Skip to main content
x

በዩኒቨርሲቲዎቻችን ፀጥታን ለማስፈን ሳይሆን ሰላምን ለማረጋገጥ  እንትጋ!

በከበደ ካሳ

ሰላምና ፀጥታ ደጋግመን የምንሰማቸውና የምንጠቀምባቸው ቃላት ናቸው። በመካከላቸው ልዩነት የሌለ እስከሚመስለን ድረስ አጣምረን እንጠቀምባቸዋለን። በዚህ ጽሑፌ በሁለቱ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት ለመጠቆም እሞክራለሁ። ይህን የማደርገው ግን ከወቅታዊ አገራዊ ሁኔታችን በመነሳት በዩኒቨርሲቲዎቻችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመዳሰስና መፍትሔ በሚያሻቸው ጉዳዮች ላይ የግል አስተያየቴን ለማስፈር እንጂ፣ በቃላቱ አጠቃቀም ላይ አቃቂር ለማውጣት ወይም ደግሞ የትርጉም ንድፈ ሐሳብ ለማቅረብ አይደለም።

በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ፀጥታ ሰፍኗል ሲባል ግጭት፣ ረብሻ ግርግር አለመኖርን የሚያመለክት ነው ሰላም ደግሞ ጭንቀት የፍርኃት፣ የንዴትና የሌሎች አሉታዊ ስሜቶች ሁሉ አለመኖርን ያመለክታል። በፍቅር የሚኖር ቤተሰብ በልጆች ጫጫታና በባልና ሚስት ምክክር ፀጥታው ደፍርሶ ዕረፍት ያጣ ምሽት ሊያሳልፍ ይችላል። ነገር ግን ፍፁም ሰላማዊ ቤተሰብ ነው። በአንፃሩ በጭቅጭቅ የሚኖር ቤተሰብ ልጆችና ወላጆች ከተኙ በኋላ ፍፁም የሆነ ፀጥታ ሊነግሥበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰላማዊ ቤተሰብ ሊባል አይችልም። ሁለት ሰዎች የቃላት ጦርነት ሊገጥሙ ይችላሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆነው ግንርስ በርስ የሚደማመጡበት በውስጣቸውም ፍፁም ሰላም ሊኖር ይችላል። በተጋጋለ ጦርነት ውስጥ ጥይት በጆሮዎቹ ላይ የሚያፏጭበት ወታደር ለውጊያ ከተነሳበት የተቀደሰ ዓላማ አንፃር በውስጡ ፍፁም የሆነ ሰላም ይሰማዋል።

በአጭሩ ሰላም በግጭት፣ በጭንቀትና በግርግር መካከል ሆኖም እንኳን ሊሰማ የሚችል የኅሊና ዕረፍት ነው። ፀጥታ በሌለበትም ሰላም ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ሰላም ከአዕምሯችንና ከኅሊናችን ጋር የተያያዘ ነው። ፀጥታ ደግሞ ውጫዊ ነገር ነው። ውስጣችን ውጪውን የመቀየር ትልቅ አቅም አለው፡፡ ውጪው ግን ውስጣችንን የመቀየር አቅሙ ዝግ ነው ባይባልም ልንቋቋመው እንችላለን። ይህ ግን ተፈጥሯዊ ሳይሆን ሰው ሠራሽ ሥራ ይጠይቃል። ለዚያም ነው በዩኒቨርሲቲዎቻችን ፀጥታን ሳይሆን ሰላምን ለማስፈን እንሥራ ብዬ የተነሳሁት።

የዚህ ዓመት የትምህርት ዘመን ከተጀመረ ወዲህ በተለይም ከኅዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተደጋጋሚ ግጭቶች ተከስተዋል። በአዲስ አበባ፣ በታዳጊ ክልሎችና በደቡብ ክልል ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውጪ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ብጥብጥ ተነስቷል ማለት ይቻላል። ላጋጠሙት ግጭቶች መንስዔአቸው በአብዛኛው ተመሳሳይ ሲሆን እንደየዩኒቨርሲቲዎቹ ባህሪ የሚለያይበት ሁኔታም አጋጥሟል። የጋራ የሆኑት ችግሮቻቸው ውጫዊው ወቅታዊ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ያስከተላቸው ሲሆኑ፣ እንደየዩኒቨርሲቲዎቹ ባህሪ የሚለያዩት ደግሞ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ ያሉ ከትምህርት አሰጣጥ፣ ከተማሪዎች አገልግሎት፣ ከአስተዳደር ሥራዎችና ተያያዥ ውስጣዊ ችግሮች ናቸው። ከእነዚህ የችግሮቹ መንስዔዎች በመነሳት መፍትሔያቸውም በአብዛኛው ተመሳሳይ ሆኖ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ከየዩኒቨርሲቲዎቹ ባህሪ ጋር ተጣጥሞ መሄድ እንዳለበት ለመረዳት አይከብድም።

አሁን ላይ ሆነን ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በተረጋጋ ሁኔታ ላይ የሚገኙና የማስተማር ሒደታቸውን የጀመሩ መሆናቸውን ማየት ይቻላል። ይህ ማለት ግን ለግጭት መንስዔ የነበሩ ጉዳዮች ሁሉ እልባት አግኝተዋል ማለት አይደለም። ተቋማቱ መደበኛ ሥራቸውን ለማከናወን ከሚችሉበት የፀጥታ ደረጃ ላይ ቢገኙም፣ ይህ ወደኋላ እንዳይቀለበስ ከሚያስችል አስተማማኝ ሰላም ላይ አልደረሱም። በዚህ ጽሑፌ ችግሮቹን ዘርዘር አድርጌ በማየት ጎን ለጎን ደግሞ ጊዜያዊ ፀጥታን ሳይሆን ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የግል አስተያየቴን ለማስፈር እሞክራለሁ። በቅድሚያ የዩኒቨርሲቲዎችን ውስጣዊ ችግሮች ቀጥሎ ደግሞ ውጫዊዎችን ነው የማየው።

ውስጣዊ ችግሮች

በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የመምህራን፣ ወዘተ . . . የተለያዩ አደረጃጀቶች አሉ። አሁን ባጋጠሙ ግጭቶች ወቅት ሚናቸው በአዎንታም ሆነ በአሉታዊ ጎልቶ የወጣው የተማሪዎች ኅብረትና የሰላም ፎረም በመባል የሚታወቁት ሁለት አደረጃጀቶች ናቸው። ሁለቱም የተዋቀሩት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት እንዲሰፍንና ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት ሁሉ እንዲያገኙ ዩኒቨርሲቲው በሚያካሂደው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመደገፍ ነው። ይህን ተልዕኮ ከመወጣት አንፃር ተጠቃሽ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ አሁንም በመፈጸም ላይ ናቸው።

ይህ እንዳለ ሆኖ አደረጃጀቶቹ በራሳቸው የቅሬታ ብሎም በተማሪዎች መካከል ያለመስማማት ምንጭ የሚሆኑበት አጋጣሚ ይስተዋላል። በእነዚህ መዋቅሮች ውስጥ አመራር ለመሆን በጥቂት ተማሪዎች መካከል ተገቢ ባልሆነ ፉክክር መጠመድ ይታያል። ለዚህም አንዱ ምክንያት ቦታዎቹን ለተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሳይሆኑ፣ ራሴን በተለያየ መልክ ለመጥቀም ያስችሉኛል ብሎ ከማሰብ የሚመነጭ ነው። ሁለተኛው ምክንያት በአደረጃጀቶቹ ሥልጣንን መያዝ የግል ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ አመለካከትን በሌሎች ተማሪዎችም ላይ ለመጫን አቋራጭ መሣሪያ ተደርጎ መወሰዱ ነው። ይህም በመሆኑ የዩኒቨርሲቲዎችን ሰላም ለማወክ አቅደው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በእነዚህ አደረጃጀቶች አመራር አካል ውስጥ የእነሱን ተልዕኮ ሊያስፈጽሙላቸው የሚችሉ ተማሪዎችን ማስረግን እንደ ሥልት ይከተሉታል። በካውንስል አመራርነት እንመረጣለን በሚል አስቀድመው እርግጠኛ የሆኑ ተማሪዎች በምርጫ ሲሸነፉ በሌላኛው ፅንፍ የግጭትና የረብሻ አቀጣጣይ የሚሆኑበት ሁኔታም አለ። በቅርቡ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ያጋጠመውም ይኼው ነው።

የሰላም ፎረምም ሆነ ሌሎች አደረጃጀቶች የአመራር ምደባ ልክ እንደ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ስብጥር ሁሉ ኅብረ ብሔራዊነት የሚንፀባረቅበት መሆን ይገባዋል። አሁን እያጋጠመ ያለው ግን ዩኒቨርሲቲው ያለበት ክልል ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች በብዛት የሚሳተፉበት መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ የተወሰነ ፍላጎት ብቻ በሌሎቹ ተማሪዎች ላይ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ እንዲጫን ዕድል ይሰጣል። ይህ ችግር አብዛኞቹ ተማሪዎች ከዚያው ክልል የተገኙ ከመሆናቸው ጋር ይያያዛል። እንደሚታወቀው ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን ሲመድብ 40/60 ቀመርን ይከተላል። ይህ ማለት ከአንድ ክልል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ካመጡ ተማሪዎች ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ በዚያው ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ሲመደቡ፣ ቀሪዎቹ 60 በመቶ ያህሉ ከክልሉ ውጪ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ ይደረጋል ማለት ነው። በመሆኑም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የአንድ ክልል ብሎም የአንድ ብሔር ተማሪዎች የሚበዙበት ሁኔታ ያጋጥማል። ይህ ሁኔታ በቀጥታ በተጠቀሱት መዋቅሮች ውስጥ ሲያጋጥም ደግሞ፣ አሁን እየታየ እንዳለው የተወሰኑ ተማሪዎች መዋቅሮቹን ተጠቅመው የራሳቸውን አመለካከት ሌሎች ላይ እንዲጭኑ ወይም ፍላጎታቸውን በግድ ለማስፈጸም እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ይሰጣቸዋል።

በሌላ በኩል በሰላም ፎረምና በተማሪዎች ኅብረት መካከል ያለው ግንኙነት ከመተጋጋዝ ይልቅ መገፋፋት፣ ከመተባበር ይልቅ መጠቃቃት የሚታይበት ሁኔታም ይፈጠራል። አንዱ በአንዱ ሥራ ጣልቃ የመግባት፣ እንዲሁም የጥቅም ግጭቶች ይስተዋሉባቸዋል። ለአብነት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ይህ የቆየ ችግር ነው። ስለሆነም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ፀጥታን ከማረጋገጥ ባለፈ ዘለቂ ሰላምን ለማምጣት፣ ከእነዚህና መሰል አደረጃጀቶች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ከምንጫቸው ማድረቅ ያስፈልጋል።

የዩኒቨርሲቲዎችን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችና አመራሮች የሞራልና የሙያ ግዴታ አለባቸው። አሁን ባለው ሁኔታ የሚበዙትን የዩኒቨርሲቲ መምህራንን የሚወክል ባይሆንም፣ ሚናቸው ክፍል የገባን ተማሪ በማስተማር ላይ ብቻ የተወሰነ አድርገው የሚቆጥሩ መምህራን አሉ። በመሠረቱ መምህራን የሚኖሩት ተማሪ ሲኖር ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን መምህራን እንደ ማንኛውምዝብ ሠርተው መኖር የሚችሉት ሰላም ሲሰፍን ብቻ ነው። ይህን የማነሳው ያለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ለማስታወስ እንጂ አያውቁትም በማለት አይደለም። ግን ደግሞ ከዚህ በተፃራሪ የተለየ የጥፋት ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ጥቂት መምህራን መኖራቸውም ሀቅ ነው። ከሰሞኑ የተከሰተውን ረብሻ የተለያዩ አካላት ተረባርበው ካረጋጉት በኋላ ወደ ትምህርት ገበታቸው ለተመለሱ ተማሪዎች ትምህርት ለማስጀመር ሲፈለጉ ያልተገኙ መምህራን ነበሩ። ከዚህ በባሰ ደግሞ አንዳንድ መምህራን ግጭቶችን የሚያባብሱ መረጃዎችን የሚያሠራጩና በእሳት ላይ ቤንዚን በመርጨት የተጠመዱ አሉ። በአዎንታዊ ጫፉ ከታየ የግቢው ሰላም እንዳይደፈርስ የመከላከል፣ ችግር ሲያጋጥምም ተቀናጅቶ የማረጋጋት ሚና ያላቸው መምህራን በእንዲህ ዓይነት አሉታዊ ተግባር ላይ ተሰማርተው ሲገኙ፣ ለዘላቂ ሰላም ሲባል ተቋማቱ በውስጥ አሠራራቸው ሥርዓት ማስያዝ አለባቸው።

በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከማስተማር ውጪ የሆኑ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የአስተዳደር አካላትና ሌሎች ቋሚና ጊዜያዊ ፈጻሚዎችም እንዳሉ ይታወቃል። በተማሪዎች ምግብ ቤት፣ በሕክምና አገልግሎት፣ በጥበቃና ፅዳት፣ በዶርሚተሪ ክትትል፣ ወዘተየተሰማሩ ሠራተኞችና አመራሮች የመማር ማስተማሩን ሥራ በማሳለጥ ረገድ ያላቸውን አዎንታዊ ድርሻ ያህል የዩኒቨርሲቲዎች ሰላም እንዲናጋ በማድረግ ረገድም አሉታዊ ሚና ሊኖራቸው ይችላል። ተማሪዎች ከእነሱ መልካም አገልግሎቶች በሚያገኙበት ወቅት ዕርካታ እንደሚሰማቸው ሁሉ፣ መጉላላትና ኢፍትሐዊነት ሲያጋጥማቸው ደግሞ ከጊዜያዊ ስሜት በሚመነጩ አሉታዊ ተግባሮች ላይ ሊሰማሩ ይችላሉ። የመልካም አስተዳደር ችግር አገራዊ ችግራችን ቢሆንም በተለይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሲያጋጥም ከወጣቶች ስሜታዊ መሆን ጋር ተዳምሮ ጥፋትን ያስከትላል። በቅርቡ በዩኒቨርሲቲዎች ያጋጠመውን ግጭት ለማረጋጋት ከተማሪዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለርካሽ ተወዳጅነት የሚያውሉ፣ የእኛ የሚሉትን አቅርበው ሌላውን የሚያርቁ ሠራተኞች መኖራቸውን ተማሪዎች አውስተዋል። የሆነ ብሔር ቋንቋን ካልተናገርን ወጥ እንኳን በትክክል አይጨለፍልንም የሚሉ ቅሬታዎች ሳይቀር ተንፀባርቀዋል። በእንደዚህ ዓይነት አስተዳደራዊ ክፍተቶች ላይ አፋጣኝ የእርምት ዕርምጃ መውሰድ ሲቻል ነው ተማሪዎች በእኔነት መንፈስ ከዩኒቨርሲቲው ጎን ቆመው ሌሎች ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ የሚሠሩት።

የአካዳሚክና የአስተዳደር ሥራዎችን አቀናጅቶ የሚመራው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራርም በሌላ አካል ሊተካ የማይችል ኃላፊነት አለበት። በእርግጥ በዩኒቨርሲቲዎች ሰላም ሲሰፍን ከማንም በላይ ይህ አካል ተጠቃሚ ነው። ሰላም ሲኖር ትምህርትን በጥራት ለማቅረብ፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን አቅዶ ለመፈጸም፣ እንዲሁም ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ በቂ ጊዜ ይኖረዋል። አሁን ግን ጊዜውን እያዋለው ያለው አደጋን ለመከላከል ነው። ሁሉንም የተቋሙን መዋቅሮች አቀናጅቶ ቀን ከሌሊት ፀጥታን ለማስከበር ይሠራል። በዚህ ይበልጥ እየለፋበት ባለ ተግባሩ ለመውቀስ የሚያስደፍር ሁኔታ ባይኖርም፣ ለችግሮች መፍትሔ ሰጥቶ መቋጨት ካልተቻለ ግን ከላይ በጠቀስኳቸው ዓቢይ ተልዕኮዎቹ መውደቁ የማይቀር ነው። እዚህም ላይ ግን በአመራር ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ሳይንቁ ማንሳት ለወደፊት ሥራ  ተገቢ ይሆናል።

በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች እንደታየው እርስ በርሱ ተደጋግፎና ተናቦ የማይሠራ የዩኒቨርስቲ አመራር አለ። በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በመርህ ላይ ቆመው ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የሚሞክሩ ፕሬዚዳንቶችን ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ ተሞክሯል። የዩኒቨርሲቲዎች የቦርድ አመራርም ሦስት ገጽታ ያለው ነው። አንዳንዱ ወጣ ገባ እያለ የሚደግፍና ሥራውንም በስልክ የሚመራ ሲሆን ምንም የማይደግፍም አለ። ሌላው ደግሞ የመደበኛ ሥራው አካል አድርጎ በቂ ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ ነው።

በዚህ ግርግር ወቅትና ቀደም ባሉት ወቅቶችም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተናጠል ያጋጥሙ በነበሩ ረብሻዎች ላይ ግጭቶችንና ሥርዓት አልበኝነትን ይመሩ የነበሩት ከዩኒቨርሲቲዎች በውጤት ማነስ ወይም በሥነ ምግባር ችግር የተባረሩ፣ ወይም ለተወሰነ ጊዜ የተቀጡ ነገር ግን በዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተደብቀው የሚኖሩ ተማሪዎች ናቸው። እነዚህ ተማሪዎች በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው ወይም በሌላ ጥፋት ከዩኒቨርሲቲ መባረራቸውን ለቤተሰባቸው ከመንገር ይልቅ፣ በዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሰጡ ከትምህርት ውጪ ያሉ አገልግሎቶችን እየተጠቀሙ መኖርን ምርጫቸው ሲያደርጉ ይታያል። ጎን ለጎንም ከቤተሰብ እየተማሩ እንደሆነ በማስመሰል ገንዘብ እንዲላክላቸው ያደርጋሉ። ረብሻ ሲኖር ደግሞ ቤተሰብ ይበልጥ ጫና ውስጥ ስለሚወድቅ ተጨማሪ ገንዘብ የማግኛ ምንጭ ያደርጉታል። እንደዚህ ዓይነት ተማሪዎች የራሳቸውን ውድ ጊዜ በከንቱ ማሳለፋቸው ሳይበቃ፣ በግቢው ውስጥ ባላቸው ቆይታ መደበኛ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ መሰናክል መሆናቸው አይቀርም። ከግጭት እንደሚያተርፉ በማሰብና ይህ ባይሆን እንኳን የሚጎዱት ነገር እንደማይኖር የተሳሳተ ግንዛቤ በመያዝ የግቢውን ሰላም በሚያውኩ ተግባራት ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ይሆናሉ። ለነገሩ የእነሱን አነሳሁ እንጂ ጭራሹኑ ተማሪ ያልሆኑ ግለሰቦች ከተማሪዎች ጋር እየበሉ የሚኖሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎችም አሉ።

የዚህ ችግር መነሻ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎቻቸውን ማንነት በአግባቡ ለይተው ካለመያዛቸው፣ የውጤት መግለጫዎችን ተከትለው ወቅታዊ ማስተካከያ ካለማድረጋቸው፣ በአስተዳደርና በአካዳሚክ ዘርፉ መካከል ተናቦ መሥራት ካለመቻሉ ጋር የተያያዙ ናቸው። በሕንፃዎች ላይ ለድጋፍናክትትል የሚመደቡ ፕሮክተሮችም ኃላፊነታቸውን በብቃት ያለመወጣታቸው ሌላው ምክንያት ነው። ዩኒቨርሲቲዎች ይህን ችግር በማስወገድ ሕጋዊ ተማሪዎች ብቻ በግቢው ውስጥ እንዲቆዩ ማድረግ ከቻሉ ነው፣ የተረጋጋና ስኬታማ የመማር ማስተማር ሒደትን ጠብቀው መዝለቅ የሚችሉት።

በውጤታቸው የተነሳ የተባረሩ ተማሪዎች በወቅቱ ከዩኒቨርሲቲው መውጣት አለባቸው፡፡ አጥፊዎችም ተለይተው መቀጣት አለባቸው። በእርግጥ ያጠፋን መቅጣትም ፈተና እየሆነ ነው። በወለጋ ዩኒቨርሲቲ መብራትና ውኃ መጥፋቱን ምክንያት በማድረግ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቁመው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ የቀሰቀሱ ሰባት ተማሪዎች፣ በዩኒቨርሲቲው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር። አሁን በቅርቡ ባጋጠመው ረብሻ በግንባር ቀደም አስተባባሪነት ከተለዩት ስድስት ተማሪዎች ውስጥ ሦስቱ ቀድሞውንም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው የነበሩት ናቸው። በተመሳሳይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሕገወጥ ሠልፎችን በማስተባበር ትምህርት እንዲቋረጥ ያደረጉ ተማሪዎችን በመለየት የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ባለፈው ዓመት ለአንድ ዓመት ከትምህርት እንዲታገዱ በወሰነበት ወቅት፣ አጥፊዎቹ ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ ሲጠይቁ ከሌሎች ተማሪዎች ደግሞ ለምን ይቀጣሉ የሚል ተቃውሞ ይሰማ ነበር። ያም ሆኖ በቅድሚያ ምክርና ተግሳፅ ላይ በማተኮር፣ ካልታረመም የቅጣት ውሳኔዎችን በማስተላለፍ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም የሕግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት። በተማሪዎች ላይ የሚተላለፉ መሠረታዊ ውሳኔዎችንም ወላጆቻቸው በቀጥታ የሚያውቁበት አሠራር መዘርጋት አለበት። ይህ ጉዳይ አስፈላጊ የሚሆነው ቅጣቱን ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲያግዝ ብቻ ሳይሆን፣ የተማሪዎችን የወደፊት ሕይወት አቅጣጫ በማስያዝ ረገድ ዋነኛ ባለድርሻ የሆኑት ወላጆች ልጆቻቸው ያላግባብ ጊዜያቸውን እንዳያባክኑ መከላከል ስላለባቸውም ጭምር ነው።

የዩኒቨርሲቲዎች መውጫ ፈተና (Exit Exam) ሌላው ከሰሞኑ ረብሻ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጉዳይ ነው። የመውጫ ፈተና ምንም እንኳን በአገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ሚኒስቴር የተዘረጋ መርሐ ግብር ቢሆንም፣ የሚፈጸመው ግን በእያንዳንዱ ተናጠል ዩኒቨርሲቲ ስለሆነ ነው በዩኒቨርሲቲዎቹ የውስጥ ጉዳይ ሥር ያካተትኩት። በዚህ ላይ የሚነሳው ተቃውሞም ቢሆን ከዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲ ልዩነት አለው። ይኼ በዋናነት ዩኒቨርሲቲዎቹ በመርሐ ግብሩ ምንነትና አፈጻጸም ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ካደረጉት ውይይትና ከፈጠሩት የግንዛቤ ደረጃ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ስለመውጫ ፈተና ምንም አናውቅም ከሚሉ ጀምሮ ውይይት አድርገንበታል፣ ግን አልተግባባንበትም የሚሉና በሌላ በኩል ትክክለኛና አምነን ለመፈጸም የተዘጋጀነው  የሚሉ አስተያየቶች በመምህራንም በተማሪዎችም ይደመጣሉ።

የመውጫ ፈተና አስፈላጊ አይደለም በማለት ሳይንሳዊና ምክንያታዊ ሆኖ የሚቀርብ አንዳችም ክርክር የለም። ሆኖም የትምህርት ጥራት ባልተረጋገጠበትና የመምህራን ብቃት ባልተገነባበት ሁኔታ ተማሪዎችን መፈተን አይገባም የሚሉ ትችቶች ይነሳሉ። እዚህ ላይ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ግን የመውጫ ፈተና በራሱ የመምህራን ብቃት የሚገነባበት ብሎም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚሠራበት መርሐ ግብር መሆኑ ነው። የትምህርት ጥራትን ከሚጎዱ ጉዳዮች አንዱ ተማሪዎች ሁሉንም ኮርሶች በተመደበላቸው የጊዜ መጠን ልክ ከመምህራኖቻቸው ጋር ተገናኝተው ሳይማሩ ለፈተና መቅረባቸው ነው።ግሬድ› እየሸለሙ ብቻ የረባ ትምህርት ሳይሰጡ የትምህርት ጊዜን የሚያባክኑ አንዳንድ መምህራን መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ተማሪዎችምግሬድ› እስከተሰጣቸው ድረስ የአስተማሪ ክፍል መግባት ያለመግባት አያስጨንቃቸውም ነበር። የመውጫ ፈተና ላይ በቂ ውይይት በተደረገባቸው ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ለውጥ መታየት ጀምሯል። ተማሪዎች አስተማሪ ሳይገባላቸው ሲቀር አመራሩን መጠየቅ ጀምረዋል። ይህ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ያልዘሩትን ማጨድ እንደማይቻል ሁሉ ባልተጨበጠ እውቀትም መውጫ ፈተናን ማለፍ እንደማይቻል ግንዛቤ ስለተያዘ ነው። በሌላ በኩል ይህ መርሐ ግብር ካሉት ሰባት ስትራቴጂዎች ውስጥ ሦስቱ የሚፈጸሙትመምህራን ላይ መሆኑም የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ሚናው ትልቅ ነው።

እዚህ ላይ ዩኒቨርሲቲዎችም ሆኖ የሚያስተዳድራቸው ትምህርት ሚኒስቴር መረዳት ያለባቸው ጉዳይ፣ መልካም ነገርም ቢሆን በአግባቡ ካልተጨበጠ ፀጥታን ማናጋት ለፈለጉ ኃይሎች መሣሪያ ሊውል የሚችል መሆኑን ነው። ስለሆነም ይኼን ከተማሪዎች ይቅርና ገና ከመምህራንም ጋር በበቂ ሁኔታ ያልተግባቡበትን መርሐ ግብር በተደጋጋሚ ውይይቶች ማስረፅና ሁሉም አካላት በጫና ሳይሆን ጥቅሙን ተገንዝበው እንዲቀበሉት ለማድረግ መሥራት አለባቸው።

አሁን አሁን መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን በገነባ ቁጥር በዋና በራቸው አቅራቢያ የተለያዩ የንግድና የአገልግሎት ተቋማትን መክፈት አዋጪ ቢዝነስ ሆኗል። እነዚህ በዩኒቨርሲቲዎች አቅራቢያ የሚከፈቱ የመጠጥ፣ጫትናሺሻ ቤቶች በተማሪዎች ጤና፣ ሥነ ምግባርና የትምህርት አቀባበል ላይ ከሚያደርሱት የከፋ ጉዳት ባልተናነሰ የዩኒቨርሲቲዎችን ሰላምና ፀጥታ በማደፍረስም በኩል ዓይነተኛ ሚና አላቸው። በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ብጥብጥ ለመፍጠር ሲታሰብ ዕቅድ የሚወጣውና ከውጭ ኃይል ሥምሪት የሚሰጠው በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ነው። በጥቅሉ እነዚህ ሕገወጥ ቤቶች የአጥፊዎች ምሽግ ሆነው እያገለገሉ ናቸው።

ተጋላጭነታቸው የአልኮል መጠጥ በሚያስከትለው አሉታዊ ጫና ብቻ የሚገለጽ የውጭ አገሮች ዩኒቨርሲቲዎች እንኳን፣ መጠጥ ቤቶችን ከዩኒቨርሲቲዎች አቅራቢያ ለማራቅ የተለያዩ ሕጎችን አውጥተዋል። ለአብነት በህንድ የተለያዩ ከተሞች 100 ሜትር ጀምሮ መጠጥ ቤቶችን ከትምህርት ተቋማት ቅጥር ግቢ የሚያርቁ ሕጎች አውጥተዋል። ታይላንድም እንዲሁ ከዩኒቨርሲቲዎች እስከ 300 ሜትር ርቀት አልኮል መጠጥ እንዳይሸጥ ገድባለች። በእነዚህ አገሮችና ከተሞች መጠጥ ቤቶች የከተሞቹ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ሆነውም ሳለ ነው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት። ይህን ዓይነት ጫና የሌለብን፣ ይልቁንም በመጠጥናጫት ቤቶቹ የከፋ ችግሮች የተጋረጠብን እኛ ደግሞ ሕጎቹን ወደ አገራችን ሁኔታ አጣጥመን መጠቀም ግድ ይለናል። በመሆኑም የዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉባቸው ከተሞች አስተዳደሮች በጋራ ሆነው ዘላቂ እልባት ሊሰጡት የሚገባ ችግር ነው። መንግሥትም እንዲህ ዓይነት ችግሮች እዚህም እዚያም እንዳይፈጠሩ የሚያደርግ ጥብቅና ወጥ አሠራር በመዘርጋት ከዩኒቨርሲቲዎቹ ጎን መቆሙን ማረጋገጥ አለበት።

አጥር የሌላቸው አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የሆነ ኮሽታ ሲፈጠር ተማሪዎች ወደ አካባቢው ነዋሪ፣ የአካባቢው ነዋሪም ወደ ተማሪዎቹ በቀጥታ የሚገቡበት በዚህ አጋጣሚም ድብቅ ፍላጎታቸውን ማስፈጸም የሚፈልጉ ኃይሎች የተጠቀሙበት ሁኔታ እንዳለ ተስተውሏል። አጥር የሌለው የድሬዳዋው ዩኒቨርሲቲ ከሁለት የአካባቢው ቀበሌዎች ጋር ይጎራበታል። ተማሪዎቹ ግርግር ሲጀመር ግቢው ውስጥ ባለው የፀጥታ ኃይል ከመተማመን ይልቅ፣ በቀጥታ ወደ ቀበሌው ነዋሪዎች መበተንን ሲመርጡ ተስተውለዋል። ይህን ስል አጥር ማበጀት ለፀጥታ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጉዳዮች ያለውን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት እንጂ አጥሩ የጥፋት ኃይሎችን ይቋቋማል ብዬ አይደለም። የዩኒቨርሲቲዎች አጥር ዩኒቨርሲቲዎቹ በውስጣቸው ሰላምን ለማስፈንና ፀጥታን ለማረጋገጥ የሚሠሩት ነው። ለምሳሌ ያህል በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የጊምቢ ካምፓስ አጥር የለውም። ሌሎቹን የዩኒቨርሲቲውን ካምፓሶች (ወለጋና ሻምቡ) ጨምሮ በብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ብጥብጥ ሲነሳና ትምህርት ሲቋረጥ በዚህ ካምፓስ ግን ትምህርት አልተቋረጠም። ተማሪዎቹ በግቢው ያለው አመራር ከወላጆች የተረከባቸውን ተማሪዎች በአግባቡ እንደሚይዝ ያምናሉ። የተማሪዎች መማክርትም ከመምህራንና ከአስተዳደሩ ጋር ተቀናጅቶ ለተማሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይሠራል፡፡ ዋናውም አጥር ይኼው ነው።

እንደሚታወቀው ብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ገና የግንባታ ሥራቸውን ያላጠናቀቁ ናቸው። በዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉ ግንባታዎች ታዲያ ግጭቶችን ለማባባስ የሚጠቅሙ ቁሶችን በተዘዋዋሪ አቅራቢ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ዩኒቨርሲቲዎቹን በማረጋጋት ሒደት የዶርሚታሪ አሰሳ ሲካሄድ የተገኙ ብረታ ብረትና ስለታም ቁሶች ከግንባታ ሳይቶቹ በቀጥታ ወደ ዶርም የተወሰዱ ናቸው። እነዚህ ቁሳቁሶች ራስን ለመከላከልም፣ ሌላውን ለማጥቃትም የተዘጋጁ ናቸው። በተጨባጭም የተማሪዎች ክቡር ሕይወት በእነዚህ መሣሪያዎች እየተቀጠፈ ነው። ፌሮ ብረት ተንተርሶ የሚያድር ተማሪ ውስጡ ሰላም ሊኖረው አይችልም፡፡ የራሱን ብቻ ሳይሆን ከጎኑ የተኛውንም ተማሪ ሰላም ይነሳል። ስለሆነም በሌሎች ቦታዎች እንደሚታየው የግንባታ ቦታዎች በአጥር የተከለሉና ከሠራተኞቻቸው ውጪ ሌሎች የማይደርሱባቸው እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። ዋና ዋናዎቹን ውስጣዊ ችግሮች ካየሁ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ችግሮቹ የተፈጠሩት ከዩኒቨርሲቲዎቹ ውጪ ቢሆንም፣ ውስጣዊውን የመማር ማስተማር ሒደት በረበሹት ውጫዊ ሁኔታዎች ላይ አተኩራለሁ።

ውጫዊ  ችግሮች

ከውጫዊ ምክንያቶች ውስጥ ዋናውና ከሞላ ጎደል በሁሉም ግጭት በነበረባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ይነሳ የነበረው ጉዳይ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት ያስከተለው የሰው ሕይወት መጥፋትና የዜጎች በስፋት መፈናቀል ነው። እንደ ድሬዳዋ፣ ሐረማያ፣ ኦዳ ቡልቱ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ዕለት ተዕለት የሚያዩበት፣ በሕክምና ካምፓሶቻቸው ደግሞ በግጭቱ የተጎዱ ዜጎች የሕክምና አገልግሎት የሰጡበት መሆኑ ልዩ ያደርጋቸዋል። እውነታው እንዳለ ሆኖ ያጋጠመውን ጉዳትና የተከተለውን ቀውስ የየብሔር ገጽታ በማላበስ ሲያራግቡ የነበሩ መገናኛ ብዙኃንና በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያው፣ የተማሪዎቹን ቁጣ በመጨመርና ስሜታዊነታቸውን በማራገብ የራሳቸው ሚና ነበራቸው።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዓቢይ ጥያቄ የነበሩት ለምን በዚያ መጠን ዜጎች ሲፈናቀሉ መንግሥት ዝም ብሎ ተመለከተ? ከተፈናቀሉስ በኋላ ለምን በካምፕ ሆነው ይሰቃያሉ? የሚሉ ናቸው። በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ የኦሮሞ ተማሪዎችም ይህን ጥያቄ አስቀድመው አንስተውታል። ይህ ጥያቄ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ የተነሳ ነው። መፈናቀልና ሞት ሲቀጥል የተማሪዎቹ ጥያቄም እየተጠናከረ ሄዶ በግጭት እንዲገለጽ ሆኗል። የኦዳ ቡልቱ ተማሪዎች የግቢው ፀጥታ ከተረጋጋ በኋላ ባደረጉት ውይይት 46 ያህል ከሌላ ክልል የመጡ ተማሪዎችን በማንነታቸው የተነሳ ብቻ አባረናቸዋል፡፡ የሚያሳፍር ነገር ነው የሠራነው፡፡ ነገር ግን ስድስት መቶ ሺሕ በላይ ኦሮሞዎች በማንነታቸው የተነሳ ብቻ ሲፈናቀሉ መንግሥትም ምንም አላደረገም ሲሉ ወቅሰዋል።

መሰል ግጭቶች በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ሲያጋጥሙን የቆዩ ቢሆኑም፣ የዚህ ዓመቱ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ግን በመጠኑ ከቀደሙትም የከፋ ነው። መንግሥት በጠንካራ ዲስፒሊን ላይ ተመሥርቶ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሲገባው፣ ተገቢ ባልሆኑ ጥቅሞች ላይ የተመሠረቱ የቡድን ትስስሮች ችግሮች እንዳይፈጠሩ የመከላከል ብቃቱን ብቻ ሳይሆን፣ ሲፈጠሩም የእርምት ዕርምጃዎችን እንዳይወስድ መሰናክል ሆነውበታል። የአሁኑን የሚለየው ሌላው ጉዳይ በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እየተጠናከሩ ከርመው፣ አሁን ከድል ጫፍ ተቃርበናል በሚል ስሌት ያለ የሌለ ኃይላቸውን በማረባረብ ወደ ሁለንተናዊ አገራዊ ቀውስ ለመክተት የተረባረቡበት መሆኑ ነው። አዲሱ ሚዲያም በዚህ ውስጥ አንድ ትልቅ ልዩነት ፈጣሪ መሆኑን አሳይቷል። እነዚህን ክስተቶች በመልካም አጋጣሚነት የወሰደው በውስጥና በውጭ ያለው ፅንፈኛ ተቃዋሚ ያገኛቸውን ዕድሎች አሟጥጦ ተጠቅሟል።

ይህ ውጫዊ ሁኔታ በግቢ ውስጥ ባሉ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና አሳድሮ ለረብሻና የእርስ በርስ ግጭት ዳርጓል። ችግሩ ውጫዊ እንደ መሆኑ መፍትሔውም ውጫዊ ነው። እዚህም ላይ እሳት የማጥፋት ያህል እየተዋከቡ ፀጥታን የማስፈን ዕርምጃዎችን ከመውሰድ ይልቅ፣ ቀልብን ሰብስቦ ዘላቂ ሰላም የሚያመጡ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ ይበጃል። ከዚህ አንፃር በቅርቡ የተጠናቀቀው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባና በቀጣይም በየብሔራዊ ድርጅቶች የሚካሄዱ ውይይቶች ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እንደሚመሩን ተስፋ አደርጋለሁ።

በዚህ ዓመት የተከሰተው ግጭት ተማሪዎቹ ከባዶ ሜዳ ተነስተው የፈጸሙት አይደለም። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ገፊ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች አሏቸው። ሆኖም ችግሮችን በሰው ሕይወትና በንብረት ማውደም ለመፍታት መሞከር ፍፁም ከሥልጣኔ የራቀ፣ በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የማይጠበቅ ተግባር ነው። ከምንም ነገር በላይ ተማሪዎች ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ከወላጆቻቸው ተነጥለው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለገቡበት ዓቢይ ተልዕኳቸው ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ በመንገዳቸው ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ደግሞ በውይይት ብቻ መፍታት ይጠበቅባቸዋል።

ነባራዊ ሁኔታው እንዲህ ዓይነት ምክንያታዊ ሆኖ የሚደግፍና የሚቃወም፣ ችግሮችን በውይይት የሚፈታ ትውልድ ከመቅረፅም አንፃር ብዙ እንደሚቀረን ያሳየ ነው። እንደሚታወቀው በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት የሥነ ምግባርና የሥነ ዜጋ ትምህርት ይሰጣል። ሆኖም የዚህ ትምህርት አሰጣጥ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የተፈለገውን ውጤት ባለማስመዝገቡ፣ ከመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ምህርት ቤቶችን አልፈው ዩኒቨርሲቲዎችን የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ስሜታዊ ሆነው ራሳቸውን፣ የትምህርት ተቋማቸውንና አገራቸውን የሚጎዳ ተግባር ሲፈጽሙ ይታያሉ። ስለሆነም ለዘላቂ ሰላማችን ሲባል የወጣቶች የሰብዕና ቀረፃ ከትምህርት ተቋማትም በተጨማሪ፣ በቋሚነትና በሰነድ ተደግፎ በተከታታይ መፈጸም ይኖርበታል።

እዚህ ላይ በልዩ ሁኔታ መታየት ያለበት ጉዳይ ግጭቶችን በማረጋጋት ረገድ የፀጥታ ኃይሎች የነበራቸው ሚና ነው። ከወቅቱ የዩኒቨርሲቲዎች ሁኔታ ጋር በተያያዘ የፀጥታ ኃይሎች የሚለውን ስያሜ የተጠቀምኩት የክልል ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊቱን ለማመልከት ነው። አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለአብነት በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የፀጥታ ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ የፀጥታ ኃይሉ በግቢው ውስጥ እንዲቆይላቸው ሲጠይቁ፣ በአንፃሩ በደብረ ታቦርናሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ረብሻውን በግንባር ቀደምነት የሚመሩ ተማሪዎች ደግሞ የፀጥታ ኃይሉ ግቢውን ለቆ ካልወጣ ትምህርት አንጀምርም በሚል ጠንካራ ግፊት አድርገዋል።

እንደሚታወቀው የአገራችን ሠራዊት በአገር ውስጥም ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ተልዕኮዎች እየተሰማራ ግዳጁን በብቃትና በከፍተኛ ወታደራዊ ሥነ ምግባር የሚወጣ ነው። ሠራዊታችን በዚህ ብቻ ሳይሆን በሕዝባዊነቱም አድናቆትን ያተረፈ ነው። በዚህ የተነሳ ይህ ተቋም ከየትኛው ተቋም በበለጠ የጠላት ዒላማ ሆኗል። ግለሰቦች በውስጡ ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እንደ ተቋም እየተወጣ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ይህ የፀጥታ ኃይል በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ገብቶ ባያረጋጋ ኖሮ ከዚህም የከፋ የሕይወትና የንብረት ውድመት ሊያጋጥም ይችል እንደነበር ግልጽ ነው። የክልሎች የፀጥታ ኃይሎችም በዚሁ ማዕቀፍ ሥር የሚታይ ሚና ነበራቸው።

ይህ ሆኖ ሳለ የሠራዊቱን ስም የማጥፋት ሥራዎች አስቀድመው በስፋት ተሠርተዋል። ሠራዊቱ በብሔር ያደላል የሚል ዘመቻ ተከፍቶበታል። አንዱን ሕዝባዊ፣ ሌላውን ፀረ ሕዝብ አድርጎ በመሳል ከፋፍሎ የማጥቃት ሥልት የተከተሉ ኃይሎች በፈጠሩት ማደናገሪያ በዩኒቨርሲቲዎችም አንዱን የፀጥታ ኃይል የእኔ ነው በማለት ሌላውን የእኔ ተቃራኒ ነው ብሎ መፈረጅ ታይቷል። በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ከሠራዊት ለመሸሽ ሲሞክሩ ብቻ ወድቀው የተጎዱ ተማሪዎች አሉ። ሠራዊቱ ከግቢ እንዲወጣ የሚደረጉት ግፊቶችም በመሠረታዊነት ምንጫቸው ከግቢ ውጭ ሲሆን፣ ዓላማቸውም ለሕገወጥ ተግባሮቻቸው እንቅፋት ሆኖ የቆመውን ሠራዊት በማስወገድ በግቢ ውስጥ የፈለጉትን ለመፈጸም ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው። ይህን ስል የሠራዊቱን በግቢ ውስጥ ቋሚ ነዋሪነት እየደገፍኩ አይደለም። ቢያንስ የሰላም መደፍረሱን ተከትሎ የገባው ሠራዊት ፀጥታን በማስከበር ረገድ ስኬታማ የመሆኑን እውነታ ለማስቀመጥ ነው እንጂ።

ማጠቃለያ

በዚህ ዓመት ያጋጠመን ችግር ከትምህርት ተቋማት ጋር በቀጥታ ለምንሠራም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሚመለከተን ሁሉ ከድክመታችንም ቢሆን ትምህርት የምንወስድበት ነው መሆን ያለበት። ከዚህ ካልተማርን ከሌላ ልንማር አንችልም። ይኼን ነገር በአገራችንም ይሁን በውጭ አገሮች በታሪክ እንደሚታወቁ የተማሪዎች ግጭት ቆጥረን ልናልፈው የምንችል አይደለም። ልክ ነው፣ ተማሪዎች በሚያነሷቸው የተቃውሞ ሠልፎች፣ አመፆች፣ ወዘተከፀጥታ ኃይሎች ጋር በሚያደርጉት ግብ ግብ ይሞታሉ፣ ንብረት ይወድማል፣ የትምህርት ቀናት ይባክናሉ። እኛ ዘንድ ግን ተማሪን የገደለው ሌላ ተማሪ መሆኑ እጅግ አሳፋሪ ያደርገዋል፡፡ እኛ ግን ንብረት ሲወድም ድህነታችንን የሚጨምርልን መሆኑ አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ እኛ ግን የትምህርት ቀናት ሲባክኑ አሳሳቢ የሆነብንን የትምህርት ጥራት ይበልጥ የሚጎዳ መሆኑ አስከፊ ውጤት ያስከትላል።

አሁን ጊዜያዊ ምላሽ ተሰጥቶ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ተጀምሯል፡፡ ሰላም ተረጋግጧል ማለት ባይቻልም አንፃራዊ ፀጥታ ሰፍኗል። ጉዳዩ ግን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው በመመለስ የሚወሰን ሳይሆን በየዩኒቨርሲቲዎች ተጠራቅመው ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የመማር ማስተማር ሒደቱ በዘላቂ ሰላም ታጅቦ እንዲቀጥል የማድረግ ነው። በማይመች ውጫዊ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም እንኳን ዩኒቨርሲቲዎች በውስጣቸው ያሉ ችግሮችን በማስወገድ ተማሪዎች ሰላም እንዲሰማቸው መሥራት ይችላሉ፡፡ ይገባቸዋልም። ውስጣቸው ጠንካራ ከሆነ ከውጭ የሚመጣ ጫና በቀላሉ እንደማያደፈርሳቸው ከላይ የጠቀስኩት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የጊምቢ ካምፓስ ዓቢይ ማሳያ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖም ውጫዊ የሆኑ አገራዊ ጥያቄዎችን በመመለስ አገር የማዳን ጉዳይም በተጀመረበት አግባብ መቀጠሉ ቸል የማይባል ነው።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡