Skip to main content
x
በቂሊንጦ ቃጠሎ ተጠርጥረው የተከሰሱ 38 ተጠርጣሪዎች ለብይን ተቀጠሩ

በቂሊንጦ ቃጠሎ ተጠርጥረው የተከሰሱ 38 ተጠርጣሪዎች ለብይን ተቀጠሩ

  • የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች እንዳይሰሙ ብይን ተሰጠ
  • ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥሰት ተፈጽሞብናል ያሉ ተከሳሾችን ጉዳይ እንዲያጣራ ታዘዘ

በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የቂሊንጦ ተከሳሾች ማቆያ ቃጠሎ ጋር በተገናኘ ክስ የተመሠረተባቸው በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ መዝገብ፣ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ 38 ተከሳሾች ለብይን ተቀጠሩ፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ ሲመለከት የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ብይኑን የሰጠው ዓርብ ጥር 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ በዕለቱ መዝገቡን ቀጥሮ የነበረው ቀደም ባለው ቀጠሮ መጥሪያ ደርሷቸው ሳይቀርቡ የቀሩ የዓቃቤ ሕግ ሁለት ምስክሮችን ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርብና ያልቀረቡበትን ምክንያት አስረድተው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች መቅረብ አለመቅረባቸውን ሲያረጋግጥ፣ በዕለቱ የቀረቡት ዓቃቤ ሕግ ‹‹የቀረበ ምስክር የለም፡፡ ፖሊስ ምስክሮቹን ለምን እንዳላቀረበ ምላሽ አልሰጠንም፡፡ ፖሊስ ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አክብሮ እንዳላቀረበ እንዲጠየቅና በሌላ ቀጠሮ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥልን ይታዘዝልን፤›› ብለዋል፡፡ የዶ/ር ፍቅሩ ጠበቆች በሰጡት ምላሽ እንደተናገሩት፣ የዓቃቤ ሕግ ምላሽ በማንኛውም ሚዛን አጥጋቢ አይደለም፡፡ ከዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ጋር በተገናኘ ብዙ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡ የዓቃቤ ሕጉ ምላሽ ሒደቱን የተዛባ ከሚያደርግ በስተቀር የተፋጠነ ፍትሕ ለመስጠት የሚያስችል ስላልሆነ ፍርድ ቤቱ የህሊናና የሕግ ፍርድ መስጠት ስላለበት፣ የዓቃቤ ሕጉን ምላሽ ውድቅ በማድረግ በተሰሙት ምስክሮች ብቻ ብይን እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ የሌሎቹም ተከሳሾች ጠበቆች ተቃውሞአቸውን በማከል፣ ዓቃቤ ሕግ አለኝ የሚለውን ማስረጃ እንዲያቀርብ እንደተፈቀደለትና ፖሊስም ተከታትሎ የደረሰበትን ሁኔታ ማወቅ ሲገባው ሳያደርግ መቅረቱ ሥራውን እንዳልሠራ የሚያሳይ በመሆኑ፣ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፍርድ ቤቱንና የጠበቆችን ጊዜ ከማጥፋቱም በተጨማሪ ዋስትና ተከልክለው በእስር ላይ የሚገኙ ደንበኞቻቸው የተፋጠነ ፍትሕ እንዳያገኙ የሚያደርግ በመሆኑ የዓቃቤ ሕግ ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ብይን እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

ከተከሳሾቹ የተወሰኑት አስተያየት እንዳላቸው ጠይቀው ሲፈቀድላቸው እንደገሉጸት፣ ምን ጊዜም ቢሆን ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ጨርሻለሁ ብሎ ብይን እንዲሰጥ የጠየቀበት ጊዜ የለም፣ አይኖርምም፡፡ ዓቃቤ ሕግ የሚፈልገው ወይም እያደረገ ያለው እልህ ማስጨረስ መሆኑንና እንደሚያዝኑ፣ ሕግ አክብረው እየተመላለሱ ዓቃቤያነ ሕግ እየተቀያየሩ አዳዲስ ነገር ይናገራሉ ብለዋል፡፡ ይህ በአገሪቱ ውስጥ ፍትሕ እንደሌለ ማሳያ መሆኑን፣ ዓቃቤ ሕግ ምንም ምስክር እንደሌለውና የመጡለትም ምስክሮች ለእነሱ መስክረው መሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ በተሰጣቸው ጊዜ ከላይ የገለጹትን ከደገሙ በኋላ፣ ብይን ይሰጥ ስለተባለው ነገር ከሌሎች ዓቃቢያነ ሕግ ጋር ተነጋግረው መልስ እንዲሰጡ የአንድ ሳምንት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ብይን፣ ዓቃቤ ሕግ ለምን ምስክሮቹ እንዳልቀረቡ አሳማኝና በቂ የሆነ ምክንያት አለማቅረቡን ገልጾ ቀሪ ምስክሮቹ ሳይሰሙ መታለፋቸውን አስታውቋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የምስክሮቹ ዝርዝርና የሰነድ ማስረጃዎቹን ማቅረቡን የተከሳሾች ጠበቆች አስታውሰው፣ ፍርድ ቤቱ በተሰሙት የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል ክሱንና ማስረጃዎቹን መርምሮ ብይን ከመስጠቱ በፊት፣ በሰነዶቹ ላይ ማብራሪያ እንዲያቀርቡ የጠየቁትን በሚመለከት እንዲያቀርቡ ፈቅዷል፡፡ መርምሮ ብይን ለመስጠትም ለመጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተገናኘ በሌላ ችሎት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የቀረበባቸው 21 ተከሳሾች ‹‹የደረሰብን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጣርቶ ትዕዛዝ ሳይሰጥልን ክሳችን መሰማት የለበትም፤›› በማለታቸው፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ ቀደም ብሎ ክሳቸው ይታይ የነበረው በሦስተኛ ወንጀል ችሎት የነበረ ቢሆንም፣ ከላይ ያነሱትን የመብት ጥሰት ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለንም በማለት በፈጠሩት ሁከት የክስ መዝገባቸው ወደ 10ኛ ወንጀል ችሎት ተቀይሯል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ለደረሰው የቂሊንጦ እሳት ቃጠሎ ምክንያቱ እነሱ መሆናቸውን እንዲያምኑ፣ በወቅቱ በተወሰዱባቸው ሸዋሮቢትና ዝዋይ ማረሚያ ቤቶች የደረሰባቸውን ድብደባ ልብሳቸውን በችሎት በማውለቅ አሳይተዋል፡፡ ወደ ማቆያ ቤት ሲገቡ በሰውነታቸው ላይ ስላለ ምልክት ተመዝግበው መግባታቸውን ገልጸው፣ የተወሰኑት በድብደባ ጥርሳቸው መውለቁን፣ የብልታቸው ፍሬ መፍሰሱን፣ እጃቸው ላይ ስብራት መድረሱን፣ ጥፍራቸው መነቀሉንና ድብደባ የደረሰባቸው ከማንነታቸው ጋር በተገናኘ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ተከሳሾቹ ስለደረሰባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያስረዱ በችሎት የተገኙት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እስረኞች አስተዳደር ኃላፊ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ጥላሁን አየለ፣ ‹‹የጠቀሱት በደል ደርሶባቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን እውነት ወይም ሐሰት ስለመሆኑ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ሕግ የያዘው ጉዳይ ነው፡፡ በማንነታቸው የደረሰባቸው ነገር ስለመኖሩም አላውቅም፡፡ ሁሉ ነገር በተሟላና ለእነሱ ማቆያ በሚመጥን ቤት ውስጥ ናቸው፡፡ እነሱ ባህሪያቸውን ካስተካከሉና በጥበቃ ላይ ያለውን ወታደር ወደ መጥፎ ነገር የሚመራ ትንኮሳ ካላደረጉ ማንም አይነካቸውም፡፡ እኛም የሕግ ተጠያቂነት አለብን፤›› ብለዋል፡፡ ኃላፊቱን ወስደው ደርሶብናል ስላሉት ነገርም ለማጣራት ቃል ገብተዋል፡፡ ‹‹ከመንግሥትም የተሰጠው አቅጣጫ ልንንከባከባቸውና ልንጠብቃቸው እንጂ ልንወነጅላቸው ስላልሆነ፣ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ተከሳሾቹ ያነሷቸው የአያያዝ ሁኔታዎች ተስተካክለውና አሉብን ያሏቸው ችግሮች ተቀርፈው በቀጣይ ቀጠሮ ኃላፊው ቀርበው እንዲያስረዱ አሳስቧል፡፡ ተከሳሾቹ ልብሳቸውን በማውለቅ ለችሎቱ ሰውነታቸውን እያሳዩ ተፈጽሞብናል ስላሉት የመብት ጥሰት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መርምሮና አጣርቶ መጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ሪፖርት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ የተከሳሾቹን ክስ ለመስማት ለጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡