Skip to main content
x
የኢዴፓ አመራሮች ውዝግብ ቀጥሏል
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያላቸው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) የብሔራዊ ምክር ቤቱን ስብሰባ ሕገወጥ ነው ብለዋል

የኢዴፓ አመራሮች ውዝግብ ቀጥሏል

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ብሔራዊ ምክር ቤት እሑድ ታኅሳስ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በቅሎ ቤት አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ አቶ አዳነ ታደሰን በፕሬዚዳንትነት መረጠ፡፡ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም የተባሉ ጉዳዮችንም ማስተካከሉንና ለቦርዱ ማስገባቱን ለሪፖርተር ቢገልጽም፣ እንደገና ተቃውሞ በመነሳቱ ውዝግቡ ቀጥሏል፡፡

ሰኞ ታኅሳስ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዋና ጽሕፈት ቤት መግለጫ የሰጡት በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተሰጣቸው የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) እና የተወሰኑ የሥራ አስፈጻሚ አካላት በበኩላቸው፣ የእሑዱ የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ሕገወጥ ነው በማለት ተቃውመውታል፡፡

የፓርቲው ብሔራዊ ምክር አባላት በፓርቲው መተዳደሪያ ድንብ አንቀጽ 20(2.1) መሠረት፣ በፔትሽን የተጠራ ልዩ ስብሰባ እሑድ ታኅሳስ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. አካሂዷል፡፡

በዚሁ ስብሰባ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ምርጫ ቦርድ የአቶ አዳነ ታደሰን በፕሬዚዳንትነት መመረጥ እንደማይቀበል የገለጸበት ደብዳቤ ላይ የተወያየ ሲሆን፣ በምርጫ ቦርድ በኩል አልተሟሉም የተባሉ ጉዳዮችን በማስተካከል ለቦርዱ ማስገባቱ ተገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት ብሔራዊ ምክር ቤቱ በምርጫ ቦርድ በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ሆኖም ሰብሰባው ሕገወጥ እንደሆነና የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ የሚጥስ ነው በማለት የተቃወሙት የፓርቲው ፕሬዚዳንትና የተወሰኑት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የብሔራዊ ምክር ቤቱን ስብሰባ የጠሩት ግለሰቦች ከሚጠቅሱት የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ጋር እየተጋጩ ነው በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡

በዚህም መሠረት የመተዳደርያ ደንቡን አንቀጽ 20(6) በመጥቀስ መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡ ይህ አንቀጽ ውሳኔን እንደገና ስለማየት የሚል ነው፡፡ ‹‹አንድ ውሳኔ ውሎ አድሮ እንደገና እንዲታይ ከተፈለገ አባሎቹ 1/3ኛዎቹ ለፕሬዚዳንቱ (ለሰብሳቢው) በጽሑፍ አቤቱታ ማቅረብ አለባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ እንደገና ይታያል፡፡ ቀደም ብሎ የተላለፈው ውሳኔ ለፓርቲው ጉዳት የሚያስከትል ከሆነና ከሚቀጥለው ስብሰባ በፊት ተፈጻሚነት የሚያገኝ ከሆነ፣ ፕሬዚዳንቱ አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራና እንደገና እንዲወሰን ያደርጋል፡፡ ሆኖም ይህ አሠራር በአንድ ጉዳይ ላይ ከአንዴ በላይ በተግባር ላይ አይውልም፤›› ይላል፡፡

በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ አጀንዳ ስብሰባ ተጠርቶ የነበረ በመሆኑ፣ አሁን ሥራ አስፈጻሚው ሳይወስን በተመሳሳይ ጉዳይ ስብሰባ መጥራት ከደንቡ ጋር እንደሚቃረን የፓርቲው ጥናትና ምርምር ኃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ታኅሳስ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በተደረገው የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ መሠረት ውሳኔ የተደረሰባቸው ነጥቦች የተካተቱበት ደብዳቤ እንደደረሰው፣ በፓርቲው ሕገ ደንብ መሠረት የተከናወነ መሆኑን እያጣራ እንደሆነ የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተስፋዓለም ዓባይ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

‹‹ቦርዱ ሁሌ እንደሚያደርገው የቀረበለትን ሰነድ በሕገ ደንቡ መሠረት መከናወኑን በጥሞና ከመረመረ በኃላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ይሰጣል፤›› ብለዋል፡፡

ኢዴፓ ከገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጋር እየተደረገ ባለው ድርድር በውክልና ምክንያት፣ በአባላት መካከል አለመግባባት መፈጠሩን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡