Skip to main content
x
ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባዔ የተሰጠ መግለጫ

ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባዔ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ አስመልክቶ ታኅሣሥ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባዔ አማካይነት መግለጫ አውጥታለች፡፡ መግለጫውን ብፁዕ እምብፁዓን ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ከመንበራቸው አቅርበውታል፡፡ ሙሉ ይዘቱ የሚከተለው ነው፡፡  

ለመላው ካቶሊካውያንና በጎ ፈቃድ ላላቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ የእግዚአብሔር ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን፡፡

እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባዔ አባላት በዚህ ሳምንት በሚጠናቀቀው በ34ኛው መደበኛ ጉባዔያችን ስለአገራችን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ከገዳማውያን፣ ገዳማውያት፣ ካህናትና ምዕመናን በያሉበት በቅዳሴ ጸሎት ስናደርስ ሰንብተን ዛሬ የሚከተለውን መልዕክታችንን ለማስተላለፍ ወደናል፡፡

ከሁሉም በፊት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት በጠፋው ክቡር የሰው ሕይወት የተሰማንን መሪር ሐዘን እየገለጽን፣ የሞቱ ወገኖቻችንን ቸሩ እግዚአብሔር አምላክ በመንግሥተ ሰማይ በምሕረቱ እንዲቀበላቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጣቸው ጸሎታችንን እንቀጥላለን፡፡ እንደዚሁም በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችንና ሀብት ንብረታቸው ለወደመባቸው ከልብ የመነጨ ሐዘናችንን እንገልጻለን፡፡

የአገራችን የኢትዮጵያ ሕዝቦች በብዝኃነት ውስጥ ያለውን አብሮ ተከባብሮ፣ ተባብሮ የመኖርን ምስጢር ብቻ ሳይሆን ይህ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ድንቅ የሆነ ፀጋ በውጭ ኃይሎች እንዳይበረዝ በጋራ በመከላከል የነፃነት ተምሳሌት በመሆን እንድንጠራ አድርገዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህን መንፈሳዊና ማኅበራዊ እሴቶቻችን አደጋ ላይ የሚጥል ፈተናዎች እየተጋረጡብን መጥተዋል፡፡ ቀጣናችን ዘርፈ ብዙ በሆኑ ምክንያቶች ቢሆንም ግን በብሔርተኝነት የሚገለጹ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ማንነታችንን የሚፈታተኑ ግጭቶች እየተከሰቱ ናቸው፡፡ በነዚህ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ወገኖች ለሕልፈተ ሕይወት፣ የተረፉት ደግሞ ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ሆኗል፡፡

እንደሚታወቀው በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለረዥም ዘመናት ልዩነታቸውን የአንድነት ምንጭ አድርገው በሰላምና በአንድነት፣ በመደጋገፍና በፍቅር ሲኖሩ ቆይተዋል፡፡

ይህም ሁኔታ ስላሳሰበን በምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባዔዎች ኅብረት አባል አገሮች ታንዛኒያ፣ ማላዊ፣ ዛምቢያ፣ ዑጋንዳ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራና ታዛቢ አገሮች ጂቡቲና ሶማሊያ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከእግዚአብሔር ስለተሰጠው የብዝኃነት፣ የሁሉም የሰው ልጅ እኩል ክቡርነትና ሰላም ስናመስግን፣ በኃጢአት ምክንያት ይህ ታላቅ ፀጋ እንዳይወሰድብንም ስንፀልይ ከርመናል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባዔን በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. ለማካሄድ ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ ጉባዔው የሚያውጠነጥነው ‹‹በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ሕያው ብዝኃነት፣ ሰብአዊ ክብርና ሰላማዊ አንድነት ለአመሰያ ሀገራት›› የሚል መሪ ቃል ላይ ነው፡፡ ይህን መሪ ቃል የመረጡበት ዋናው ምክንያት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየታዩ ያሉ የብሔርተኝነት ጉዳዮች ወደ ዘረኝነት ሊያመሩ የሚችሉ አዝማሚያዎች በመገንዘብ ነው፡፡

ይህንን አስከፊ ክስተት ለመቀልበስና አካባቢውን ዳግም ወደነበረበት የሰላምና ተከባብሮ አብሮ የመኖር ቀጣና ለመመለስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ለቀጣናው ሕዝብ በተለይም ለአገራችን ሕዝቦች እርቀ ሰላሙ፣ እንዲሁም ደግሞ ኅብረቱ ተፋቅሮ የመኖር ፀጋ ተመልሶ እንዲመጣ በማድረግ ሒደት የበኩሏን ነቢያዊና ሞራላዊ ኃላፊነት ትወጣ ዘንድ እንደሚገባት ትገነዘባለች፡፡ ይህንን አንገብጋቢ ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት ትችል ዘንድ ደግሞ በሒደቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሚናና ድርሻ ምንነትና አስፈላጊነት ላይ በጥልቀት መመርመርና ማሰላሰል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የምሥራቅ አፍሪካ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔዎች ኅብረት ይህንን ጉባዔ ጠርቷል፡፡ በኢትዮጵያም እንዲካሄድ ምልዓተ ጉባዔው ከአራት ዓመት በፊት ወስኗል፡፡ ጉባዔው በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በጥልቀት እንደሚወያይ ይጠበቃል፡፡ በአመዛኙ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡

በ19ኛው የኅብረቱ ጉባዔያችንና ‹‹በእግዚአብሔር ላይ የተመሠረተ ሕያው ብዝኃነት፣ ሰብአዊ ክብርና ሰላማዊ አንድነት ለአመሰያ አገራት›› በሚለው መሪ ቃል መሠረት የቀጣናውን ሁኔታ በጥልቀት መመርመር፣

  • ሕያው ብዝኃነት በቀጣናው ለሚኖሩ ሕዝቦች አብሮ የመኖርን ጉልበት፣ ተስፋ እንደሆነ፣
  • ለሁለንተናዊ ዕድገት ብዝኃነትን ስለመቀበል፣
  • ሰብአዊ ክብርን ለእውነተኛ አንድነት ስለማስተዋወቅ፤

በመሆኑም የአገራችንም ተጨባጭ ሁኔታ የዚሁ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አካል በመሆኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን የብዝኃነት ፀጋዎች ሁኔታዎች ጎልተው መሰማትና መታየት ጀምረዋል፡፡ የብዝኃነት እሳቤዎች ምንጩ ከእግዚአብሔር ስለሆነ መልካም ነው፤ ሆኖም በአንዳንድ አጋጣሚዎች እነዚህን የብዝኃነት እሳቤዎችን ተከትለው የሚነሱ ጥያቄዎችን በጊዜና በአግባቡ አለማስተናገድ የሚፈጥረው የፍርኃት ጫናና የእርስ በርስ ጥርጣሬ ቢስተዋልም የሰው ልጅ ሕይወት ግን ከማንኛውም ጥያቄና ፍላጎት በላይ በእግዚአብሔር የተሰጠን ክቡር ስጦታ ስለሆነ በሰው ሕይወት ላይ የሚመጣው አደጋ ፍፁም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፡፡

በሕይወትና በንብረት አደጋ የሚያመጣ አካሄድ ለዘመናት አብሮ ለኖረው ሕዝብና ብሎም ለአገራዊ አንድነት፣ በሰላም ድህነትን በጋራ ለማሸነፍ ተስፋዎችን የሚያመነምን በመሆኑ ልናስወግደው ይገባል፡፡ ማኅበረሰባችን ሌላውን የማዳመጥ የመቀበል፣ የማክበር፣ ይቅር የማለትን ወርቃማ ባህል እያዳበረ የሕይወት ትስስራችንንም በማሳደግ ሁሉም የኅብረተሰብ አካላት የመጠበቅ ግዴታችሁን እንድትወጡ በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን፡፡

እግዚአብሔር ፍጥረትን ሲፈጥር በብዝኃነት እሳቤ ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም ይህ ብዙኃነት እርስ በርስ በሚደጋገፍ ትስስር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የተፈጥሮ ልዩነቶች የአንድነትም መሠረት መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ እኛም እንደዚሁ ልዩነቶቻችንን እንደ ተፈጥሮ ፀጋ በመቀበል እርስ በርስ በመከባበር በመቻቻል፣ በመደጋገፍ፣ በመረዳዳት በይቅር ባይነት መንፈስ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችን በመርዳት፣ ከቤት ንብረታቸውም የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ በማገዝ የአብሮነታችንን ውበትና ጥንካሬ እንደገና እንዲያንሰራራ የማድረግ የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

የብዝኃነት ጉዳይ ሲነሳ በተለይ የአገራችን ሕዝብ በደም፣ በሥጋ፣ በጋብቻ፣ በባህልና በማኅበራዊ ኑሮ የተሳሰረ በመሆኑ የአንዱ ሐዘንና ችግር የጋራ ሐዘናችንና ችግራችን ነው፡፡ አንዱ ሲደሰት ሌላውም ይደሰታል፣ አንዱ ሲያለቅስ ሌላውም ያለቅሳል፡፡ በተለይም በቅርብ ጊዜ ከኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መካከል እንዲሁም በሌሎች የአገራችን ክፍሎች በተነሳው ግጭት የጠፋው የሰው ሕይወት ያሳዝናል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የፍቅርና የወንድማማችነት መገለጫ መሆን የሚገባቸው የስፖርት ውድድሮች የጥላቻና የተቃርኖ መገለጫዎች ሆነዋል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዕውቀት መገብያ ማዕከል መሆን ሲገባቸው የግጭትና የሕይወት መጥፊያና የንብረት ማውደሚያ ማዕከል ሆነው መታየታቸው ያስቆጨናል፡፡ ይሁንና ለዘመናት የቆየው የማኅበራዊና ቤተሰባዊነት ትስስራችን በአሁኑ ሰዓት ለተከሰተው ግጭትና አለመተማመን የእርቅ ተምሳሌትነት በመሆን በጨለማ ውስጥ የእርቅ ብርሃን እንዲፈነጥቅ፣ የተጋጩ እንዲታረቁ በማድረግ፣ የተፈናቀሉትም ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ፣ ንብረት ለወደመባቸው እንደገና እንዲያንሰራሩ በማገዝ የቆሰሉ ልቦችን ለመፈወስ መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች በጎ ፈቃድ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን የበኩላችሁን ድጋፍ እንድታደርጉ እንማጸናለን፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ አለመግባባቶች ወደ እርቅና ሰላም ለማሸጋገር የሚቻለው በመደማመጥና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ወገኖች በሆደ ሰፊነት መርህ የመነጋገር፣ የመደማመጥ፣ የመከባበር፣ ብሎም የመቀባበል ባህል በማሳደግ እርስ በርሳችን ሰላም ለመፍጠር መትጋት አለብን፡፡ እኛ የእምነት አባቶች ደግሞ ነቢያዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት የሰላምና የእርቅ መሣሪያ ለመሆን በየአካባቢያችንም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ድምፃችንን ከፍ አድርገን በማሰማት የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፤ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው የሰው መብት እንዲከበር፤ ያለፍርኃት የጥፋት ኃይሎችን መገሰጽ ይጠበቅብናል፡፡ የእምነት አባቶች የተጣሉትን በማስታረቅ የሰላም መሣሪያ የመሆን የሞራል ኃላፊነት ከአምላክ የተሰጠን አደራም ስለሆነ የተለያዩ የኅብረተሰብ አካላትን፣ ማኅበረሰቦችንም፣ የመንግሥት አካላትንም፣ ያለምንም ወገናዊነትና ፍርኃት ተግሳጽ የሚገባውን በመገሰጽ ይቅርታ መጠየቅ ያለበትን እንድንጠይቅ፣ ይቅርታ መስጠት ያለበት እንዲሰጥ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቃሉም በዮሐንስ ወንጌል እውነት ነፃ ያወጣችኋል! (ዮሐ 8፡32) እንደ ሚለው፣ እውነትን መሠረት ያደረገ እርቀ ሰላም እንዲሰፍን የነቢይነትን ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል፡፡

በአገራችን ያለፈው 2009 ዓ.ም. ፈታኝ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በ2010 ዓ.ም. የማኅበረሰቡን አብሮነትና አንድነት በአደጋ ላይ እየጣለ ነው፡፡ በመሆኑም፡-

1ኛ. የተከበራችሁ የመንግሥት አካላት በሙሉ አገራዊ ቁስሎችን የማዳን፣ እርቅን የማውረድ ኃላፊነት የመጀመርያው ባለቤት እንደመሆናችሁ፣ በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር ለሰላም ሥራ የበኩሉን ሚና እንዲጫወትና ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግ አደራ እንላለን፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች የአገርን ሕልውናና የሕዝቡን አንድነት ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ ማንኛውንም ዓይነት ልዩነት ወደ ጎን በመተው ሕዝብንና አገርን ለማዳን ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርባችኋል፡፡ የውስጥ ልዩነት እንኳን ቢኖራችሁ የግጭት መልክ ይዞ ወደ ሕዝብ እንዳይወርድ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንድታደርጉ እናሳስባለን፡፡ ማንኛውንም ልዩነት በውይይትና በድርድር በመፍታት፣ የውይይት መድረክ እንዳይዘጋ አስፈላጊውን መስዋዕት በመክፈል፣ አገሪቷን ከውድቀት፣ ሕዝብንም ከሞትና ስደት የመታደግ ከባድ ሞራላዊና መንግሥታዊ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡ ይህን ክፍተት በመጠቀም ቋንቋንና የዘር ሐረግን በመከተል ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ የጥፋት ኃይሎች በሕዝብ ላይ የባሰ ትርምስና ጉስቁልና እንዳያስከትሉ ጥበብ የተሞላበት የሕዝቡን ታሪካዊ አንድነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡

2ኛ. የዕውቀት ማዕከላትና የአገራችን ምሁራን ወጣት ልጆቻችን በሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ እናሳስባለን፡፡ 3ኛ. የቤተ ክርስቲያናችን ካህናት ገዳማውያን/ያት፣ ካቴኪስቶች፣ ምዕመናን ሁላችሁ፣ እንደዚሁም በትምህርት ቤቶቻችን የምታስተምሩ አስተማሪዎችና በተቋሞቻችን የምትሠሩ በሙሉ የፍቅር፣ የሰላም፣ የመቻቻል ተምሳሌት እንድትሆኑ አደራ እንላለን፡፡

4ኛ. የሃይማኖት ተቋማትና የሃይማኖት መሪዎች ፈጣሪያችን በሚያዘን መልኩ የሰላም የእርቅና የአንድነት መሣሪያዎች እንዲሆኑ እናሳስባለን፡፡ ተከታዮቻቸውን ሁሉ በግልም በጋራም ለእርቅ፣ ለሰላምና ለአንድነት እንዲሠሩ እንዲያተጓቸው በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፡፡ የሃይማኖት መሪዎች ተመሪዎቻቸውና መልዕክቶቻቸው በሙሉ የሰላም የእርቅ የፍቅር እንዲሆኑና በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም እንዲውል መጣር ይኖርባቸዋል፡፡

5ኛ. የተከበራችሁ የአገር ሽማግሌዎች፣ ክቡራን ወላጆች ለትውልድ የሚተላለፉ በጎ እሴቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው በአባቶችና በአገር ወዳድ ሽማግሌዎች መሆኑን ተገንዝባችሁ አገር ተረካቢ ለሆነው ወጣቱ ትውልድ ምክራችሁንና መልካም አርአያነታችሁን እንድታበረክቱ አደራ እንላለን፡፡

6ኛ. የተከበራችሁ የአገራችን ወጣቶች፣ በአገራችን ሠርታችሁ፣ ለኑሮ በቂ የሆነውን ገቢ አግኝታችሁ፣ ቤተሰብ መሥርታችሁ ክብር ያለው ሕይወት ለመኖር ያላችሁን ምኞትና ቁርጠኝነት ቤተ ክርስቲያን ትገነዘባለች፡፡ ይህንን ሊያሰናክሉ የሚችሉ ውጫዊ ፈተናዎችን አሸንፋችሁ ለነገው አገር የመረከብ ኃላፊነታችሁ እንድትበቁ ከመንግሥት፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሌሎች መልካም ፈቃድ ካላቸው አካላት ጋር በመከባበርና በመደማመጥ ላይ በመመሥረት እንድትወያዩ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

7ኛ. ለሴቶች እናቶቻችንና እህቶቻችን በሙሉ፣ ለሰላም መስፈንና ለግጭቶች መፈታት እልባት ማግኘት ያላችሁ ሚና ከሁሉም የላቀ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ስለዚህ ቤተሰብን ያለአንዳች አድልኦ አንድ አድርጋችሁ እንደምትይዙ ሁሉ፣ ለአገርም ጉዳይ የበኩላችሁን ሚና በአንድነት እንድትጫወቱ አደራ እንላለን፡፡

በመጨረሻም ሁሉም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰቦች፣ በጎ ፈቃድ ያላችሁ ወገኖቻችን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስለአገራችን ሰላም፣ ስለሁሉም የሰው ልጅ ክብርና ፍትሕ አሁንም በጸሎት በእግዚአብሔር ፊት እንድትቆሙ አደራ እንላለን፡፡  እግዚአብሔር አገራችንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፡፡ አሜን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡