Skip to main content
x
ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ይደውልላቸዋል

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ይደውልላቸዋል

[ክቡር ሚኒስትሩ በከተማችን ትልቁ ሆቴል ውስጥ የሚስታቸውን ልደት ደግሰዋል፡፡ በልደቱ ከተገኙ እንግዶች መካከል ከአንዱ ጋር እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ነው የሚገርመው፡፡
 • ምኑ ነው የሚገርመው?
 • ከደገሱ አይቀር እንዲህ ነው እንጂ፡፡
 • እኔን ታውቀኝ አይደል እንዴ?
 • በእውነት ክቡር ሚኒስትር ኮራሁብዎት፡፡
 • በምኑ ነው የኮራህብኝ?
 • እዚህ ልደት ላይ መቼም የወጣው ወጪ አምስት መለስተኛ ሠርግ ይደግሳል፡፡
 • ሚስቴ እኮ ለእኔ ሁሉ ነገሬ ናት፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • አሁን ለደረስኩበት ስኬት ዋነኛውን ሚና የተጫወተችው እሷ ናት፡፡
 • ለነገሩ ስለሚስትዎ ሰምቻለሁ፡፡
 • ምንድነው የሰማኸው?
 • ሁሉም የእርስዎ ቢዝነስ በሚስትዎ ስም ነው አሉ፡፡
 • የቢዝነሶቼ ሐሳብ ሁሉ የመነጨው ከእሷ እኮ ነው፡፡
 • የሚወራውማ ብዙ ነው፡፡
 • ምንድነው የሚወራው?
 • ክቡር ሚኒስትሩ የሚዘርፉትን ገንዘብ በሚስታቸው ስም ነው የሚያንቀሳቅሱት ይባላል፡፡
 • ሰው መቼም ምቀኛ ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ለምን ሠራህ? ለምን ተለወጥክ? ለምን አደግህ ነው?
 • አይ ክቡር ሚኒስትር ሰው መቼም ዝም ብሎ አያወራም፡፡
 • አሁን ለሚስቴ እዚህም ደገስኩ ቀበሌ አዳራሽ ውስጥም ደገስኩ ሰው ማውራቱን አያቆምም፡፡
 • ታዲያ ሰው ከመሬት ተነስቶ ነው የሚያወራው?
 • ወዳጄ የሰውን ወሬ ትተህ በጊዜ መያዝ ያለብህን መያዝ ነው የሚያዋጣው፡፡
 • እሱስ እውነትዎትን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስማ ይኼን ሁሉ ሰው ቀጥሬ በማሠራቴ ልመሰገን ነበር የሚገባኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ግን ትንሽ ደፋር ነዎት፡፡
 • እንዴት?
 • ባለሥልጣን ሆነው እንዲህ በአደባባይ የሚስትዎትን ልደት ሲደግሱ ይገርማል፡፡
 • ሠርቼ ነዋ ያመጣሁት፡፡
 • ሠርቼ ነው ሰርቄ ያሉት?
 • ምን አልከኝ?
 • ሠርቼ ነው ያሉኝ?
 • እኔ እኮ አንድ አይሉ ሁለት ፋብሪካ ነው ያለኝ ሰው ነኝ፡፡
 • እ…
 • ከአንድ ሺሕ በላይ ሠራተኛ ቀጥሬ አሠራለሁ፡፡
 • ምን ይቀልዳሉ?
 • ቅፅል ስሜ ማን እንደሆነ ታውቃለህ?
 • ማን ነው?
 • ኢንዱስትሪ ፓርክ፡፡
 • ዋናው ጥያቄ ይኼን ሀብት ከየት አመጡት የሚለው ነው፡፡
 • ሠርቼ አልኩህ እኮ፡፡
 • እሱን ሲጠየቁ ያወራሉ፡፡
 • ማን አባቱ ነው የሚጠይቀኝ?
 • ለማንኛውም ከሰሞኑ ሊጣራ ይችላል፡፡
 • ምኑ?
 • የሀብት ምንጭዎ!

[ክቡር ሚኒስትሩን ከሆቴሉ የሺፍት ማናጀር ጋር እያወሩ ነው]

 • እንግዶቹን በደንብ እያዝናናችኋቸው ነው?
 • በሚገባ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በየጠረጴዛው የምትጠየቁትን ሁሉ አቅርቡ፡፡
 • አያስቡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ድግሱ ሲያልቅ እንደተለመደው አምጥተህልኝ እፈርማለሁ፡፡
 • ምኑን ነው የሚፈርሙት?
 • ቢሉን ነዋ፡፡
 • አልሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑን?
 • አሠራራችንን ቀይረናል፡፡
 • ለምን?
 • ባለቤቱ ገቢ ስለተደረጉ  ነዋ፡፡
 • እና ፈርሞ መጠቀም ቀረ?
 • በፊርማ መጠቀም ቀርቷል፡፡
 • ታዲያ በምንድነው መጠቀም የሚቻለው?
 • በክፍያ!

[በክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ልደት ማግሥት የፋብሪካቸው ሠራተኞች በማመፃቸው ፋብሪካ በፍጥነት ይሄዳሉ]

 • ፀጥታ፣ ፀጥታ ተወካይ አላችሁ?
 • እኔ ተወካያቸው ነኝ፡፡
 • ስለዚህ ከአንተ ጋር እንነጋገር፡፡
 • ይቻላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምንድነው በጠዋት ፋብሪካውን የምትበጠብጡት?
 • ጥያቄና ቅሬት አለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የምን ጥያቄ ነው ያለህ?
 • መቼም እኛ የማንሰማው ነገር እንደሌለ ያውቃሉ?
 • ጥያቄህን አቅርብ እኮ ነው የተባልከው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ የደመወዝ ጭማሪ ጠይቀን ነበር፡፡
 • ታዲያ ምን ተባላችሁ?
 • ድርጅቱ አሁን የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ አይችልም ተባልን፡፡
 • የገንዘብ አቅም ስለሌለን እኮ ነው፡፡
 • እርስዎ ግን ትናንትና ለሚስትዎ ልደት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማውጣትዎን ሰምተናል፡፡
 • ምን?
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን የደመወዝ ጭማሪ ካልተደረገልን አመፃችንን እንቀጥልበታለን፡፡
 • እኔ በገዛ ብሬ የፈለግኩትን ባደርግበት ምን አገባችሁ?
 • ገንዘቡ የራሴ ነው የሚሉ ከሆነማ ሥራውን ራስዎ ይሥሩት?
 • አንተ ግን ከእኔ ጋር እንዴት ብትናናቅ ነው እንደዚህ የምታወራው?
 • ክቡር ሚኒስትር እየጠየቅን ያለነው መብታችንን ነው፡፡
 • አንተ ለመሆኑ ትክክለኛው የሠራተኛ ማኅበር  ተወካይ ነህ?
 • እርስዎማ የሠራተኛ ማኅበር እንዳይቋቋም ይፈልጉ ነበር፡፡
 • አሁን ምንድነው የምትፈልጉት?
 • እንዲጨመርልን ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው የሚጨመረው?
 • ደመወዛችን ይጨመርልን፣ ካልተጨመረልን ምንም ሥራ አንሠራም፡፡
 • እንደዚያ ከሆነማ ሁላችሁንም አባርራችኋለሁ፡፡
 • እሱንማ ማድረግ አይችሉም፡፡
 • እንዴት?
 • ቋሚ ሠራተኞች እኮ ነን፡፡
 • ብትሆኑስ?
 • እንደዚያ ካደረጉ ለእኛ የሚከፍሉት ካሳ ፋብሪካውን ያሸጥዎታል፡፡
 • ምን ይደረግ ነው ታዲያ የምትሉት?
 • ደመወዛችን ከፍ ይበል፡፡
 • የእናንተ ደመወዝ ከፍ ሲል ሌላ ነገሬ ከፍ ይልብኛል፡፡
 • ሌላ ምን?
 • ደሜ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከፋብሪካቸው ወደ መሥሪያ ቤታቸው እንደገቡ ግቢው ወስጥ ጫጫታ ይሰማሉ፡፡ ጸሐፊያቸውን ወዲያው ጠሯት]

 • የምን ጫጫታ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ችግር ተፈጥሯል፡፡
 • የምን ችግር?
 • ሠራተኞቹ አምፀው ሥራ አንገባም እያሉ ነው፡፡
 • ምን ማለት ነው ሥራ አንገባም ማለት?
 • ክቡር ሚኒስትሩ ካላናገሩን ወደ ሥራ አንመለስም እያሉ ነው፡፡
 • አማካሪዬ ለምን አያናግራቸውም?
 • ሞክሯል ግን አልቻለም፡፡
 • አንቺስ አላናገርሻቸውም?
 • እኔም ሞክሬ አልቻልኩም፡፡
 • ምንድነው ችግራቸው?
 • ጉዳዩን አላወቅኩትም፡፡
 • ተወካይ አላቸው?
 • አንድ ተወካይ አላቸው፡፡
 • እሱን አስጠሪው፡፡

[የሠራተኞቹ ተወካይ የክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገባ]

 • ምን ተፈጥሮ ነው?
 • ቅሬታ አለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው ቅሬታችሁ?
 • ዋነኛው ኪራይ ሰብሳቢ እዚሁ እኛ ውስጥ ነው ያለው፡፡
 • ምን?
 • እኛ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስናን እንዋጋለን ስንል ዋናው ሙሰኛ ለካ በመካከላችን ነበር፡፡
 • ይኼንንማ በድንጋይ መውገር ነው፡፡
 • የዚሁ መሥሪያ ቤት ሠራተኛ ሆኖ የከተማችን ሀብታም ተርታ ውስጥ ገብቷል፡፡
 • ምን ትቀልዳለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር አንድ አይሉ ሁለት ፋብሪካ አለው አሉ፡፡
 • እ…
 • መርከብ ሳይቀር አለው አሉ፡፡
 • አገሪቷ ወደብ የላትም እኮ?
 • ለነገሩ የመዝናኛ መርከብ ነው ያለው፣ ግን ወደፊት በዚሁ ከቀጠለ የንግድ መርከብም ይኖረዋል፡፡
 • እ…
 • ሰሞኑን ለሚስቱ ልደት ድግስ ያወጣው ወጪ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ነው፡፡
 • ይኼን ሰውዬ አውቀዋለሁ ልበል?
 • ሊያውቁት ይችላሉ?
 • ታዲያ ምሕረት ቢደረግለት አይሻልም?
 • ለምን ሲባል?
 • ያው መንግሥት ራሱ ሰሞኑን ለታሰሩ ፖለቲከኞች ምሕረት አድርጓል አይደል?
 • ይኼ ግን ምሕረት አይገባውም፡፡
 • ወይም ይምከራ?
 • ለእሱ የሚያስፈልገው ምክር አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የሚያስፈልገው?
 • መወገር!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ይደውልላቸዋል]

 • ክቡር ሚኒስትር ስልክዎ እኮ በጣም አስቸገረኝ?
 • ዛሬ ስንት ጣጣ ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡
 • ምነው?
 • ሲያቀብጠኝ የሚስቴን ልደት አክብሬ ሠራተኞቼ አመፁብኝ፡፡
 • በዚህ ወቅት እንዲህ በግልጽ ድግስ ማድረግ ምን አስፈለገ?
 • እኔማ ትልቅ ትምህርት ነው የተማርኩት፡፡
 • አሁን የደወልኩት አንድ ነገር ላማክርዎት ነው፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • አንድ ሁለት ሰው ደውሎ ሲጠይቀኝ ለምን ወደ ቢዝነስ አንቀይረውም ብዬ ነው፡፡
 • ጉዳዩ ምንድነው?
 • መንግሥት ምሕረት አደርጋለሁ ብሏል አይደል?
 • አዎ ብሏል፡፡
 • ታዲያ ይኼን ለምን ወደ ቢዝነስ አንቀይረውም?
 • እንዴት አድርገን?
 • እንዲፈቱላቸው የሚፈልጉ ሰዎች አናግረውኝ ነበር፡፡
 • እሺ?
 • አንዱ ደውሎ የሚደረገውን ነገር አደርጋለሁ ብቻ ወንድሜን አስፈቱልኝ ብሏል፡፡
 • ኧረ እባክህ? ሁሉን ነገር ማድረግ ይችላል?
 • ስለእሱ አያስቡ ስልዎት? ከእኛ የሚጠበቀው ሊስት ውስጥ ወንድሙ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡
 • የምኑ ሊስት?
 • የሚፈቱት ሊስት ውስጥ ነዋ፡፡
 • ይቺ አሪፍ ሐሳብ ናት፡፡
 • አሁን ወደ ሥራ መግባት ነው፡፡
 • ምንድነው የምናደርገው?
 • ካስፈለገ ማስታወቂያ ማስነገር ነው፡፡
 • ምን ብለን?
 • የታሰሩ እናስፈታለን!