ያለ ፖለቲካ አጫፋሪ ከመሆን የሚርቁበት መንግሥትና ቡድኖችም ቤተ እምነቶችን መሣሪያ ለማድረግ ከመታከክ የሚቆጠቡበትን የተግባር ጨዋነት ማጎልበት፣

መ) • መንግሥታዊ የሕዝብ አገልግሎት አውታራት እንደ ተቋም ከፖለቲካ ወገናዊነት ነፃ ይሁኑ ማለት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የፖርቲዎች የምልመላ መሻሚያ ሜዳ መሆናቸውም በሥራ ላይ ጉዳት አድርሷልና ሠራተኛን ሁሉ አባል እያደረጉ የመንግሥት መሥሪያ ቤትን ወደ ፓርቲነት ከመቀየር ይልቅ፣ ህሊናን በመርታት ላይ መሥራት ለሁሉም የሚበጅ መሆኑ ላይ መግባባት፣

 • የሥልጣንና የፍትሕ ምሰሶ በሆኑ ተቋማት ውስጥ የተሰማሩ፣ ማለትም በቀጥታ የፓርቲ አባል መሆን የማይችሉ ሠራተኞችም ፓርቲ ከመቃወምና ከመደገፍ መብታቸው በገዛ ውዴታቸው ተቆጥበው ወደ ገለልተኛነት ማዘንበላቸው፣ ለዴሞክራሲና ለእኩል አስተዳደር መጠናከር ትልቅና የቅርብ ጠቀሜታ እንዳለው እንዲረዱ መሥራት፣
 • በሕዝብ አገልግሎት ውስጥ የሥራ ኃላፊነትንና ተገልጋይን አክብሮ በቅልጥፍናና በጨዋነት ሥራን የማከናወን ትጋት ከጊዜያዊ መነቃቃት ያለፈ ወረትን የተሻገረ ባህርይ ውስጥ የገባ ምግባር ሆኖ እንዲዘልቅ፣ የሥራ ስሜትን ለማደስ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን ዘርግቶ መረባረብ፣
 • የቴሌ ልዩ ልዩ የግንኙነት አገልግሎቶችን፣ የሥራ አስፈጻሚው አካል ባሻው ጊዜ እንዳያቋርጥና የሰብዓዊ መብትን ለመጣስ እንዳያውላቸው ለመከታተልና ለመጠየቅ የሚያስችል የአወቃቀርና የሕግ  መጠበቂያ ማበጀት፣
 • በመሬት ይዞታ ሥርዓቱ ላይ አስፈጻሚው የመንግሥት አካልና ቅርንጫፎቹ የመሬት አገናኝነትን እንዳሻቸው እንዳያዙበት (መሬት የመንግሥታዊና የግል ነቀዞች መቀራመቻ እንዳይሆን) የሚያስችል የአወቃቀር፣ የግልጽ አሠራርና ከሕዝብ ዓይን ውስጥ የማስገባት ማሻሻያ ማድረግ እንዲሁም መሬቶችን ለታወቁ ዓላማዎች የተመደቡና የማይነኩ ጥብቅ ብሎ መለየትና በዚያ ውስጥ ተወስኖ መሥራትን ተግባራዊ ማድረግ፣
 • በእነዚህ ተግባሮች ላይ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ከሞላ ጎደል መገናኘት ከቻሉ በወጣት የተሞላው ኅብረተሰባችን እነዚህን ተግባሮች ማትኮሪያ፣ ፍላጎቶቹና ጥያቄዎቹ ካደረጋቸው የአገራችንና የሕዝቦቿ ዕጣ ብሩህ እንደሚሆን ተስፋችንም ምኞታችንም ነው፡፡

የተስፋችንና የምኞታችን ተጨባጭነት ‹‹ሀ›› ብሎ የሚጀምረው የኢትዮጵያ ችግሮች በአንድ ፓርቲ ገዢነትና መንከውከው ወይም መፍጨርጨር ብቻ ወይም በማማረር ወይም በጠመንጃ ኃይል እንደማይቃለሉ ከማወቅ ነው፡፡ እስካሁን በ25 ዓመታት ውስጥ ኢሕአዴግ ብቻውን ዴሞክራሲን በመገንባት በኩል ያደረገው ጥረት ወይም አደረግሁት ያለው ጥረት ለራሱምና በራሱም መለኪያ እንኳን የሚፈልገውንና የሚፈለገውን ያህል ውጤት አላስገኘም፡፡ የጠላትነት ፖለቲካ ሕዝብ ድረስ ዘልቆ ማወኩ እየሰፋና እየከፋ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱንና ሐሳብን በመግለጽ በኩል የነበረው ውስን ነፃነት በድኅረ 1997 ዓ.ም ምርጫ ወደኋላ መመለሱ የዚህ ምስክር ነው፡፡ አንዱ ማስረጃ ነው፡፡

በጥላቻና በፍጥጫ መስክ ላይ ዴሞክራሲ ሊገነባ አይችልም፡፡፡ ኢሕአዴግ ከሥልጣን ከወረደ ወይም አንድ ወይም ሌላ ፓርቲ ሥልጣን ላይ ከወጣ አገሪቷ ትበታተናለች፣ የብሔር ብሔረሰቦች መጨፋጨፍ ይመጣል የሚል ፍርኃትና እምነት ይዞ የሚታመስ አገር ዴሞክራሲን ሊገነባ አይችልም፡፡ እነዚህን ፍራቻዎች፣ ጥርጣሬዎችና ጥላቻዎች እንዲጠናከሩ የሚሹም ዴሞክራሲን በጭራሽ ሊያጎለብቱ አይችሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ኃይሎች በለየለት ጠላትነት ውስጥ ተጠማምደውም ሆነ ላይ ላዩን እየተሳሳቁ የሚገኙበት አጥፊ ሁኔታ መቀየር አለበት፡፡ ከ1997 ዓ.ም የምርጫ ጊዜ ጀምሮ በተለይም በዚያ ጊዜ አካባቢ ይባል እንደነበረው የገዢው ፓርቲና የተቃዋሚ አብሮ መሥራት ዛሬም ሲበዛ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አብሮነት በሥልጣን ላይ ቢገለጽም ጥሩ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አብሮ የመሥራት ቅድመ ሁኔታ ሊሆን አይገባም፡፡

በአሁኑ ወቅት ከልዩነት ጋር ተቻችሎ አብሮ የመሥራቱ ሒደት ከአንድ ትልቅ ኮንፍረንስ ተነስቶ ዓላማው የሰፋ የፓርቲዎች የጋራ መድረክ በመፍጠር፣ በአገሪቱ ልዩ ልዩ ችግሮች ላይ በመመካከርና በመተጋገዝ ሊጀምር ይችላል፡፡ ፓርቲዎች የገዛ ራሳቸውን ነፃ ህልውና ይዘውና በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያቸውም አብበው መቆም ያለባቸው መሆኑ ሳይረሳና ሳይድበሰበስ፣ ፓርቲዎች ቅርበታቸውንና የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን እያሻሻሉና ከሕዝቦች ጋር እየተጣጣሙ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ብዙ ተግባር ሊያከናውኑ ይችላሉ፡፡ የሚቀጥለውን ምርጫም ሆያ ሆዬው፣ ቱልቱላውና ክብረ በዓላዊ ባህርይው ያሰለቸ ግርግርና የበጀት ጥፋት ከመሆን አትርፈው እርስ በርስ ተባብረው የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታውን ለማሳካት የሚጓዙበትና የመላውን ሕዝብ ይሁንታ ያገኘ ርብርብ መክፈቻ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ የሚቀጥለው ምርጫ ማለት ከሕገ መንግሥቱ ውጪ መሆን ወይም ሕገ መንግሥቱን ማከምም ሆነ መዝለል ሳያስፈልግ ከ2012 ዓ.ም በፊት ማድረግም ይቻላል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 ተፈጻሚነት ይህንን ይፈቅዳል፡፡

ወደዚህ የ2012 ዓ.ም ምርጫም በሰላም ለመድረስና ከዚያም በፊት ሊኖር ስለሚችል ምርጫ ለማውራት የፖለቲካ ኃይሎች አብሮ መሥራት መጀመር የሚያስገድደው፣ በአገሪቱ ላይ ያንዣበበውን ማንም ወገን ለብቻው በአሸናፊነት የማይወጣበትን አደጋ መገንዘብ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የግድ አብሮ መሥራት አለባቸው፡፡ አብሮ በመሥራት የጨዋታው ሕግ ላይም መስማማት ይገባቸዋል፣ ማፈርም የለባቸውም፡፡

የፖለቲካ ኃይሎች አብሮ መሥራት ከጀመሩ ፀረ ዴሞክራሲያዊና አድሏዊ የሆኑ ችግሮችንና መሰናክሎችን ማቃለል አያስቸግርም፡፡ የአንድ ፓርቲ ባህርይ በራሱ የውስጥ ማንነት ብቻ ሳይሆን በተቀናቃኙም ባህርይ የሚወሰን ነውና በጎ ግንኙነት የሁለት ወገን የጠባይ መሻሻልን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ በብሔራዊ መግባባት ውስጥ እየተለያዩና እየተከራከሩ፣  እየተቻቹና እየተራረሙ ሕዝቦች በስሜት የሚሳተፉበት የዴሞክራሲ፣ የፍትሕና የኢኮኖሚ ጉልህ ዕርምጃ ሊያቀጣጥሉ እንደሚችሉ አያጠራጥርም፡፡ የዚህ ምክንያት በሕዝቦች ውስጥ ሲታዩ የቆዩት የመሸካከር፣ የመፈራራት፣ የመጠራጠርና የዝምታ ገጽታዎች ዞሮ ዞሮ ከፖለቲካ ቡድኖች የሚመነጩ ነበሩና፣ የፖለቲካ ኃይሎች አብሮ መሥራት በቀጥታ የብሔር ብሔረሰቦችንና የሕዝቦችን መተማመን ይዞ ይመጣል፡፡ ሌሎች ጥቅሞችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፣

 • የመንግሥት ከግጭቶችና ከሁከቶች ጋር መተናነቅ ይመነምናል ተቃውሞን ለመከላከል የሚውለው የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የጊዜ አቅም አቅጣጫውን ቀይሮ በተሃድሶና በለውጥ ላይ ያተኩራል፡፡ ከዚህ አይነት የመንግሥት ወጪ ጋር ተያይዞ ከሚመጣ የዋጋ ግሽበት ለመዳን ይቻላል፡፡
 • በትምህርት ጥራት ውድቀት በወጣት አጥፊነት ለዕፅ ተገዢነት፣ በኤድስ ሥርጭት ላይ ፈጣን መዳከም የሚያስከትል ለውጥ ስሜት ይቀጣጠላል፣ ወዘተ…

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡