Skip to main content
x
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያልተለመዱ ግምገማዎችና ውሳኔዎች ተግባራዊነት በጉጉት እየተጠበቀ ነው
የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች መሪዎች አቶ ለማ መገርሳ፣ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ አቶ ደመቀ መኮንንና ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያልተለመዱ ግምገማዎችና ውሳኔዎች ተግባራዊነት በጉጉት እየተጠበቀ ነው

  • የሚፈቱ ፖለቲከኞች ዝርዝር ጉዳይ ከአሁኑ አከራካሪ ሆኗል

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ዝግ ስብሰባ አጠናቆ በመጨረሻ ባወጣው መግለጫና አራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጀቶች ሊቃነ መናብርት ታኅሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችና ሌሎች ግለሰቦች እንደሚፈቱና ‹‹ማዕከላዊ›› በመባል የሚታወቀው የምርመራ ማዕከል እንደሚዘጋ ማስታወቃቸውን ጨምሮ ‹‹ያልተለመዱ›› የተባሉት ግምገማዎችና ውሳኔዎች ተግባራዊነት በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባ አጠናቆ በመጨረሻ ባወጣው መግለጫ፣ የችግሩ ዋነኛ ምንጭ ሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል መሆኑን አሳውቋል፡፡ መግለጫውን ከሰጡት መካከል አንዱ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ‹‹በዓቃቤ ሕግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር ላይ የሚገኙና የተፈረደባቸው ፖለቲከኞችም ሆኑ የተለያዩ ግለሰቦች ይፈታሉ፡፡ ይህም የሚደረገው የተሻለ አገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት በማሰብ ነው፡፡ ታሳሪዎቹ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በይቅርታ ይለቀቃሉ፤›› ብለዋል፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባላት በአገሪቱ ለተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በጥልቀትና በዝርዝር በመምከር የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ስብሰባውን ‹‹ከዚህ ቀደም ከተደረጉት ሁሉ በዓይነቱ ለየት ያለ ነው፤›› ብለውታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ የነበረው ሰፊ መጠራጠርና አለመተማመን በመንግሥታዊ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሮ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ በገዥው ፓርቲ ቸልተኝነትና በውስጡ ያሉ ጉዳዮችን በአግባቡ መፍታት ባለመቻሉ ምክንያት አገሪቱ ለቀውስ ተዳርጋ መቆየቷንም አምነዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፣ ‹‹በመደበኛ አሠራራችን የጋራ አሠራራችንን መሠረት አድርገን በየጊዜው ሥራዎችን የምንገመግምበትና አቅጣጫዎችን የምናስቀምጥበት አሠራር አለን፡፡ ይኼኛው ለየት የሚያደርገው አሁን ያለንበት አገራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? አሁን ካለንበት ሁኔታ ለመውጣት መሪ ድርጅቱ ምን ሊያደርግ ይችላል? የችግሩ ጥልቀት ምን ይመስላል? ይኼ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ የሚፈጥረው ችግርና አንደምታ ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎች ላይ በስፋትና በጥልቀት ተወያይተን የተስማማን በመሆናችን ነው፡፡ በዋነኛነት በችግሩ ዙሪያ መግባባት መቻል፣ በሚመጣው አደጋ ላይ የጋራ ግንዛቤ መያዝና ከዚህ ሊያወጣ በሚችል መፍትሔ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰናል፤›› ብለዋል፡፡

የኦሕዴድ ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳም በመግለጫው ወቅት ሲናገሩ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ለአገሪቱ በርካታ መልካም ነገሮችን እየሠራ የመጣ ቢሆንም፣ በሒደት በርካታ ግድፈቶች ያሉበት ግንባር ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች ቆም ብለን ውስጣችንን እንድናይና እንድንፈትሽ የሚያስገድዱ ናቸው፡፡ በግለሰብና በቡድን ደረጃ እንዲሁም በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የነበረው መጠራጠርና አለመተማመን በጣም ሰፊ ነበር፡፡ ይህ ችግር ሳይፈታ አገር መምራት አይቻልም፡፡ አሁን ባለንበት ወቅታዊ ሁኔታ የአገር ህልውና ጥያቄ ውስጥ ወድቋል፡፡ የአገር ህልውና ደግሞ ከግለሰቦች፣ ከባለሥልጣናትና ከቡድኖች ክብር በላይ ነው፡፡ በስብሰባው አሉ ብለን የምንላቸውን፣ የሰማናቸውንና የምንታዘባቸውን ጉዳዮች በግልጽ ተወያይተናል፡፡ ሁላችንም አንዳችን በአንዳችን ላይ የሰላ ትችት እያቀረብን የተገማገምንበት መድረክ ስለሆነ፣ በግሌና እንደ ድርጅት ኦሕዴድ ደስተኞች ነን፡፡ መታየት የሚገባቸው ጉዳዮች በሚገባ ታይተዋል ብለን እናምናለን፡፡ በመጨረሻ ችግሮቻችንን በሚገባ ዓይተን በጥሩ መንፈስና መግባባት የወጣንበት መድረክ ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳችን አንድ ትልቅ እመርታ ነው፡፡ ነገር ግን የበለጠ ውጤቱ የሚለካው በተግባር ስንተረጉመውና መሬት ላይ ያለውን ችግር ስንፈታው ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ከዚህ በፊት ያላየናቸውን አዳዲስ ጉዳዮች ጊዜ ወስደን በጥልቀት ተወያይተንባቸዋል፡፡ በውስጣችን የነበሩ አንዳንድ ክፍተቶች፣ መጠራጠሮች፣ አለመተማመኖችና የአመራር አንድነት ችግሮች ለመፍታት ያስቻለ መድረክ ነው፡፡ አራቱም ድርጅቶች እርስ በርስ ተማምረዋል፡፡ ለምሳሌ ሕወሓት ያላየውን ችግር ሌሎች ድርጅቶች እንዲፈትሽ ዕድል ሰጥተውታል፤›› ብለዋል፡፡  

በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መግለጫ ላይ ገዥው ፓርቲ የውስጠ ዴሞክራሲ ችግር እንዳለበት መግለጹ ይታወሳል፡፡ አቶ ደመቀ ይህን አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹አሁን በደረስንበት ደረጃ በኢሕአዴግ ውስጥ የዴሞክራሲ ችግሮች በስፋት ታይተዋል፡፡ የአሳታፊነት ችግር በውስጡ ይታያል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ችግር ነበረበት፡፡ የመደማመጥ ችግር ነበር፡፡ እኔ ያልኩት ካልሆነ ሌላው ሐሳብና አካሄድ ሁሉ ጉድለት ያለበትና የማያስኬድ እንደሆነ አድርጎ መውሰድ ነበር፡፡ ይኼ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዳይጠናከሩ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ መሪዎች ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው ብለን ካቀነቀንን ያንን በተግባር የሚተረጉም ዝግጁነት ይጠይቀናል፤›› ብለዋል፡፡        

የፖለቲከኛ እስረኞች መለቀቅ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ስቧል፡፡ ይሁንና የሚለቀቁት እስረኞችና ግለሰቦች ዝርዝር ማንነት ለጊዜው አልተገለጸም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና የመሳሰሉት በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች እንደሚለቀቁ ግን ይጠበቃል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ እስክንድር ነጋ፣ ዶ/ር መራራ ጉዲና ይፈታሉ ተብሎ ከሚጠበቁ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እስረኞቹ በምን መሥፈርትና መቼ ይፈታሉ? የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ካልተመለሰ ከመፍትሔ ይልቅ ሌላ ችግር ይዞ እንደሚመጣ የሕግ ባለሙያውና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ያሳስባሉ፡፡ 

ይህ ውሳኔ ይፋ ከተደረገ በኋላ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ውሳኔውን ‹‹በጎ ጅምር›› በማለት ስሜት ሲገልጹ ነበር፡፡ ለሳምንታት ተዘግቶ የነበረው ማኅበራዊ ሚዲያም በዕለቱ የተከፈተ ሲሆን፣ ይኼው አጀንዳ ዋነኛው የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡

አንዳንዶች ይህ ቀን ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ በቆየው ግጭት፣ ብጥብጥና የፖለቲካ አለመረጋጋት መንፈሳቸው ታውኮ ለከረሙት ዜጎች ታኅሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የብርሃን ብልጭታ ያዩበት ነው ብለውታል፡፡

ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒ ውሳኔው የአገሪቱን ችግር ለመፍታት እንደ መልካም ጅማሮ ምልክት ከማሳየት ባለፈ፣ እውነተኛ የሆነ ለውጥ ለመሆኑ የሚጠራጠሩ አስተያየት ሰጪዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስማቸው በፌስቡክ አድራሻቸው የተገለጸውን ጨምሮ የፖለቲከኞችን ከእስር መለቀቅ አስመልክተው የተናገሩት ንግግር በተደጋጋሚ ዕርማት ተደርጎበታል። የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች ውሳኔውን አንዴ ምሕረት ሌላ ጊዜ ደግሞ ይቅርታ እያሉት ይገኛሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመርያ መግለጫ ምሕረት እንደሚደረግ ነበር ያስታወቀው፡፡

‹‹የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት›› ላለመ መንግሥት የወንጀል ሪከርድ ስለሌለውና ጉዳያቸው በመታየት ላይ ያሉትንና የተፈረደባቸውን ግለሰቦች ስለሚያካትት ምሕረት የተሻለ ምርጫ እንደሆነ ተንታኞችና የሕግ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ለዚች አገር መሠረታዊ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት የፖለቲከኞች መፈታት ብቻውን የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች ይመለክታሉ። መንግሥት ላይ ተቃውሞውን ያሰማው ሕዝብ የጠየቀውም እነዚህ ያለ አግባብ የታሰሩ ሰዎች ይፈቱ የሚለውን ጥያቄ ብቻ እንዳልሆነም አስታውሰዋል።

ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት ማጣቱ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ለተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ እንደ መሠረታዊ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ገዥው ፓርቲ የሕዝብ አመኔታን መልሶ ለማግኘት እንደሚሠራ መግለጹ ይታወሳል፡፡    

ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ እየተሸረሸረ የመጣው የሚያቀርባቸው ወሳኝ ጥያቄዎች ምላሽ በማጣታቸው ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ዜጎች ለመንግሥት በተደጋጋሚ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች ውስጥ ፍትሐዊ የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል እንዲፈጠር፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብት ሳይሸራረፍና የፖለቲካ ሥሌትን መሠረት ሳያደርግ እንዲፈጸም፣ በተለይ ለሥራ ዝግጁ ለሆኑ ወጣቶች በቂ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፣ ለብዝኃነትና ለልዩነት ከተሰጠው ትኩረት ባላነሰ አገርን አንድ በሚያደርጉ የጋራ እሴቶችና ተቋማት ግንባታ ላይ ይበልጥ እንዲሠራ፣ እንድሁም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ክልሎች ከፌዴራል መንግሥቱ ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖና ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ዕድል እንዲሰጣቸው መባላቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡  

እርግጥ ነው የዜጎች በገለልተኛና በተዓማኒ የዳኝነት አካል ፍትሐዊ ፍርድ የማግኘት መብት እንዲከበር ለዓመታት ጥሪ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ ይህም የፖሊስ የተጠርጣሪ አያያዝና የምርመራ ወቅት፣ የዓቃቤ ሕግ የክስ ዝግጅትና አቀራረብ፣ የፍርድ ቤቶች ቀጠሮዎችና ክርክሮች፣ እንዲሁም የእስረኞች አያያዝ ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማስቀረትን ይጨምራል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹በደርግ ዘመን በምርመራ ስም ልዩ የጭካኔ ተግባር ሲፈጸምበት የነበረውና በተለምዶ ማዕከላዊ በመባል የሚታወቀው የምርመራ ማዕከል እንዲዘጋ ተደርጎ፣ ይህ እንዳይደገም ለማድረግ ማዕከላዊ ሙዚየም እንዲሆን ተወስኗል፤›› ብለዋል፡፡

ማዕከላዊ የሚባለው የምርመራ ተቋም በደርግ ዘመን በእስር ቤትነት እስረኞችን ለማሰቃየት ይውል እንደነበር፣ አሁን ግን ተዘግቶ ወደ ሙዚየምነት እንደሚቀየር መግለጫው መግለጹን በርካቶች ውሳኔው በግማሽ ልብና ቁርጠኝነት የተሰጠና መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ገዥው ፓርቲና መንግሥት አሁንም እንደሚያመነቱ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የብዙዎች ጥያቄ ይህ ችግር የነበረው በደርግ ዘመን ብቻ ነበር ወይ? መጠኑ ቢለያይም ተመሳሳይ የመብት ጥሰት ለ27 ዓመታት ሥልጣን ላይ በቆየው መንግሥትስ አልተፈጸመም ወይ? የሚል ነው፡፡

ጥቂት አስተያየት ሰጭዎች መንግሥት በዚህ ወቅት ይኼን የወሰነው አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ የመጣውን የሕዝብ ተቃውሞና አመጽ ፀጥ ለማድረግ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ይህ ተጠራጣሪነት የመጣው ቀደም ሲል መንግሥት በተደጋጋሚ የእውነት የለውጥ ጎዳና ጀምሯል ሲባል፣ ሒደቶቹን ለራሱ ጠባብ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት ሲጠቀምባቸው በመስተዋሉ ነው፡፡

ያለፈው የኢሕአዴግ ባህሪ የወደፊቱን እርግጠኛ ሆነው እንዳይጠብቁ እንዳደረጋቸው የገለጹም አሉ፡፡ መንግሥት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን አንቦርቅቆ በመተርጎም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መሪዎችና ጋዜጠኞች እንቅስቃሴ እንዲገታ በማድረግ የፖለቲካ ምኅዳሩን እንዳጠበበም ይተቻል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን ያህል መጠነ ሰፊ ተቃውሞ ያስነሳ ሌላ ሕግ ማስታወስ ይከብዳል፡፡ እንደ ሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች ገለጻ ከሆነ፣ ሕጉ ከሕገ መንግሥቱና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ጋር ይጋጫል:: በፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ተከሰው ነፃ የሆኑ ዜጎች ቁጥር እዚህ አይባልም:: የተፈረደባቸው ሰዎች ደግሞ የሚዲያ ሰዎች፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መሆን ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎት ቆይቷል::

ሕጉ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ከአገሮችና ከአኅጉራዊ ድርጅቶች፣ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከምሁራንና ከሚዲያ ተቋማት ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበታል:: ብዙዎቹ በሕጉ የተከሰሱትና የተፈረደባቸውን በመጥቀስ ‹‹መንግሥትን በማውገዛቸው ብቻ የተከሰሱ ሰዎች›› እንደሆኑ የሚጠቁሙ ሲሆን፣ በፍርድ ቤት የቀረበውንም ማስረጃ ‹‹ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ በላይ ማረጋገጫ ያላቀረበ፤›› ሲሉ ሲያጣጥሉት ነበር::

ሕጉ የአገር ደኅንነት ጉዳይን ከዜጎች ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጋር ለማመጣጠን አለመቻሉም እንደ ትልቅ ድክመት ይቆጠራል:: ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሁንም ሕጉ ተቀናቃኝ አማራጭ የፖለቲካ ኃይሎችን ለማዳከም ጥቅም ላይ ውሏል ሲል ይሞግታል::

መንግሥት በበኩሉ በአመለካከቱ የተነሳ የታሰረና የተፈረደበት አንድም ሰው እንደሌለ በመጥቀስ ይከራከራል፡፡ መንግሥት ኢትዮጵያ ለሽብር ሥጋት ከምዕራባውያንና ከሌሎች አገሮች በከፋ ሁኔታ ተጋላጭ መሆኗን ይገልጻል:: ይሁንና ሕጉ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር እያደረገበት ነው፡፡

ውሳኔው በራሱ ጥሩ ጎን ቢኖረውም ኢሕአዴግ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ባሻው ወቅት የሚያከብር፣ ካልመሰለው ግን የሚከለክል ኃይል መሆኑንም የሚያሳይ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ጠቁመዋል። ፈቅዶም ሆነ ተገዶ እንደ በዓል ስጦታ የሰጠው ውሳኔ መጀመርያም አግባብነት በሌለው ውሳኔ ለእስር የተዳረጉ ዜጎችን አስመልክቶ መሆኑን በመጥቀስ፣ እንደ ትልቅ ለውጥ መታየቱን የኮነኑም አሉ። በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ኦሮሚያ ክልልና በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው አማራ ክልል ኢሕአዴግ እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ ግፊት ማድረጋቸውን አንዳንድ ሪፖርቶች ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ውሳኔውን የሕዝብ ትግል ግፊት ያመጣው ውጤት ነው ብለውታል፡፡ 

በቀጣይ ጊዜያት መንግሥት ለሕዝቡ ጥያቄዎች ትክክለኛ መፍትሔ እንዲሰጥ እንደሚጠበቅ፣ ይኼን ለማድረግ ተጨማሪ ዕርምጃዎችን መውሰድ የግድ መሆኑን፣ ይህንን በጎ ጅምር በመጠቀም ሌሎቹን ዕርምጃዎች መውሰድ ይቻላል የሚሉ አሉ፡፡ ተቀዳሚው ዕርምጃ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ጣልቃ ከመግባት ራሱን ማቀብና ለተግባራዊነታቸው አስቻይ ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሆን እንዳለበት በርካታ አስተያየት ሰጭዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ዜጎችን ከመኖሪያቸው ያፈናቀሉ፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ያስከተሉ፣ እንዲሁም ሕይወት እንዲጠፋ ያደረጉ፣ እንዲሁም ሙስና ውስጥ በስፋት ገብተዋል ተብለው የሚታመኑ ባለሥልጣናት ተጠያቂ ስለመደረጋቸው ወይም ለፍርድ ስለመቅረባቸው፣ በሕግ ከመግዛት ተወጥቶ የሕግ የበላይነት ስለመስፈኑ፣ ሲናገር ለመስማት እንደጓጉ ጠቁመዋል፡፡

በመግለጫው ከ‹‹ማዕከላዊ›› መዘጋት ባሻገር የፍትሕ ሥርዓቱ ከምርመራ ሒደት ጀምሮ ያሉበት ችግሮች ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚታይ ቃል መግባቱ፣ ሙስናን በሚመለከት ትልልቆቹ አሳዎች ላይ ጭምር አመራሩ ትግል እንደሚያደርግ መነገሩ፣ ግጭቶችን ጨምሮ የተፈጠረው ችግር የፌዴራል ሥርዓቱ የፈጠረው ሳይሆን ሥርዓቱ በአግባቡ ሥራ ላይ ባለማዋሉ የተፈጠረ ነው መባሉ፣ የዴሞክራሲው አለመስፋትና ሕዝቡ ሐሳቡን በነፃነት ለመግለጽ አለመቻሉ ወደ ግጭት እንዲያመራ ምክንያት ሆኗል መባሉ፣ የገዥ መደቦች የበላይነት እንጂ እንደ ሕዝብ የሕዝብ የበላይነት ያለበት ሥርዓት የለም መባሉ፣ የማናችንም ሥልጣንና ክብር ከአገር በታች ነው መባሉ ለዚህ የለውጥ ድባብ በተስፋ እንዲሞሉ እንዳደረጋቸው አንድ አስተያየት ሰጪ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ገልጸዋል፡፡