Skip to main content
x

የአፍሪካ ቀንድና የገልፍ አገሮች ጂኦ ፖለቲካዊ ትስስር አንድምታ

በልዑልሰገድ ግርማ

ከቀይ ባህር በስተምሥራቅ የሚገኙት ኩዌት፣ ኳታር፣ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከቀይ ባህር በስተምዕራብ በሚገኙ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ማኅበራዊናባህላዊ ምኅዳር ላይ ጥልቀት ያለው ተፅዕኖ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሁለቱ አካባቢዎች የቀይ ባህር የሚለያቸው ቢመስልም፣ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ በማያቋርጥ ሁኔታ ይገናኛሉ፡፡ ዋና ዋና ሃይማኖቶቻቸውና አስተምህሮቶቻቸው ቀይ ባህርን በቀላሉ በመሻገር የአፍሪካ ቀንድን መገኛቸው አድርገዋል፡፡ የንጉሥ ሰሎሞንና የንግሥት ሳባ ግንኙነት፣ እንዲሁም የሙስሊሞች ወደ ኢትዮጵያ ስደት ዋናዎቹ ሃይማኖት ነክ ታሪኮች ናቸው፡፡ ..አ. 1973 .ም. ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ ጣራ በመንካቱ ምክንያት የገልፍ አገሮች በአፍሪካ ቀንድ አገሮች የመንግሥት አስተዳደሮች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡ የነፃ አውጭ ቡድኖችንም በመርዳት ይታወቃሉ፡፡ የገልፍ አገሮች ኢኮኖሚ እጅግ የተሻለ በመሆኑ፣ የቀንዱ አገሮች ዜጎቻቸው በሚችሏቸው የሥራ መስኮች እንዲሰማሩ ወደ አካባቢው ይልኳቸዋል፡፡  ሠርተው የሚያገኙትን ጥሪትም ወደ አገር ቤት እንዲልኩ አድርገዋል፡፡ የቀንዱ አገሮች ከልማት ትብብር አንፃር የገልፍ አገሮች ጥገኛ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የአገሮቹ ግንኙነት ፖለቲካዊ ልኩ እጅግ ከፍ ያለ ቢሆንም፣ የገልፍ አገሮች የቀንዱን አገሮች የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጥም ሆነ በደኅንነት ጉዳዮች ትብብሮች እጅግ ከፍ እያሉ የመጡ ሲሆን፣ ለቀንዱ አገሮችም ዕድልን ሰንቀውና ሥጋትን አዝለው ብቅ ብለዋል፡፡

የቀንዱ አገሮች የሚታወቁት መሬት፣ ውኃና የሰው ኃይል በማቅረብ ሲሆን፣ በምላሹ ዶላርና ቴክኖሎጂን  ለማግኘት ችለዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለወታደራዊ ጥቅም የሚውሉ የወደቦች አቅርቦትን እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ እነዚህ ገንዘብጠር መንግሥታት ከወደብ ኪራይና የመን ውስጥ በሚካሄደው ጦርነባላቸው ተሳትፎ የሚያገኙትን ዶላር አገዛዛቸውን ለማነቃቃትና ለማጠናከር እያዋሉት ነው፡፡

የገልፍ አገሮች በቀንዱ የሚያደርጉት የወደቦች ኪራይና ልማት ጂኦ ፖለቲካ ይዘትን የተላበሰ ነው፡፡ የገልፍ አገሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል፡፡ የአገሮቹ የሱኒና ሺዓ ፍጥጫ በኢንቨስትመንት መልኩ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች የተንፀባረቀ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በሌላ በኩል በመሆን ፍጥጫው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ የዓረቡን ዓለም ለመምራት ያላት ጉጉት በኳታርና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥታትም ይንፀባረቃል፡፡ ይህ ውጥረት በአሁኑ ወቅት የኳታርንና የኢራንን ያልተጠበቀ ጥምረት ፈጥሯል፡፡ አገሮቹ በቀንዱ አገሮች የሚያደርጓቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የውጭ ግንኙነታቸው መገለጫዎች ሆነዋል፡፡

ቀይ ባህር የገቢና የወጪ ዕቃዎችን፣ የጦር መሣሪያዎችና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች የሚተላለፉበት እጅግ ጠቃሚ የሆነ የባህር መስመር ነው፡፡ ለዓለማችን ኃያላን አገሮች የንግድ ካርጎዎች፣ እንዲሁም የገልፍ አገሮች የነዳጅ አቅርቦት በዚህ የቀይ ባህር መተላለፊያ ይስተናገዳል፡፡ ከንግድ መስመርነቱ ባሻገርም ቀይ ባህር በገልፍ አገሮችና  በአፍሪካ ቀንድ ለሚከሰተው ፍልሰትም እንደ መተላላፊያ መስመር ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሽብርተኞችም ይንቀሳቀሱበታል፡፡ የአፍሪካ ቀንድና የገልፍ አገሮች በዚሁ የውኃ ክፍል አማካይነት የሚገናኙ ቢሆንም፣ ውኃው የሁለቱን የዓለም ክፍሎች የፖለቲካና ማኅበራዊ መስተጋብር አንድነትና ልዩነት ግምት ውስጥ ሳያስገባ ሁለት ጂኦግራፊያዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀጣናዎች አድርጓቸዋል፡፡

የቀይ ባህር አካባቢ የወታደራዊ ፍጥጫና እስላማዊ ፖለቲካ በሰፋ ሁኔታ የሚስተዋልበት አካባቢ ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ራሱን የቻለ አካባቢያዊ ኃይል ሆኖ አለመውጣቱም ለወታደራዊናፖለቲካዊ ፍጥጫ የተጋለእንዲሆን አድርጎታል፡፡ እንደ ሱዳን፣ ጂቡቲና ሶማሊያ የመሳሰሉ አገሮች የዓረብ ሊግ አባል በመሆናቸው የጠነከረ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እንዳይወጣ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡ ለቀንዱ አለመረጋጋትም የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በገልፍ የተፈጠረው የፖለቲካ ስንጥቅ በአጭር ጊዜ መፍትሔ የሚገኝለት አይመስልም፡፡ የዚህ ውጥረት መነሻዎች ሳዑዲ መራሹ የየመን ጦርነት፣ በገልፍ አገሮችና በኢራን መካከል ያለው ፍጥጫና የነዳጅ ዋጋ መዳከም ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡ የየመን ጦርነትና እሱን ተከትሎ የመጣው የገልፍ አገሮች ቀውስ ከቀይ ባህር በስተምዕራብ በሚገኙት የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ላይ ጥልቀት ያለውና መጠነ ሰፊ የሆነ የኃይል አሠላለፍ ለውጥ አስከትሏል፡፡ ለቀንዱ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያም የራስ ምታት ሆኖባታል፡፡ በአንፃሩ ዓለም አቀፍ ተቀባይነታቸው አሽቆልቁሎ የነበረው ኤርትራና ሱዳን የገልፍ አገሮችና ሌሎች በሚያበረክቱላቸው ዶላር ምክንያት የንፋሱ አቅጣጫ ተስማምቷቸዋል፡፡

በቀይ ባህር ግራና ቀኝ የሚደረጉ የንግድ ልውውጦች ቀላል ቦታ የሚሰጣቸው አይደሉም፡፡ የሶማሊያ ዋነኛ የቀንድ ከብቶችና የከሰል ወጪ ንግድ ተቀባይ ሳዑዲ ዓረቢያ ነች፡፡ የሳዑዲ 70 በመቶ በላይ የግብርና ኢንቨስትመንት በዋነኛነት በሱዳንና በኢትዮጵያ የሚከናወን ነው፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ የተባበሩ ዓረብ ኤምሬትስ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ 48 ኩባንያዎች  ያሏት ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ ሌሎች 55 ኩባንያዎች 4.5 ቢሊዮን ዶላር በመያዝ ኢንቨስትመንቱን ይቀላቀላሉ፡፡ ኳታርም በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመት መስኮች የምትሳተፍ ሲሆን፣ በቅርቡም በመሀል አዲስ አበባ የሚገኝ ስድስት ሔክታር መሬት በመረከብ የቱሪስት መዝናኛዎችን እንደምታጎለብት ይጠበቃል፡፡

በጂቡየሚገኙት የተለያዩ አገሮች የጦር ሠፈሮች የቀይ ባህርን ስትራቴጂካዊ አስፈላጊነት ከሚያጎሉት ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የጂቡቲ ቅኝ ገዥ የነበረችው ፈረንሣይ በጦር ሠፈር አመካኝታ አሁንም እዚያው ጂቡቲ ትገኛለች፡፡ 9/11 የአሜሪካ የሽብር ጥቃት በኋላ አሜሪካ የጦር ሠፈሯን እዚሁ ጂቡቲ መሥርታለች፡፡ ቻይና፣ ጃፓን፣ ጀርመንና ሳዑዲ ዓረቢያ የጦር ሠፈር መሥርተዋል፡፡ ቱርክም በሶማሊያ ትልቅ ሊባል የሚችል የጦር ሠፈር ከመመሥረቷም ባሻገር፣ በቅርቡም በሱዳን ተመሳሳይ የጦር ሠፈር ለመመሥረት ከስምምነት ላይ ደርሳለች፡፡

የገልፍ አገሮች ውጥረት በአፍሪካ ቀንድ ተፅዕኖ ማሳረፉን ለማወቅ የአሰብ ወደብን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ይኸው ከአስመራ 600 ሎ ሜትር፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጠረፍ 50 ሎ ሜትር ብቻ የሚርቀው ወደብ ከኢትዮጵያናኤርትራ ጦርነት በፊት ለኢትዮጵያ ጥቅም ሲሰጥ ቆይቷል፡፡  ከዚህ ጊዜ በኋላም ኢራን ስትጠቀምበት ቆይታለች፡፡ አሁን ደግሞ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የባህር ኃይል የጦር ሠፈር በመሆን የየመኑን ጦርነት ለማቀጣጠል እየጠቀመ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በመስከረም 2016 የሁቲ አማፅያን በዚህ ወደብ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፡፡ አማፅያኑ በዚሁ አካባቢ በሚገኝ በአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው አሜሪካ ተበቅላቸዋለች፡፡ ይህ የቀይ ባህርን አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ገጽታ እንዲሁም ከፍተኛ ተጋላጭነት የሚያሳይ ክስተት ነው፡፡ በአሰብ ወደብና በየመን ድንበር መካከል 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ነው ያለው፡፡ ይህም በገልፍ አገሮችና በአካባቢው የሚነሳ ማንኛውም ኮሽታ በአፍሪካ ቀንድ በቀላሉ ሊሰማ እንደሚችል ማሳያ ነው፡፡

ሽብርተኝነት የሁለቱን አካላት ቅርበት የሚያሳይ መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ ... 1998 የገልፍ አገሮችን በማቋረጥ ወደ አፍሪካ ቀንድ የመጡት የአልቃይዳ አሸባሪዎች በኬንያናታንዛንያ የሚገኙትየአሜሪካ ኤምባሲዎችን አጥቅተዋል፡፡ አይኤስ ከኢራቅናሶሪያ ቢደመሰስም በየመንናአፍሪካ ቀንድ ያለው የጅሃድ እንቅስቃሴ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የመሣሪያና የአመለካከት አቅርቦቱ ከገልፍ አገሮች ለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በመሆኑም የቀይ ባህር አካባቢ በቀላሉ የጦርነት አውድማ ለመሆን የተዘጋጀ አካባቢ ሊባል ይችላል፡፡ አብዛኞቹ ከአፍሪካ ቀንድ የሚሰደዱ ሰዎች ዋና ዓላማቸው በገልፍ አገሮች ሥራ መፈለግ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ስደተኞቹ ለቤተሰቦቻቸው በሚልኳቸው ሐዋላዎች የአገራቸውን ኢኮኖሚ እየደጎሙ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ሱዳናውያንና ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ የፑንትላንድ ሶማሌዎችም ቀይ ባህርንና የዓረብ ባህርን በማቋረጥ ወደ የመን ከዚያም ወደ ባለፀጋዎቹ የገልፍ አገሮች ይቀላቀላሉ፡፡

ከነዳጅ ዋጋ መውደቅ ጋር ተያይዞ የገልፍ አገሮች የኢኮኖሚያቸውን ምንጭ ማስፋት እንዳለባቸው ቆርጠው የተነሱበሁኔታ ተከስቷል፡፡ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥም በምግብ ምርትና በአግሮ ቢዝነስ ዘርፍ ለመሰማራት የመረጡት የቀይ ባህርን የምዕራብ ዳርቻ አገሮችን ነበር፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በዚሁ ላይ የተሰማራች ሲሆን፣ ዲፒ ወርልድ በተባለው ተቋሟ አማካይነት ወደቦችን በማስተዳደር ላይ ትገኛለች፡፡ የኪስማዩና የጂቡቲ ወደቦች በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህ ወደቦችን በስፋት የማስተዳደሩ ሥራ የወደብ አገልግሎት ዋጋን ማናር ተጠቃሚዎችን እንዳይጎዳ የሚል ሥጋት እየተንፀባረቀ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከሌሎች አገሮች የግብርና ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ ብትሆንም ከቀይ ባህር በስተምዕራብ የሚደረጉ የገልፍ አገሮች እንቅስቃሴዎች ሥጋት ውስጥ ከተዋታል፡፡ ለገቢናወጪ ንግዷ፣ እንዲሁም የውጭ ኢንቨስትመንት (የውጭ ምንዛሪ) ላይ ጥገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ አካባቢዋ የጦር ሠፈር መናኸሪያ መሆኑ አሳስቧታል፡፡ ውዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በኤርትራና በጂቡቲ ያሏቸው የባህር ኃይል ጦር ሠፈሮች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያናሱዳን ያላቸው ኢንቨስትመንቶች የፀጥታ ጉዳይና ኢኮኖሚን ያስተሳሰረ ሆኗል፡፡ ሆኖም የቀንዱ አገሮች ራሳቸውን የአንድ አካል ሥሪቶች አድርገው አይቆጥሩትም፡፡ በመሆኑም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በተናጠል እንጂ፣ በጋራ የሚሠሩባቸው የኢኮኖሚና የደኅንነት ማዕቀፎች እምብዛም አያስጨንቃቸውም፡፡

ሳዑዲ መራሹ የየመን ጦርነት ከቀይ ባህር ወዲህ ባሉ የአፍሪካ አገሮች ውሳኔ ጭምር የተጀመረ ነው፡፡ ሱዳንና ኤርትራ ለጦርነቱ ሠራዊት ያዋጡ ሲሆን፣ ለጦርነቱ ጥምረት እንዲውል የባህር ኃይል የጦር ሠፈሮችን ፈቅደዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች ከፖለቲካ ተገልለው የቆዩ ከመሆናቸው በላይ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የነበረባቸው ናቸው፡፡ ይህንን ችግራቸውን ለጊዜው ለመቅረፍ ችለዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች ሠራዊት በማዋጣት የውጭ ምንዛሪያቸውን እያካበቱ ይገኛሉ፡፡ የአውሮፓ ሕገወጥ ስደትን የመክላት ፍላጎትም ሁለቱን አገሮች ተጨማሪ ገንዘብ ያስገኘላቸው ከመሆኑም ባሻገር፣ ውስጣዊ የፖለቲካ አቅማቸውንና በአካባቢያቸው ያላቸውን ቁመናቸውን አሻሽሎላቸዋል፡፡ ሱዳን 400 ወታደሮችን በጦርነቱ አጥታለች የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በአንድ በኩል ኳታር በሌላ በኩል በመሆን የፈጠሩት ቀውስ የአፍሪካ ቀንድን በቀጥታ ነክቷል፡፡ ሁለቱ አገሮች ኳታርን በማስገደድ ፀረ ኢራን አጀንዳቸውን እንድትከተል ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኳታር በአፍሪካ ቀንድ የነበራትን የሰላም ማስከበር ሚና በይፋ አቋርጣለች፡፡ ኤርትራ በኳታር ላይ የሰላም ትችት መሰንዘሯና ጂቡቲ ከሳዑዲና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር በመወገኗ በአካባቢው ውጥረት ነግሷል፡፡ የዳርፉር ጉዳይም የኳታርን አዎንታዊ ጣልቃ ገብነት እየጠየቀ የነበረ ሲሆን፣ ዕጣ ፈንታው አልታወቀም፡፡ ሱዳን በተፈጠረው ቀውስ ማንንም ያልወገነች መሆኗና በቅርቡም ከኳታር ጋር የተፈራረመቻቸው ወደብ የማልማት እንቅስቃሴዎች የገልፍ አገሮች ምን ያህል እንደተከፋፈሉ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ሱዳን በቅርቡ ከቱርክ ጋር ስትራቴጂካዊ የትብብር ምክር ቤት ለማቋቋም የተስማማች ሲሆን፣ ከሳዑዲ ጋር በባንኮቻቸው መካከል የነበሯቸውን ግንኙነቶች ለማደስ ተስማምተዋል፡፡

የገልፍ አገሮች የፖለቲካ ስንጥቅ ሶማሊያንም እየሰነጣጠቃት ይገኛል፡፡ የሶማሊያ ሦስት ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደሮች ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያቋረጡ ሲሆን፣ የሞቃዲሾው መንግሥት ደግሞ ከዶሃ ጋር የመተባበር አዝማሚያ አለው፡፡ በራስ ገዞቹ የሚገኙት ወደቦች በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ይተዳደራሉ፡፡ በርካታ ሶማሊያውንም በገልፍ አገሮች በሥራ ላይ በመሰማራት ለአገራቸው ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እያደረጉ በመሆኑና በሌሎችም ምክንያት የገልፍ አገሮች ቀውስ የሶማሊያን አንድነትና መረጋጋት የሚፈታተን ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል የገልፍ አገሮች ቀውስ ያመጣውን ንፋስ በአግባቡ የምትጠቀምበት ሱዳን በዳርፉር፣ በኮርዶፋንና በብሉ ናይል ጉዳይ የምታደርገውን ድርድር ችላ እያለች መጥታለች ተብሎ ይታመናል፡፡ በመሆኑም የገልፍ አገሮች ፖለቲካዊ ሞገድ የአገሮችን የውስጥ ጉዳይ እያመሰው መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በአሜሪካ በከፈል የተነሳላት ማዕቀብና ሕገወጥ ስደትን በተመለከተ ከአውሮፓ ያገኘችው ድጋፍም በውስጥ ጉዳይ ተፅዕኖ እያሳደረበት ይገኛል፡፡

ይህ ሁሉ የፖለቲካ ጨዋታ ኢትዮጵያን ዋጋ የሚያስከፍላት ይመስላል፡፡  የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የሚሊታሪ የጦር ሠፈር የመሠረተችው በኤርትራ ነው፡፡ ግብፅ ኳታርን አግላይ ከሆኑ አገሮች ዋነኛዋ በመሆኗና ቀይ ባህርን ለመቆጣጠር ብርቱ ጥረት እንደማድረጓ የኢትዮጵያ ራስ ምታት ሆና ትቀጥላለች፡፡ ግብፅ የአፍሪካ ቀንድንና የገልፍ አገሮችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጨዋታ ለመቀየር ሱዳንና ኢትዮጵያን አንደኛውን የገልፍ ምህዋር ብቻ እንዲከተሉ ኢቀጥተኛ ተፅዕኖ ልታደርግ ትችላለች፡፡ የሳዑዲ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ምህዋርን ወይም የካታርን ምህዋር ብቻ መከተል ሱዳንን ሆነ ኢትዮጵያን ዋጋ ሊያስከፍላቸው ይችላል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ የኢጋድ መሪነት ሚናን ሊያዳክም የሚችል ውሳኔ ለማስወሰን ግብፅ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ኤርትራም ግብፅ በቀላሉ የምትጋልባት ፈረስ መሆኗም ለኢትዮጵያም ሆነ ለሱዳን ማይመች ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ከቀይ ባህር በስተምሥራቅ የሚገኙ የባህረ ሰላጤው አገሮች የኢንቨስትመንትና የልማት ፋይናንስ ምንጭ፣ እንዲሁም ለግብርና ምርቶች ሰፊ ገቢያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቁማል፡፡ በመሆኑም የአካባቢውን ሰላምና መረጋጋት በጋራ ማረጋገጥ ተገቢ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ የአክራሪነትና የሽብርተኝነት ደጋዎች በአካባቢው እየተጠናከረ መሄዱንም በሥጋትነት ያየዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት በተሟላ ምርምርና ጥናት ላይ የተመሠረተ የውጭ ግንኙነት ማድረግ፣ በዓባይ ጉዳይ ያለንን ፖሊሲ ማስረዳት፣ በሃይማኖት እኩልነት ላይ ያለንን ፖሊሲና ተግባር ማስመስከር፣ የአካባቢው መንግሥታትና ሕዝቦች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን የተዛባ አመለካከትና ዝቅተኛ ዕውቀት ማስተካከል፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ከአካባቢው አገሮች ጋር መመካከርና መደጋገፍ፣ እንዲሁም በጎ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚሉት ነጥቦች የፖሊሲ አቅጣጫዎች በመሆን ተቀምጠዋል፡፡

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ የገልፍ አገሮች  የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ምንጮች፣ እንዲሁም ለግብርና ምርቶች ሰፊ ገበያ መሆን የሚችሉ መሆኑን ዕውቅና ቢሰጥም፣ የምዕራብ አገሮችን ዋነኛ የኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ምንጮች አድርጎ ያስቀምጣል፡፡ አሁን ዓለም በደረሰችበሁኔታ የምዕራባውያንን ድጋፍ ብቻ እንደ ዋነኛ ምሰሶ መቁጠሩ ተግባራዊነት የሌለው አመለካከት ነው የሚሆነው፡፡ እንደ ቻይና፣ ብራዚል፣ ህንድና የገልፍ አገሮችን ዋና የልማት አጋር በማድረግ ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ዓለም ከዩኒፖላር አስተሳሰብ እየወጣች ለመሆኑ ግልጽ ምልክቶች አሉ፡፡ ቻይና ያቋቋመቻቸው እንደ ብሪክስ የቻይና የልማት ባንክና የኤሺያን የልማትና ኢንቨስትመንት ባንክ ምዕራባውያን ላቋቋሟቸው የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የተሰጡ ምላሾች ናቸው፡፡ የገልፍ አገሮች የሚያደርጉት የልማትና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ከምዕራባውያኑ ጎን ለጎን ተፅዕኖ የሚያሳርፉ እየሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ለእነዚህ አካላት ተመጣጣኝ ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በተግባር እየታየ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው በግልጽ ሊቀመጥ ይገባል፡፡

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን በገልፍ አገሮች አካባቢውን ሰላምና መረጋጋት በጋራ ማረጋገጥ ተገቢ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ በጋራ የተሠሩና ጎልተው የወጡ ጉዳዮች አይታዩም፡፡ ኢትዮጵያ የምታደርገው የሰላም ማስከበር ሒደት እጅግ የጎላና የተከበረ ሆኖ ሳለ፣ በምዕራባውያንና በራሷ ዛቢያ ብቻ የሚሽከረከር የትብብር ማዕቀፍ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የሚደርሱ ከአክራሪነትናሽብርተኝነት ጋር የተያያዙ አደጋዎች መነሻቸውም ሆነ የገንዘብ ምንጫቸው ከገልፍ አገሮች አካባቢ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገሮች ጋር ተባብራ መሥራት አለባት፡፡ ኢትዮጵያ ባላት ታሪካዊ ሚናና በኢጋድ ውስጥ ባላት የአስተባባሪነትና የመሪነት ሚና የቀንዱን አገሮችም ለዚሁ ዓላማ ማስተባበር አለባት፡፡ የአፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ በቀይ ባህር አካባቢ በሚከናወኑ ጂኦ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሲያስቡም ሆነ ሲንቀሳቀሱ አይስተዋልም፡፡ በዚህም ምክንያት አካባቢው በአብዛኛው በሁለትዮሽ ጉዳዮች ናጥ ይስተዋል፡፡ የአካባቢውን ጂኦ ፖለቲካዊ፣ ጂኦ ኢኮኖሚያዊና ጂኦ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን የሚከታተልና የሚያስተባብር አንድ የደኅንነት ተቋም መቋቋም እንዳለበት የሚያመለክቱ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ የቀይ ባህር አካባቢ የአፍሪካ ኅብረት፣ የዓረብ ሊግ፣ ኢጋድና የአካባቢው አገሮች የሚመለከቷቸው በመሆኑ ኢትዮጵያ አንድ ዓለም አቀፍ የቀይ ባህር አካባቢ የደኅንነት ተቋም እንዲቋቋም መንቀሳቀስ ይኖርባታል፡፡

ገልፍ አገሮች በቀንዱ አካባቢ የሚገኙ ወደቦችን የመቀራመት እንቅስቃሴ ጥቂት አገሮችን ቢጠቅምም፣ ኢትዮጵያን የበለጠ ተጋላጭ የሚያደርጋትና ሥጋቷንም በእጅግ የሚጨምር ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው በሚገኙ ወደቦች እየተጠቀመች ቢሆንም፣ የገልፍ አገሮች ተገዥ የምትሆንበት ጊዜ አይመጣም ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጡ ከሞኝነትም በላይ ነው፡፡ የወጪናገቢ ንግዷ፣ እንዲሁም ብሔራዊ ደኅንነቷ የሚረጋገጥበትን መንገድ መሻት አለባት፡፡ ከኤርትራ ጋር ያለችበት ሁኔታ ተቀይሮ ወደ መደበኛ ግንኙነት በሚለወጥበትና የአሰብ ወደብን በጋራ የመጠቀም መብት እንዲፈጠር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ቅኝ ገዥዎች የአገሮችን ድንበር በሚፈጥሩበት ጊዜ ወደቦችን እንዲያገኙና ሰላምና መረጋጋት አብሯቸው እንዲኖር ማድረጋቸውን ከበርካታ የአገሮች ታሪክ መማር ይቻላል፡፡ የኤርትራን አንድ አካሏን በቀጭኑ በማስረዘም ኢትዮጵያ ወደብ እንዳታገኝ በሚመስል አኳኋን የተደረገው ሴራ ለደኅንነት ሥጋት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላትና በቆዳ ስፋቷ ሰፊ ወደብ አልባ አገር በመሆን ተወዳዳሪ አይገኝላትም፡፡ በዓለማችን 475 ሚሊዮን አካባቢ ወደብ አልባ የሆኑዝቦች ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ደግሞ 23 በመቶ በላይ መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ከጎረቤት አገሮች ጋር የምናከናውነውን የኢኮኖሚ ውህደት ፖለቲካዊ ውህደት በማሸጋገር፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ደኅንነትን ማጠናከርና ማስከበር ተገቢ ነው፡፡

የዓባይ ጉዳይን በተመለከተ የገልፍ አገሮች ግንዛቤ ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የባህረ ሰላጤው አገሮች መንግሥታትና ሕዝቦች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው የተዛባ አመለካከትና ዝቅተኛ ዕውቀት ምን ያህል እንደተስተካከለ ለማወቅ ምርምርና ጥናት ቢጠይቅም፣ የተወሰኑ መሻሻሎች እንዳሉ አያጠራጥርም፡፡ ግብፅ ዓረቡ ዓለም ያላትን ተሰሚነት መሠረት በማድረግ ለዓባይ ወንዝ ግድብ መሥሪያ የሚሆን ገንዘብ እንዳይገኝ ስትከላከል ቆይታለች፡፡ አሁንም ግብፅ የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ተስፋ የሚሰጡ አይደሉም፡፡ ወታደራዊ ከበባም ለማድረግ ሌት ተቀን በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህንን እንቅስቃሴዋን ለመግታት ኢትዮጵያ የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ እንቅስቃሴ የገልፍን አገሮች ያካተተ መሆን አለበት፡፡ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ በግብፅ ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማይደርስባት፣ በአካባቢው በሚደረገው የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭትም የገልፍ አገሮች ኢንቨስትመንትን ጭምር እንደሚደግፍ ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የአካባቢውን ደኅንነት በጋራ መጠበቅ አስፈላጊ ነው ሲባልም፣ የግብፅንም የውኃ ደኅንነት ጨምሮ መሆኑን ማስገንዘብ ይጠይቃል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ አገሮችና የገልፍ አገሮች ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ትብብሮከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መጥተዋል፡፡ እነዚህ ትብብሮች ጊዜያዊ ፍላጎቶችን ከማስተንፈስ በላይ በጋራ ፍላጎትና ዘላቂ የልማት ግቦችን ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በሁለቱም አካባቢዎች ትርጉም ያለውና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ውህደት የተቃኘ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን ሐሳብ የማመንጨትና የማስተባበሩን ሥራ መውሰድ ይኖርባታል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው ኢኮኖሚያዊ በሆነ ምክንያት ኑሯቸውን በገልፍ አገሮች አድርገዋል፡፡ አብዛኞቹ ሕገወጥ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞም በሳዑዲ ዓረቢያ የተከሰተው ሕገወጦችን ከአገር የማስወጣት ዘመቻ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ ማስከተሉ ይታወቃል፡፡  ሕገወጥነትን መስመር በማስያዝ በኩል በኢትዮጵያና በገልፍ አገሮች መካከል እየተደረገ ያለው ውይይትና ስምምነት እጅግ የተንቀረፈፈ ከመሆኑ አንፃር፣ የዜጎችን ገወጥ ስደትና መጉላላት ማስቆም አልተቻለውም፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ከአገሮቹ ጋር ሊኖረው የሚገባውን ሕገወጥ ስደትን የመከላከል ሥራ ጊዜ በማይሰጠው አግባብ ማከናወን አለበት፡፡

በአካባቢው አገሮች መካከል በርካታ ግጭቶች ሲደርሱ እየተስተዋለ ነው፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን፣ በኤርትራና በጅቡቲ እንዲሁም በሳዑዲ መራሹ የአገራት ጥምረትና በኳታር መካከል ያልተፈቱ ችግሮች የአካባቢውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ዕድገት ከማዘግየት በቀር የሚፈይዱት አንዳችም ነገር የለም፡፡ በገልፍ አገሮች መካከል ግጭት በተከሰተበት ወቅት ኢትዮጵያ ወገንተኛ አለመሆኗና ኩዌት ለጀመረችው የዕርቅ ማዕድ ድጋፏን መስጠቷ፣ ውዝግቦችን በሸምግልናና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት በሚደረጉ የወደፊት ሁኔታዎች ሥፍራ ሊኖራት እንደሚችል አመላካች ነው፡፡

በአጠቃላይም በገልፍ አገሮች የሚፈጠር ማናቸውም ትኩሳትና ቅዝቃዜ የማናመልጠው ሀቅ መሆኑን ተገንዝበንና የውስጥ ጉዳያችንንም በጥልቀት በማሻሻል የሚደርሱብንን ተፅዕኖዎች በመቋቋም፣ እንዲሁም የሚገጥሙንን ዕድሎች እየተጠቀምን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለቀንዱ አገሮችና ለቀይ ባህር አካባቢ፣ እንዲሁም ለገልፍ አገሮችም ሰላምና ልማት ጠንክረን ለመሥራትና ለመውጣት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ለጦርነት የሚጋብዙና ጠርዝ ላይ የወጡ ጉዳዮችን ወደ ቦታቸው በመመለስ ዲፕሎማሲና ዲፕሎማሲ ብቻ የወዝግቦች መፍቻ እንዲሆን ማድረግ ግዴታችን ነው፡፡

ከአዘጋጁ- ጸሐፊው በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ የጥናት ኢንስቲትዩት   ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡