Skip to main content
x

የሚያለያዩንን እንለያቸው

በሳሙኤል ረጋሳ

የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት የምንችለው በአንድ ባሰብነው መንገድ ብቻ በመጓዝ ላይሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴ በተለያየ መንገድ ተጉዘን ሁላችንም አንድ ቦታ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ያሰብነው ሳይሆን መንገዶቹ ሄደው ሄደው ሳይገናኙ ይቀሩና በተለያየ አቅጣጫ ነጉዶ መቅረትም አለ፡፡

ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የተለያዩ የፖለቲካ አካላት ለአገሪቱ ይበጃሉ ብለው ያሰቡትን የተለያዩ መንገዶች ተከትለው ሲታገሉ ኖረዋል፡፡ በትግሉ ሒደት ውስጥ የማሸነፍ ዕድል የገጠማቸው የሚያምኑበትን ወይም የሰሙትን የፖለቲካ ርዕዮት ተከትለው አገሪቱን ለማሳደግ በሚል እሳቤ፣ መንግሥታቸውንና ሥልጣናቸውን ለማስቀጠል ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ ሕዝቡ ኑሮዬን የለወጠ ዕድገት አይቼአለሁ፣ ተከታታይ የሆነ አስተማማኝ ሰላም ወርዷል፣ መብቴ ተከብሯል፣ ወዘተ ያለበት ጊዜ የለም፡፡ ይኼ ሊሆን ያልቻለው በዋነኛነት ሕዝቡ ተወያይቶና ተስማምቶ ይበጀኛል ያለውን አቅጣጫ ለመንግሥት የጠቆመበትና መንግሥትም የሕዝቡን የልብ ትርታ አዳምጦ የሄደበት ወቅት ያለመኖሩ ነው፡፡

 ሕዝብና መንግሥት በተለያየ መንገድና በተለያየ አቅጣጫ ነው የሚነጉዱት፡፡ ዋናው የዴሞክራሲ ዕጦት መገለጫም ይኼ ነው፡፡ መንግሥት ያመነጨው ሕግ፣ ያዋቀረው መስተዳድር፣ የቀየሰው ልማት፣ ወዘተ ብቻ ናቸው በተግባር ላይ የሚውሉት፡፡ ሕዝብ ለራሱ የሚበጀውን ራሱ በፈለገው አቅጣጫ ማስኬድ አልቻለም፡፡ የረዥሙን ጊዜ ትተን አሁን ያለንበትን ሁኔታ ለማየት እንሞክር፡፡

አገራችን እስከ ኢሕአዴግ ዘመን ድረስ ጥብቅ በሆነ አሀዳዊ መንግሥታት ሥር ስትተዳደር ኖራለች፡፡ በእነዚህ ዘመናት የኢትዮጵያ አንድነት ማለት ወደ አንድ ጫፍ የተጠጋ በመሆኑ፣ የብሔር ጭቆናን ማንሳት በኢትዮጵያ አንድነት ላይ እንደመዶለት ተቆጥሮ በሕይወት ጭምር ዋጋ የሚከፈልበት ነበር፡፡

ኢሕአዴግ በኃይል ሥልጣን ከያዘ በኋላ አገሪቱን ከዚህ ዓይነት አሀዳዊ ሥርዓት አውጥቶ በፌዴራል ሥርዓት እንድትተዳደር አድርጓል፡፡ በጥሬው የፌዴራሊዝምን ሥርዓት በገሃድ የሚቃወሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለጊዜው በአደባባይ የታዩ ወይም የሚታወቁ የሉም፡፡ ለፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ይሁንታ ያልሰጡትም ቢሆኑ በአተገባበሩ ላይ ሊታረቁ የማይችሉ በሚመስሉ ሁለት ጎራዎች ተከፍለው በከባድ የገመድ ጉተታ ጨዋታ ተጠምደዋል፡፡

የመጀመርያው ወገን ኢሕአዴግ በፊታውራሪነት የሚመራው የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ነው፡፡ ይኼውም የብሔር ብሔረሰብን መብት በማስቀደምና ብሔር ብሔረሰቦችን በፖለቲካ በማደራጀት ቋንቋን ማዕከል ያደረገ የግዛት ክልልን መፍጠር ነው፡፡ ኢትዮጵያም መፈጠር ወይም መኖር የምትችለው የእነዚህ ክልሎች ሁለንተናዊ መብት ተከብሮ፣ እነሱ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ሲፈጥሩ ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ እያንዳንዱ ክልል ተገንጥሎ የራሱን መንግሥት ሊያቋቁም እንደሚችል ሕገ መንግሥታዊ መብት ጭምር ሰጥቶአቸዋል፡፡

ሁለተኛው ወገን ደግሞ ኢትዮጵያ በየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ዓይነትም ቢሆን፣ በዘመናት እልህ አስጨራሽ ትግል አሁን ያለችበትን ቅርፅና ማኅበረሰብ ይዛ የኖረችና ያለች አገር ናት፡፡ በመሆኑም ይህችን አገር አንድነቷንና ዳር ድንበሯን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በነበረበት እንዲቀጥል ማድረግና የብሔር ብሔረሰቦችን መብት በተመለከተ፣ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ መደራደር እንደሚቻል የሚገልጽ ሐሳብን የሚያራምድ ነው፡፡

አሁን በብሔር ብሔረሰብ የተዋቀረውን ክልላዊ አስተዳደርም በመቃወም፣ የግዛት ወሰን መቀመጥ የሚገባው እንደየቀረቤታቸው ሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ በማመሳጠር በተፈጥሮአዊ አከላከል (በወንዝ፣ በተራራ፣ በሸለቆ በመሳሰሉት) በማካለል ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ አሁን አገሪቱ ሰለም አጥታ እየተናጠች ያለችው ልዩ ልዩ የማስዋቢያና የማሳመሪያ ምክንያት ካልጨመርንበት በስተቀር ዋናው ጉዳይ የእነዚህ ሁለት ጎራዎች አራማጅ ክፍሎች ልዩነት ነው፡፡ አሁን በአገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ትኩሳት ከዚህ የተለየ አይመስለኝም፡፡ ካለም መጨመር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ወደ መግባባት ለመድረስ የሚለያዩንን መለየት ግድ ስለሆነ ነው፡፡ በእርግጥ የመንግሥት ለውጥ ማምጣትንም እንደ አማራጭ የሚያቀርቡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይኼኛው አስተሳሰብ ፍሬ እንጂ ዘር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ መነሻቸው ከሁለቱ አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ጽንፎች አሁን ያለውን ያለመረጋጋት ፈጥረዋል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ነገሩን በዝርዝር ለማየት የሚከተሉት ሁለት ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው፡፡

  1. ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማስቀጠል የግድ የብሔር ብሐረሰቦች መብት ሙሉ በሙሉ መከበር ቅድመ ሁኔታ መሆን አለበት ወይ?
  2. ኢትዮጵያን እንደ አገር ማስቀጠል የሚቻለው የግድ እስከ ዛሬ እንደነበረው የአገሪቱን ክልሎች በመሉ በኃይል ጨፍልቀን የብሔር ብሔረሰቦችን መብት በሁለተኛ ደረጃ አውርደን መሆን አለበት?

ለኢትዮጵያ አንድነት የብሔር ብሔረሰቦች መብት መቅደም አለበት ብለን ከተነሳን መንገዱ አሁን ያለንበት ጉዞ ነው፡፡ ይኼንን በተጨባጭ ስናየው ደግሞ ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት አብዛኛው ክልልና ብሔር ብሔረሰቦች መብቴ ተጠብቆልኛል የሚሉ ሳይሆኑ፣ በተቃራኒው ልዩ ልዩ ተጨማሪ ጥያቄዎችን እያቀረቡና ምሬቱም እየጨመረ ነው የሄደው፡፡ ከመብት ጥያቄም አልፎ በብሔረሰቦች መካከል ቅራኔን እየፈጠረ ሕዝቡ በጥላቻ ዓይን እየተያየ ነው ያለው፡፡ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በሱማሌ…መካከል በቅርብ የተከሰቱትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በእርግጥ እነዚህን ችግሮች ኢሕአዴግ የሌላ ሦስተኛ ወገን ችግር አድርጎ ነው የሚያየው፡፡ ግፋ ቢል ወደ ራሱም የሚያመጣው ከሆነ ከፖሊሲ ጋር ሳይሆን የሚያያዘው የግለሰቦች የአፈጻጸም ጉድለት ነው ባይ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች እንዴት ይታረማሉ ለሚለው ጥያቄም እስካሁን ተጨባጭና አሳማኝ የሆነ መልስ የለውም፡፡ ችግሮች እየፈጠጡና እያገጠጡ መጥተዋል፡፡ በሁሉም ክልል ሊባል በሚችል ደረጃ ምሉዕ የሆነ አስተማማኝ ሰላም የለም፡፡ ችግር ካልሆነበትና ግድ ካልሆነ በስተቀር ዛሬ ማንም ሰው ከራሱ ክልልና ብሔረሰብ ውጪ ሠርቶ ለመኖርም ሆነ ለሌላ በጊዜያዊነትም ሆነ በዘላቂነት ለመኖር አይፈልግም፡፡

 ዘመናዊና ሥልጡን አስተሳሰብ ይመነጭበታል፣ የሕዝቦች ነፃነትና መብት ይዘመርበታል፣ የወደፊት የአገሪቱ ተስፋዎችና ተረካቢዎች ይመረቱበታል፣ ተመራምረውና ተነጋግረው እነዚህን ችግሮች ይፈቱልናል ብለን ተስፋ የጣልንባቸው በመላ አገሪቱ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ዋና ዋናዎቹ የችግሮቹ መሥፈሪያ ሆኑ፡፡ በአገሪቱ አሉን የምንላቸው የፖለቲካና የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎችና ምሁራን ያሉበት ተቋማት ችግር ፈቺ ሳይሆኑ፣ ችግር ፈጣሪ ከሆኑ ለችግራችን የሚሆን መፍትሔ ከየት እንጠብቅ? ምናልባትም የውጭ አገር አምባሳደሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ችግራችንን የሚፈቱልን አካላት አድርገን ሳንቆጥር አልቀረንም፡፡ ይኼ ግን አይሆንም፡፡ በሁሉም ክልሎች ማለት በሚቻል ደረጃ የግለሰቦች ወይም የብዙዎች ሞት ከአስደንጋጭ ዜናነት አልፎ የተለመደ የዕለት ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ የተፈጥሮን ጫና መቋቋም አቅቶን በዓለም ላይ የምንታወቅበት የረሃብተኞች አገር መባል ሳያንሰን፣ መገዳደልንም ሌላው መለያችን ልናደርገው ነው፡፡

ሰላምን በማስከበር በጎረቤትና በዓለም አገሮች ዕውቅናን አትርፏል የተባለው የመከላያ ሠራዊት የራሱን አገር ሰላም ማስከበር ሳይችል ቀርቷል፡፡ በወንድማማች ሕዝቦችና በክልሎች መካከል የሚካሄደውን ሁከት፣ ሞትና መፈናቀልን ማስቆም ያለመቻላችን ግርምትን ፈጥሯል፡፡ በሌላ በኩል የተፈጠረውን ችግር መሠረት አድርገው ሕዝቡ በተለይ ወጣቱ ወደ ስሜት እንዲገባ ተጨማሪ ጥፋቶችን በየዕለቱ እንዲፈጽም የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎችና ግለሰብ መናፍቃን የጥፋትን ተልዕኮ በስፋት እየሰበኩ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግሥታትን በመቃወምም ሆነ በመደገፍ ወጣቶችን ስሜት ውስጥ እያስገቡ የተልዕኮዋቸው ማስፈጸሚያ የሚያደርጉ ክፍሎች፣ ሊመለስ ወደማይችል ጥፋትና በቀላሉ ሊቆም ወደማይችል ዕልቂት እየመሩን መሆኑን ለደቂቃም አንዘንጋ፡፡ በስሜታዊነት የሚካሄድ ትግል በአሸናፊነት ወጥቶ አያውቅም፡፡ በአብዛኛው ከቁጥጥር ውጭ ነው፡፡ “Mob is Mad” ይላል ፈረንጅ፡፡

በደርግ ውድቀት ማግሥት ኦሮሚያ ውስጥ ሕዝቡ ሲደርስበት የነበረውን ጭቆናና ብዝበዛ መሠረት አድርጎ በኦነግ አስተምህሮ ወጣቱ ከፍተኛ ብሔራዊ ስሜት ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ያለበቂ ዝግጅትና ዕውቀት ለትጥቅ ትግልም ጭምር ወደ በረሃ መግባት ተጀምሮ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ትግሉ ተጨባጩን የኦሮሞ ሕዝብ ችግር መሠረት አድርጎ የተፈጠረ ቢሆንም፣ ስሜታዊነት በጣም የተጫነው ስለነበር ምክንያዊነት ቦታ አልነበረውም፡፡ በምክንያት ሊሞግቱዋቸው የተነሱትንም እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ጠላት መፈረጅ ነበር፡፡ በወቅቱ የአማራን ሕዝብና ሌሎችንም በከፊል በጠላትነት የመፈረጅ አዝማሚያ ነበር፡፡ ያን ግድቡን ደርምሶ ወጥቶ አገርን ያጥለቀለቀ የመጠፋፋት ተልዕኮ በወቅቱ የፈጠረውን ድርጅትና ያደራጀውን ወጣት ኦነግ ጭምር መቆጣጠር አልቻለም፡፡ የዚያን ጊዜ በሌሎች ላይ ሲደረግ የነበረው ውግዘት ተወግዶ ዛሬ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ የጋራ የትግል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ግሩም ነው፡፡ ሁላችንንም ያስተምረናል፡፡ የትናንቱን ስሜታዊነት ዛሬ ከተማርንበት የዛሬውም ለነገ እንዲሁ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ጤና፡፡ አሁንም ስሜታዊነት በብዙ ቦታዎች ይታይሉ፡፡ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ሁሉም ነገር ሳይበላሽ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሊያስቡበት ይገባል፡፡

በተፃራሪው ጎዳና የሚሄዱት ደግሞ ሳንሸፋፍነው እንነጋገር ካልን ኢትዮጵያን እንደ አገር ማስቀጠል የምንችለው፣ ቀደም ሲል እንደነበረው የኢትዮጵያ ግዛቶች በሙሉ በውድም ሆነ በግድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አንድ ላይ ጨፍልቀን መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ይኼ ምንም አማራጭ ሳይኖር ወይም መሻሻል ሳይደረግበት እንደ በፊቱ መቀጠልን ለበርካታ ዓመታት ብዙዎቻችን ስናቀነቅነው ነው የኖርነው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ መጠነኛ መሻሻል ተደርጓል ቢባል ከንጉሣዊ ፈላጭ ቆራጭ አስተዳደር ወጥተን ወደማይታወቅ አቅጣጫ መጓዛችን ነው፡፡ አሁን የብሔር ብሔረሰብን የተሟላ መብት የመጠበቅና ያለመጠበቅ ጉዳይ የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ደረጃ ላይ አይደለም ወይ? ይኼ ደግሞ አብዛኛዎቻችን የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን ኢሕአዴግ ያመጣው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ነው ስንል ይሰማል፡፡ ነገር ግን የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲከ ማንም ያምጣው ከየትም ይምጣ በአገራችን ውስጥ ገዥ ሐሳብ ሆኖ አልወጣም ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው መመለስ ያለበት፡፡ በዚህ የምናምን ከሆነ ደግሞ በአገሪቱ የፖለቲካና የሰላም ጥያቄ ቦታ የሚነፈገው አይሆንም፡፡ ዝም ተብሎ በኅብረተሰብ ውስጥ የሌለ ጥያቄና መሠረት የሌለው ለማስመሰል ‹‹የጎሳ ፖለቲካ››፣ ‹‹የዘረኝነት ፖለቲካ›› እና መሠረት የሌለው የፖለቲካ ሥራ ነው ብሎ ማሳነስ አይገባም፡፡ የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አሁን የደረስንበት ዘመን አይመጥንም፡፡

ተጨባጭ ሁኔታውም ይኼን አስተሳሰብ ለማስተናገድ አይችልም፡፡ የኢትዮጵያን ነፃነትና አንድነትን ጠብቆ ማስቀጠል ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የሌለበት የተቀደሰ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ አንድነት ዕውን የሚሆነው በአንድነት ውስጥ የብሔር ብሔረሰብን መብት የሚያካትት በቂ ቦታ ሲኖረው ነው፡፡ በአገር ውስጥ ያለን ተቃዋሚ ድርጅቶች አንዳንዶቹ ልቦናቸው የሚያውቀውንና በዓይናቸው የሚያዩትን፣ እነሱም ቢሆኑ በአገር ውስጥ ደፍረው በግልጽ የማይቃወሙትን ይኼን አቋም በውጭ አገር ላሉ ዳያስፖራዎችና ደጋፊዎቻቸው በአገር ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የብሔር ብሔረሰብ ጥያቄ፣ እንደ ተራ የጎሰኝነት የመንደር ፖለቲካ አድርገው ወይም በሌሎች የተቀነባበረ የፖለቲካ አጀንዳ አድርጎ አሳንሶ ማቅረብ ከጊዜው ሁኔታ ጋር አለመጣጣም ከመሆኑም በላይ አሳሳች ግንዛቤ መፍጠርም ነው፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያን አንድነትንና የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እንዴት አጣጥመን ለሁላችንም የምትበጅ አገር እንፍጠር የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሁለት አማራጮች አሉ፡፡ እኛ ግን ወደ አንድ ስንጥል ከሌላው እንርቃለን፡፡ የችግሮቻችን መንስዔ ደግሞ ይኼ ወደ አንድ ቀርቦ ከሌላው የመራቅ ጉዳይ ነው፡፡ እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው አሁን የምሁራንን ዕርዳታ እንፈልጋለን፡፡

ምሁራን ስንል የተግባር ምሁራንን ነው፡፡ የተግባር ምሁር ስንል ምንም ዓይነት የፖለቲካ አቋም ይኑረው በአገር ላይ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ከተጨባጭ ሁኔታ ተነስቶ በመተንበይ፣ ያለምንም ወገንተኝነት ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ከተጨባጭ ሁኔታ ተነስቶ በመተንበይ የመፍትሔ ሐሳብ አካል የሚሆንልን ማለት ነው፡፡ ችግሮችን እየኖርንበት ስለሆነ እናውቀዋለን፡፡ ለጊዜው የሚያስፈልገን ምሁር የመፍትሔ አካል ጭምር የሚሆነን ነው፡፡ ምሁራን በግልም ሆነ በሚያገኙት ጠባብ የሚዲያ ሰዓት የሚነግሩን የኢሕአዴግን ወንጀል ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው የኢሕአዴግን የአመራር ጥንካሬና ቅዱስነትን ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱም ወገኖች የሚነግሩን አዲስ ነገር የለም፡፡ እኛ በውስጡ እየኖርን ስለሆነ ሁሉንም እናውቃለን፡፡ እነሱ ለፖለቲካቸው ማጣቀሻ የሚነግሩን ፕሮፓጋንዳ የበለጠ ሕዝብን ከሕዝብ እያለያየ፣ ይኼው አሁን የደረስንበት የመተላለቅ መጀመርያ ላይ ደርሰናል፡፡ ክፉም ሆነ ደግ የሚፈጸመው በሕዝቦቿና በአገሪቱ ላይ ነው፡፡ ለምን በሌለ የአየር ሰዓት የአዋጁን በጆሮ ሊነግሩን እንደሚዳዳቸው ግልጽ አይደለም፡፡

ከሰሞኑ በደብረ ብርሃን በተደረገው የምሁራን ኮንፈረንስ ተስፋ ሰጪና ምሁር ምሁር የሚሸቱ አስተሳሰቦች ተንሸራሽረውበታል፡፡ አሁን ያለውን የአገሪቱን ተጨባጭ ችግር ዳሰዋል፣ ወደፊትም መሆን ስላለበትና መጠንቀቅ ስለሚያስፈልገን ነገር ባላቸው ጠባብ የአየር ሰዓት ነግረውናል፡፡ ነገር ግን የዚህ ዓይነት ጠቃሚ የሆኑ ምሁራዊ አስተሳሰቦች አንደኛ ዘግይተው የመጡ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ሐሳቦቹ በእዚያው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የታጠሩና ወደ ሕዝብ ወርደው የዳበሩ አይደሉም፡፡ ከዚያ ወዲህ አልፎ አልፎም ቢሆን ጥቂቶች በተለያየ መድረክ የሚሰጡት ሐሳብ ተስፋ የሚያጭር ነው፡፡

ከላይ ስለተነሱት የአገራችን ጉዳዮችም ምሁራን በሰፊው የፌዴራሊዝምን ጽንሰ ሐሳብ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አያይዘው የመፍትሔ ሐሳብ ያቅርቡልን፡፡ ይኼን ለማድረግ ደግሞ በመጀመርያ የሚያለያዩንን እንለያቸው፡፡ ልዩነታችን ስለሰፋ ነው አሁን ያለንበት ደረጃ የደረስነው፡፡ ልዩነታችንን መሠረት አድርገን የሚጨመረው ላይ ጨምረን፣ የሚቀነሰውንም ቀንሰን ወደምንጋራው ነጥብ እንሂድ፡፡ ይኼ ደግሞ ሊመጣ የሚችለው የሀቀኛና የአገር ወዳድ ምሁራን ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ነፃ ሆኖ ሲቃኝ ብቻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡