Skip to main content
x

የዘመነ አክሱም ጸዳል

ቀደምት የሆኑ ኢትዮጵያውያን ክብረታቸውና ብልጽግናቸው ከማዕድን በተገኘው ዕቃ በኩል መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ለዚሁም ማስረጃ በዚያ ዘመን በአክሱም ላይ ነግሦ የነበረው ንጉሥ በስሙ የሠራቸው የወርቅና የብር ገሞቦዎችና የወርቅም ጋሻዎች የፈረስና የበቅሎ መጣምሮች ከጦርም መሣሪያ ወገን የሰይፍ ሽኾሮና የጉራዴ አሽሟጣጭ ናቸው፡፡ ከቀንድም ዕቃ ወገን ዋንጫና ከዘራ የካራና የጭራ እጄታ፤ እነዚህን የመሳሰሉት ዕቃዎችና የንግድ መለዋወጫ የሚሆኑትንም ገንዘቦች በአዱሊስ ወደብ ላይ አግኝቶ በማድነቅ አውሮፓዊው ጸሐፊ ጽፎአል፡፡

      የአዱሊስን ከተማ አይቶ ከሄደ በኋላ ወደ ደጋው ኢትዮጵያ ወጥቶ አሁን ቆሐይቶ ወደ ተባለችው ያን ጊዜ ግን ቆሎየ ስትባል ወደነበረችው ከተማ ደረሰ፡፡ ከዚያም ከተማ ተነስቶ ወደ አክሱም ሲሄድ የተጠረገ ደኅና መንገድ አገኘ፡፡ ያውም የተጠረገው ሰፊ ጎዳና ከአዱሊስ ጀምሮ እስከቆሎየ፤ ከቆሎዬ እስከ አክሱም ዋና ከተማ ድረስ የሚያደርስ ነበረ፡፡ የመንገዱም ርቀት ከአዱሊስ ጀምሮ እስከ ቆሎየ ድረሰ በእግረኛ መንገድ ሦስት ቀን ያስጉዛል፡፡ ከቆሎየ ጀምሮ እስከ መናገሻይቱ ዋና ከተማ እስከ አክሱም ድረስም አምስት ቀን የሚያስኬድ መሆኑን ገልጾ በታሪክ መጽሐፉ ላይ ጽፎ አስረድቶአል፡፡

  • አባ ጋስፖሪኒ ገብረ ማርያም ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› (1948)