Skip to main content
x
‹‹ኢትዮጵያና ጂቡቲ የኤርትራን ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት በመውሰዳቸው ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል››

‹‹ኢትዮጵያና ጂቡቲ የኤርትራን ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት በመውሰዳቸው ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል››

ፒተር ቭሩማን፣ ተሰናባቹ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ

ፒተር ቭሮማን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ላለፉት አሥር ወራት ጉዳይ ፈጻሚ በመሆን አገልግለዋል፡፡ የአገልግሎት ዘመናቸውም ማክሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ተጠናቋል፡፡ ቭሩማን ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት በተለያዩ አገሮች የአሜሪካ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች በተለያዩ ኃላፊነቶች በማገልገል ሰፊ ልምድ እንዳካበቱ የግል ማኅደራቸው ያስረዳል፡፡ በዋነኛነት ካገለገሉባቸው አገሮች ውስጥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአሜሪካ መንግሥት ተልዕኮ ጨምሮ፣ ቴላቪቭ፣ ኒው ዴልሂ፣ ቤሩት፣ ባግዳድ፣ ጂቡቲ፣ ሞቃዲሾና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በዲፕሎማሲ መስክ የሠሩባቸው ይጠቀሳሉ፡፡ እንዲሁም በአልጄሪያ፣ በግብፅና በተለያዩ አገሮች በመሥራት ሰፊ ልምድ እንዳላቸውም ይነገራል፡፡ ፈረንሣይኛ ዓረብኛ በተጨማሪ የሚናገሯቸው ቋንቋዎች ሲሆኑ፣ የሁለት ልጆች አባትም ናቸው፡፡ ባለፉት አሥር ወራት የቀድሞዋን የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሽያ ሐስላኽ ስንብትን ተከትሎ የኢምባሲው ጊዜያዊ ተጠሪ ሆነው ያገለገሉት ቭሮማን የኢትዮጵያ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ሄደዋል፡፡ ስለአዲሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖር የሚችለውን ግንኙነት በተመለከተ፣ በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ የአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታና ስለአፍሪካ ቀንድ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ፒተር ቭሩማንን ዮናስ ዓብይ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያና አሜሪካ ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በርካታ ዓመታት ማስቆጠሩ ይታወቃል፡፡ ግንኙነታቸው ባለፉት ዓመታት ወደ ላቀ ደረጃ ማደጉንም አገሮቹ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓመት ሥልጣን ከያዙት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተያያዞ አሜሪካ የውጭ ግንኙነቷን በተመለከተ ብዙ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ በኢትዮጵያና በአሜሪካ ግንኙነት ላይ በጉልህ የሚታይ አዲስ ነገር ካለ፣ ወደፊት የሚከሰትና ካሁኑ ሊተነበይ የሚችል ነገር ካለም ሊያስረዱን ይችላሉ?

ፒተር ቭሩማን፡- ይኼንን ጉዳይ በሁለት መንገዶች መመልከት እችላለሁ፡፡ አንደኛው እንደሚታወቀው ከዚህ ዓመት ጀምሮ አዲስ አስተዳደር ወይም አዲስ ፕሬዚዳንት አለን፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ይህ ዓመት ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አካል የሆነችበት ነው፡፡ እኔ በግሌ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ ዲፕሎማት ተልዕኮ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2005 ባሉት ጊዜያት ለአምስት ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ በዚህ ልምዴ ውስጥ እስከማውቀው ድረስ አዲስ የተመረጠ የአሜሪካ መሪ በጥቂት ወራት ውስጥ የፀጥታው ምክር ቤት አባላትን የእንቁላል ቅርፅ ባለው ነጩ ቤተ መንግሥት ውስጥ በመጋበዝ ያነጋገረ መሪ አላውቅም፡፡ ምናልባት ይኼ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የመጀመርያው ነው ለማለት እርግጠኛ ባልሆንም፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በፀደይ ወራት (ሚያዝያ ወር አካባቢ) ይኼንን ማድረጋቸው ለእኔ የመጀመርያው ይመስለኛል፡፡ በእሳቸውም ግብዣ ላይ በኒውዮርክ የፀጥታ ምክር ቤት ውስጥ የሚገኙት ከኢትዮጵያ አምባሳደር ተቀዳ ዓለሙ (ዶ/ር) ተገኝተው ነበር፡፡ እንደሚታወቀው አምባሳደር ተቀዳ በዲፕሎማትነት ባካበቱት ልምድ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሱት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ አምባሳደሩም በግብዣ ሥነሥርዓቱ ላይ ኢትዮጵያንም ሆነ አፍሪካንም እንደ መወከላቸው፣ የአኅጉሪቱን ጥቅም በሚያስከብሩ ጉዳዮች ላይና በቀጣናዊ የሰላምና የፀጥታ ዓቢይ ጉዳዮች ላይ፣ እንዲሁም በልማትና በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ በሚገባ ንግግር አድርገዋል፡፡ ይኼ ደግሞ በጣም ጥሩና ጠቃሚ የሚባል አጋጣሚ እንደነበርም አስባለሁ፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ የፀደይ ወር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ወደ ኒውዮርክ ተጉዘው፣ በፀጥታው ምክር ቤት የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ ተሳትፈው ነበር፡፡ ይኼ ጉባዔ በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ላይ የሚመክር ነበር፡፡ በወቅቱ ከአሜሪካ አቻቸው ከሬክስ ቲሌርሰን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡ የሁለቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገናኝቶ መወያየት ሌላው ትልቅና አስፈላጊ የሚባል መልካም አጋጣሚም እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ከእነዚህ አጋጣሚዎች በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም በሲሲሊ ተደርጎ በነበረው የቡድን ሰባት አገሮች ጉባዔ ላይ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ጋር በመሆን በተገኙበት ወቅት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቲሌርሰን ጋር የጋራ ውይይት በማድረግ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ማስቀጠል ስለሚቻልበት ጉዳይ መክረዋል፡፡ ከእነዚህም በመነሳት በሁለቱ አገሮች መካከል በርካታ ውይይቶችና ምክሮች መካሄዳቸው፣ በተለይ የአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ሥልጣን በያዘባቸው የመጀመርያ ጥቂት ወራት ብቻ መሆኑ ራሱ የግንኙነታቸውን ደረጃ ይነግረናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አወቃቀርን በተመለከተ፣ አዲሱ የሰው ኃይል ምደባ ምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው?

ፒተር ቭሩማን፡- እንደሚታወቀው ይኼ ጉዳይ በሒደት ላይ ይገኛል፡፡ ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የሚገኙት የሥራ ዘርፎች ሙሉ ለሙሉ የሰው ኃይል ምደባው ተሟልቶ አልተጠናቀቀም፡፡ ምንም እንኳ የትራምፕ አስተዳዳር ለአፍሪካ ጉዳይ ምክትል የውጭ ጉዳዩ ሚኒስትር የሾመ ቢሆንም፡፡ በእርግጥ ተሿሚውም በቀጥታ ሥራ ጀምረዋል፡፡ ተጨማሪ ምደባ ይቀጥላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚሁ ምደባ ጋር ተያይዞ የአምባሰደሮችም ሹመት ይጠበቃል፡፡ ለኢትዮጵያም እንዲሁ አዲስ አምባሳደር እንደሚመደቡ ይጠበቃል፡፡ እርስዎም ቢሆኑ በወኪልነት የተመደቡበት ጊዜ በመጠናቀቁ፣ ስለመጪው አዲስ አምባሳደር የሚሉት ካለ ቢያስረዱን?

ፒተር ቭሩማን፡- እኔም ልገልጸው እያሰብኩት የነበረው አንዱ ቁልፍ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ የምደባ ቦታዎች ገና ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቁም ያልኳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከአዳዲስ ሹመቶች ውስጥ ለኢትዮጵያ ጨምሮ የአምባሳደሮች ሹመቶች ይገኙበታል፡፡ እናንተም እንደምታውቁት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በመጀመርያ አካባቢ ከመረጧቸው ዕጩ አምባሳደሮች መካከል አንዱ ለኢትዮጵያ የታጩት ይገኙበታል፡፡ ለኢትዮጵያ አምባሳደርነት የተመረጡት ማይክል ሬይነር ናቸው፡፡ ሬይነር በዲፕሎማሲ ተልዕኮ የካበተ ልምድ ያላቸው ሲሆኑ፣ በተለያዩ አገሮች በዲፕሎማትነት በማገልገል ስመ ጥር ናቸው፡፡ በአፍጋኒስታን በምክትል አምባሳደርነት ሠርተዋል፡፡ በቤኒን፣ በአፍሪካ ቀንድ ጂቡቲን ጨምሮ እስከ ሰባት በሚደርሱ የአፍሪካ አገሮች አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል፡፡ የአፍሪካ ቀንድን በተመለከተ በሚገባ ልምድ አካብተውበታል፡፡ እኔም እንዲሁ በዚህ የአፍሪካ ቀንድ አገልግያለሁ፡፡ ስለዚህ በሬይነር ምደባ (ዕጩ ቢሆኑም) አዲሱ የትራምፕ አስተዳዳር ለኢትዮጵያ ቀደም ብሎ ማዘጋጀቱ ትልቅ ጉዳይ አድርጌ እመለከተዋለሁ፡፡ የእኔም የወኪልነት መጠናቀቂያን ያረጋገጠ ሲሆን፣ አሁን የዕጩውን አምባሳደር ምደባ የአሜሪካ ሴኔት እንዲያፀድቀው እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ ሴኔቱም ሹመቱን በጥቂት ቀናት እንደሚያፀድቀው እጠብቃለሁ፡፡ ዕጩ ተሿሚው የኢትዮጵያ መንግሥትንም ይሁንታ አግኝተዋል፡፡ በቅርቡም ሬይነር አምባሳደር ሆነው አዲስ አበባ እናያቸዋለን ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በተመለከተ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መንግሥት ዕርዳታ ከሚያገኙ አገሮች ውስጥ በመጀመርያው ረድፍ ውስጥ ስሟ ይጠቀሳል፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለውጭ ግንኙነት ይደረግ የነበረው የገንዘብ ድጋፍ  ቅነሳ እንዲደረግ በይፋ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የበጀት ቅነሳው ስለባ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ ሥጋቶችና ግምቶች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው? በትክክል የበጀት ቅነሳው በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል?

ፒተር ቭሩማን፡- ምናልባት ሊኖረው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ተፅዕኖው ሊኖረው እንደሚችል ከአሜሪካ የበጀት አስተዳደር አንፃር ቢያብራሩት?

ፒተር ቭሩማን፡- በእኛ ሕገ መንግሥት አሠራር መሠረት ፕሬዚዳንቱ ረቂቅ የበጀት ቀመር ለኮንግረሱ ወይም ለኮሚቴው ያቀርባሉ፡፡ ኮሚቴው ወይም ኮንግረሱ የቀረበለትን ረቂቂ በጀት መርምሮ በአግባብነቱ ላይ ይወስናል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. ለ2017 የበጀት ዓመት በቀረበው የበጀት ቀመር ላይ ውሳኔ ተሰጥቶበት እየተተገበረ ሲሆን፣ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ ይቀጥላል፡፡ በዚህ መሠረት ባለፈው በጀት በሚቀርበው ላይ ምንም ዓይነት የተለየ ለውጥ አልነበረውም፡፡ ነገር ግን በቀጣይ ስለሚቀርበው በጀት ፕሬዚዳንቱ ወይም የበጀት አስተዳደር የሚመለከተው ቢሮ በውጭ ግንኙነቶች ለልማትም ሆነ ለዲፕሎማሲያዊ ሊመደብ ከሚችለው በጀት ላይ ቅነሳው ምን ያህል እንደሚሆንና የሚኖረውም ተፅዕኖ የቱን ያህል እንደሚሆን ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ስንመለከተው ግን ፕሬዚዳንቱ ባለፈው በቫቲካን ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አሁንም ቢሆን ፕሬዚዳንቱ በተለይ በድርቅ ጉዳይ አሜሪካ ያላትን አጋርነት በድጋሚ ለማስቀጠል ያላቸውን ኃላፊነት በድጋሚ ማረጋገጥ የሞከሩበትን ቁም ነገር በሚዲያዎች ትኩረት ተነፍጎት ያለፈ ቢመስልም፣ አንድ ተስፋ የሰጡበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰብዓዊ ዕርዳታና ረሃብን የመከላከል ኃላፊነት አድሎአዊነት ሳይኖር የሚቀጥል እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ካለፈው ዓመት ጀምሮ ረሃብ በደቡብ ሱዳን እያስከተለ ያለውን ጉዳት ማየት ይቻላል፡፡ ድርቅ በከፍተኛ ደረጃ ሶማሊያን አጥቅቷል፡፡ በቦኮ ሐራም ሰላሙን ያጣው ሰሜናዊ የናዳጄሪያ አካባቢም እንዲሁ ከፍተኛ የረሃብ ሥጋት እንዳንዣበበት ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በቀይ ባህር አካባቢ የተፈጠረውን የረሃብ አደጋንም ማስተዋል ይቻላል፡፡ ስለዚህ ችላ ሊባሉ የማይገባቸው ተመሳሳይ ቦታዎች አሉ፡፡

ይኼው የድርቅ ክስተት በኢትዮጵያም በቆላማ ሥፍራዎች እንዲሁ ጉዳት አስከትሏል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ እስካሁን ትልቁ ዕርዳታ ሰጪ አገር እኛው ነን፡፡ አሁን ባለው አስተዳዳርም ቢሆን አስቸኳይ የምግብ አቅርቦትን በተመለከተና ድርቅን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ በቦረና፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ቅድሚያ እየተሰጣቸው በሚገኙ ቁልፍ ወረዳዎች ሁሉ፣ በመገኘት የዕርዳታ ሥራውን እያከናወንን ነው፡፡ ከእነዚህ እውነታዎች አኳያ በሰብዓዊ ልገሳዎች የኢትዮጵያ ትልቅ አጋር ሆነን ቀጥለናል፡፡ ምንም እንኳ ትልቅ የልማት አጋር ለማለት ባይቻልም፣ የበጀት ቅነሳውን በተመለከተ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚታይ ቢጠበቅም፣ የበጀት ዓመቱ ከሚጀምርበት እስከ ጥቅምት 1 ቀን ድረስ ባሉት ወራት የሚኖሩ ድርድሮችና ውይይቶች በቀጣይ ዓመት ሊኖር የሚችለውን ዕርዳታና ተያያዥ ጉዳዮች ቅርፅ የሚያሲዝ ዕርዳታ ቀድሞ መከናወኑ ወሳኝነት አለው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡-  እርስዎ እንዳሉት በሰብዓዊ ዕርዳታ ካላችሁ ቀጥተኛ ተሳትፎ በተጨማሪ፣ በመንግሥት በኩል የምታደርጉት ዕርዳታ አለ፡፡ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የሚገኙትን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ጋር በአጋርነት እንደምትሠሩ ይታወቃል፡፡ የአገር በቀል ድርጅቶችም ቢሆኑ ከመንግሥት በቀጥታ ወይም በዩኤስኤአይዲ በኩል በሚደረገግላቸው የገንዘብ ድጋፍ ለተጠቃሚዎች የሚያደርጉት እገዛም አለ፡፡ ነገር ግን እነዚህ አገር በቀል ድርጅቶች የበጀት ቅነሳው በፈጠረባቸው ሥጋት ምክንያት ቢያንስ ወደ ኤምባሲያችሁ በመምጣት ሥጋታቸውን ገልጸውላችኋል?

ፒተር ቭሩማን፡- አዎ፡፡ በተወሰነ ደረጃ የመጡ አሉ፡፡ እንደሚታወቀው ባለፈው ሰኔና ቀደም ብሎ ከግንቦት ወር ጀምሮ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታን በተመለከተ ሪፖርት ተደርጎ ነበር፡፡ እኔም እራሴ በአካል ሄጄ የጎበኘኋቸው ሥፍራዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በሶማሌ ክልል በዶሎ ዞን ዋርዴር አካባቢና አቅራቢያዎች፣ እንዲሁም እስከ ኦጋዴን ድረስ በሄድኩበት ወቅት በርካታ ሕዝብ በድርቁ ክፉኛ ተጠቅቷል፡፡ በእነዚህ ሥፍራዎች በርካታ የረድኤት ድርጅቶች አስቸኳይ የዕርዳታ ሥራ ሲያከናውኑ ነበር፡፡ እንደ ሜርሲ ኮር የመሳሰሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድርጅቶች አንገብጋቢ ሥራዎችን  በማከናወን ተጠምደዋል፡፡ የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) አንዱ ድርጅት ነበር፡፡ የእሶም የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤትም አስፈላጊ ትብብር ሲያደርግ ነበር፡፡ ሲዲሲም እንዲሁ የጤና ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ የራሱን አስተዋፅኦ በማድረግ አስፈላጊ ዕርዳታ በማድረግ  ላይ ይገኛል፡፡ አሁን ካለው ሰፊ የቆዳ ስፋት አንፃር የችግሩን ጥልቀት ከግምት በማስገባት፣ የአሜሪካ መንግሥት የሚፈለገውን አስቸኳይ ምላሽ ካልሰጠ ችግሩ የበለጠ አስጨናቂ ወደ ሆነ ደረጃ እንደሚሄድ ማስተዋል ይቻላል፡፡

ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት እስካሁን የቀዳሚነት ሚና እየተጫወትን ነው፡፡  ሌሎች አጋሮች ሆኑ መንግሥት ማቅረብ ከሚችሉት በላይ ያለንን ሀብት ሁሉ በመለገስ የተጎዳ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመርዳት እየጣርን ነው፡፡ መንግሥትም ቢሆን የራሱን ጥረት በማጠናከር ለዕርዳታ ፈላጊዎች ሁሉ አስፈላጊውን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተገንዝቢያለሁ፡፡ በቅርቡ በአደጋ መከላከልና ሥጋት አመራር ኮሚሽነር በአቶ ምትኩ ካሳ የተሰጠው መግለጫ ይኼንኑ አረጋግጦልኛል፡፡ ኮሚሽነሩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኰንን የበላይ ተቆጣጣሪነት አጠቃላይ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ማስፈለጉ ግልጽ በሆነበት ጊዜ ሁሉ፣ መንግሥት ወደኋላ እንደማይል ማረጋገጣቸውን ሁላችንም እናስታውሳለን፡፡ ከዚህ በመነሳትም ማንኛውንም አስፈላጊ መረጃም ሆነ ማስረጃ በመንግሥት በሚቀርብበት ጊዜ እኛም ተጨማሪ ልናደርገው በሚገባ ነገር ሁሉ ቀድመን ዕቅድ ለማውጣትና የበኩላችንን ለማድረግ ይጠቅመናል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩልና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በተመሳሳይ ዕቅዶቻቸውን ለመተግበር ይረዳቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ትልልቅ ዕርዳታ ለጋሾችም እንዳሉ ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረትም፣ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (DFID)፣ የአቻ አጋር ድርጅቶች፣ የስዊዲንና የኖርዌይ መንግሥታትን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ልክ እ.ኤ.አ. በ2015/16 በጋራ እንዳደረግነው ሁሉ በተለይም የህንድ ውቅያኖስ ያስከተለው የአየር ንብረት መዛባትን ተከትሎ፣ በደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል የታየውን ዓይነት ችግር በአንድነት ተረባርበን ከክልል ቢሮዎችም ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ሁሉ ዕርዳታ ማድረግ እንችላለን፡፡  

ሪፖርተር፡-  ከአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ በተጨማሪ ሌሎችም እገዛ የሚደረጉላቸው ዘርፎች አሉ፡፡ ለአብነት የሴቶችን አቅም ማጎልበት፣ የወጣቶች፣ የጤናና በመሳሰሉት፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ መንግሥት ለወታደራዊ ዘርፉ የሚደረግለት ዕርዳታ ከፍተኛ ነው የሚል ግምት አለ፡፡ ከዚህ አንፃር የአሜሪካ መንግሥት በጀት ቅነሳ ዕውን ከሆነ የትኛው ዘርፍ የቅነሳው ሰለባ ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ መገመት ይቻላል?

ፒተር ቭሩማን፡- እዚህ ላይ እኛ ከምናደርገው ዕርዳታ ከፍተኛ ድርሻ ለፀጥታው ወይም ለወታደራዊ ዘርፍ ይሄዳል የሚል የተሳሳተ ግምት አለ፡፡ እኛ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ለሰላምና ለፀጥታ ማስከበር በደቡብ ሱዳን የምታደርገውን ተልዕኮ፣ እንዲሁም ሽብርተኝነትን በመዋጋት ሰላም ለማስከበር በምታደርገው ዘመቻ የራሳችንን ዕርዳታ እናበረክታለን፡፡ ይኼ ዕርዳታ ግን ውስን ሊባል የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ ለእነዚህ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያደረግነው ዕርዳታ ባለፉት ዓመታት ከአሥር ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም፡፡ አሁን በሁለቱ ሱዳኖች የተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታ ማስከበር ኃይል አለ፡፡ ለዚህ ኃይል እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባልነታችን የምናደርገው መደበኛ መዋጮ ነው፡፡ በተጨማሪም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ለሚሰማራው የኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይል አስፈላጊ ነው የሚባል ዕርዳታ እናደርጋለን፡፡ ይኼ ዓይነቱ ዕርዳታ ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡ የዚህ ዋና ዓላማው ደግሞ በደቡብ ሱዳን ለረሃብ መንስዔ የሆነውን ግጭት በማስቆም ተፋላሚ ቡድኖች ወደ ዕርቀ ሰላም እንዲገቡ ማሳያ ነው፡፡ በሌላ በኩል ስናየው በቀጣናው እኛ ‹ትሮይካ› በተባለው ጥላ ሥር የአባልነታችንን፣ ኢትዮጵያም የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) መሪ እንደ መሆኗና ከፀጥታው ምክር ቤትና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ተጣምረን የምንሠራው አንዱ አካል በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ ለሌሎች የዕርዳታ መስኮችም በጥያቄው ላይ የተጠቀሱትን በተመለከተ ያለ ጥርጥር አሜሪካ የመሪነት ቦታዋን ይዛ፣ ጠቃሚ የሚባሉም ድጋፎችን አጠናክራ ትቀጥላለች የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ሰላምና ፀጥታ ማስፈን አንዱ የጋራ ሥራችሁ መሆኑ ካልቀረ፣ በቅርቡ በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የተፈጠረው ወታደራዊ ፍጥጫ የመንግሥትዎ አቋም ምንድነው? ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላው ክስተት የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራው ቡድን በኳታር ላይ የወሰደው ማግለል ወደ ባሰ ወታደራዊ ግጭት ቢያመራ፣ በአፍሪካ ቀንድ ሊከሰት የሚችለውን ችግር እንዴት ታዩታላችሁ?

ፒተር ቭሩማን፡- ኤርትራና ጂቡቲ ወደ ባሰ ጦርነት ያመራሉ የሚል ግምት የለኝም፡፡ በእነዚህ አገሮች ጉዳይ ከተለያዩ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቻለሁ፡፡ በእርግጥ በሁለቱ አገሮች ቀደም ብሎ ለተነሳው ውዝግብ የኳታር ሚና አስፈላጊ የነበረ ሲሆን፣ አሁን የኳታር መውጣት በመጠኑ አሳሳቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥሩ ሥራ እያከናወነች ነበር፡፡ ኢትዮጵያና ጂቡቲ የኤርትራን ጉዳይ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት መወሰዳቸው አንድ ጥሩ ሥራ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ሊፈጽሙት የሚገባ ተግባር እንደሆነ እመለከታለሁ፡፡ በቂ ማብራርያም ሰጥተውበታል፡፡ አሁን የሁለቱ አገሮች ውዝግብ ማንሰራራት የኢትዮጵያንም ፍላጎት የሚነካ በመሆኑ፣ ስለዚህ ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት በመውሰዳቸው ትክክለኛ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ እንዲሁም የባህረ ሰላጤው አገሮችን ፍጥጫ በተመለከተ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ኅብረት አቋም መደገፏ ትክክለኛ ሲሆን፣ ሶማሊያም ያደረገችው ያንኑ ነው፡፡ ለማንኛውም ወገን አድልኦ ሳይደረግ የኩዌትን ዓይነት አቋም በመያዝ ማግባባቱን ነው ኢትዮጵያ የመረጠችው፡፡ የእኛንም አስተዳደር ከተመለከትን ፕሬዚዳንቱም ሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሁሉም አገሮች መሪዎች ወደ ጠረጴዛ  ውይይት እንዲመጡና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ነው ጥሪ ያስተላለፉት፡፡ እንዲያውም ፕሬዚዳንቱ ራሳቸው በቀጥታ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ከአሜሪካ ጋር በመሆን ችግራቸውን ፈተው አሸባሪነትን በጋራ ድል በመንሳት በቀጣናው በፍጥነት ሰላም እንዲሰፍን ነው ጥሪ ያስተላለፉት፡፡ አሁን በጋራ እየሠራን ነው፡፡ የባህረ ሰላጤው ችግር ተባብሶ የአፍሪካ ቀንድን ሊለበልብ ይችላል የሚል ሥጋት ብዙም መረጃው የለኝም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ኤርትራ ለብዙ ጊዜ ጠብ አጫሪ በመሆንና ዜጎቿን በማሰቃየት ለስደት ስታጋልጥ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ይኼ ችግር አሳሳቢ ነው፡፡ ለጊዜው ግን በአካባቢው ጉዳይ መናገር የምችለው ኢትዮጵያና ጂቡቲ በጋራ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ወደ ሥልጣን በመጣበት የመጀመርያ ሳምንታት ከወሰዳቸው ወታደራዊ ዕርምጃዎች አንዱ በሶማሊያ በሚንቀሳቀሰው አልሸባብ በተባለው ቡድን ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አስተዳደሩ በዚህ የፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ የቀድሞ አስተዳደሮችን ተመሳሳይ ዕርምጃ ለማስቀጠል ያለውን አቋም ያሳያል ተብሎ ሊወሰድ ይችላል?

ፒተር ቭሩማን፡- አልሸባብን በሶማሊያ ውስጥ በመዋጋት ረገድ የአፍሪካ ኅብረት በሰላም አስከባሪ ኃይሉ (AMISOM) በኩል ትልቅ ዋጋ ያለው ሥራ እያከናወነ ነው፡፡ እንዲሁም ለሶማሊያ በቅርቡ አዲስ አስተዳደር ነው የመጣው፡፡ አዲሱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር  የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ላይ ተገኝተው ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር ተወያይተው ነበር፡፡ የሁለቱ ውይይትም የእኛን ሥጋት የሚጋራ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መሪዎች መካከል የተደረገው የሁለትዮሽ ውይይትም በጣም አስደንቆኛል፡፡ የሶማሊያ መሪዎችም አልሸባብን በመዋጋትም ሆነ የተሻለ አስተዳደር በመገንባት ረገድ ተጨማሪ ዕርምጃ መሄድ እየቻሉ ነው፡፡ የአልሸባብ ይዞታዎች ላይ በሚወስዱት ዕርምጃ የተሻለ ነገር ማድረግ ጀምረዋል፡፡ በተጨማሪም እኛም ለመዋጋት በምናደርገው ጥምረት ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል ባደረግነው ጥያቄ መሠረት፣ ኢትዮጵያም የፀረ ኤይኤስ ጥምረቱ በሚቀጥለው ወር በሚያካሂደው ውይይት ትሳተፋለች፡፡ እንደሚታወቀው በአልሸባብ ቡድኖች መካከል መከፋፈል እየተፈጠረ በመምጣቱ፣ ግማሹ አይኤስን እየተቀላቀሉ ናቸው፡፡ ሌሎቹ አልቃይዳን በመደገፍ ሒደት ላይ ናቸው፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ነቀርሳ ናቸው፡፡ ይኼ ደግሞ አሁንም ቢሆን ለቀጣናው ሌላ ፈታኝ ችግር መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህም ምክንያት አዳዲስ ህዋሳት ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ነው ኢትዮጵያም በፀረ አይኤስ ጥምረት እንድትቀላቀል የተጋበዘችው፡፡ 

ሪፖርተር፡-  ወደ ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ስንመለስ ከሁለት ዓመት በፊት የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ ኃላፊዋ ዌንዲ ሼርማን ሲሆኑ፣ በወቅቱ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ ግንቦት 7ን በተመለከተ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ መንግሥታቸው የትጥቅ ትግል የሚያነሱ ቡድኖችን እንደ አሸባሪ እንደሚያይ ገልጸው ነበር፡፡ የአሁኑ አስተዳዳር በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አቋም ምንድነው?

ፒተር ቭሩማን፡- በዚህ ጉዳይ ያኔ ከተነገረው ተነስቼ ዛሬ እንዲህ ነበር ማለት አልችልም፡፡ አስታውሳለሁ እሳቸው [ዌንዲ ሼርማን] የመጡት እ.ኤ.አ. በ2015 የፀደይ ወራት ውስጥ ነበር፡፡ የመጡትም በኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣ ነበር፡፡ በወቅቱ ግልጽ አቋም ነበር ያሳዩት የአሜሪካ መንግሥት ማንኛውንም አጋር መንግሥት በኃይል ለመጣል የሚደረግ ትግልን እንደማይደግፍ ነበር ያንፀባረቁት፡፡ ይኼ ደግሞ ኢትዮጵያንም ይጨምራል፡፡ አሁን እሳቸው የተናገሩት ሐሳብ ቃል በቃልም ባይሆንም ለመግለጽ ነው የሞከርኩት፡፡ መሣሪያ አንግቦ መንግሥትን በኃይል ለመጣል የሚደረግን እንቅስቃሴ እንደማይደግፉ ነው ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት የገለጹት፡፡ አሁንም ቢሆን  አዲሱ የአሜሪካ አስተዳዳር እንደዚህ ያሉ ድርጅቶች (ግንቦት 7 እና ተመሳሳይ ድርጅቶች) ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተለየ ቦታ ይሰጣቸዋል ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡-  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአሜሪካ መንግሥት ብዙ ጊዜ ከሚታወቅበት በዕርዳታ ላይ ከተመሠረተ እገዛ ወደ ልማት ወይም ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት የመግባቱ ጉዳይ ይገለጻል፡፡ በተለይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት ይኼንኑ አንፀባርቀዋል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ በፕሬዚዳንቱ አነሳሽነት በፓወር አፍሪካ ኢኒሼቲቭ አማካይነት ለኢትዮጵያ የኮርቤቲ እንፋሎት ኃይል ማመንጫ ተፈርሞ ግንባታ ተጀምሯል፡፡ ምናልባትም ኢንሼቲቩ የኦባማ ‹ሌጋሲ› ተደርጎ ስለሚቆጠር፣ በተተኪው ፕሬዚዳንት ትራምፕ መምጣት  ሳቢያ ችግር ላይ ነው የሚል ሥጋት ስላለ እንዴት ያዩታል?

ፒተር ቭሩማን፡- የዚህ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ለኢትዮጵያ ትልቅ ነገር ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የሚገርምህ ነገር የእኔም የዚህ አገር ቆይታዬ ተጠናቆ የመጨረሻው የስንብት ሥራዬ የሆነው ለዚህ ፕሮጀክት ጉዳይ ከአዲሱ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪሲቲ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢንጂነር) ጋር ያደረግኩት ውይይት ነው፡፡ አዲሱ ሚኒስትር በውኃ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ሥራና ግንኙነት ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ እናም ለኮርቤቲ ፕሮጀክት ወደፊት መግፋት ጠቃሚው ሰው ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱ ሁለት ምዕራፎች ነው ያሉት፡፡ ነገ ግን ፕሮጀክቱ እስከ አንድ ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይችላል፡፡ ይኼ የእንፋሎት ኃይል ደግሞ ከንፋስ ኃይልና ከፀሐይ ኃይል በዚህ አገር ሊመረት የሚችለውን ጨምሮ ሲታይ በዚህ አገር ያለው ዕምቅ ኃይል ትልቅ ነው፡፡ በእርግጥ እስካሁን ለዚህ አገር ትልቁ የኃይል ምንጭ ከውኃ ኃይል እየተመረተ ያለው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የተለያዩ የአሜሪካ ኩባንያዎችም በእዚህ አገር በውኃ ኃይል ላይ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ለአካባቢ ተስማሚ የሆነና ታዳሽ ኃይልን የሚያረጋግጥ የኃይል ምንጭ ላይ ያለች ሥፍራ ነች፡፡ ያለው የኃይል ስብጥርም በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡

በቅርቡ ወደ ሐዋሳ ሄጄ የኢንዱስትሪ ፓርኩን ጎብኝቼ ነበር፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ደግሞ ኮርቤቲ ኃይል ማመንጫ ካለበት ሩቅ አይደለም፡፡ ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ከንፋስ ኃይል የተገኘ ኃይል ብቻ በማቅረብ ፍላጎቱን ማሟላት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ከውኃ ኃይል የሚገኘውን ማቅረብ ሊኖርብን ይችላል፡፡ ያም ብቻውን በቂ ሊሆን ስለማይችል ተጨማሪ ኃይል ከንፋስና ከፀሐይ ለማሟላት መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ደግሞ ኃይድሮ (ከውኃ ኃይል) ማመንጨት ደግሞ ውድ የሚባል በጀት ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን የኃይል አቅርቦቱን ከእንፋሎት ፕሮጀክት ጋር ማስተሳሰር ከተቻለ መደበኛ፣ ተለዋዋጭ ያልሆነና አስተማማኝ የኃይል ምንጭ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የእንፋሎት ኃይል ማቅረብ ሲቻል ኢትዮጵያ እየገነባቻቸው ላሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች አርኪ የኃይል ፍላጎት ማሟላት ይቻላል፡፡ በሐዋሳም ሆነ በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ላሉት በሙሉ በዚህ መንገድ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ስለዚህም ኮርቤቲና መንግሥት በጋራ ፕሮጀክቱን ወደፊት ለማስኬድ ከግቡ ለማድረስ በጥሩ ሒደት ላይ ናቸው፡፡ ዕድገቱም በጠንካራ መሠረት ላይ እየተጓዘ እንደሆነ አስባለሁ፡፡

አሁን የእንፋሎት ኃይልን በተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ አለ፡፡ የማስፈጸሚያ ደንቡም እየተተገበረ ይገኛል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ደግሞ በደህና መሠረት ማስኬድ ተችሏል፡፡ ለዚህ ዕድገት ደግሞ አዲሱ ሚኒስትር ጥልቅ ሥራ እያከናወኑ ነው፡፡ በተለይ ፕሮጀክቱን በትክክለኛ ዕድገት ለማስቀጠል ከኩባንያው፣ ከፓርላማውና ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይኼ ደግሞ ልክ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግብ መሠረት እየተተገበረ እንደሆነ የሚያሳይና የአገሪቱን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ፣ የአካባቢ ጉዳትን በመከላከል ታዳሽ ኃይል ማመንጨት እንደሚችል፣ እንዲሁም አገሪቱን የብዙ ሜጋ ዋት የታዳሽ ኃይል ባለቤት እንደሚያደርጋት አስባለሁ፡፡ ይኼ ስኬት ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ደንበኞች፣ ለመንግሥትም ሆነ ለአሜሪካ መንግሥት የቀድሞው አስተዳደር ጭምር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በአሜሪካ ደግሞ የቀድሞ አስተዳደርን ፖሊሲዎች ከአዲስ መጪው አስተዳደር ጋር መገምገም የተለመደ በመሆኑ፣ በአሁኑ ስኬት አዲሱ አስተዳደር ፖሊሲውን በመደገፍ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል ይረዳል፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ ሆኖ አዲሱ አስተዳደር ፓወር አፍሪካ የተባለውን የኦባማ ኢኒሼቲቭ ሊያስቀጥል እንደሚችል ወይም የሚለወጥ ነገር እንደሚኖር ለመገመት ጊዜው ገና ነው፡፡ ነገር ግን የፕሮጀክቱ ስኬት በራሱ የቀጣይነቱን ሁኔታ ይወስነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሚኒስትሩ ጋር በተገናችሁበት ጊዜ የግል ባለሀብቶች በኃይል ማመንጨትና ሽያጭ ላይ (Independetnt Power Agreement) በተመለከተና በሕግ ማዕቀፉ መዘግየት ላይ የተወያያችሁትንና የመንግሥት ምላሽ ካለ ቢነግሩን? ምክንያቱም የሕግ ማዕቀፉ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ካልተገባ ኮርቤቲንም ሆነ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን አያደናቅፍም?

ፒተር ቭሩማን፡- ማደናቀፉ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ይኼኛው የስምምነት ጉዳይ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ እኔ ወደዚህ አገር ካመጣሁበት ከሦስት ዓመት በፊት በስምምነት ውስጥ በተካተተው ዋናው የስምምነት አካልና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት ተደርጎ ነበር የተጀመረው፡፡ በትክክልም እስከ ዛሬ ድረስ የሕግ ማዕቀፉ ሲያነጋግር የቆየ መሆኑንና በቅርቡም የተለያዩ የጽሑፍ ዘገባዎችን አንብቤያለሁ፡፡ መንግሥትም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ላይ በሰፊው እያጤነው ምን መደረግ እንዳለበት ለማየት እየተሞከረ ነው፡፡ የኮርቤቲ ፕሮጀክት ቢሆን በግንባር ቀደምትነት የራሱን ጥረት እያበረከተ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር ቀላል ወይም አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይደለም፡፡ ጊዜም ወስዷል፡፡ ቢሆንም በቆየሁባቸው ሦስት ቀናት ሳላደንቅ የማላልፈው ጉዳይ ቢኖር የፈለገ ጊዜ ቢወሰድ እንኳ በሁለቱ አገሮቻችን መካከል፣ ከሲቪል ማኅበረሰቦች ጋር ወይም ከሌሎች ባለ ድርሻዎች ጋር ወደ ጋራ መግባባት ከደረስንና ተጨማሪ የሐሳብ ግብዓቶች ከታከሉበት፣ ቸኩሎ አንድ ነገር ከመወሰን ይልቅ መዘግየቱ ወደ ተሻለ ውጤት ሊወስደን እንደሚችል ማየቴ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ሕጉ መዘግየቱ ችግር መፍጠሩ የማይቀርና አንዳንዴም እጅግ ፈታኝ ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ ስለዚህም በሁሉም ወገን መግባባት ሲደረስበትና ሕጉ የበለጠ ተቀባይነት ሲኖረው የበለጠ ስኬታማ ይሆናል፡፡