Skip to main content
x
‹‹የሙያ ዕርካታ የሚሰጠን ሕይወቷ አደጋ ላይ የነበረችን እናት ማዳን መቻላችን ነው››

‹‹የሙያ ዕርካታ የሚሰጠን ሕይወቷ አደጋ ላይ የነበረችን እናት ማዳን መቻላችን ነው››

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ኃላፊዎች

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የዓለም የጤናማ እናትነት ወርን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህም መግለጫ ላይ በእናቶች ጤናና ተዛማጅ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከጋዜጠኞች ለቀረቡት ጥያቄዎች የኮሌጁ የሕክምና ዘርፍ ምክትል ፕሮቨስት ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢና የጽንስና ማሕፀን ዲፓርትመንት ኃላፊ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ የሰጡትን መልስ መግለጫውን የተከታተለው ታደሰ ገብረማርያም እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡

ጥያቄ፡- ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከተለውን የእናቶች ሞት ምክንያት ለማወቅና የሞቱንም መጠን ለመቀነስ የተደረገውን ጥረት ቢያብራሩልን?

መልስ፡- በሕክምና ኮሌጁ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከተለውን የእናቶች ሞት ምክንያት ለይቶ ማውጣት የሚችል ‹‹ማተርናል ኬዝ ኦዲት ኮሚቴ›› ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ኮሚቴው የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ምክንያት በየወሩ ይከታተላል፡፡ ይገመግማልም፡፡ በዚህም ግምገማ ሞቱ ሊከሰት የቻለው በእኛ አቅም ልናስቆመው ባለመቻላችን፣ ወይስ ከአቅም በላይ ሆኖ በመገኘቱ፣ በባለሙያው ቸልተኝነት የተነሳ፣ እናቶች ዘግይተው ለሕክምና ወደ ኮሌጁ በመምጣታቸው ሳቢያ፣ ወይስ ከመሠረተ ልማት ችግር በሚሉት ዙሪያ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ያጣራል፡፡ ኮሚቴው ለአንድ ዓመት ያህል ባካሄደው በዚሁ ግምገማ በኮሌጁ ውስጥ የተከሰተው የእናቶች ሞት ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር ሲታይ በጉልህ ቀንሷል ወይም የተጋነነ የእናቶች ሞት አለ ብለን አናምንም፡፡

ጥያቄ፡- ባለፈው ዓመት ለስንት እናቶች የወሊድ አገልግሎት ተሰጠ? ምን ያህሉስ ሞት አጋጥሟቸዋል?

መልስ፡- ባለፈው ዓመት የሕክምና ኮሌጁ ወደ 11,000 ለሚጠጉ እናቶች የወሊድ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለሕልፈተ ሕይወት የተዳረጉት 13 እናቶች ብቻ ናቸው፡፡ ከሞቱትም መካከል ስድስቱ ሕክምና ኮሌጁ ቅጥር ግቢ እንደደረሱ (ዴዝ ኦን አራይቫል) ነው የሞቱት፡፡ ለዚህም የሞት ሠርቲፊኬት (ማረጋገጫ) የምንሰጠው እኛ ስለሆንን እኛ ዘንድ እንደሞቱ ይቆጠራል፡፡ ባለፈው ዓመት ለእናቶች ጤና ችግር እንደነበር በተለይ ኦሮሚያ አካባቢ በተከሰተው ችግር የትራንስፖርት መስተጓጎልና አምቡላንሶችን በጊዜ አግኝቶ ወደ ሕክምና ኮሌጁ የመግባት ችግር ወይም እንቅፋት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ተቋሙ ሪፈር የተደረጉ እናቶች አምቡላንስ በመጠበቅ ብቻ ችግር ውስጥ ተገብቶ እንደበር አይዘነጋም፡፡

ጥያቄ፡- የስንት ሰዓት መዘግየት ነው ለችግር ሊዳርግ የሚችለው?

መልስ፡- የአንድ ሰዓት መዘግየት ትልቅ ቀውስ ያስከትላል፡፡ አንዲት እናት እዚህ መጥታ አስፈላጊውን የወሊድና የሕይወት ማዳን ሥራ ከተከናወነላት በኋላ እንድታገግም ማድረግ ሲቻል የአንዱን ሰዓት መልካም አጋጣሚ (ዊንዶው ኦፍ ኦፖርቹኒቲ) በማጣቷ የተነሳ ለሕልፈተ ሕይወት ትዳረጋለች፡፡

ጥያቄ፡- ለእናቶች ከምትሰጡት የወሊድ አገልግሎት ባሻገር ጤናቸውን የሚጠብቁበትን ዘዴ በምን መልኩ ለማስረዳት ወይም ለማስተማር የምትሞክሩት?

መልስ፡- በሆስፒታሉ ልዩ ልዩ ዋርዶችና ክፍሎች እንዲሁም በምቹ ክሊኒክ ውስጥ ለታካሚዎች ከሚደረግላቸው የመደበኛው ሕክምና ባሻገር የጤና ትምህርት ይሰጣል፡፡ በዚህም ትምህርት ላይ የልዩ ልዩ በሽታዎች የመጀመርያ ምልክቶቹ ምን እንደሚመስሉ የሚገልጹ መረጃዎችን በበራሪ ጽሑፍ፣ በፓንፍሌቶችና በብሮሸር እያዘጋጀን እንዲደርስላቸው እናደርጋለን፣ መረጃዎቹ በአማርኛና በኦሮሚኛ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በኦሮሚኛ ለማዘጋጀት ያስፈለገውም ዋናው ምክንያት ከታካሚዎች መካከል አብዛኞቹ ከኦሮሚያ ክልል የመጡ በመሆናቸው ነው፡፡

ጥያቄ፡- ወላዶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ኩላሊታቸው ላይ ጫና ሊደርስባቸው እንደሚችል ይነገራል፡፡ ይህን ችግር በምን መልኩ ነው የምትከታተሉት የልብ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውንስ እንዴት ትረዳችኋላችሁ?

መልስ፡- ኩላሊት ላይ ለሚደርሰው የጤና ችግር በዲያሊስስ አገልግሎት ማስወገድ ወይም መፍትሔ መስጠት ይቻላል፡፡ ይህንንም አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሕክምናው ኮሌጅ የመጡ በርካታ እናቶችን ለመታደግ ችለናል፡፡ ቀደም ሲል ደግሞ የልብ ሕክምና አገልግሎት እዚህ አይሰጥም ነበር፡፡ ስለዚህ እያንዳንዷ እናት የልብ ሕክምና አገልግሎት ሲያስፈልጋት ወደ ሌላ ተቋማት ነበር የምንልከው፡፡ አሁን ግን በግቢያችን ውስጥ መሥራት ችለናል፡፡ እስከ መጨረሻው ዓለም በደረሱበት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የልብ ማዕከልም አቋቁመናል፡፡ የካንሰር ሕክምናንም ከጨረራ (ራዲዬሽን) ውጪ ሌላውን በሞላ እዚህ መሥራት ችለናል፡፡ ከዚህም ሌላ አንዲት እናት በጡቷ ላይ የሚታየው እባጭ ካንሰር ከመሆኑ በፊት የሚለይ ወይም የሚያሳይ ‹‹የማሞግራፊ›› አገልግሎት የሙከራ ሥራ ተጀምሯል፡፡ ይህንንም አገልግሎት በበለጠ አጠናክረን የምንንቀሳቀስበት ይሆናል፡፡ እንደ አገር የተሻለ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር አለ፡፡ ይህ ችግር እየተሻሻለ ሲመጣ የተሟላ ወይም ሙሉ የሆነ የእናቶችን ጤና የሚንከባከብ ተቋም ይወጣናል ብለን እናስባለን፡፡

ጥያቄ፡- የሰጣችሁት የወሊድ አገልግሎት ከሌሎቹ ተመሳሳይ ተቋማት ጋር ሲመዘን የበለጠ ያደርገዋል ለማለት ይቻላል? የአገልገሎቱ መጠን ሊበዛ የቻለው በምን ምክንያት ነው?

መልስ፡- የወሊድ አገልግሎት የተፈጥሮ ሒደት ነው፡፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ተፈጥሮአዊ ሒደት በተለያየ ምክንያት ሊወሳሰብ ይችላል፡፡ የጽንሱ የጤንነት ሁኔታ ሊረበሽ፣ የእናቲቱ የጤንነት ይዘት አደገኛና ሕይወት እስከማጣት የሚደርስበት አጋጣሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ጤና ጣቢያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት ውስጥ የወሊድ አገልግሎት ቢሰጡም የሕክምና ኮሌጁ ግን በብዛት የሚቀበለው የተለየ ክትትትል የሚያስፈልጋቸው እናቶችን ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ተጓዳኝ የሆነ የሕክምና አገልግሎት በመስጠታችን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ወደ ሕክምና ኮሌጁ የሚመጡ ከቁጥራቸው ብዛት በተጨማሪ የተወሳሰበ ያደርገዋል፡፡ ቁጥሩ ብቻ ቢታይ እንኳን በአገሪቱ ውስጥ ትልቁ የወሊድ አገልግሎት የሚሰጥ የሕክምና ኮሌጅ ያደርገዋል፡፡ እኛ ግን የበለጠ የሙያ እርካታ የሚሰጠን ተፈጥሮአዊ የሆነውን የወሊድ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ሕይወቷ አደጋ ላይ የነበረችን እናት ማዳን መቻላችን ነው፡፡

ጥያቄ፡- ሕክምና ኮሌጁ ጠቅላላ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኖሩ ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያ ክልል በሪፈራል ሲስተም ለሚመጡትም በርካታ ታካሚዎች ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን በመግባቢያ ቋንቋ ችግር ሳቢያ በአገልግሎቱ ሰጪዎችና ከተጠቀሰው ክልል በሚመጡ ታካሚዎች መካከል ክፍተት ይታያል፡፡ ይህ ጉዳይ እንዴት ሊስተካከል ታስቧል?

መልስ፡- ይህ ችግር ክፍተት መፍጠሩ ተለይቶ ታውቋል፡፡ ከኦሮሚያ አካባቢ የሚመጡት ታካሚዎችና አስታማሚዎች አማርኛ የማይችሉ ሲሆን አገልግሎቱን ከሚሰጡትም መካከል አብዛኞቹ ኦሮምኛ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ስለዚህ መጀመርያ ያደረግነው ነገር ቢኖር ኦሮምኛ ቋንቋ ለመማር አጋጣሚው ቢፈጠርላችሁ ትማራላችሁ ወይ? የሚል ጥያቄ ለሁሉም የአገልግሎት ሰጪዎች ቀርቦላቸው 94 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ለመማር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹ሜዲካል ኦሮሚፋ›› የሚል ፕሮጀክት ቀረጽን፡፡

ጥያቄ፡- ፕሮጀክቱን ከማን ጋር በመተባበር ነው የተቀረጸው? ዓላማውስ ምንድነው?

መልስ፡- ፕሮጀክቱ የተቀረጸው የሕክምና ኮሌጁ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሚኛ ዲፓርትመንት ጋር በመተባበር ነው፡፡ ለተግባራዊነቱም ከተጠቀሰው ዲፓርትመንት ጋር ስምምነት ተደርጓል፡፡ በስምምነቱ መሠረት የሕክምና ኮሌጁ ለመማር ማስተማሩ ሥራ የሚሆን በጀት ይመድባል፡፡ መምህራንን ደግሞ ዲፓርትመንቱ ይመድባል፡፡ ለትምህርት የሚያገለግል የመጀመርያው መመርያ ወይም ማንዋል (ሞጁል) ተሠርቷል፡፡ ሁለተኛው ሞጁል በመዘጋጀት ላይ ነው፡፡ ትምህርቱንም የሚከታተሉት ከጥበቃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የሕክምና ሙያ ውስጥ ያሉት ባለሙያዎች ሲሆኑ ትምህርቱም የሚሰጠው ለ12 ሳምንታት ያህል ነው፡፡