Skip to main content
x
‹‹መቄዶኒያ እንደ መስጊድና ቤተ ክርስቲያን ማንም ሊኖርበት የሚችል ቦታ ነው››

‹‹መቄዶኒያ እንደ መስጊድና ቤተ ክርስቲያን ማንም ሊኖርበት የሚችል ቦታ ነው››

አቶ ቢኒያም በለጠ፣ የመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መሥራች

አቶ ቢኒያም በለጠ በብዙዎች ዘንድ የመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በመሥራችነታቸው ይታወቃሉ፡፡ እሳቸው ግን በተቋሙ ከሚሠሩ በርካታ በጎ ፈቃደኞች መካከል ‹‹አንዱ ነኝ›› በማለት፣ በተቋሙ ከሌሎቹ በጎ አድራጊዎችና ተረጂዎች በተለየ ኃላፊነት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ መቄዶኒያ በአገሪቱ ከሚገኙ አገር በቀል የመረዳጃ ተቋማት መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል፡፡ በአገር ውስጥ ገቢ ማሰባሰብና አርዓያነት ያለው ሥራ ማከናወን እንደሚቻል ያሳየ ማዕከል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከተቋቋመ ስድስት ዓመታትን ባስቆጠረው በመቄዶኒያ ከ1,500 በላይ ተረጂዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ተረጂዎች የተለያየ የኋላ ታሪክ ያላቸው፣ በተለያየ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ፣ ውስብስብ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ የተለያዩ እምነቶች ተከታይ ሲሆኑ፣ እንደእምነታቸው የሚያስፈልጉዋቸውን ነገሮች ሁሉ ለማሟላት ጥረት እንደሚያደርግ ይነገራል፡ ጎዳና ላይ የወደቁና የተጎዱ ዜጎች ሰብዓዊ ክብር እንዲሰማቸው በሚያደርገው በመቄዶኒያ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች፣ እንክብካቤ የሚሹ ወገኖቻቸውን ለመርዳት ደፋ ቀና ይላሉ፡፡ በተለይም ደግሞ በዓውደ ዓመት የሚኖረው ድባብ የተለየ ድምቀት አለው፡፡ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግም ከሳምንት በፊት ልዩ ዝግጅት ተሰናድቶ ነበር፡፡ አጠቃላይ የተቋሙን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን አቶ ቢኒያም በለጠን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- መቄዶኒያን ለመመሥረት ያነሳሳዎ አጋጣሚ ምን ነበር?

አቶ ቢኒያም፡- መቄዶኒያን አቋቁሜያለሁ ማለት አልችልም፡፡ እኔ ካቋቋሙት ብዙ ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ እነዚህን የተጎዱ ዜጎች መርዳት ዋጋ ስላለው ለመሞከር ብለን የጀመርነው ነው፡፡ አብረውኝ የሚሠሩ የቦርድ አባላትና ቤተሰቦቼ፣ እንዲሁም ሌሎች በጎ ፈቃደኞች አሉ፡፡ መቄዶኒያ ራሳቸውን ችለው መፀዳዳት የማይችሉ አልጋ ላይ የቀሩ ዜጎችን ለመርዳት የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ እነዚህን ሰዎች በመርዳት ከእግዚአብሔር የሚገኘው ፀጋ ከአዕምሮ በላይ ነው፡፡ ሥራውን የጀመርነው ብዙ ሆነን ነው፡፡ መቄዶኒያ የብዙ ሰዎች ድምር ነው፡፡ ሥራውን ስንጀምር ከአዲስ አበባም ከሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች የተገኙ ከሌሎች በተለየ የተጎዱ አርባ ተረጂዎች ይዘን ነው፡፡ ለምሳሌ ደብረ ዘይት ከተማ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የነበሩ ሰዎችን አንስተናል፣ ሐዋሳም ሄደን የተወሰኑ ሰዎችን ሰብስበናል፡፡ በአዲስ አበባም በየበረንዳውና በየቤተ ክርስቲያኑ የወደቁትን አንስተናል፡፡ ትኩረታችን አልጋ ላይ የቀሩ መንቀሳቀስ የማይችሉ ሰዎችን መርዳት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 1,500 ያህል ተረጂዎች በማዕከላችን ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራውን የጀመራችሁት ኮተቤ በሚገኘው በወላጆችዎ ቤት ነበር፡፡ ነገር ግን ቅጥሩ ከተረጂዎች ቁጥር ጋር መመጣጠን አልቻለም ነበረና ብዙ ተቸግራችሁ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ትገኛላችሁ? መንግሥት በሰጣችሁ 30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታስ ምን ያህል ተጠቅማችኋል?

አቶ ቢኒያም፡- እንግዲህ ሥራውን የጀመርነው ኮተቤ በሚገኘው በቤተሰቦቼ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ አባቴ ድሮም ሰው ይረዳ ነበር፡፡ እኛ ቤት ውስጥ ከአንድ አባትና እናት የምንወለድ አሥር ልጆች አለን፡፡ እኛ ቤት ውስጥ ግን 30 የሚሆኑ ሰዎች አብረውን ይኖሩ ነበር፡፡ በወቅቱ አባቴ ሼል ነበር የሚሠራው፣ ጥሩ ደመወዝም ያገኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ካለው የሰው ብዛት አንፃር እንኖር የነበረው ተንደላቀን ሳይሆን በድህነት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ወላጆቼና ወንድም እህቶቼ አሜሪካ ነው የሚኖሩት፡፡ ይኖሩበት የነበረውን ቤት ለመርጃነት እንድንጠቀምበት አባቴን ስጠይቀው እሺታውን ለመግለጽ አላቅማማም ነበር፡፡ በዚህ ቤት መሥራት ከጀመርን ወደ ስድስት ዓመት ሆኖናል፡፡ በጣም ጠባብ ስለነበር ብዙ ተቸግረናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን አያት ኮንዶሚኒየም አጠገብ ወደሚገኘው መንግሥት ከሊዝ ነፃ በሰጠን ቦታ ላይ ግንባታዎች አካሂደን ከኮተቤ በመልቀቅ አያት ገብተናል፡፡ ለሥራ ስለማያመች ጠቅልለን ነው አያት የገባነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዓመት በፊት አያት የሚገኘውን ቅጥር በጎበኘሁበት ወቅት ጊዜያዊ ቤቶች ተሠርተው ነበር፡፡ እነዚያን ጊዜያዊ ቤቶች አፍርሳችሁ ሌላ ራሱን የቻለ ቤት ገንብታችሁ፣ ለሕንፃ ማስገንቢያ የሚሆናችሁን የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ቃል የተገባውን ገንዘብ አገኛችሁ?

አቶ ቢኒያም፡- ደንበኛ ቤት ነው የተገነባው፡፡ ግንባታው በአጭር ጊዜ ነው የተጠናቀቀው፡፡ በመቄዶኒያ የፈጣሪን ኃይል ነው የምናየው፡፡ መንግሥት ከሊዝ ነፃ በሰጠን ቦታ ላይ ሕንፃ ለመገንባት ባዘጋጀነው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ወደ አሥር ሚሊዮን ብር ቃል ተገብቶልን ነበር፡፡ ነገር ግን ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ አላገኘንም፡፡ ቃል የገቡትን እንዲፈጽሙ ተከታትሎ ማስታወስም ይፈልጋል፡፡ በትንሽ ወጪ ብዙ መገንባት ችለናል፡፡ በርካታ በጎ ፈቃደኞች ረድተውናል፡፡ ሌላ ተጨማሪ ሕንፃ ለመገንባትም ዕቅድ ይዘናል፡፡ ሕንፃው 300 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ነው፡፡ ሠርቶ ለመጨረስ  ከፍተኛ ዕርዳታ ያስፈልገናል፡፡ ዮቴክ ኮንስትራክሽን ሙሉ ለሙሉ በሙያ ለማገዝ ቃል ገብቶልናል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ ለመገንባት ያቀዳችሁት ሕንፃ ግንባታ ሲጠናቀቅ ተረጂዎችን የመቀበል አቅማችሁን ምን ያህል ያሳድገዋል?

አቶ ቢኒያም፡- ዓላማችን አጠቃላይ 3,000 ሰዎች ለመያዝ ነው፡፡ ወደ ክልሎችም የመስፋፋት ዕቅድ አለን፡፡ በሁሉም ክልሎች የመስፋፋት ዕቅድ አለን፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሬ በታዘብኩበት ወቅት በርካታ ሰዎች በአስከፊ ድህነት እንደሚኖሩ ተመልክቻለሁ፡፡ ጫት በሚበዛባቸው የአገሪቱ ክፍሎችና አንዳንድ ከተሞች የአዕምሮ ሕመምተኞች ይበዛሉ፡፡ የክልል መንግሥታት ቦታ ቢሰጡን ብዙ ነገር መሥራት እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከምግብና ከተለያዩ ወጪዎች አንፃር ለዕርዳታ የምታገኙት ገንዘብ ምን ያህል በቂ ነው?

አቶ ቢኒያም፡- መቄዶኒያን ብዙ ሰዎች ይረዱታል፡፡ ወጪው ግን ከዚያ የበለጠ ነው፡፡ የምግብ ብቻ ቢታሰብ ካሉት 1,500 ተረጂዎች በተጨማሪ 500 የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች አሉ፡፡ በአጠቃላይ 2,000 ሰዎች ማለት ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ሰው በወር ለምግብ ብቻ 750 ብር ነው የሚመደበው፡፡ 750 ብር በ2,000 ሰዎች ሲባዛ በወር ለምግብ ብቻ 1.5 ሚሊዮን ብር ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ የማይችሉ በቀን ሦስት ጊዜ ዳይፐር የሚቀየርላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ለእነዚህ ሰዎች በየቀኑ የሚያስፈልገው የዳይፐር ወጪ በጣም ብዙ ነው፡፡ ድርጅቱ በዋናነት የሚረዳው የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ሰዎችን ነው፡፡ ስለዚህም ከፍተኛ የሕክምና ወጪዎች አሉብን፡፡ በእርግጥ ኅብረተሰቡ የተለያዩ እንደ ሠርግ፣ ልደት፣ ሙት ዓመት ያሉ ፕሮግራሞችን ከእኛ ጋር ስለሚያከብር የተወሰነ ያግዘናል፡፡ ለምሳሌ ሰይፉ ፋንታሁን መልሱን እኛ ዘንድ ነበር ያዘጋጀው፡፡ አንዳንድ ድርጅቶችም ፕሮግራሞቻቸውን እኛ ጋር ያከብራሉ፡፡ ይኼ ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ያለብንን የምግብ ወጪም ያግዘናል፡፡ መቄዶኒያ የሚያስፈልገው ድጋፍ ግን ብዙ ነው፡፡ ሌላው አንድ ሚሊዮን ብር ሲረዳ፣ አንድ ብር ይዞ የመጣው ሰው የእኔ ብር ዋጋ የለውም ብሎ ማሰብ የለበትም፡፡ የልግስናው መጠን ሳይሆን የልቡ ትልቅነት ነው የሚታየው፡፡

ሪፖርተር፡- በግለሰብና በተቋም ደረጃ በቋሚነት የሚረዷችሁ ይኖራሉ?

አቶ ቢኒያም፡- መቄዶኒያ የውጭ ፈንድ የለውም፡፡ ይኼንን ሁሉ ዕርዳታ የሚያገኘው ከአገር ውስጥ በሚገኝ ድጋፍ ብቻ ነው፡፡ ድርጅቱ ቋሚ ዕርዳታ የለውም፡፡ ሰው በቻለ ጊዜ ነው የሚሰጠን፡፡ በርካታ ሰዎች ባላቸው ሁሉ ይረዱናል፡፡ በበዓላት ጊዜ ምግብና እህል የሚያመጡልን አሉ፡፡ የሃይማኖት ተቋማትና ማኅበራት፣ የግልና የመንግሥት ድርጅቶች ሁሉ ይደግፉናል፡፡ ከላይ እስከ ታች ያሉ ሁሉ ይረዱናል፡፡ የሚገርመኝ አጋጣሚ አለ፡፡ አንድ ቀን የመኪና ታርጋ ለማውጣት መገናኛ አካባቢ ሄድን፡፡ አንድ ደላላ እኔ አስጨርስላችኋለሁ ብሎ ጉዳያችንን ተቀበለን፡፡ ሁለት ሰዓታት ፈጅቶ አስጨረሰልን፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ገንዘብ አልጠየቀንም ነበር፡፡ ከዚህ ሌላ በነፃ የመኪና ጥገና አገልግሎት የሚሰጡን ጋራዦች አሉ፡፡ በተጨማሪ እኛን መጎብኘት በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የአልጋ ቁራኛ የሆነና ሰው የተፀየፈው ሰው የሚፈልገው ፍቅር ነው፡፡ ኅብረተሰቡ እየመጣ ቢጎበኘን ደስ ይለናል፡፡ ፈጣሪም የሚገኘው ከእነዚህ ከተጎዱ ሰዎች ጋር ነው፡፡ እነዚህን ሰዎች መጎብኘት በረከት ማግኘትም ነው፡፡ የአረጋውያን ምርቃትም ጥሩ ነው፡፡ የተያዩ የሕክምና ሙያ ያላቸው ሰዎች እየመጡ ይረዱናል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ የፊዚዮቴራፒ ሙያ ያላቸው አረጋውያኑን ቢያሹልን (ማሳጅ) ደስ ይለናል፡፡ ሁሉም ሙያ ያስፈልገናል፡፡ ሜካኒክ፣ ሾፌር፣ ግንበኛ፣ አናፂና ሌሎችም እንዲረዱን እንፈልጋለን፡፡ ልናስገነባ ላቀድነው ቤትም አሸዋ፣ ጠጠርና ሌሎችም የግንባታ ግብዓቶችን የሚያቀርቡልንን እንፈልጋለን፡፡ ፀጉር ቆራጮች ሳይቀሩ ይመጣሉ፣ በሙያቸው ይረዱናል፡፡ ትምህርት ቤቶቹም ይጎበኙናል፣ ለተረጂዎች የትምህርት ዕድል ይሰጣሉ፡፡ እኛ ጋ ሁሉም ነገር ያስፈልገናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ጥቂት የማይባሉ እንደ መቄዶኒያ ያሉ የመርጃ ማዕከላት አሉ፡፡ ነገር ግን በስኬት ደረጃ የመቄዶኒያን ያህል የለም ማለት ያስደፍራል፡፡ እናንተ ከሌሎቹ የተለያችሁበት አጋጣሚ ወይም ጥንካሬያቸሁ ምንድነው?

አቶ ቢኒያም፡- ለድርጅቱ ሰኬታማ መሆን ዋናው ነገር የፈጣሪ ዕርዳታ የታከለበት መሆኑ ነው፡፡ መቄዶኒያ በድሆች የተቋቋመ በድሆች የሚረዳ ተቋም ነው፡፡ ሀብታሞችም ይረዱናል፡፡ ግን ፈጣሪ ድሆችን ይመርጣል፣ እነሱን ይደግፋል፡፡ እነሱ የሚሰጡን አንድ ብር የተባረከ ከሆነ ከሚሊዮን ብር ይበልጣል፡፡ በቅንነት የምንሠራው ሥራ መሆኑ ለስኬታማነቱ ቁልፍ ነው፡፡ እንዲያውም መቄዶኒያ የፈጣሪ እንጂ የእኛ ሥራ አይደለም፡፡ በረከት የበዛበት ከሚያገኘው ዕርዳታ በላይ እየሠራ ያለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በድርጅቱ ውስጥ ምን ምን ዓይነት ሰዎች ይገኛሉ?

አቶ ቢኒያም፡- በድርጅቱ ውስጥ የተለያዩ ሰዎች አሉ፡፡ መቄዶኒያ እንደ መስጊድና ቤተ ክርስቲያን ማንም ሊኖርበት የሚችል ቦታ ነው፡፡ በዋናነት ግን የምንረዳው የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ዜጎችን ነው፡፡ በእነሱ ላይ የተለየ ትኩረት አድርገን እንሠራለን፡፡ ለአካል ጉዳተኞችም ልዩ እንክብካቤ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- የአዕምሮ ሕሙማን የሆኑ ተረጂዎችን ከሌላው ለይታችሁ የምታስቀምጡበት የተለየ ክፍል አላችሁ?

አቶ ቢኒያም፡- የአማኑኤል ሆስፒታል ሐኪሞች ወደኛ እየመጡ ሕክምና ይሰጧቸዋል፡፡ ከዚያ ውጪ አስፈላጊውን እንክብካቤና ፍቅር እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በፊት ድንጋይ ይወረውሩ የነበሩ የአዕምሮ ሕመምተኞች አሁን አልጋ የሚያነጥፉና ምግብ የሚያቀርቡ አሉ፡፡ የአልጋ ቁራኛ የነበሩም በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ ውስጥ ልብስ ሰፊ፣ ግንበኛ፣ ወዘተ ሆነዋል፡፡ የእንጨትና የብረት ወርክሾፖች ውስጥ ይሠራሉ፡፡ የቢሮ ሠራተኛ የሆኑም አሉ፡፡ በአጠቃላይ ከ300 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ችለው እዚያው ተቋሙ ውስጥ መሥራት እንዲችሉ ተደርጓል፡፡ ከ400 በላይ የሚሆኑ ሰዎችም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ማድረግ ችለናል፡፡ ለምሳሌ እንደ ጀመርን ሰሞን አንድ በጣም የተጎዳ ወጣት ከቤተ ክርስቲያን አካባቢ አንስተን ነበር፡፡ ልጁ የአዕምሮ ሕመም ያለበት ሲሆን፣ ጎዳና የወጣውም በአጋጣሚ ከቤት ወጥቶ መንገዱ ስለጠፋበት ነበር፡፡ ይህ ልጅ እኛ ዘንድ እየኖረ ሳለ በአጋጣሚ የሚያውቁት ሰዎች ሊጎበኙን ይመጡና እዚህ ያገኙታል፡፡ ከዚያም ለቤተሰቦቹ ነግረዋቸው እያለቀሱ መጥተው ወሰዱት፡፡ የሚገርመው ነገር ጥሩ ኑሮ የሚኖሩ ነበሩ፡፡ ከዚያም ከስድስት ወራት በኋላ እኛን ሊጠይቀን ከቤተሰቦቹ ጋር መጣ፡፡ ተመልሼ አልሄድም ብሎ በመከራ ነው የሄደው፡፡ ቤተሰብ ያላቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው፣ የሌላቸው ደግሞ እዚያው እንዲያገለግሉ ይደረጋል፡፡ እኛ ጋ ቀርተው በጎ ፈቃደኛ ሆነው ሲያገለግሉ ብዙ ወጪ ይቀንሱልናል፡፡ ለምሳሌ የሕንፃውን ግንባታ በምናከናውንበት ወቅት ቢሮዎችና ሌሎች የግንባታ ግብዓቶች የተሠሩት በእነሱ ነው፡፡ በትንሽ ወጪ ብዙ መሥራት ያስቻለን በሙያና በጉልበት የሚያግዙን ብዙ ስላሉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሚሠሩት ሥራ በጣም የተደሰቱበት አጋጣሚ ካለ ቢያካፍሉን?

አቶ ቢኒያም፡- ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ የማይችሉ የነበሩ ተሸክመን ወደ መረዳጃው ያስገባናቸው ሰዎች ቆመው ሲሄዱ ሳይ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ሁሌም ከሚያስደስቱኝና ተዓምር ከሚሆኑብኝ ሰዎች መካከል አንዱ ከዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ያነሳነው የ25 ዓመት ወጣት ጉዳይ ነው፡፡ ወጣቱ ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ አይችልም፣ ከወገቡም በጣም የጎበጠ ነበር፡፡ የሚንቀሳቀሰው በዊልቸር እየተገፋ ሲሆን፣ ይፀዳዳ የነበረውም ዊልቸሩ መሀል ላይ ቀዳዳ ተበጅቶለት ከሥሩ በሚቀመጥለት ፕላስቲክ ነበር፡፡ በሽታው የአጥንት ቲቢ ነበር፡፡ ከዚያም ለስድስት ወራት ያህል የቲቢ ሕክምና ተሰጠው፡፡ አሁን ጤናው ተመልሷል፡፡ ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን የጉልበት ሥራዎችን ሁሉ ይሠራል፡፡ ከደብረ ዘይት ከተማ ያነሳነው አንድ ሰው ጉዳይ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ተዓምር ነው፡፡ በደብረ ዘይት ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ መንደር ውስጥ በላስቲክ በተሸፈነ ዳስ ውስጥ የእንጨት አልጋ ላይ ነበር ያገኘነው፡፡ መንቀሳቀስም ሆነ መናገር አይችልም፡፡ የመንደሩ ነዋሪዎች የሚሰጡትን ምግብ እየበላ እዚያው ሲተኛ ነበር የከረመው፡፡ ከቦታው ሳይንቀሳቀስ ስድስት ወራት ያህል ሲቆይ የሚፀዳዳው ራሱ ላይ ነበር፡፡ ሽታው ከባድ ስለነበር ለመጠጋት ሁሉ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሽታውን ችለን ስንቀርበው ሰውየው ሙሉ ለሙሉ ጀርባው ቆስሎ ነበር፡፡ ገላውም ተልቶ ነበር፡፡ ስናጥበው ሁሉ ከቁስሉ ላይ ይራገፍ የነበረው ትል በጣም ብዙ ነበር፡፡ ትንሽ የአዕምሮ ችግርና የቲቢ በሽታ ነበር ለዚህ የዳረገው፡፡ እኛ ከወስድነው በኋላ ለምስንት ወራት ያህል የቲቢ መድኃኒት እንዲወስድ ተደረገ፡፡ ቀስ በቀስም ሰውነቱ እየተስተካከለ መምጣት ጀመረ፡፡ ከስምንት ወራት በኋላ መንቀሳቀስና ማውራት ጀመረ፡፡ ያለበት የአዕምሮ ችግር ጨርሶ አለቀቀውም፡፡ ነገር ግን መንቀሳቀስ ይችላል፣ በደንብ ያወራል፡፡ ለእኔ የእሱ መለወጥ ተዓምር ነው የሚሆንብኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በዓላት በመቄዶኒያ እንዴት ይከበራሉ?

አቶ ቢኒያም፡- የክርስትናና የእስልምና እምነት በዓላት በደንብ ይከበራሉ፡፡ በዓሉን ከእኛ ጋር ማሳለፍ የሚፈልጉም ወደኛ ይመጣሉ፡፡ በተለይም የረመዳን ፆም ጊዜ በደንብ ይከበራል፡፡ የሚዘጋጀው ምግብ ለእኛም ይደርሰናል፡፡ ያው እንግዲህ በአገሪቱ ያሉት ዕምነቶች እነዚህ ሁለቱ ናቸው፡፡ የሁለቱንም በዓላት በደመቀ ሁኔታ ነው የምናከብረው፡፡

ሪፖርተር፡- ‘ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው’ በሚል መርህ መቄዶኒያን እዚህ አድርሳችኋል፡፡ ይኼ መርህ ወደ ፊትም አብሯችሁ ይቆያል?

አቶ ቢኒያም፡- ‘ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው’ ስንል ለወሬ አይደለም፣ በጣም የምናምንበት ነገር ስለሆነ ነው፡፡ ብዙዎች መርዳት ይችላሉ ብለው የሚያስቡት ሀብታሞችን ብቻ ነው፡፡ ይኼ ግን ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ ማንም ሰው መርዳት ይችላል፡፡ እንዲያውም መቄዶኒያን እንዳቋቋምን ሰዎች እባክህን ሀብታሞችን መያዝ አለብህ ይሉኝ ነበር፡፡ እኔ በጣም የምቃወመው ነገር ነው፡፡ ሀብታሞች እየረዱን ነው፣ እንዲረዱንም እንፈልጋለን፡፡ እነሱ ካልረዱን መሥራት አይቻልም ማለት ግን፣ ፈጣሪ ሥራውን አይሠራም ማለት ነው፡፡ ሰው ሆኖ አለመርዳት የማይችል የለም፡፡ ሰው መሆኑ በራሱ መርዳት እንዲችል ብቁ ያደርገዋል፡፡ አንድ ሰው ፈጣሪ ከረዳው ዓለምን መቀየር ይችላል፡፡ ስላልተማረ ወይም ገንዘብ ስለሌለው የመርዳት አቅም የለውም ማለት አይደለም፡፡ ሰዎች አቅማቸውን ማወቅ አለባቸው፡፡ ማንም ከማንም አያንስም፡፡ ይኼንንም በመቄዶኒያ እየተመለከትን ነው፡፡ ይኼንን የሚያነብ ሰው በሙሉ መርዳት ይችላል፡፡ ሰው አይችልም ማለት ፈጣሪንም መናቅ ነው፡፡ ሰዎችን መርዳት ደሃ አያደርግም፡፡ ደሃ ብንሆንም መርዳት አለብን፡፡ የተቸገረን መርዳት ከተረጂው ባለፈ ለረጂው ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ አለመርዳት በፈጣሪ ዘንድ ያስጠይቃል፡፡ መርዳት ደግሞ የበለጠ ዋጋ አለው፡፡ አለመርዳት እኮ በዓለማዊ ሕግም የሚያስጠይቅበት አግባብ አለ፡፡ አንድን አደጋ ውስጥ የገባን ሰው መርዳት በረጂው ላይ የሚፈጥረው ችግር እስከሌለ ድረስ መርዳት ግዴታው ነው፡፡ መርዳት እየቻለ በቸልተኝነት ካለፈው ግን ኮሚሽን ባይ ኦሚሽን (ወንጀሉን በድርጊት ባይፈጽምም ባለው አቅም ድርጊቱን ማስቀረት እየቻለ በማለፉ) አግባብ በሕግ ይጠየቃል፡፡

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ የትምህርት ሁኔታዎ ምን ይመስላል? በተመረቁበት የሕግ ሙያ አገልግለዋል?

አቶ ቢኒያም፡- ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፡፡ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በቅዱስ ዮሴፍ ትህምርት ቤት ተማርኩ፡፡ በትምህርት ብርቱ ከሚባሉት ተርታ ከአንድ እስከ ሦስት ነበር የምወጣው፡፡ የአሥራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አራት ነጥብ አስመዝግቤ ነበር ያለፍኩት፡፡ ማትሪክ የወሰድኩት በ1985 ዓ.ም ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ሰባት ልጆች ብቻ ነበርን አራት ነጥብ ያስመዘገብነው፡፡ ጥሩ ውጤት ስለነበረኝ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት መርጬ ተማርኩ፡፡ ሕግ መማር የመረጥኩት የሚያበላ ሥራ ስለነበር እንጂ ፍላጎቴ አልነበረም፡፡ ከሕግ ትምህርት ቤት ተመርቄ እንደወጣሁ በዓቃቤ ሕግነት ተቀጠርኩ፡፡ በዚህ ሙያ ለሦስት ዓመታት ያህል ካገለገልኩ በኋላ ቤተሰቦቼ ወደሚኖሩበት አሜሪካ ሄድኩ፡፡ አሜሪካ እንደገባሁ ለስድስት ወራት ያህል የጉልበት ሥራ ሠርቻለሁ፡፡ ሥራው ኤርፖርት ውስጥ እንደ ልባቸው መንቀሳቀስ የማይችሉ አረጋውያንን በዊልቸር መግፋት ነበር፡፡ ከዚያም ንብረትነቱ የቤተሰቦቼ በሆነ ሱፐርማርኬት ውስጥ አብሬ መሥራት ጀመርኩ፡፡ እየሠራሁ በመካከል እዚህ እመላለስ ነበር፡፡ በትርፍ ጊዜዬም ፊላንትሮፒና ዴቨሎፕመንት በማስተርስ ፕሮግራም ተምሬ ነበር፡፡ ከዚያም ከምኖርበት ግዛት ወደ ዴንቨር ሄጄ ሌላ ሥራ ጀመርኩ፡፡ ሥራው የአዕምሮ ሕሙማን የሆኑ ሰዎችን ማስተማር ነው፡፡ እዚህ በምመላለስበት ወቅት ደግሞ ችግረኛ የሆኑ የሠፈሬን ልጆች አሰባስቤ ዕረዳ ነበር፡፡ ነገር ግን የልቤን ያህል መሥራት ስላልቻልኩ ከሰባት ዓመታት በፊት ሙሉ ለሙሉ ጠቅልዬ አገሬ ገባሁ፡፡