Skip to main content
x
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋስትናው አንድነቱ ብቻ ነው!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋስትናው አንድነቱ ብቻ ነው!

‹‹አንድ ከሆንን ፀንተን እንቆማለን፣ ከተከፋፈልን ግን እንገረሰሳለን›› የሚባለው ታዋቂ አባባል በዓለም ዙሪያ ሰፊ ተቀባይነትን ያገኘ ነው፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ አንድነት ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ የአንድነትን ትርጉም ለመግለጽ ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር››፣ ‹‹ለአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ››፣ ‹‹ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ››፣ ወዘተ. ዕድሜ ጠገብ አገር በቀል አባባሎች በስፋት ይታወቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ የሚታወቀውም የሚወዳት አገሩን ከባዕዳን ወራሪዎችና ተስፋፊዎች ለመከላከል በከፈለው ወደር የሌለው መስዋዕትነት ነው፡፡ ይህ በደምና በአጥንት የተለሰነ የአገር ፍቅር ስሜት የአንድነቱ አንፀባራቂ ህያው ምስክር ነው፡፡ አገር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተቀባበለች እዚህ የደረሰችውም ጨዋውና አስተዋዩ ሕዝብ በአንድነት ቆሞ ስለጠበቃት ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት ይህ ምሥጉን ተግባር በመቀጠሉም አሁን ያለንበት ዘመን ላይ ተደርሷል፡፡ ይህ አርቆ አሳቢ ሕዝብ በደግም ሆነ በክፉ ጊዜያት ከልዩነት በላይ አንድ የሚያደርጉት በርካታ የጋራ ጉዳዮች ስለነበሩ አገሩን ለዚህ ትውልድ አስረክቧል፡፡ ይህ ትውልድም ከምንም ነገር በላይ ይህንን አኩሪ እሴት የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ የአገርና የሕዝብ ዋስትና አንድነት ብቻ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህንን የጋራ አኩሪ እሴት የሚሸረሽሩ አሳዛኝ ድርጊቶች እየታዩ ነው፡፡ የሕዝብን ፍላጎት የማይወክሉ፣ ለዘመናት የተገነባውን የአንድነት ስሜት የሚሸረሽሩ፣ ለሥልጣን በሚደረግ ፍትጊያ የአገር አንድነት ዋልታና ማገርን የሚሰባብሩ፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት ግጭት የሚቆሰቁሱ፣ የግለሰብ የዕለት ጠብን ወደ ብሔር እየቀየሩ ደም የሚያፋስሱና የአገር አንጡራ ሀብት የሚያወድሙ ድርጊቶች ብቅ ጥልቅ እያሉ እየተስተዋሉ ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ የአገሪቱ ሕዝብ ልጆች የሚማሩባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በብሔር በመቧደን ጥቃት የሚፈጸምባቸው መሆን ጀምረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው በመረጡት ሥፍራ የመኖር፣ የመሥራት፣ የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብታቸው እየተጣሰ እንደ ባዕድ የሚሰደዱበት ጊዜ ላይም ተደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በዚህ ዓይነቱ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት የሚታወቅ አይደለም፡፡ ይህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ እንኳንስ የገዛ ወገኑን ባዕዳንን በሚገባ አስተናግዶ ወደ መጡበት በመሸኘት የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን ግን ይህንን የመሰለ የአገር ፀጋ የሚጋፉ አሳዛኝ ድርጊቶች እየተንሰራፉ የአገር አንድነት ሥጋት ውስጥ ወድቋል፡፡

ማንም ሰው በማንነቱ የመኩራት፣ ማንነቱን የማስተዋወቅና በገዛ አገሩ በእኩልነት የመኖር መብት ሊኖረው ይገባል፡፡ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረትም ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጠቀም፣ በራስ የመዳኘትና የመተዳደር መብቱም መከበር አለበት፡፡ ይህ ደግሞ በአገር ደረጃ እየሰፋና እያደገ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባትና ዴሞክራሲያዊት አገር ለመፍጠር ይጠቅማል፡፡ የግለሰብና የቡድን መብቶች በአግባቡ ተከብረው በገዛ አገር ባይተዋር ሳይሆኑ መኖር ሲቻል ደግሞ፣ የአገር አንድነት እየጠነከረ የብልፅግና ጉዞ ይጀመራል፡፡ ሁሉም ዜጋ በሕግ የበላይነት ሥር የሚመራ ሥርዓት ለመፍጠር  በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ የድህነት አረንቋ ውስጥ ሆኖ ብሔር እየለዩ ከመወዛገብ ይልቅ፣ በሠለጠነ መንገድ በመነጋገር ለማኅበራዊ ፍትሕና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን እጅ ለእጅ ተያይዞ መተጋገዝ ባህል ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን አርቆ ማሰብ የተሳናቸውና የአንድ አገር ሕዝብን በብሔር መለያየትና ማፋጀት የሚያምራቸው ወገኖች አሉ፡፡ ዘመኑ ከሚፈልገው የአስተሳሰብ ደረጃ ወርደው ሰዎች ሳይፈልጉ ባገኙት ማንነት ምክንያት የሚፈርጁና ለጥቃት የሚያመቻቹ ወገኖች አደብ ሊገዙ ይገባል፡፡ ይህ ድርጊት አድማሱን እያሰፋ አገር ይለበልባልና፡፡

ይህ ዓይነቱ አደገኛ ችግር ክልሎችን አልፎ የፌዴራል መዋቅሮች ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ በረሃና ባህር አቋርጠው የተሰደዱና በሰው አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አዳርሷል፡፡ ምሁራን ሳይቀሩ የአክራሪ ብሔርተኝነት ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ መሠረታዊ መብቶቹ ተከብረውለት በኢትዮጵያዊነት ስሜት ማሳደግ ሲገባ፣ በአክራሪ ብሔርተኝነት አስተምህሮ እየመረዙ በገዛ ወገኑ ላይ እንዲነሳ ማድረግ አፍራሽ ነው፡፡ የወጣቶች አዕምሮ ልክ እንደ ለም መሬት የሚሰጡትን የሚቀበል በመሆኑ ቀናውን ጎዳና ማስያዝ ሲገባ፣ እንዲመረዝ ማድረግ ውሎ አድሮ ጠንቁ ለመላው ሕዝብ ይተርፋል፡፡ ሥልጣንም ሆነ ሀብት በሕጋዊ መንገድ ብቻ መገኘት ሲገባቸው፣ ሁሉንም ነገር ከብሔር ጋር እያያዙ ሒሳብ ማወራረድ እንኳንስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ባለበት ለመቀጠል አያስችልም፡፡ የሕዝብንና የአገርን አንድነት እየሸረሸሩ መደላደል በፍፁም አይቻልም፡፡ ይህች ታሪካዊ አገር እስካሁን የኖረችው በዚህ አርቆ አሳቢና ጨዋ ሕዝብ ምክንያት መሆኑ  እየተዘነጋ፣ የአገር አንድነት በመናድ ውጤት ይገኛል ማለት ዘበት ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በብሔር መነጽር ብቻ በማየት የትም መድረስ አይቻልም፡፡

ኢትዮጵያዊነት ትልቅ መስዋዕትነት የተከፈለበት ታላቅ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮችና ሌሎች በቅኝ ገዥዎች በሚማቅቁበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ ግንባር ቀዳሚ አፍሪካዊት የነፃነት ቀንዲል ነበረች፡፡ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በጀግኖች ልጆቿ ተጋድሎ ያንበረከከች ብቸኛ አገር ናት፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ምርጧ ምሳሌ ነበረች፡፡ ይህ ተረት ወይም አፈ ታሪክ ሳይሆን በበርካታ የዓለም ድርሳናት የደመቀ ታሪክ ነው፡፡ ጀግኖቹ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን እየተራቡ በቁር፣ በውርጭና በንዳድ በባዶ እግራቸው በመጓዝ በኋላ ቀር መሣሪያዎች እስከ አፍንጫው ከታጠቀ ወራሪ ባዕድ ጋር ሲተናነቁና ድል ሲነሱ የኖሩት፣ በአንዲት ሰንደቅ ዓላማ ሥር በአገር ፍቅር ስሜት ነበር፡፡ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ ወይም ሌላ ልዩነት ሳይበግራቸው ለአገር አንድነት በፅናት በመቆማቸው ነው፡፡ ይህንን ታላቅ አርዓያነት በተግባር አሳይተው ያለፉ የዘመናት ትውልዶች በዚህ ዘመን ትውልድ መካድ የለባቸውም፡፡ የአገር አንድነት ሲነሳባቸው የሚያቅለሸልሻቸው ወገኖች የቀደሙት ትውልዶች ለዚህች አገር ህልውና ሲሉ የከፈሉትን መስዋዕትነት ማጤን አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም የቀዳሚዎቹን ታሪክ የሚዘክረው ለብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማው ክብር በመስጠት ጭምር ነው፡፡ አንድነት ኃይል መሆኑን ስለሚገነዘብ ነው፡፡

በዚህ ዘመን በየደረጃው አገር የሚያስተዳድሩ ወገኖችም ሆኑ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚታገሉ፣ እንዲሁም በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩና በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ወጣቶች አንድ ነገር በአጽንኦት ሊያስተውሉ ይገባል፡፡ ይህም ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር እንደሌለ፡፡ በባዕድ አገር የሚኖሩም ቢሆኑ የአገር ጉዳይ ምን ማለት እንደሆነ በውል ይገባቸዋል፡፡ በገዛ አገር መኖርና ባዕድ መሆን ልዩነቱ ግልጽ ነው፡፡ እነሱን እንኳ ባዕድ መሆናቸውን እያወቀ አስጠልሎ እንጀራ የሚያበላቸው አገር፣ በአንድነቱ ፀንቶ የቆመው በአገሬው ሕዝብ መሆኑን ሊያስቡ ይገባል፡፡ ትልቁ ነገር የአገር ህልውና ነው፡፡ ለአገር ህልውና ሲባል ደግሞ የግድ የጋራ ራዕይና ግብ ሊኖር ይገባል፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው የሥልጣን ተገዳዳሪውን ጠላት እያደረገ መዝለቅ አይችልም፡፡ ሥልጣን ፈላጊውም እንዲሁ፡፡ ዴሞክራሲ በዚህ ዓይነቱ አደገኛ የመመራረዝ አስተሳሰብ የትም ቦታ ሰፍኖ አያውቅም፡፡ ይልቁንም ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ በመስጠት፣ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ መብቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ቁጭ ብሎ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ የሚሻሻለው፣ የሚታረመው፣ ጨርሶ አያስፈልግም፣ ወዘተ. የሚባለው ሁሉ ሳይቀር መቅረብ ያለበት ለውይይት ብቻ ነው፡፡ ውይይቱም ጨዋነትን የተላበሰ፣ የሰከነና በመርህ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የዓመታት ስህተቶችን ማረም ይገባል፡፡ ስህተቶችን እየደጋገሙ ውጤት ማግኘት አይቻልም፡፡ በቂምና በጥላቻ፣ እንዲሁም ባለመተማመን ላይ የተመሠረተ አጉል ግንኙነት ለዘመኑ አይመጥንም፡፡ በዛቻና በፉከራ የታጀበ አጉል እሰጥ አገባም ለአገር ፋይዳ የለውም፡፡ ከዚህ ይልቅ የሕዝቡን ታሪካዊ የጋራ እሴቶች በመጠበቅ ለሥልጡን ግንኙነት ራስን ማዘጋጀት ይጠቅማል፡፡ ትልቁ የአገር ጉዳይ እያለ ብሔርተኝነትን በማራገብ አገርን ማተራመስ ይቁም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋስትናው አንድነቱ ብቻ ነው!