Skip to main content
x

የውጭ ጉዲፈቻ ሲቀር የአገር ውስጥ ጉዲፈቻን መጨመር ታስቦ ይሆን?

በኢዮብ ጌታሁን

ወደ አሜሪካ ብቻ ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ 15,000 ኢትዮጵያዊ ልጆች በጉዲፈቻ ልጅነት ተወስደዋል፡፡ ወደ አሜሪካ በማደጎ ልጅነት ከሚገቡ መቶ ሕፃናት 20ዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 እና በ2011 ብቻ 1,200 ኢትዮጵያዊ ሕፃናት በስፔይን አሳዳጊዎች ዕቅፍ ወደ አውሮፓ ተወስደዋል፡፡ እነዚህን ቁጥሮች ስናይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወላጅ አልባ ሕፃናት ላሉባት አገር ጥቂት አድርገን ልናስብ እንችል ይሆናል፡፡ ግን እነዚህን ልጆች በሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ብናሳድጋቸው የሚወጣው ወጪ እጅግ ከባድ እንደሚሆን መገመት አይከብድም፡፡ ከሕፃናት ማሳደጊዎች ከወጡስ በኋላ ልጆቹ መልካም ዜጋ ይሆናሉ ወይ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ በአብዛኛው አሉታዊ ቢሆን መደነቅ አይኖብንም፡፡ ምክንያም እነዚህ ልጆች የወላጅ ወይም የአሳዳጊ የቅርብ ክትትል እያገኙ አያድጉም፡፡ 

ሰሞኑን ኢትዮጵያውን ልጆች በጉዲፈቻ ወደ ውጭ አገር እንዳይሄዱ የሚከለክለው ሕግ መፅደቁ ተሰምቷል፡፡ በአንድ ወቅት በአንድ ኢትዮጵያዊ ልጆችን ከጉዲፈቻ አሳዳጊዎች ጋር የሚያገናኝ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ እሠራ ነበር፡፡ በሕፃናት ማሳደጊያው ያደጉ የምቀርባቸው ልጆች ደግሞ አሉ፡፡ ከእነዚህ ልምዶቼ በመነሳት አንድ ነገር ለማለት ስለወደድኩ ነው ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ የተነሳሁት፡፡

የውጭ ጉዲፈቻ በልጆች ላይ የሚያመጣው ችግር ምንድነው? ከባህላቸውና ከሕዝባቸው ርቀው ማደጋቸው የሚፈጥረው ችግር አንዱ ነው፡፡ ብዙዎቹ በነጭ አሳዳጊዎች በማደጋቸው ልዩ መሆናቸውን ገና በልጅነታቸው እየተረዱት ማደጋቸው ይህን ችግር ይፈጥራል፡፡ ልጁ ያለ እነሱ ዕርዳታ መኖር እንደማይችል፣ የመጣልና የመተው ስሜት እንዲሰማው አድርገው በማሳደግ በአንዳንድ አሳዳጊዎች የሚፈጸም ሥነ ልቦናዊም ጉዳትም አለ፡፡ እጅግ አልፎ አልፎ የሚከሰት አካላዊ ቅጣት አንዳዴም እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት በውጭ አሳዳጊዎች ይፈጸማል፡፡ በመጨረሻ ወንጀላቸው ሲታወቅ በሕግ መቀጣታቸው አይቀሬ ቢሆንም፡፡ ሌላውና የውጭ ጉዲፈቻን ተከትሎ የመጣው እጅግ አሳፋሪ ወንጀል ደግሞ የጉዲፈቻ ልጆችን ከአሳዳጊዎች ጋር የሚያገናኙ ድርጅቶች ሠራተኞች ሥራውን እንደ ቢዝነስ ማየታቸው የሚፈጥረው ነው፡፡

እነዚህ ሰዎች ስለውጭ ኑሮ የተጋነኑ እውነታዎችን በመንገርና የልጁን ወላጅ/ወላጆች ወይም ዘመዶች በማሳመን አገር ውስጥ ማደግ የሚችለውን ልጅ ያላግባብ ወደ ውጭ እንዲወሰድ ማድረጋቸው ነው፡፡ በዚህ መልኩ በመቶዎች ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት በየዋህ ወይም በራስ ወዳድ ወላጆቻቸው ውሳኔ ምክንያት በፈረንጆች አሳዳጊዎች ለማደግ ተገደዋል፡፡ የኢትዮጵያዊ ሕፃናት ወደ ውጭ በብዛት መጉረፍ፣ “አገሪቷ ልጆቿን ማሳደግ አቅቷታል” የሚል አንድምታ ስላለው፣ መንግሥትንም ብዙ የሚያስደስት አይደለም፡፡ በእነዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች ነው ሕጉ እንዲፀድቅ የተደረገው ብዬ አምናለሁ፡፡

ኢትዮጵያዊ ልጆችን ከጉዲፈቻ አሳዳጊዎች ጋር የሚያገናኝ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ስሠራ የሌላ አገር ዜግነት ባላቸው የጉዲፈቻ አሳዳጊዎች ወደ ውጭ የሚወሰዱ ሕፃናት፣ ብዙ ፍቅርና ትኩረት ከአሳዳጊዎቻቸው እያገኙ እንደሚያድጉ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ አሳዳጊዎቹ ልባዊ ፍቅር እንኳን ለልጆቹ ባይኖራቸው የበለፀጉ አገሮች ሕዝቦች ሕግ አክባሪ በመሆናቸውና አገሮቹም የሕግ የበላይነት በተግባር የተረጋገጠባቸው ስለሆኑ ሕጉ ለልጆቹ ጥበቃ ያደርግላቸዋል፡፡

እኔ እሠራበት የነበረው ድርጅት በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሠራ ስላልሆነ፣ ለጉዲፈቻ አሳዳጊ ልጆቻቸውን ከሰጡ ኢትዮጵያዊ እናቶች መካከል የአንዷ ልጅ አሳዳጊዎች ለእናቷ እንዳቀብል ስለልጅቷ በየዓመቱ ፎቶግራፎችና መረጃ በኢሜይል ይልኩልኛል፡፡ ልጅቷ በጉዲፈቻ ስትወሰድ የሁለት ዓመት ልጅ ነበረች፡፡ አሁን የአሥር ዓመት ልጅ ሆናለች፡፡ በጉዲፈቻ የሚያሳድጓት የዩኒቨርሲቲ መምህራን የሆኑ ጥንዶች ናቸው፡፡ እኔ እንደተረዳሁት ልጅቷ በዕድሜ ደረጃዋ ማግኘት ያለባትን ትምህርትና ሥልጠና በተሟላ መልኩ እያገኘች በፍቅር እያደገች ነው፡፡ ከመደበኛ ትምህርት ቤት ማግኘት ካለባት ውጪም ተጨማሪ ትምህርቶችን ተምራለች፡፡ ለምሳሌ የዋና፣ የባሌ ዳንስ፣ የጂምናስቲክና የሙዚቃ መሣሪያዎችን የመጫወት የመሳሰሉ ሥልጠናዎችን እንድታገኝ አድርገዋል፡፡ በቀለም ትምህርቷም በቅርበት ስለሚከታተሏት ጎበዝ ነች፡፡ በበኩሌ ብዙዎቹ የጉዲፈቻ አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን በፍቅርና በእንክብካቤ እንደሚያሳድጉ አምናለሁ፡፡ ከጉዲፈቻ ልጆቻቸው ጋር የሚያገናኛቸው በአገራቸው ያለው ድርጅት፣ ልጆቹ 18 ዓመት እስኪሞላቸው ዓመታዊ መረጃ እንዲልኩ አሳዳጊዎቹን ያስገድዳል፡፡ በየዓመቱ ወደ አሳዳጊዎቹ ቤት እየሄዱ ልጁ ወይም ልጅቷ ያለችበትን ሁኔታ በአካል ተገኝተው የሚያረጋግጡ ድርጅቶችም አሉ፡፡

ከላይ እንደጠቀስኩት ለአንድ ሕፃናት ማሳደጊያ ባለኝ ቅርበት፣ በሕፃናት ማሳደጊያው የሚያድጉና ከማሳደጊያው የተሸኙ በርካታ ልጆች ያሉበትን ሁኔታ አውቃለሁ፡፡ ብዙዎቹ ውድ ትምህርት ቤት ቢላኩም ትምህርታቸውን በሥርዓቱ አይከታተሉም፡፡ ከ50 ልጆች አንዱ ለዩኒቨርሲቲ ከበቃ እንደ ትልቅ ተዓምር ይቆጠራል፡፡ ልጆቹ የተመጣጠነ ምግብ፣ በቂ ልብስ ተሟልቶላቸው፣ ጥሩ ቤት ድርጅቱ ተከራይቶላቸው ይኖራሉ፡፡ በሕፃንነታቸው ሞግዚት፣ ካደጉም በኋላ ምግብ አብሳይ ሠራተኛና የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሙያ (ሶሻል ወርከር) ተቀጥሮላቸው ቢኖሩም፣ በመጨረሻ ውጤታማ ዜጎች ለመሆንና ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅሎ ለመኖር የሚቸገሩ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ልጆች ከወላጅ ወይም ከአሳዳጊ የሚገኘውን ልዩ ትኩረትና ፍቅር ሳያገኙ የሚያድጉ ናቸው፡፡ ሞግዚቶቻቸው ምንም መልካም ቢሆኑ የወላጅ ወይም የአሳዳጊን ያህል ትኩረትና ፍቅር ሊሰጧቸው አይችሉም፡፡ ለብዙዎቹ ሞግዚቶች ሕፃናቱን መንከባከብ ሥራ ነው፡፡ ወላጅ ወይም አሳዳጊ ከሚሰማው በእጅጉ ያነሰ ኃላፊነት እንደሚሰማቸው ግልጽ ነው፡፡ ወላጅ ወይም አሳዳጊ የሚሰጠውን ፍቅር በሰፊውና በጥልቀት ሊሰጡ አይችሉም፣ ምክንያቱም ልጆቹ ብዙ ናቸው፡፡ 

እነዚህን ልጆች ለማሳደግ በድርጅቱ የሚወጣው ወጪ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ አንድ መልካም እውነታ ግን እነዚህ ልጆች በሙሉ በቤተሰባቸው ማደግ ያልቻሉ፣ ወላጅ አልባ የሆኑና በትክክልም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸው ነው፡፡    

ሕጋዊ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ በአገራችን የለም ማለት ይቀላል፡፡ የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ኅብረት (ሲሲአዲኤ) በቅርቡ ባዘጋጀው የመልካም ተሞክሮ ውድድር ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የመገኘት ዕድል አጋጥሞኝ ነበር፡፡ በውድድሩ ለወላጅ አልባና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሕፃናት ድጋፍ በሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ውድድር በአንደኝነት ያሸነፈው ቤተኒ ክርስቲያን ሰርቪስስ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት የተሸለመው፣ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻን ለማስፋፋት ባከናወነው ጅምር ሥራ ነው፡፡ ቤተኒ “ፎስተር ቱ አዶፕት” በሚለው ፕሮጀክቱ፣ በመጀመሪያ ልጆቹን በአደራ ለአሳዳጊዎቹ ይሰጣል፡፡ አሳደጊዎቹ ልጆቹን የአደራ አሳዳጊ (ፎስተር ፓረንት) ሆነው ለተወሰነ ጊዜ ይንከባከቡና ልጆቹን በጉዲፈቻ ልጅነት ለመቀበል ካመኑበት፣ በፍርድ ቤት ሕጋዊ ሒደቱን በድርጅቱ በኩል አጠናቀው ልጁን ወይም ልጅቷን የጉዲፈቻ ልጅ ያደርጋሉ፡፡ የጉዲፈቻ ልጅ የሆነ ሕፃን ሙሉ የልጅነት መብት፣ ሀብት እስከ መውረስ ድረስ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ቤተኒ ባለፉት ስድስት ዓመታት በብዙ ጥረት ለአደራና ለጉዲፈቻ ልጅነት ያበቃቸው 184 ሕፃናት ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሕፃናት 70 ገደማ የሚሆኑት በአደራ ልጅነት የተሰጡ ናቸው፡፡ አሳዳጊዎቻቸው ገና ልጆቹን የጉዲፈቻ ልጅ ለማድረግ አልወሰኑም ማለት ነው፡፡

ብዙዎች ኢትዮጵያዊ አሳዳጊዎች የሚጨነቁት ስለውርስ ጉዳይ ነው፡፡ አዘውትሬ ባልከታተለውም በቃና ቴሌቪዥን የሚታየው “ሽንቁር ልቦች” የተባለ ፊልም ላይ ካንሱ የተባለችው ልጅ የሥጋ ወላጆቿ ባልሆኑ ጥንዶች እንዳደገች እናያለን፡፡ ግን የሥጋ ልጃቸውን ካወቁና ካገኙም በኋላ ሁለቱ ጥንዶች ለካንሱ ያላቸው ፍቅር ቅንጣት ሲቀንስ አናይም፡፡ መቼም ፊልሙ ልብወለድ ቢሆንም፣ ልብወለድ የገሀዱ ዓለም ነፀብራቅ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በአገራችንም “መወለድ ቋንቋ ነው” እንደሚባለው በእርግጥም ያሳደግናትንና በቅርብ የምናውቃት ልጅ ብንወድ አይገርምም፡፡ ግን አሁንም ኢትዮጵያውያን አሳዳጊዎች ከሥጋት የተላቀቅን አንመስልም፡፡ ልጁ በሕግ የጉዲፈቻ ልጅ ከሆነ በኋላ፣ ወላጅ እናቱ ወይም አባቱ አቅሙ ኖሯቸው ማሳደግ ቢፈልጉ እንኳን ልጁን እንዲወስዱ አይፈቀድላቸውም፡፡ ልጁን ከወላጆቹ ጋር እንዲገናኝ እየፈቀዱ እንዲሳድጉ ቢመከርም፣ አሳዳጊ ወላጆች እንዲገናኝ ካልፈለጉም ወላጆቹን መከልከል መብታቸው ነው፡፡ ቁልፉ ነገር ፍቅር ነው፡፡ የአሳዳጊዎቹን ሙሉ ፍቅር እያገኘ ያደገ ልጅ ወላጆቹን ቢያውቅም፣ አሳዳጊዎቹን ከመውደድና የእነሱ ልጅ ከመሆን ወደኋላ አይልም፡፡   

በደንብ የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም በዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ በዓመት እስከ አምስት ሺሕ ኢትዮጵያዊ ሕፃናት ወደ ውጭ ይሄዱ ነበር፡፡ ቤተኒ ክርስቲያን ሰርቪስስ ከስድስት ዓመት ጥረት በኋላ ባለፈው አንድ ዓመት 44 ልጆችን በአደራና በጉዲፈቻ ልጅነት በዓመት መስጠት በመቻሉ እንደ ትልቅ ስኬት ቆጥሮታል፡፡ ምክንያቱም በቀደሙት አምስት ዓመታት በዓመት በድርጅቱ በኩል በኢትዮጵያዊ አሳዳጊዎች ከሕፃናት ማሳደጊያዎች የሚወሰዱ ልጆች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነበር፡፡

በውጭ ዜጎች ኢትዮጵያውያን ልጆች በጉዲፈቻ ልጅነት እንዳይወሰዱ የሚከለክለው ሕግ ሲፀድቅ ሁለት ትልቅ ክፍተቶችን ይሉት ይመስላል፡፡ አንዱ የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን “ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” እንደሚባለው፣ በውጭ ዜግነታቸው ምክንያት ኢትዮጵያዊ ልጅ በጉዲፈቻ እንዳያሳድጉ መከልከላቸው ሲሆን፣ ሌላው በአገር ውስጥ ኢትዮጵያውያን አሳዳጊዎች ልጆችን በጉዲፈቻ ልጅነት እንዲያሳድጉ በመንግሥትና በሌሎች አጋዥ አካላት የሚሠራው ሥራ እጅግ ደካማ በሆነበት ሁኔታ ሕጉ መፅደቁ ነው፡፡

አገሪቷ ወላጅ አልባ ልጆችን በሕፃናት ማሳደጊያዎች ውስጥ ለማሳደግ በቂ ሀብት የላትም፡፡ ቢኖራትም በዚህ መልኩ ማደጋቸው ለሕፃናቱ ጥሩ አይደለም፡፡ እጅግ የተሻለው አማራጭ በጉዲፈቻ ልጅነት በኢትዮጵያውን ቤተሰቦች ውስጥ ማደጋቸው ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ግን ምን ተሠርቷል? ሚዲያ ላይ የጎላ የቅስቀሳና የማበረታታት ጥረት ሲደረግ አይታይም፡፡ ብዙ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ ሕፃናትን የራሳቸው አድርገው ማሳደግ እንደሚችሉ ማወቃቸውን በበኩሌ እጠራጠራለሁ፡፡ ሕጉ የውጭ ጉዲፈቻን በር ሲከረችም፣ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ በር ወለል ብሎ እንዲከፈት ቀደም ብሎ ሥራ ተሠርቶ ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ይህንኑ ሸክም ባሉበት ሆነው እንዲጋሩ መፈቀዱም አስፈላጊና ጠቃሚ ይሆን ነበር፡፡ እንግዲህ ቀሪዎቹ ሥራዎች ወደፊት እንደሚሠሩ ተስፋ እናድርግ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡