Skip to main content
x

በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች

በውብሸት ሙላት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2009 ዓ.ም. መደበኛ የሥራ ዘመኑን ከማጠናቀቁ በፊት ከሚኒስትሮች ምክር ቤት በመቀበል ወደ ቋሚ ኮሚቴዎች ከመራቸው ረቀቂ አዋጆች አንዱ የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ አጋርነትን (Public Private Partnership) የሚመለከተው ነው፡፡

የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚባለው አሠራር በበርካታ አገሮች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በግሉ ዘርፍ በኩል ማቅረብ ከተጀመረ በርካታ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በታወቀና በተረዳ መልኩ፣ አተገባበሩ በሕግ ተለይቶና ተገልጾ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ ረዥም ዕድሜ የለውም፡፡ ሦስት አሥርታት ገደማ የሚቆጠር ዕድሜ ያለው ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ የግል ድርጅቶች ጋር በጥምረት የመሠረተ ልማት አውታሮችን የመገንባት ተግባራት ሲያከናውን  ይታወቃል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ አሠራር በተለያዩ ጊዜያት በወጡት የኢንቨስትመንት አዋጆች ውስጥም የተደነገገ ነው፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ለሕዝብ መቅረብ ያለባቸውን መሠረታዊ አገልግሎቶች የግሉ ዘርፍ በራሱ ገንዘብ አስቀድሞ በማቅረብ፣ ኋላ ላይ ወጪውንና ትርፉን ከመንግሥትም ይሁን ከተገልጋዩ የሚሰበስብበት አሠራር ግን በኢትዮጵያ አልተለመደም፡፡ የረቂቅ አዋጁ ዓላማም እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ቅርፅ አስይዞ ማስለመድ ነው፡፡

 የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ይህንን ረቂቅ አዋጅ መፈተሽ ነው፡፡ ፍተሻውን ለማከናወን በቅድሚያ የአዋጁ ይዘት በአጭሩ ይቀርባል፡፡ ቀጥሎም አዋጁ  በፌዴራል ሥርዓቱ በተለይም የፊስካል መዋቅሩ ውስጥ የሚኖረውን አንድምታ፣ ትኩረትና አጽንኦት ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ሌሎች የሕግ ጉዳዮችም ያቀርባል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ጉዳዩን የበለጠ ለመገንዘብ እንዲረዳ፣ ስለመንግሥትና ስለግሉ ዘርፍ አጋርነት ምንነትና ዓይነት ጥቂት ነጥቦችን ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡

የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ምንነትና ዓይነት በጨረፍታ

ለጉዳዩ ቁርጥ ያለ፣ በየትኛውም ቦታና ሁኔታ ተቀባይነት ያለው አንድ ወጥ ትርጉም የለውም፡፡ ለነገሩ ይኖረውም ዘንድ አይጠበቅም፡፡ አገሮች እንደ ነባራዊ ሁኔታቸው በሚመቻቸው መንገድ የሚተረጉሙት በመሆኑ ነው፡፡ አንድ ዓይነት ትርጓሜ ከመፈለግ ይልቅ ምንነቱን ሊገልጹ የሚችሉ ባህርያቱን ማስቀመጡ ይቀላል፡፡ በመሆኑም ይህንኑ አካሄድ መከተል በዚህ ጽሑፍ ተመርጧል፡፡

የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ዋነኛ መለያው፣ የግሉ ዘርፍ መንግሥት ለሕዝብ አገልግሎት ማቅረብ በሚገባው ዘርፍ ውስጥ መሳተፉ ነው፡፡ ሁለተኛው መለያው ደግሞ የሁለቱ ዘርፎች ግንኙነት ወደፊትን ታሳቢ ያደረገ፣ ስምምነታቸውም ረዘም ላለ ጊዜ የሚዘልቅ መሆኑ ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች የውል ጊዜው እስከ 25 ዓመታት መዝለቅ እንዳለበት በሕጋቸው አስቀምጠዋል፡፡

የአጋርነቱ ሦስተኛው ጠባይ ደግሞ ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ኪሳራ ለሁለቱም ማከፋፈሉ ነው፡፡ የተወሰነውን ኪሳራ አጋር ለሚሆነው ድርጅት፣ ቀሪውን ለመንግሥት መስጠቱ ዓይነተኛ ባህሪው ነው፡፡ ከኪሳራ በተጨማሪ ሀብትና ክህሎትንም ይጋራሉ፡፡ መንግሥትም ያለውን ሀብትና ሌሎች አቅሞች፣ የግሉ ዘርፍም ያለውን ሀብት፣ የአስተዳደር ችሎታና ክህሎት በማዋጣት በጋራ የሚሠሩበት ዘዴ ነው፡፡ በመሆኑም ከኪሳራ በተጨማሪ ሀብትና ክህሎትንም የሚጋሩበት ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ሲባል ግን፣ በዋናነት የግዥ ዓይነት ባህርይው ይጎላል፡፡ መንግሥት በራሱ ጊዜ ማቅረብ የሚገባውን አገልግሎት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት እንዲቀርብ የሚያደርግበት ሥርዓት ነው፡፡ ስለሆነም ለዚሁ ዓላማ መሳካት ምቹ የሆኑ ዝርዝር የግዥ ሕጎችን ይይዛል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በአጋርነት የሚሠሩት በተፈጥሯቸው የግሉ ዘርፍን የማይስቡና ከገበያ ሥርዓት አንፃር ሲለኩ በአጭር ጊዜ ትርፍ የማያስገኙ መስኮች ናቸው፡፡ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚደረጉ ስምምነቶችም ሆኑ አጠቃላይ አስፈላጊነታቸውን በሚመለከት፣ አገሮች የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል፡፡ የግሉ ዘርፍ በገበያ ውስጥ የሚኖረውን ተሳትፎ ርዕዮተ ዓለሙ ስለሚወስነው፣ በአንዱ አገር ለግል ባለሀብት የተተዉት፣ በሌላው አገር በመንግሥት ሊያዙ ስለሚችሉ፣ አገሮች በአጋርነት ለሕዝብ የሚያቀርቧቸው የአገልግሎት ዓይነቶች ይወስነዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ አሁን የምትከተለው የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም የራሱ ጥላ እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ሚናና ውሳኔ ሰጪነት፣ እንዲሁም ለፖለቲካ አመራሩ የሚሰጠው ሥልጣን ሊሰፋ ይችላል፡፡ በአዋጁና እሱን ተከትለው በሚወጡት ደንብና መመርያዎች ውስጥም ይሄው ሊንፀባረቅ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ለዚህ ዓይነቱ አሠራር እንደ ቁልፍ ዓላማና መለኪያ የሚወሰደውን ግልጽነት ሊፈታተነው እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚከናውኑ ተግባራት እንደ የአገሮቹ ተጨባጭ ሁኔታ ስለሚለያይ፣ ዓይነታቸውም እንዲሁ የተለያዩ ናቸው፡፡ አምራች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች፣ ሥራ ላይ የሚውሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምርና ጥናት ሥራዎችን ማከናወን፣ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለመዘርጋት የሚደረጉ ብሎ በሦስት መክፈል ይቻላል፡፡ በሌላ መልኩ የፋይናንስ ምንጫቸውን መነሻ በማድረግም መከፋፈል ይቻላል፡፡ የግል ድርጅቶች ከመንግሥት በጀት ገንዘብ የሚያገኙ፣ ከበጀት ውጪ ነገር ግን ከሌሎች የመንግሥት የፋይናንስ ምንጮች ወይም ከፋይናንስ ውጪ የሚደገፉ በማለትም መከፋፈል ይቻላል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በአጭሩ

አዋጁ በአሥራ አንድ ምዕራፎችና በ68 አንቀጾች የተሸከፈ ነው፡፡ በመግቢያውም የአዋጁ ዓላማዎች ሠፍረዋል፡፡ የመሠረተ ልማቱንና አጠቃላይ አገሪቱን የልማት ግቦች ለማሳካት የግሉ ዘርፍ አጋር መሆኑን ዕውቅና በመስጠት፣ ይኼንን የሚገዛ ሕግ ማስፈለጉ የአዋጁ አንዱ ዓላማ ነው፡፡ ለአሠራሩም ግልጽነትና ፍትኃዊነትን ማስፈን፣ ዘላቂነት እንዲኖረው ማድረግ፣ እንዲሁም በአጋርነት የሚሠሩ ድርጅቶች የሚመረጡበትን የግዥ ሥርዓት መወሰን ሌላው ዓላማ ነው፡፡

በአዋጁ ምዕራፍ አንድ ሥር ከተካተቱትና ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ጽንሰ ሐሳቦች፣ የተፈጻሚነት ወሰን የመንግሥትና የግል አጋርነት ስምምነት ዓላማዎች፣ ዓይነቶችና ከመንግሥት በኩል ሊኖር የሚችለውን ተዋዋይ ወገን የሚመለከቱት  ናቸው፡፡

በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚከናወኑ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች የሚባሉት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለሕዝብ አገልግሎት ጥቅም የሚሰጡ ግዙፍ ሀልዎት ያላቸው ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህን የመሠረተ ልማት አውታሮች የመገንባት ኃላፊነት ያለበት የመንግሥት አካል ከግል ተቋማት ጋር ውል በማሰር ያስገነባል፡፡ በግሉ ዘርፍ ለአገልግሎት ሊቀርቡ የሚችሉትን ሳይሆን፣ መንግሥትን የሚመለከቱት ላይ ነው፡፡ ግንባታው የሚከናወነውም በድርጅቱ የራስ ገንዘብ ነው፡፡ ክፍያና ትርፉ የሚፈጸመው፣ ሠርቶ ለሕዝብ አገልግሎት ሲያቀርብ ከተጠቃሚው ከሚገኝ ክፍያ፣ ወይም ከመንግሥት፣ ወይም ከሁለቱም በአንድነት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት አስቀድሞ ለግንባታ የሚውል ገንዝብ ከመፈለግ፣ ካጣም ይቀር የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ይረዳዋል፡፡

በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ስምምነት መሠረት የሚከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ፣ አዋጁ በአንቀጽ አራትና አምስት ውስጥ በሁለት ዓይነት አቅርቦታል፡፡ የመጀመርያው አንቀጽ አምስት ውስጥ የተገለጹት ሲሆኑ፣ በአጋርነት ሊከናወኑ የሚችሉትን ይመለከታል፡፡ በአዋጁ የሚገዙና በአጋርነት የሚከናወኑት ተግባራት አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን መገንባት፣ ወይም ነባሮቹን ማደስና ማዘመንን የሚመለከት ሲሆን፣ ንድፋቸውን መሥራት፣ መገንባት፣ ወጪያቸውን መሸፈን፣ መጠገን፣ ሥራቸውን ማስኬድን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም ሥራው የመሠረተ ልማቶቹን ማስተዳደር፣ መምራትና ሥራ ማስኬድም ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም በአጋርነት የሚከናወኑት የመሠረተ ልማት ግንባታና ጥገና፣ እንዲሁም ማስተዳደርን ብቻ የሚመለከት ተግባር ነው ማለት ይቻላል፡፡

 እንደሌሎች አገሮች ሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ምርምርና ጥናት ማድረግን አይጨምርም፡፡ የመሠረተ ልማት አውታሮች የሚባሉት ግዙፍ ህልውና ያላቸውን ብቻ የሚይዝ በመሆኑ፣ ግዙፋዊ ሀልዎት የሌላቸውን ለአብነት ሶፍትዌር መሥራትን ወይም የቴክኖሎጂ ጥናት ማድረግን አይጨምርም ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው በአጋርነት ቢከናወኑም እንኳ አዋጁ ተፈጻሚ የማይሆንባቸው ናቸው፡፡ እነሱም ነዳጅ፣ ማዕድንና የከርሰ ምድር ሀብት፣ እንዲሁም የአየር ክልል መብት በአንድ በኩል ሲጠቀሱ፣ በሌላ በኩል ቀድመው የመንግሥት የነበሩትን ወደ ግል በማዛወር የሚፈጠረውን ግንኙነት ወይም አጋርነት የማይመለከተው አካሄድም ተጠቃሽ ነው፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳ በእነዚህ ዘርፎች ማዕቀፍ ውስጥ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በአጋርነት ቢሠሩም ከአዋጁ ውጪ ሆነዋል፡፡

ረቂቁ በመጀመርያው ምዕራፍ ከያዛቸው ቁም ነገሮች አንዱ የሚፈጸምበትን ማስቀመጡ ነው፡፡ ተፈጻሚነቱ በፌዴራል መንግሥቱና በክልልም ቢሆን እንኳ በፌዴራል በጀት በሚከናወኑት ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህን ዓይነት አዋጅ ማውጣት ለፌዴራሉ ወይም ለክልሎች ተለይቶ የተሰጠ ባለመሆኑ፣ ሁሉም በየፊናቸው ለየራሳቸው ሊያወጡ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ሥልጣን የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድሮችንም ይጨምራል፡፡ የፌዴራል ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች የሚከተሉትም ይኼንኑ አካሄድ ነው፡፡ ሩስያ፣ ሜክሲኮ፣ አርጀንቲና ለዚህ አብነት ናቸው፡፡ ጠንካራ የማዕከላዊ መንግሥትና ሥልጣን ያላቸው ፌዴራላዊ አገሮችም ሳይቀሩ ተመሳሳይ ሞዴል ይከተላሉ ማለት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ አንድ መነሳት ያለበት ነጥብ አለ፡፡ ይኼውም የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች በስፋት የገፉበት፣ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን፣ ፋብሪካዎችን፣ የንግድ ተቋማትን ከግል ባለሀብቶች ጋር በመሆን ማቋቋሟቸውን የሚመለከት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ይኼንኑ በተመለከተ የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ በማውጣት ላይ እያለ ክልሎች ቀድመው እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸውን ተችተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሁለቱ ክልሎች ተግባራት ከመንግሥትና ከግል አጋርነት ዓላማና ትርጉም ጋር ተመሳሳይ አይደለም፡፡ በእነዚህ ዓይነት ሕጎችም የሚገዙ አይሆኑም፡፡

የመንግሥትና የግል አጋርነት ስምምነት፣ የሚደረገው ለሕዝብ አገልግሎት መንግሥት ማቅረብ ያለበትን እንጂ በግሉ ዘርፍ እየቀረቡ ያሉትን አይመለከትም፡፡ ለአብነት የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የብረታ ብረት ሥራ፣ የጭነትና የሕዝብ ማጓጓዣ ትራንስፖርት ወዘተ. በዋናነት ከእንዲህ ዓይነት አሠራር ውጪ ናቸው፡፡ በዘላቂነት የግል ባለሀብቱም ባለቤት የሚሆንባቸው አይደሉም፡፡ በጊዜ የተገደቡ ውሎች ናቸው፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልል መንግሥታትና በግል ባለሀብቶች መካከል አክሲዮን በመሸጥ የተቋቋሙትና የሚቋቋሙት፣ የሚመሩበትና የሚተዳደሩበት ሕግ በእዚህ አዋጅ ብቻ ሳይሆን፣ ክልሎቹም በሚያወጧቸው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የአጋርነት ሕጎች የሚተዳደሩ አይሆኑም፡፡ 

የአዋጁ ሁለተኛው ምዕራፍ በጥቅሉ የያዘው፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት አስተዳደርን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ነው፡፡ የተለያዩ ሚኒስቴሮችን ያቀፈ ቦርድ አለው፡፡ ተግባር፣ ኃላፊነትና ሥልጣኑንም ተዘርዝሯል፡፡ በአጋርነት የሚከናወኑ ተግባራትን ከማፅደቅ ጀምሮ፣ ባለሀብቶች የሚመረጡበትን ሒደትና ውጤት ላይ የመወሰን ሥልጣንም አለው፡፡ ሰብሳቢው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ነው፡፡ ቦርዱ ለሌላ አካል ተጠሪነት የለበትም፡፡ በመሆኑም በሚወስናቸው ውሳኔዎች ላይ ችግሮች ቢስተዋሉ፣ ከአስተዳደራዊ ውሳኔ ይልቅ በፍርድ ቤት መፍትሔ ይሰጥበታል  ማለት ነው፡፡

ከቦርዱ በተጨማሪ እንደ አዲስ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሥር የሚቋቋም የመንግሥትና የግል አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ይኖራል፡፡ በጣም በርካታና ውስብስብ ሥራዎች የሚኖሩት ተቋም ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች ራሱን ችሎ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ይቋቋማል፡፡

የአዋጁ ምዕራፍ አራትና አምስት ውስጥ የተዋዋይ መሥሪያ ቤቱን ተግባርና ኃላፊነት የሚመለከት ሲሆን፣ ሌላኛው ፕሮጀክት የሚዘጋጅበትንና የሚፀድቅበትን ሒደት ይገልጻል፡፡ በአጋርነት የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን የመለየት ዋናው ኃላፊነት እነዚህን ሥራዎች የማከናወን የሕግ ግዴታ የተጣለበት መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ በተጠቀሰው ዳይሬክቶሬት ጄኔራልና በሚኒስቴሩ መፅደቃቸው ግድ ነው፡፡ ከዚህ በማስከተል የአዋጭነት ጥናት መከናወን አለበት፡፡

ከስድስተኛው እስከ ዘጠኝ ያሉት የረቂቅ አዋጁ ምዕራፎች የሚደነግጉት፣ ተዋዋይ ሊሆኑ የሚችሉ ባለሀብቶች የሚመረጡበትን ሒደት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የግዥ ሥርዓትን ይደነግጋሉ፡፡ አራት ዓይነት የግዥ ሥርዓቶች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሦስቱ በሌሎች የግዥ ሁኔታዎችም ዘንድ የታወቁ ናቸው፡፡ በተወሰነ መልኩ ግን ልዩነት አላቸው፡፡ እነዚህም ግልጽ ጨረታና ባለ ሁለት ደረጃ ጨረታዎች ናቸው፡፡ የተለያዩ ባለሀብቶች በአንድነት (Participation of Consortia) አንድ ጨረታ ላይ ሊሳተፉ የሚችሉበትን አሠራርም አስቀምጧል፡፡

ይኼኛው የግዥ ዓይነት ግን በግዥ ሕጉ ውስጥ አልተካተተም፡፡ አንዱ በውድድር ላይ የተመሠረተ ውይይት (Competitive Dialogue) ይባላል፡፡ ከላይ በቀረቡት ሁለት ዓይነት የግዥ ሥርዓቶች ቢካሄድ ውስብስብና ልዩ ስለሆነ፣ ሒደቱ ተገቢ አለመሆኑን ዳይሬክቶሬት ጄኔራሉ ሲያምንና ቦርዱ ሲወስን፣ የቅድመ ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓቱን ያለፉ ተጫራቾችን በማወያየት ማወዳደርን ይፈቅዳል፡፡

አራተኛው የግዥ ዓይነት ደግሞ የቀጥታ ግዥ ነው፡፡ በአስቸኳይነታቸው፣ በቆይታ ጊዜያቸው አጭር የሆኑ፣ ከመከላከያና ደኅንነት ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶችን፣ እንዲሁም የአዕምሯዊ ንበረትነታቸው በብቸኝነት የተያዙ ከሆነ፣ በቀጥታ ግዥ ሊከናወኑ ይችላሉ፡፡

ከላይ የተገለጹት እንደተጠበቁ ሆነው፣ ባለሀብቱ በራሱ የሚያመጣቸውን ፕሮጀክቶች እንደምን አድርጎ ሊገዛ እንደሚችል የሚገልጽ ሥርዓትም ከወትሮው የግዥ ሥርዓት በተለየ ሁኔታ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ በእርግጥ የተለየ የግዥ ሥርዓት ሳይሆን፣ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ለመጠቀም የመርጠ አካሄድ አምጥቷል፡፡

ምዕራፍ አሥር በመንግሥትና በግል አጋርነት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የሚደረጉ ስምምነቶች ይዘታቸው ምን መምሰል እንዳለበትና እንደሚተገበር ዘርዘር ያለ ሥርዓት አስተዋውቋል፡፡ ጨረታውን በማሸነፍ ተዋዋይ የሚሆነው አካል፣ ፕሮጀክቱን የሚተገብር አዲስ ድርጅት በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት እንዲቋቋም ይጠይቃል፡፡

የመንግሥትና የግል አጋርነትን በሚጠቀሙ አገሮች ውስጥ እንደተለመደው ለተለየ ዓለማ፣ ለአንድ ፕሮጀክት ትግበራ ብቻ የሚሆን ድርጅት (Special Purpose Vehicle/Entity) ይቋቋማል፡፡ ድርጅቱ የሚቋቋመው ከመንግሥት የተረከበውን ፕሮጀክት ለመፈጸምና የውል ዘመኑ ሲያልቅ ለማስረከብ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የሚቋቋመውም፣ በአንድ በኩል የፕሮጀክቱ ኪሳራና ኃላፊነት ወደሌላ የተዋዋይ አካላት ሀብት እንዳይተላለፍ ለማድረግ ሲሆን፣ በሌላ መልኩ ደግሞ የፕሮጀክቱ ፋይናንስ ለሌላ ዓላማ እንዳይውል ለመቆጣጠር ነው፡፡

ረቂቅ አዋጁም የፕሮጀክት ኩባንያ የሚባል በጨረታ ያሸነፈው አካል መቋቋም እንዳለበት ከመግለጽ የዘለለ ምን ዓይነት የንግድ ድርጅት (ለምሳሌ የአክሲዮን ማኅበር፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ወዘተ.) መሆን እንዳለበት የሚገልጸው ነገር የለም፡፡ በተጨማሪም አሸናፊው አካል የውጪ ድርጅት ከሆነ፣ በውጭ ባለሀብቶች የሚቋቋሙ ድርጅቶች በርካታ ስለሆኑ፣ በምን ሁኔታ እንደሚቋቋሙ አይዘረዝርም፡፡

አዋጁ የፕሮጀክት ኩባንያ በማለት የሚጠራው ተቋም ለአገሪቱ አዲስ በመሆኑ፣ የንግድ ሕጉ ውስጥ ከተገለጹት የሚለይበት ባህርያት እንዳሉት ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ በርካታ ነገሮቹ የሚገዙት በስምምነት ሊሆን እንደሚችል፣ እንዲሁም ተዋዋይ የሆነው የመንግሥት ባለሥልጣን፣ በፕሮጀክት ኩባንያው ወይም ኩባንያው ውስጥ አክሲዮን ከሚኖረው ሌላ ኩባንያ ላይ አነስተኛውን (ከ50 በመቶ በታች) አክሲዮን ሊይዝ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

 በእዚህ ምዕራፍ ከተካተቱት ውስጥ ስምምነቱ ሊቆይ የሚችበትን ጊዜ በፕሮጀክቱ መገለጽ እንዳለበት፣ የግል ባለሀብቱ ገንዘብ የሚያገኝበትን ሁኔታ፣ ብድርና ለዋስትና የሚሆኑ ንብረቶችንና ማስያዣዎችን የሚመለከተው ሌላኛው ድንጋጌ ነው፡፡ አንድ ፕሮጀክት በግል የሚቆይበትን፣ ሊራዘም የሚችልበትንም የጊዜ ገደብ በሕግ ማስቀመጥ በሌሎች አገሮች ዘንድ የተለመደ ቢሆንም፣ ረቂቅ አዋጁ ግን በስምምነት እንዲወሰን ትቶታል፡፡

አበዳሪ ተቋማትም በማስያዣው ላይ የሚኖራቸው መብት ጠቅለል ባለመልኩ ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ የሚሠራ ፕሮጀክትን በማስያዣነት ሲሰጥ፣ ብድሩ ሳይመለስ በሚቀርበት ጊዜ አበዳሪው ወይም ገዥው አካል ሊኖሩት የሚችሉትን መብቶች በሕግ መወሰን ተገቢ ነው፡፡ ካልሆነ ግን የሕዝብ አገልግሎት መስጠታቸው ሊቆም፣ ሊቀየርም ይችላል፡፡ ለአብነት የሚገነባው ፕሮጀክት ትምህርት ቤት ቢሆን፣ ብድሩ ሳይመለስ በመቅረቱ ምክንያት ይሸጥ ቢባል፣ በትምህርት ቤትነቱ እንጂ ለሌላ አገልግሎት (ለሆቴል፣ ለሆስፒታል፣ ወዘተ.) የሚውል ከሆነ ዓላማውን ይስታል፡፡ በተጨማሪም፣ ተዋዋዩ ባለሀብት የሚኖሩበት ግዴታዎችም ተዘርዝረዋል፡፡

የፕሮጀክት ስምምነቶችን በተዋዋይ ባለሥልጣኑ ፈቃድ ለሌላ ሦስተኛ አካል ማስተላለፍንም ሕጉ ይፈቅዳል፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ምን ያህል መጠኑ ከተከናወነ በኋላ መተላለፍ እንደሚችል ከሌሎች አገሮች በተለየ ሁኔታ የተቀመጠ ዝቅተኛ መሥፈርት አልተጠቀሰም፡፡ ፕሮጀክቱ እንዴት እንደሚቋረጥ፣ በሚቋረጥበት ጊዜ ሊከፈል የሚችለው ካሳ በውል መካተት እንዳለበትና የግጭት አፈታት ሥርዓትንም አካቷል፡፡ የመጨረሻው ምዕራፍ የተሻሩ ሕጎችን፣ ደንብና መመርያ የማውጣት ሥልጣንን የሚመለከቱ አንቀጾችን ይዟል፡፡

በረቂቅ አዋጁ አጭር ማብራሪያ ሥር እንደተገለጸው፣ የመንግሥትና የግል አጋርነት ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመተግበር ቁልፍ የፋይናንስ ምንጭ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁ እንኳ ሳይፀድቅ ዕቅዱ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ አስቆጥሯል፡፡ ደንብና መመርያ ያስፈልገዋል፡፡ በርካታ የአሠራር ዘዴዎችን የሚገልጹ ማብራሪያዎችም ያስፈልጉታል፡፡ ዳይሬክቶሬት ጄኔራሉ አልተቋቋመም፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶችም ጥናት እያደረጉ ለማቅረብ ይረዳቸው ዘንድ ሕጉንና አሠራሩን አውቀው ከዚያም ጥያቄ  ውስጥ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገሩ ‹‹ከቀረ የዘገየ ይሻላል፤›› ነው እንጂ፣ አዲሱ አዋጅ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጊዜ ውስጥ ተፈጻሚ የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ነው፡፡

ረቂቅ አዋጁ በአጭሩ ከላይ የተገለጸውን ይመስላል፡፡ በዚህ አዋጅ አማካይነት ሥራ ላይ የሚውለው የመንግሥትና የግል አጋርነት ፊስካል ፌዴራሊዝም ላይ የሚኖረው አንድምታ፣ በተለይም በፌዴራል በጀት ክልልን ከመደገፍ አንፃር የሚተገበሩት፣ የፕሮጀክት ኩባንያ ምንነት፣ ከተዋዋይ ወገኖችና ከሌሎች ሕጎች ጋር ያለውን ተዛምዶና ተቃርኖ፣ የዋስትናና የሽያጭ/የማስተላለፍ ውጤት፣ በውል የተተወው ጉዳይ መብዛትና አንድምታውን በሚቀጥለው ክፍል እንመለስባቸዋለን፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡