Skip to main content
x

የዋጋ ቅናሽ የሚናፍቀው ሸማች

በዓላት በተቃረቡ ቁጥር ሰውን ሁሉ ራስ ምታት ከሚያሲዙ ጉዳዮች አንዱ የዋጋና የገበያ ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከበዓላት አከባበር ልማድ አኳያ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ እንደ በግ፣ ዶሮ፣ ቅቤ፣ እንቁላል ወዘተ. ምርቶች ዋጋቸው ምን ያህል ጨምሮ ይሆን? የሚለው ያሳስባል፡፡ ሁሉም እንደየአቅሙ በዓሉን ለማክበር ተለቅቶና ተበድሮ የቋጠራትን ጥሪት በመያዝ ወደ ገበያ ያቀናል፡፡

በበዓላት ዋዜማ የሚቆመው የገበያ ዋጋ፣ ከቀደመው ጊዜ አኳያ ቀንሶ ማየት ዘበት ነው፡፡ የገበያ ሕግ እዚህ ባይተዋር ነው፡፡ ገበያን መሠረት ያደረገ የግብይት ባህል ብርቅ ነው፡፡

የተትረፈረፈ ምርት የቱንም ያህል ቢኖር በበዓል ገበያ የሚታየው ዋጋ ከቀደመው ጊዜ ቀንሶ አይገኝም፡፡ ሲቀንስም አልታየም፡፡ ይህ በአገራችን የተለመደ ክስተት ሆኖ በመዝለቁ፣ ሸማቾችም ኪሳቸውን በዚሁ አግባብ አዘጋጅተው ገበያ ቢወጡ አይፈረድባቸውም፡፡

ሥር እየሰደደ የዘለቀው አጉል የበዓል ሰሞን የተጋነነ ዋጋ የበዓሉ አከባበር ሲያበቃ አብሮ ቢያበቃ እሰየው ነበር፡፡ ለበዓል ገበያ እንዳሻው የሚሰቀለው ዋጋ ግን በዚያው ቀጥሎ አልወርድ ሲል አይተናል፡፡ ለምሳሌ ልኳንዳ ቤቶች ዋጋ የሚሰቅሉበት አመቺ ጊዜ ቢኖር እንደ ገና ያለው በዓል ሲመጣ ነው፡፡

‹‹በዓል ስለሆነ የበሬ ዋጋ ጨምሯል፤›› በሚል ሰበብ፣ የአንድ ኪሎ ሥጋ የመሸጫ ዋጋውን ከፍ ያደርጉታል፡፡ ይሁንና ከበዓሉ በኋላም የተጨመረው ዋጋ የከብት አቅርቦት ቢሻሻልና ዋጋም ቢቀንስ እንኳ፣ አብዛኞቹ ያደረጉትን ጭማሪ ሲያስተካክሉ አይታዩም፡፡ ሌላው ከበዓሉ ቀን ቀደም ብሎ ይሸጥበት የነበረው ዋጋ ላይ የተወሰነ በማከል የመሸጫ ዋጋውን በዚያው ተክሎ የሚያስቀረው ጥቂት አይደለም፡፡ በዓል በመጣ በሄደ ቁጥር እንዲህ ያለው አድራጎትም አብሮ ይቀጥላል፡፡

የበሬ ዋጋ የቀድሞ ቦታው ቢመለስ ወይም ቢቀንስ እንኳ ዓውድ ዓመቱን ታኮ የተጨመረ ዋጋ ሲቀንስ አይታይም፡፡ ልብ ብላችሁ እንደሆነ፣ የእንቁላል ዋጋ ለውጥ የሚታይበትና እስካሁን የታዩት ጭማሪዎች የተከሰቱት ከዓመት በዓልን በማስታከክ ነው፡፡

እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች የሚፈጠሩ የዋጋ ጭማሪዎች የግብይት ሥነ ምግባርን የሚጋፉ ከመሆናቸውም በላይ፣ ለሸማቹ ደንታ እንደሌላቸው የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገሩን ከፍ አድርገን ካሰብነው ግን፣ ከልክ በላይ ለማትረፍ የሚፈጸሙት ድርጊቶች ለዋጋ ግሽበት ጦስ ሆነው የሸማቹን ምሬት እንደሚያባብሱት ግልጽ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ደንበኞችን መሠረት ያደረገ፣ ፍላጎትና አቅማቸውን ያገናዘበ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የበዓል ሰሞን ገበያ ለበዓሉ እንደ ዋነኛ ግብዓት የሚቆጠሩ ምርቶች ብቻ የሚሸመቱበት ሳይሆን፣ ተጓዳኝ ምርቶችም ገበያው የሚደራላቸው ከመሆናቸው አኳያ፣ በበዓሉ ሰበብ የዋጋ ጭማሪ የሚደረግባቸው ምርቶች የትዬለሌ ናቸው፡፡ በበዓል ገበያ ሰበብ በዋጋ ጭማሪ እየታጀቡ ሸማቹን መከራ የሚያሳዩ ነጋዴዎች እንዲህ መጓዛቸው ሊገታ፣ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባዋል፡፡

በዚህ ወቅት ሸማቾች እንደመሻታቸውና አቅማቸው በአነስተኛ ዋጋ የሚሸምቱበት የገበያ ዕድል ሊፈጠርላቸው በተገባ ነበር፡፡ በሌላው ዓለም በዓል ሲቃረብ፣ በተለይ በአዲስ ዓመት ወቅት፣ ኩባንያዎች ደንበኞቻቸውን አስበው እውነተኛ ቅናሽ ያደርጋሉ፡፡ በእጃቸው የሚገኘውን ምርት ያጣራሉ፡፡ እንደውም አንዳንዶች 90 በመቶ፣ መቶ በመቶ የዋጋ ቅናሽ አድርገናል እያሉ ምርቶቻቸውን በነፃ ሲያድሉ ሁሉ ይታያሉ፡፡

በዚህ ተግባራቸው አብዛኞቹ በአነስተኛ የትርፍ ህዳግ ብዙ ሸጠው ይጠቀማሉ፡፡ ደንበኞቻቸውም ለቅናሽ ዋጋው ኩባንያውን አመስግነው ለከርሞ እንዲገናኙ በመመኘት የሚበቃቸውን ያህል ይሸምታሉ፡፡ የሚሸምቱት ዕቃም ሸቀጥም ዋጋው ስለቀነሰ ጥራቱ አይቀንስም፡፡ አይበረዝም፡፡   

ይህንን ጉዳይ ወደ እኛ አገር መልሰን ስናየው የተገላቢጦሹን ያሳየናል፡፡ የበዓል ገበያ እጥፍ ድርብ ትርፍ የሚታፈስበት ስለሆነ፣ ደንበኞችን መሠረት በማድረግ ሊፈጸም የሚገባው የግብይት ባህል የማይታሰብ፣ የዋጋ ቅናሽ ማድረግ የገበያውን ሃድራ አለማወቅ ሁሉ ሊመስል ይችላል፡፡ እርግጥ ነው ‹‹ታላቅ ቅናሽ›› እየተባለ በሚለጠፍ ያሸበረቀ፣ የተሽቀረቀረ ጽሑፍ የሚዥጎደጎዱ ሱቆችን ማየት የተለመደ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ቅናሽ የሚሉት ዋጋ እውነተኛ ሆኖ አይገኝም፡፡

ስለዚህ የግብይት በዓላትን ታሪክ ለመቀየር ከሚታሰቡ ብርቱ ጉዳዮች አንዱ ቢያንስ በዓመት ሁለቴ ወይም ሦስቴ ደንበኞች በልዩ የዋጋ ቅናሽ ሊስተናገዱ የሚችሉበት ገበያን መፍጠር አንዱ ነው፡፡ እርግጥ ነው እንዲህ ያለውን ገበያ ለማምጣት ትልቁና ዋናው ቁምነገር አምራች ኢኮኖሚ መፍጠር መቻል ነው፡፡ በኢኮኖሚው አምራች ፋብሪካዎች እንደልብ እስካልተስፋፉ ድረስ፣ የዋጋ ቅናሽን ማምጣት ቀላል አይሆንም፡፡ ሌላው ቢቀር ከውጭ የሚገባ ዕቃ ከቀረጥና ከሌላው ወጪ ባሻገር የሚታከልበትን የ40 በመቶ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ወጪ መቀነስ የሚያስችሉ ምርቶችን እዚሁ እንደልብ ማምረትና ማግኘት መቻል በምን ዕድል ያሰኛል፡፡

ይህ እስኪሆን ግን ቀና ኩባንያዎች ዋጋ መቀነስን ቢያስለምዱ እንዴት በተወደዱ፡፡ ከዚህ በተራቃኒው ግን በቅናሽ ዋጋ ሸማቾች ይስተናገዱባቸው የሚባሉ ባዛሮች ውስጥ የሚቀርቡ ሸቀጣ ሸቀጦች የዋጋ ቁልል እየታየባቸው ነው፡፡ የመሸጫ ዋጋቸው በመደበኛ መደብሮች ከሚሸጥባቸው ዋጋ በላይ ሲሆኑ ማየት ተለምዷል፡፡ ነጋዴዎች ደንበኛውን አስበው ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ በቅናሽ ቢሸጡ ምን ይላቸዋል ያሰኛል፡፡

ለይምሰል ዋጋ ቅናሽ አድርገናል የሚሉ ተቋማት፣ ማስታወቂያቸው የይስሙላ ስለመሆኑ ከማናችንም የተደበቀ አይደለምና በበዓል ገበያዎች ወቅት ቅናሹ እንኳ ቢቀር ምናለ ትክክለኛ ዋጋ ቢያስክፍሉን? በበዓላት ሰሞን የሚፈጠሩ የዋጋ ቁልሎች ይናዱልን ዘንድ መንግሥትንም ነጋዴም አቤት እንላለን፡፡ መልካም በዓል፡፡