Skip to main content
x
‹‹ከቱሪስቱ በላይ እኛ ዘንድ ያለው ችግር ነው መሠረታዊ ለውጥ የሚፈልገው››

‹‹ከቱሪስቱ በላይ እኛ ዘንድ ያለው ችግር ነው መሠረታዊ ለውጥ የሚፈልገው››

ወ/ሮ መዓዛ ገብረ መድኅን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ

‹‹ኢትዮጵያን ብዙ ብናስተዋውቅ፣ ገጽታ ብንገነባና በርካታ ቱሪስቶች ብናመጣ የማስተናገድ አቅማችን ዝግጁ ካልሆነ፣ በርካታ መዳረሻዎችን ካልገነባን አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፤›› የሚሉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ መዓዛ ገብረ መድኅን፣ በቱሪዝም ዘርፉ በርካታ ያልተነኩ ሀብቶች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ የዘርፉ ማነቆዎች በግሉ ዘርፍ ተሳትፎም ጭምር መፈታት አለባቸው ብለው ያምናሉ፡፡ መስኅብ ከመለየት፣ መዳረሻ ቦታዎችን ከማልማት ችግሮች ባሻገር፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል ችግርም የዘርፉ መገለጫ ነው፡፡ በቱሪዝም መስክ ያለው የሠለጠነ የሰው ኃይል ከሚፈለገው አኳያ 23 በመቶ ብቻ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስርት ዴኤታዋ፣ ማንኛውም የሥራ ዘርፍ በተማረና በሠለጠነ የሰው ኃይል መመራት እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ሥራዎችን ማከናወን ዘመኑ የሚጠይቃቸው ግዴታዎች በመሆናቸው በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች በቱሪዝም መስክ ሥልጠና ቢሰጡም፣ ንድፈ ሐሳብን ከተግባር አዛምዶ ሥልጠና የሚሰጠው ግን አንጋፋው የሆቴልና ቱሪዝም ማሠልጠኛ ተቋም እንደሆነ፣ በመስህብ መለየት ሥራ መስክ በርካታ ሥራዎች ማከናወን እንደሚገባ ምሳሌ ሲጠቅሱም፣ በዚህ ዓመት በኦሮሚያ ክልል በተከበረው የዓለም ቱሪዝም ቀን ከአዲስ አበባ በ100 ኪሎ ሜትር ከወንጪ ሐይቅ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ዳንዲ የምትባል ሐይቅ አለች፡፡ እነ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን የተወለዱበት አካባቢ የምትገኘው ይህች ሐይቅ በስምንት ቁጥር ቅርፅ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ያላት ነች፡፡ በመቱ አካባቢ የሚገኘው ሶር ፏፏቴ፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ከጭስ ዓባይ ቀጥሎ የሚጠቀስ ነው፡፡ እነዚህ ግን በአብዛኛው ሰው ዘንድ አይታወቁም፡፡ ‹‹እግዜርና ወፍ ብቻ ነው የሚያውቁት፤›› ይላሉ፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ቢተዋወቁ በርካታ ቱሪስቶች ሊጎበኟቸው የሚችሉ ናቸው፡፡ በጋምቤላ የማጃንግ ደን በባዮሴፍቲ ጥበቃ መዝገብ ተመዝግቧል፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ የማናውቃቸው መስህቦች የሚገኙባት በመሆኗ እንዲለዩና እንዲጠኑ ማድረግ እንደሚገባ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ የቅርስና የፓርኮች ጥበቃ፣ የሆቴሎች ምደባ፣ የቱሪዝም ገቢና መሰል ጉዳዮችን በማስልከት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ መዓዛ ገብረ መድኅንን ብርሃኑ ፈቃደ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ኢትዮጵያ ብዙ ሀብት እንዳላት የታወቀ ነው፡፡ ሚኒስቴሩም ሕዝብና አገር የሚጠቀምባቸውን ሥራዎች እያከናወነ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ከዚህም በመነሳት ይመስላል ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አምስት ዋና ዋና የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ እንድትሆን ያቀደው፡፡ አሁን ይህ ዕቅድ ሲገመገም ይሳካል ብለው ያምናሉ? በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ እንዲሳካስ ምን ምቹ ሁኔታዎች አሉ? እንዳይሳካ የሚያደርጉት ፈታኝ ነገሮችስ ምንድን ናቸው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- የቱሪዝም ዘርፍ የሚኒስቴሩን ብቻ ሳይሆን የአብዛኛውን ኅብረተሰብ ትኩረት ያገኘ ዘርፍ ነው፡፡ የትውውቅና ግብይት ሥራ በዋናነት ይሠራል፡፡ የመስህብ ልየታ ሥራም ይሠራል፡፡ የመዳረሻ ቦታ ልማት፣ እንዲሁም የሰው ኃይል ልማት፣ የዱር እንስሳትና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ጨምሮ በፓርኮች ልማትና በኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ ሥራዎች በሚኒስቴሩና በሥሩ ባሉ ተቋማት በኩል ይከናወናሉ፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት፣ አንጋፋው የሆቴልና ቱሪዝም ማሠልጠኛ ተቋም፣ የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን በሚኒስቴሩ ሥር የሚገኙ ተቋማት ናቸው፡፡ በዋናው መሥሪያ ቤት የብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ በተለይ የሆቴሎች፣ የአስጎብኝ ድርጅቶች የዕውቅና ፈቃድ አሰጣጥ፣ የሆቴሎች ከቀረጥ ነፃ ዕድል የማግኘት አገልግሎት፣ የግንባታ ጥራት ቁጥጥርና የስታትስቲክስ ክፍል አለን፡፡ በየሩብ ዓመቱ የሚወጣው የቱሪዝም ዘርፉ መረጃ በስታትስቲክስ ክፍል የሚወጣ መረጃ ነው፡፡ በእነዚህ የሥራ ዘርፎች አማካይነት ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ እንደ መንግሥት የቱሪዝም ልማት ፖሊሲ፣ ልዩ ልዩ ስትራቴጂዎች፣ የአሥር ዓመት ማስተር ፕላንና የቱሪዝም ትራንፎርሜሽን ምክር ቤት አለን፡፡ ምክር ቤቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይመሩታል፡፡ የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሁሉም ክልሎች የቱሪዝምና የባህል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የአስጎብኝ ድርጅቶች፣ የሆቴሎች ማኅበራት፣ በቱሪዝም ዘርፍ ዕውቀቱ ያላቸው ምሁራን በምክር ቤቱ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ በየስድስት ወራት በመገናኘት ይወያያል፡፡ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት በመሥራት በኤምባሲዎች በኩል በሚሠሩ ሥራዎች የቱሪስት ቁጥር እንዲጨምር፣ ባለሀብቶች እንዲያለሙ የሚከናወኑ ሥራዎች አሉ፡፡ በትልልቅ ዓውደ ርዕዮችም እንሳተፋለን፡፡

እዚህ ላይ የአስጎብኝዎችና የባለሙያዎችን ሥራ ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ በራሳቸው መንገድ በብዙ መንገድ ኢትዮጵያን አስተዋውቀዋል፡፡ ከ13 ወራት ፀጋ (13 Months of Sunshine) ከሚለው ጀምሮ በራሳቸው ጥረትና ብርታት አገራችንን ለማስተዋወቅ ትልቅ ጥረት በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡ ባለሙያዎቹም ቢሆኑ ብዙም የተመቻቸ ነገር ባልነበረበት ወቅት እንኳ የወደፊት ተስፋ በመያዝ አገራቸውን ሲያስተዋውቁ ኖረዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ተጠቃሹ አቶ ኃብተ ሥላሴ ታፈሰ ናቸው፡፡ የቱሪዝም መሠረት የሆኑና የቱሪዝም አባት ናቸው፡፡ ይህንን ካልን በችግር ደረጃ ከሚጠቀሱት መካከል አንደኛው ቁልፍ ችግራችን የመዳረሻ ልማት ላይ ያለው ነው፡፡ ግብይትና ትውውቅ ልንሠራ እንችላለን፡፡ ቱሪስቶቹ ከመጡ በኋላ ግን ሊጓዙባቸው የሚችሉባቸው መሠረተ ልማቶች ከሌሉ፣ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ሆቴሎች ከሌሉ፣ ከባህላቸው ጋር ተቀራራቢ የሆነ መስተንግዶ ማቅረብ ካልቻልን እኛው ላይ ተመልሶ አሉታዊ ጫና ያሳድራል፡፡ አንዳንዱ ቦታ ላይ ‹አድቬንቸር ቱሪዝም› የሚወድ ጎብኝ በራሱ መንገድ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ዘውጎች አሉ፡፡ በርካታ የቱሪዝም ዘውጎች ግን አሉ፡፡ እዚህ ላይ አልነጃሺ መስጂድን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዓለም የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን አልነዳሺ የት ነው ያለው ሲባል ኢትዮጵያ ነው፣ በኢትዮጵያም እንዲህ የሚባል ቦታ ውስጥ ይገኛል ብሎ መናገርና ማስተዋወቅ የእኛ ሥራ ነው፡፡ ጥሩ ይህንን ሠራን፡፡ ሌሎችም ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችን የሚጎበኙ እንዲመጡ አደረግን እንበል፡፡ ግን ምንድነው በሚጎበኙበት ቦታ ማግኘት የሚችሉት፡፡ የሚመጣውን ቱሪስት የሚሸከም ሆቴል በቦታው አለ ወይ? አዲግራት አካባቢ መስጂዱን ለማየት የሚመጣው ቱሪስት ከሚያርፍበት ቦታ ባሻገር፣ ሶላት ማድረግ ቢፈልግ፣ ዱዓ ማድረግ ቢፈልግ፣ ከመጠጥ ነፃ አገልግሎት ማግኘት ቢፈልግ ይህንን ለማቅረብ የሚያስችል ሥራ ላይ ገና ነን፡፡

ሌላ እንደ ምሳሌ የማነሳው በፊት የሚመጣው ቱሪስት የአውሮፓና የአሜሪካ ነው፡፡ አሁን ግን ከእስያ አገሮች እንደ ቻይና፣ ጃፓን፣ ኮሪያና ሲንጋፖር ያሉት አገሮች በርካታ ዜጎቻቸው ጎብኝዎች እየሆኑ ነው፡፡ ከቻይና አንድ በመቶ ጎብኝ ወደ እኛ አገር ቢመጣ ብዙ ነገር ይቀይራል፡፡ ነገር ግን የቻይና ቱሪስቶች በአብዛኛው የተፈጥሮ መስህቦችን ይመርጣሉ፡፡ ሲመጡም ምርጫቸው የሆነውን ምግብ፣ ከባህላቸው ጋር የሚስማማውን አገልግሎትና የቋንቋ ክህሎት ሊኖረን ይገባናል፡፡ አስጎብኝዎቻችን የቋንቋ ችግር አለባቸው፡፡ እነዚህ ከድሮ ጀምሮ ሲንከባለሉ የመጡ የችግር ድምሮች ናቸው፡፡ ድሮ ቱሪስቶች ጎብኝተው ብቻ ነው የሚሄዱት፡፡ አሁን እንደዚያ አይደለም፡፡ ባህልና አኗኗር ውስጥ ራሳቸውን መክተትና በዚያ አግባብ ተሞክሮ ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ ስንናገረው ቀላል ይመስላል፡፡ ግን የመፀዳጃ ቤት አቅርቦት ሊኖረን ይገባል፡፡ ከተፈጥሮ ጋር የሚስማማ የኢኮቱሪዝም እንዲስፋፋ፣ ኅብረተሰቡም ለቱሪስት አመቺ አገልግሎቶችን በማቅረብ መጠቀም የሚችልባቸው ነገሮች አሉ፡፡ በቅሎ በማቅረብ፣ ምግብ በማብሰልና ሌሎችም ብዙ ነገር የማይጠይቁ አገልግሎቶችን ማቅረብ ይጠይቃል፡፡ ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ አስተሳሰባችንና አገልግሎታችንን ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ በአስጎብኝ ድርጅቶችና በአካባቢ አስጎኝዎች መካከል የመናበብና ተግባብቶ የመሥራት ችግሮች አሉ፡፡ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለአካባቢ አስጎብኝዎች መስጠቱ ላይ የሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ችግሮች እንዳሉ ተገንዝበናል፡፡ ይህንን ለመቅረፍም ሥልጠና መስጠት እንደሚገባ ተግባብተናል፡፡

ከሕግ አወጣጥ አኳያ ሊታዩ የሚችሉ ነገሮች አሉ፡፡ አንዳንዱን እኛ ብቻ አንቆጣጠርም፡፡ ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያን ካሏት ቅርሶች አኳያ ገቢውን ራሷ ትቀበላለች፡፡ ላሊበላን የሚጎበኝ ቱሪስት 50 ዶላር ሊጠየቅ ይችላል፡፡ ይህ ገንዘብ በዝቶ ወይም አንሶ ሳይሆን፣ ጎብኝው ግን ካሉት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ መጎብኘት የሚፈልገው ሁሉንም ባይሆንስ? እንዲህ ባሉት ነገሮች ላይ የጋራ አሠራር ሊኖረን ይገባል፡፡ ቱሪስቶቹ በሄዱበት ቦታ ሁሉ በአካባቢ አስጎብኝዎች ገንዘብ ይጠየቃሉ፡፡ አስጎብኝ ድርጅቶች እንደሚያወሱት ቱሪስት ሊስቡ የሚችሉ እግረ መንገዱን ለማየት ከመኪናው ሲወርድ ገንዘብ እንዲከፍል ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ አስጎብኝ ድርጅቱ ወጪው ስለሚበዛበት ቱሪስቱ ብዙም ሳይጎበኝ እንዲሄድ ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን ቱሪስቱ ሁለትም ሦስት ቀንም ቢቆይ ተጠቃሚው አስጎብኝዎች ብቻ ሳይሆኑ ኅብረተሰቡም ጭምር ነው፡፡ የአካባቢ አስጎብኝዎች የአስጎብኝ ድርጅቶችን የሚወቅሱት በዚህ ነው፡፡ ቱሪስቶችን ብዙ እንዲቆዩ አያደርጉም እያሉ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን የምንፈታው በስታንዳርድ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ተሞክሮንም ወስደን የቱሪዝም ዘርፉን በአጠቃላይ የሚያቅፍ አዋጅ ለማውጣት እየሠራን ነው፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብዙ ጥናት ተደርጎ ትልቅ ሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስመንት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ከኢሚግሬሽንና ከሌሎችም ጋር የሚያገናኙን ጉዳዮች አሉን፡፡ ከእያንዳንዱ ጋር አብሮ በቅንጅት ለመሥራት ረቂቅ ሕግ እየተዘጋጀ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይህ ሁሉ ከሆነ ኢትዮጵያን ከአምስቱ ዋና ዋና አገሮች ውስጥ አንዷ ማድረግ ይቻላል ማለት ነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- አዎን፣ እናሳካዋለን፡፡ ተስፋ የሚሰጡ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታውም ያስገድደናል፡፡ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታው እያደገና እየተቀየረ ሲሄድ በዚያው ልክ መጓዝ የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ያልተነካ ሀብት አላት፡፡ እንዴት እንጠቀምበት ነው ጥያቄው፡፡ አንዳንዱ አገር ጥቂት ኖሮት ነው በአጠቃቀም የሚበልጠን፡፡ የእኛ ቱሪዝም ምንም አልተነካም፡፡ እንዴት እንጠቀምበት? እንዴት እንሥራበት? የሚለው ነው ዋናው ነገር፡፡

ሪፖርተር፡- ያልታየውና ያልተነካው ብዙ የመሆኑን ያህል የታየውንና የታወቀውንም የመጠበቅና የመንከባከቡ ነገር ችግር አለበት፡፡ የረዥም ዓመታት ቅርሶች፣ ሥዕሎች፣ እንደ ላሊበላ ያሉትን ጨምሮ ትልቅ ጥያቄና ጭቅጭቅ ማስነሳት የጀመሩት ከክብካቤና ከጥበቃ አኳያ አያያዛቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ነው፡፡ እዚህ ላይ ምንድነው ሊባል የሚችለው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ለዚህ ዘርፍ የተመደበ የቅርስና ጥናት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት አለን፡፡ ዘርፉ የሚጠይቀው ሙያዊ ነገሮች አሉት፡፡ ሳይንሳዊ ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ በርካታ ሀብት ይፈልጋል፡፡ ባለፈው ላሊበላ ላይ በተለይ ቤተ ገብርኤል ሲጠገን በከባድ ጥንቃቄ ነው ሥራው የተከናወነው፡፡ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው በገቡ ዕቃዎች ነው የተጠገነው፡፡ ይህ ትልቅ ሀብት ይጠይቃል፡፡ የዳበረ የቴክኖሎጂ ሽግግር የለንም፡፡ በዚህ ሳቢያ የሚመጡ ተያያዥ ችግሮች አሉ፡፡ ይህም ሆኖ እያንዳንዱን ችግር በሚገባ ተገንዝቦ፣ የትኛው ጉዳይ ከየትኛው መቅደም አለበት ብሎ በመወሰን ረገድ ስትራቴጂካዊ የአመራር ክፍተቶች አሉ፡፡ ሥራው የቴክኖሎጂና የዕውቀት ችግር ብቻም ሳይሆን ከባድ በጀት ይጠይቃል፡፡ አገሪቱ በርካታ ቅርሶች አሏት፡፡ በተለይ በሰሜኑ ክፍል ብዙ ቅርስ አለ፡፡ አብዛኛው ጥያቄም ቅርስ ይጠገንልን የሚል ነው፡፡ ሁሉንም ጥያቄ ማስተናገድ ከባድ ነው፡፡ መጠገን የምንችላቸውንና የትኞቹን ማስቀደም እንደሚገባ፣ የትኞቹ ቅርሶች ጥገና በመንግሥት አቅም ይሸፈናል፣ የየትኞቹስ በውጭ ደጋፊ አካላት ይሸፈናል፣ የትኛውስ በሕዝብ አቅም ይሸፈናል የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ላይ ክፍተት አለ፡፡ በስትራቴጂ መመለስ ያለባቸው ናቸው፡፡ አንዳንዱ ከኅብረተሰቡ አቅም በላይ ላይሆን ስለሚችል መፈታት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በባህር ዳር ከተካሄደው የአስጎብኝ ድርጅቶችና የአካባቢ አስጎብኝዎች ውይይት ወቅት ከተነሱ በርካታ ነጥቦች አንዱ የንፅህና ጉዳይ ነው፡፡ የሰሜን ተራሮችን የሚጎበኙ ቱሪስቶች የሚጥሏቸው ቆሻሻዎችና የምግብ ትራፊዎች ጭላዳዎቹና ቀይ ቀበሮዎቹ እየተመገቡ ነው፡፡ በመሆኑም ችግር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ይደረግ ሲሉ የአስጎብኝ ድርጅች ያነሱት ሥጋት ነበር፡፡ በጣና ሐይቅ የተከሰተው እምቦጭ አረም መነሻው ከብክለት እንደሆነም እየተነገረ ስለሆነ፣ ከቱሪዝም አኳያ በዚህ መስክ ምን ይታሰባል?

ወ/ሮ መዓዛ፡- በሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ስለተነሳው ጉዳይ በአካል ሄደን ለማረጋገጥና ለማየት እንፈልጋለን፡፡ ችግሩ ካለም በቅንጅት መፈታት ይኖርበታል፡፡ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊን ጨምሮ እኔና ሌሎችም ወደ ፓርኩ በመሄድ እንጎበኛለን፡፡ የችግሩ ስፋት ምን ያህል ነው? የሚለውን ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ጣናም ላይ ጥናት መደረግ አለበት፡፡ ምን መደረግ አለበት ለሚለውም በጥናት ችግሩን መለየትና ማወቅ ግድ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በአስተሳሰብ ደረጃ ስለንፅህና ስንነጋገር ከቤታችን፣ በዙሪያችን ከምናየው ነገር ተነስተን አስተሳሰብ ላይ ለውጥ ሊኖረን ይገባል፡፡ ከቱሪስቱ በፊት እኛው ነን ንፁህ መሆን የሚገባን፡፡ ቤታችንን ማንፃት፣ ልጆቻችንን ስለንፅህና ማስተማርና አካባቢያችንን ማፅዳት ግድ ይለናል፡፡ በጋራ ስንተባበር ነው ይህ ሁሉ የሚሆነው፡፡ የንፅህና ጉዳይ የትም ቦታ የሚታይ ነው፡፡ ጥሩ ሕንፃ ሠርተው ውስጡ ሲገባ ግን ሌላ ነገር ይታያል፡፡ አንዳንድ ቤት መግባት በጣም ከባድ ነው፡፡ መንገድ የወጣ ሰው የሆነ ቦታ ማረፍ ሲፈልግ የሚያየው ነገር የሚያሳቅቅ ነው፡፡ ቸግሮ እኮ አይደለም፡፡ አንዳንዴ ገጠር አካባቢ ይሻላል፡፡ ባለው ነገር በንፅህና ይጠቀማል፡፡ ከቱሪስቶች አኳያ በሰሜን ፓርክ የተነሳው ነገር በቀላሉ ማስተካከል የሚቻል ነው፡፡ የፕላስቲክ ውኃ መጠጫዎችን በየቦታው ጥለው እንዳይሄዱ መንገር ቀላል ነው፡፡ የተጠሙበትን ምግብ በአንድ በተወሰነ ቦታ ላይ እንዲያስቀምጡ ማድረግ ይቻላል፡፡ ወደ ፓርኩ ሲገቡ ቆሻሻ አጣጣልን ብቻም ሳይሆን፣ የእንስሳቱን ደኅንነት የሚረብሽ ነገር እንዳያደርጉ፣ ድምፅና ሌላውም ነገር ላይ ጥንቃቄ እንያደርጉ ማሳሰብ ይቻላል፡፡ ከቱሪስቱ በላይ ግን እኛ ዘንድ ያለው ችግር ነው መሠረታዊ ለውጥ የሚፈልገው፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝም ዘርፉ ላይ በርካታ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት የፓርኮች ህልውና አደጋ ውስጥ መግባቱን ስም በመጥቀስ በቱሪዝም ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ሲናገሩ ነበር፡፡ በፖለቲካ ግጭትና በአካባቢው ማኅበረብ የዕለት ጉርስ ፍለጋ ሳቢያ አደጋ ውስጥ የገቡ ፓርኮች አሉ፡፡ ሰሜን ፓርክ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዩኔስኮ የአደጋ መዝገብ ውስጥ እንደነበር ይታወሳልና ልናጣቸው የምንችላቸው ፓርኮች አሉ ወይ? ተለይተው አጣዳፊ ሥራ የተሠራባቸው ይኖሩ ይሆን?

ወ/ሮ መዓዛ፡- በፌዴራልና በክልል ደረጃ የምንከታተላቸው ፓርኮች አሉ፡፡ አብዛኞቹ ፓርኮች ከኅብረተሰቡ መኖሪያ አካባቢ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ጎን ለጎን ከኅብረተሰቡ ጋር የሚኖሩ ናቸው፡፡ መኖሪያ መንደሮች እየሰፉ በሄዱ ቁጥር የፓርኮቹ የመነካት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ አከባቢው ድርቅና በረሃ በሚሆንበት ጊዜ፣ ሰው የሚበላውና የሚጠጣው በሚቸግረው ጊዜ ወደ ፓርኮች ገብቶ የሚጠለልባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ መጋፋት የማንችለው የተፈጥሮ ክስተትም አለ፡፡ አንዳንዱ ፓርክ ውስጥ የገቡ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ውኃ ማግኘት ስላልቻሉና ድርቅ ስለሆነ በፓርክ ውስጥ መጠለል እንዳለባቸው ይጠይቃሉ፡፡ ወቅቱ ሲሻሻልና ዝናብ ሲመጣ የሚወጡ ነዋሪዎች አሉ፡፡ ሰው ሠራሽ አደጋም አለ፡፡ የእንስሳት አደንን እንደ ጀግንነት በመቁጠር ከሚደረገው ባሻገር፣ ሕገወጥ የእንስሳት አደንና ዝውውርም ለፓርኮች ሥጋት ነው፡፡ በተደራጀ መንገድ ዓለም አቀፍ ገጽታ ያለው የእንስሳት አካላት ዝውውር ይደረጋል፡፡ አንድ ኪሎ የዝሆን ጥርስ ስንት እንደሚሸጥ የታወቀ በመሆኑ ሥጋቱ ግልጽ ነው፡፡ በእኛ አገር ኅብረተሰቡ ብልህና አስተዋይ ስለሆነ ፓርኮችና የዱር እንስሳት በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ ፓርኮቻችን ኬንያ ሄደን፣ ታንዛንያ ሄደን ልናይ በምንችለው ልክ ሰፊ የዱር እንስሳት ጥበቃ የሚደረግበት የዳበረ ሥርዓት አለን ማለት አይቻልም፡፡

ሌላው መሠረታዊ ችግር የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው፡፡ ከፓርኩም ሆነ ከቱሪስቶች ከሚገኘው ነገር የጥቅም ተቋዳሽ ሲሆን፣ ሕዝቡ ራሱ ይጠብቀዋል፡፡ ሰሜን ፓርክ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ፓርኩ ከአደጋ መዝገብ የወጣው ኅብረተሰቡ ከአካባቢው መስተዳድር ጋር በመሆን መንከባከብ በመቻሉ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል፡፡ ፓርኩ አደጋ ውስጥ ከገባ ቱሪስቶች ሊገበኙ እንደማይሄዱ በማወያየት፣ በፓርኩ ውስጥ የሠፈሩ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ወጥተዋል፡፡ ከፓርኩ ወጥተው እንዲሰፍሩና ካሳ እንዲከፈላቸው ተደርጓል፡፡ በዚያ አካባቢ የምታገኘው ማንኛውም ሰው ይህንን ጉዳይ ያስረዳሃል፡፡ ኅብረተሰቡ ፓርኩ በመኖሩ ምክንያት ሊጎበኙ ለሚመጡ ቱሪስቶች በቅሎ በማቅረብ፣ ምግብ በማብሰል፣ አጅቧቸው ጥበቃ በማድረግና በመሳሰሉት ተጠቃሚ እየሆነ ነው፡፡ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚ በሆነ ቁጥር ፓርኮችን በባለቤትነት ስሜት ይጠብቃል፣ ይንከባከባል፡፡ ይህ በሌሎችም ፓርኮች ላይ መተግበር አለበት፡፡ ለምሳሌ ቱሪስቶች ሲመጡ ከሚከፈል ክፍያ ፓርኩ የሚያገኛቸው ገቢዎች አሉ፡፡ ከመቶው የተወሰነውን መጠን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ማዋል አለበት፡፡ በረቂቅ ደረጃ የሚገኝ የዱር እንስሳት ጥበቃ ማቋቋሚያ አዋጅና የትረስት ፈንድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጆች እየተዘጋጁ ነው፡፡ ከሚገኙ ገቢዎች እስከ 30 በመቶው ለማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲውሉ የሚሉ ረቂቅ ይዘቶች አሏቸው፡፡ የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት በሕግም ረገድ ዋስትና እንዲያገኝ ብለን እያዘጋጀነው ያለ ሕግ ነው፡፡ ሌላው ችግር በአንድ ክልል ብቻ የማይተዳደሩ አዋሳኝ ፓርኮችም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ በባህር ዳር መወያያ የነበረው የሆቴሎች ምደባ ሁለተኛው ምዕራፍ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረገው ምደባ ከ350 በላይ ሆቴሎች ተመዝነዋል፡፡ የተወሰኑትም ውጤታቸውን አውቀዋል፡፡ በአዲሱ ምደባ ወቅት ምን ያህል ሆቴሎች ናቸው ደረጃ የሚያገኙት? ባለፈው ተመዝነው ውጤት ያላወቁትስ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን አጠቃላይ ሁኔታውን ቢገልጹልን?

ወ/ሮ መዓዛ፡- የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ጠቀሜታዎች ከሆኑት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን፣ ዘርፉ ዘመናዊ እንዲሆን፣ ተገቢውን አገልግሎት ለዜጎችም ለቱሪስቶችም ለማቅረብ እንደሚያስችል በዝርዝር አብራርተናል፡፡ ከዚህ ቀደም የተደረገው የሆቴሎች የደረጃ ምደባ በውጭ ዜጎች የተደገፈ ነው፡፡ የአሁኑ ግን በራሳችን የሰው ኃይል የሚደረግ ነው፡፡ 50 የሠለጠኑ ባለሙያዎች አሉን፡፡ ብንሳሳትም፣ ብንወድቅም ከራሳችን በመማር ማጎልበት ይኖርብናል፡፡ ይህም ሲባል በቀጥታ ወደ ምዛና መግባት ሳይሆን የዘርፉን ተዋንያን በማወያየት ነው የጀመርነው፡፡ ያሉት መልካም ነገሮችና መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው ለሚለው መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባና በባህር ዳር ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በሐዋሳና በመቀሌም የሚደረጉ አሉ፡፡ ይህንን ማድረግ ያስፈለገው ዘርፉ በምክክር መመራት ስላለበት ነው፡፡ ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መሥፈርት ብቻ መመደብ ስለማይገባ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ባለድርሻ የሆኑ ሆቴሎች፣ ማኅበራትና ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ እኛም በሚገባ አዳምጠን ተገቢውን ዕርምጃ በመውሰድ ለደረጃ ምደባው መሥፈርት ማውጣት አለብን፡፡ አሁን ይህን ያህል ሆቴል ይመዘናሉ ማለት ያስቸግራል፡፡ አዳዲስ ሆቴሎች ተሠርተዋል፡፡ ከዚህ በፊት ደረጃ ያላገኙ ነገር ግን ለምዘና የሚያበቃ ማሻሻያ ያደረጉ ሆቴሎችም ይመዘናሉ፡፡ ቀደም ሲል በተቀመጠው መሥፈርት ሳያሻሽሉ ቀርተው አሁን ያሻሻሉ ካሉም በድጋሚ ምደባ ይወጣላቸዋል፡፡ ደረጃ ተሰጥቷቸውም በተባለው መሥፈርት ያልተገኙትም በተመሳሳይ ምደባ ይደረግባቸዋል፡፡

ለምሳሌ ሆቴሎች በሙያው በሠለጠኑና በተማሩ ሰዎች መመራት እንዳለባቸው ከተቀመጡት መሥፈርቶች አንዱ ነው፡፡ ይህ ስለተባለ ግን አንዱ ሥራ አስኪያጅ ሦስት አራት ቦታ እየሄደ ልክ እንደ ሆቴሉ ባልደረባ ራሱን ካቀረበ ራስን ማታለል ነው፡፡ እንዲህ ያለው ጉዳይ በውይይቱ ወቅት ሲነሳ ነበር፡፡ ይህ ተገቢ ስላልሆነ በዚህ ረገድ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓታችንን እናጠናክራለን፡፡ ይሻሻሉ የሚሏቸውን ነጥቦች በመውሰድ፣ መመዘኛው ማየት ካለብንም እንደገና የመከለስና ደረጃ የሚመድቡ ሰዎችንም ማጠናከር ይገባናል፡፡ እንዳለፈው ምዘናውን ያከናወነው አካል በቀጥታ ወደ ሚኒስቴሮቹ ውጤቱን መላክ ሳይሆን፣ በመሀል ዳኝነት የሚሰጡና ውጤቱን የሚገመግሙ አካላት የሚያዩበት አደረጃጀት ይፈጠራል፡፡ ይህ እንግዲህ አንዱ የሠራውን ሌላኛው መቆጣጠር የሚችልበት አሠራር እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡ በቻልነው መጠን ሒደቱን ግልጽና አሳታፊ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከገቢ አኳያ እርስዎ ‹‹የሰይጣን ጆሮ›› ይደፈን እንጂ ዘንድሮ ጥሩ እንቅስቃሴ አለ ብለው ነበር፡፡ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች ግን አሉ፡፡ በአንዳንድ ክልሎች ከውጭ ቱሪስት ይልቅ የአገር ውስጥ ጎብኝው ከፍተኛ ቁጥር እንዳለው መረጃቸውም ያሳያል፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከጎበኙ 3.5 ሚሊዮን ቱሪስቶች ውስጥ የውጭ 26 ሺሕ ያህል ቱሪስቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ አኃዙ እንዴት ነው የሚዘጋጀው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- መረጃውን የምንወስደው ከኢሚግሬሽንና ከዜግነት ጉዳዮች መሥሪያ ቤት ነው፡፡ በአየርም ሆነ በየብስ የሚገቡ ሰዎች የቪዛ ሒደቱን አልፈው ነው የሚገቡት፡፡ በዚህ መነሻነት መረጃውን ብንመዘግብም ድግግሞሽ እንዳይፈጠር እንጠነቀቃለን፡፡ ለምሳሌ አንተ የተለያየ ስልክ ቁጥር ቢኖርህና የተለያየ ቦታ ብትጎበኝ በድጋሚ የመቆጠር ዕድል አለህ፡፡ ይህንን ለማስቀረት ነው ከኢሚግሬሽን መረጃው የሚሰበሰበው፡፡ አለበለዚያ አንድ ቱሪስት ፋሲል ሲሄድ ይቆጠርና መልሶ ወደ ኦሞ ሲሄድም ስለሚቆጠር፣ ያንን ድግግሞሽ ለማስቀረት ነው ከመነሻው ከኢሚግሬሽን መረጃው የሚወሰደው፡፡ ክልሎች ግን ክልላቸውን የጎበኘውን ሁሉ ስለሚቆጥሩ አንዱ ቱሪስት ብዙ ጊዜ የመመዝገብ ዕድል አለው፡፡ በዓለም የቱሪዝም ድርጅት ትርጓሜ መሠረት ቱሪስት ማለት ማን ነው የሚለውን የሚያሟሉ ሰዎች ናቸው በቱሪስትነት የሚመዘገቡት፡፡ በዚህ አግባብ ከተለዩ በኋላ ሳይንሳዊ ቀመር አለን፡፡ የቱሪዝም ገቢው በዓለም ቱሪዝም ድርጅት ሳይንሳዊ መሥፈርት መሠረት ተዘጋጅቶ ለዚሁ ተቋም ብቻም ሳይሆን፣ ለዓለም ባንክም ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ የቱሪስቱ ቀጥር በጣም ጨምሯል፡፡ ይህንን በተለያየ መንገድ ማረጋገጥ ትችላላችሁ፡፡ አሁን ዝቅተኛ የቱሪስት ቁጥር የሚመዘገብበት ወቅት ቢሆንም፣ አስጎብኝ ድርጅቶች ከፍተኛ ቁጥር እያስተናገዱ እንደሚገኙ፣ መዳረሻ አካባቢዎችንም ስናጣራ በጣም በርካታ ጎብኝዎችን እያስተናገዱ እንደሚገኙ በራሳችሁ ልትደርሱበት ትችላላችሁ፡፡