Skip to main content
x
የፕሪሚየር ሊጉ መርሐ ግብር ቅዳሜና እሑድ በክልሎች ሲቀጥል በአዲስ አበባ አይኖርም
አርባ ምንጭ ከተማ ከፋሲል ከተማ (ፎቶ ፋይል)

የፕሪሚየር ሊጉ መርሐ ግብር ቅዳሜና እሑድ በክልሎች ሲቀጥል በአዲስ አበባ አይኖርም

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ13ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር በመጪው ቅዳሜና እሑድ በክልሎች ሲቀጥል፣ በአዲስ አበባ እንደማይኖር ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የአሠልጣኞች ስንብትና ሹመት እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የውድድር ክፍል እንዳስታወቀው ከሆነ፣ ቅዳሜ ጥር 19 ቀን ወላይታ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሐዋሳ ላይ ሐዋሳ ከተማ ከአርባ ምንጭ ከተማ፣ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና፣ አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ እሑድ ጥር 20 ቀን ደግሞ ጎንደር ላይ ፋሲል ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ መቐለ ላይ መለ ከተማ ከሲዳማ ቡና የሚደረጉ የ13ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር ናቸው፡፡

ለሁለት ሳምንት ያህል የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታ ሳያስተናግድ የሰነበተው የአዲስ አበባ ስታዲየም፣ ረቡዕ ጥር 23 ቀን መሪው ደደቢት ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናግዳል፡፡ ጥር 24 ቀን ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከተማ ተስተካካይ ጨዋታ ይጫወታሉ፡፡ እንደ ውድድር ክፍሉ ከሆነ የካቲት 18 ቀን ወልድያ ከተማና መከላከያ ተስተካካይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመቱ ግማሽ መርሐ ግብር ባልተጠናቀቀበት በዚህ ወቅት የአሠልጣኞች ስንብትና ሹመት ቀጥሏል፡፡ እስካሁንም የድሬዳዋ፣ የአርባ ምንጭ፣ የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለቦችና ዘንድሮ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ክለብ የቡድኖቻቸውን ዋና አሠልጣኞች ያሰናበቱ ሆነው በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል፡፡