Skip to main content
x

ጀግንነት በአካባቢ ተወላጅነት አይቃኝም

ከወራቶች በፊት ኢቢኤስ EBS ቴሌቪዥን ጃገማ ኬሎ ሐውልት እንዲቆምላቸው የሚጠይቅ ኮሜቴ በቀድሞው ፕሬዚዳንት የመቶ ዓለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የበላይ ጠባቂነት መቋቋሙን የሚያበስር ዝግጅት ተላልፎ ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ ፕሬዚዳንት ግርማን ለረዥም ጊዜ የማውቃቸው በመቶ እልቅናቸው ስለሆነ ይኼንኑ ማዕረጋቸውን ተጠቅሜያለሁ)፡፡ መቶ አለቃ ግርማ በንጉሡና በደርግ መንግሥት በተለያዩ ኃላፊነቶች ማገልገላቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በአሁኑ መንግሥትም ፕሬዚዳንት ሆነው ተሿሚና ተሰናባች አምባሳደሮች ሲቀበሉና ሲሸኑ እንደቆዩ ይታወቃል፡፡ በጉዳዩ ዙርያ ጥያቄ እንዳቀርብ ይፈቀድልኝና ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯ ተከብሮና አንድነቷ ተጠብቆ እንድትኖር የገዘፈ ታሪክ ሠርተው ያለፉ ሲቪልና የጦር መኰንኖች ተረስተው የአንድ ግለሰብ ዝና ጎልቶ የወጣበት ምክንያት ምንድነው? የዝክረ ጃገማ ኬሎ ጊዜያዊ ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ ቀርቦ ለመነጋገር ፕሮግራም እንዲያዝለት ታኅሳስ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ሲጠይቅ፣ ተከብረው ስላስከበሩን እውቅናና ከበሬታ ስለተቸራቸው ወታደራሮች፣ ጠበብቶችና ዲፕሎማቶች ለምን አላነሳም? ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?

ከውትድርናው ዓለምና ጄኔራል መርዕድ መንገሻ፣ ሙሉጌታ ቡቢ፣ ኢሳያስ ገብረ ሥላሴ፣ መንግሥቱ ነዋይና ከበደ ገብሬንና ሌሎችንም ሳላነሳ የሦስት ጄኔራሎችና የአንድ ኮሎኔል ገድል ከዘረዘርኩ በኋላ አራት ሲቪል ዲፕሎማቶች በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ስለነበራቸው እውቅና አብራራለሁ፡፡ ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም የተወለዱት በግብፅ (ካይሮ) ሲሆን ትምህርታቸውንም እዚያም ተከታትለዋል፡፡ ንጉሡ ከስደት ሲመለሱ ሱዳን ውስጥ ተቀላቅለው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት አንዱ ናቸው፡፡ በትውልድ ኤርትራዊ ቢሆኑም በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ የሠራዊቱ ምሰሶ የነበሩ ናቸው፡፡ በ1956 ዓ.ም ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በተካሄደው ጦርነት በሦስተኛ ክፍለ ጦር አዛዥነታቸው በሰጡት ወታደራዊ አመራር ይታወቃሉ፡፡ አዛውንት ሶማሊያውያን ጀግና እያሉ ሲያወድሷቸው እኛ ደግሞ አማን ‹‹ኮዳ ትራሱ›› እያልን እንጠራቸዋለን፡፡ ጄኔራሉ በአሜሪካ የኢትዮጵያ የትምህርት አታሺ፣ በኮሪያ ለዘመተው የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል አዛዥ፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልና በኋላም የደርጉ ሊቀመንበር በነበሩበት ጊዜ የኤርትራን ችግር በፖለቲካዊ አግባብ ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንዳሉ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚባል ተራ ነፍሰ ገዳይ በሰጠው ትዕዛዝ፣ በኮሎኔል ዳንኤል አስፋው የሚመራ ቅልብ ኃይል መኖሪያ ቤታቸው እንደተከበበ ሲያውቁ ተታኩሰው ራሳቸውን አጥፍተዋል፡፡

ጄኔራል ዓቢይ አበበ (የንጉሡ አማች) የአገር መከላከያ ሚኒስትር፣ በኤርትራ ክፍለ አገር የንጉሡ እንደራሴ፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ በፈረንሣይ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ሠርተዋል፡፡ ጄኔራል ዓቢይ በኤርትራ የነበረውን የፖለቲካ ውጥረት በማርገብ ሕዝቡ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ከማስቻላቸው በተጨማሪ በፈረንሣይ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተዋጣላቸው ዲፕሎማት ለመባል በቅተዋል፡፡ አውቀን እንጠንቀቅ የሚል መጽሐፍ ደራሲም ነበሩ፡፡ በመጨረሻም ደርግ በሚባል የጁንታ ስብስብ ያለፍርድ ተገድለዋል፡፡

ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ከሐረር ጦር አካዳሚ በማዕረግ ከተመረቁ በኋላ አየር ኃይሉን በመቀላቀል በአገር ውስጥ ባካበቱት ልምምድና በአሜሪካ የበረራ ትምህርት ቤት በወሰዱት ሥልጠና የተዋጊ ጄት አይሮፕላኖች አርክቴክት እየተባሉ ለመጠራት በቅተዋል፡፡ ለገሠ ተፈራ በ1969 ዓ.ም. በተካሄደው የኢትዮጵያ ሶማሌ ጦርነት በፈጸሙት ጀብዱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ይታወቃሉ፡፡ በደርግ መንግሥትም በወቅቱ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የጀግና ሜዳሊያ ተጠልቆላቸዋል፡፡ የሶማሊያ አውሮፕላኖች እርስ በእርሳቸው እየተጋጩ እንዲወድቁ በማድረግ ላይ እንዳሉ ተመርተው በመውደቃቸው ተማርከዋል፡፡ 11 ዓመት በእስር ቤት ማቀዋል፡፡ በፀሐይ ብርሃን ዕጦት የማየት አቅማቸው ቀንሷል፡፡ ከ69ኙ ጦርነት በፊት ባሌ አካባቢ ተደርጎ በነበረ ውጊያ ተመተው የነበሩ ቢሆንም፣ በጃንጥላ እንደወረዱ 30 ዓመታት አሜሪካ ኖረዋል፡፡ በመጨረሻም በተፈጥሮ ሞት ሕይወታቸው አልፎ ለአገራቸው አፈር በቅተዋል፡፡

ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ደግሞ በሥራ ባልደረባቸው ለበረራ የተፈጠረ ሰው በመባል ይታወቃሉ፡፡ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የበረራ ትምህርት ቤት መምህር በነበሩበት ጊዜ በርካታ ፓይለቶችን ማሠልጠናቸው ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ አየር ኃይል የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና በመውሰድ ከቀዳሚዎቹ አብራሪዎች ተርታ መሠለፍ አስችሏቸዋል፡፡ በዛብህ ጴጥሮስ በሶማሊያ ጦር ላይ ባወረዱት የቦንብ ናዳ ሠራዊቱ ተበታትኖ እንዲቀርና ቀሪውም እጁን እንዲሰጥ በማድረግ ወታደራዊ ተልዕኳቸውን ከተወጡ በኋላ እንደገና ዘመቻ ፀሐይ ግባት (Operation Sunset) ተብሎ በተሰየመው የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ኤርትራ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ወታደራዊ ምሽጎችን አፈራርሰው ሲመለሱ ተመተው በመውደቃቸው በሻዕቢያ ተዋጊዎች ተማርከዋል፡፡

እኚህ ጀግና በሕይወት ይኖራሉ ተብሎ ባይገመትም ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት መረጃ የመስጠት ግዴታቸውን አልተወጡም፡፡ እኛም በፀፀት እያሰብናቸው እንኖራለን፡፡ የኢቢሲ ጋዜጠኞችም ለሥርዓቱ ያላቸውን ታማኝነት ለመግለጽ ከመሽቀዳዳም ያለፈ ራዕይ ስለሌላቸው ሕዝቡ ማግኘት የሚገባውን መረጃ ነፍገውታል፡፡ ጋዜጠኝነት እነበዓሉ ግርማ ያለፉበት ሙያ መሆኑን አያውቁትም፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ጋዜጠኞች የተመረቁት የት ነው?

ከሲቪሉ ዓለም እነ መኰንን ሀብተ ወልድ፣ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ (ፀሐፊ ትዕዛዝ)፣ ተስፋዬ ገብረ እግዚአብሔር፣ ዶ/ር እንዳልካቸው መኰንን ልጅ፣ ተክለ ሐዋሪያት ተክለ ዮሐንስ (ደጃዝማች)፣ ታከለ ወልደ ሐዋሪያት (ደጃዝማች) እና ይልማ ደሬሳን ከቀደሙት ደግሞ ኃይለ ጊዮርጊስ ዲነግዴን (ፊት አውራሪ) እንዲሁም ሌሎች ገናናዎችን ሳላካትት ወይም ሳልጨምር ማለት ነው፡፡

አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ ሎሬንሶ (መብራህቱ) ትዕዛዝ፣ በየነ ባራኪ (ደጃዝማች)፣ አስፍኃ ወልደ ሚካኤል (ቢትወደድ) እና ዲሚጥሮስ ገብረ ማርያም (ንቡረዕድ) ስለኢትዮጵያ የከፈሉትን የሕይወት መስዋዕትነት ሳላነሳ ለማለፍ ብሞክር የሕሊናዬ እረፍት ማጣት ዋጋ ያስከፍለኛል፡፡

ከፈረንሣይ በሕግ የተመረቁት ምሁሩ አክሊሉ ሀብተ ወልድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከማቋቋም ጀምሮ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በነበራቸው አርቆ አስተዋይነትና ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ኤርትራ ከጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ታላቅ የኢትዮጵያ አካል መሆን የሚያስችላትን አጀንዳ በመጀመርያ ሊግ ኦፍ ኔሽን (League of Nations) በኋላም ዩናይትድ ኔሽን (United Nations) በመባል ለሚታወቀው ዓለም አቀፍ ተቋም በማቅረብና ይሁንታን ለማግኘት ያልወጡት ተራራ ያልወረዱት ቁልቁለት አልነበረም፡፡ ጣሊያን ኤርትራን በቅኝ ግዛት ለማቆየት በነበራት ፍላጎት የላቲኖቹን የድጋፍ ድምፅ በማግኘቷና የሐይቲው ተወካይ በወሰደው ያልተጠበቀ የአቋም መንሸራተት የኤርትራ ጉዳይ ውሳኔ ሳያገኝ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ጠቢቡ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ተቃውሞ ጎራ የተሠለፉትን መሪዎች በተናጠል በማግኘት ከዓድዋ ጦርነት ማግስት ጀምሮ የነበረውን የታሪክ ክፍተት እንዲገናዘቡ ካደረጉ በኋላ በሰበሰቡት ድምፅ፣ ጣሊያን በኤርትራ ላይ የነበራት የቅኝ ግዛት ጥያቄ በመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ተቀባይነት እንዲያጣ ያስቻሉ የዲፕሎማሲ ሳይንቲስት ነበሩ፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ ለጥቁር አሜሪካኖች፣ ኢንድ ራጋንዲ ለህንድ ሕዝቦች፣ የሀብተ ወልድ ልጅ ለኢትዮጵያ አንድነትና የባህር በር ባለቤትነት ያደረጉት ተጋድሎ በተመሳሳይነት ሲወጣ ይኖራል፡፡ እኚህ ሰው በአሁኑ ወቅት ዚምባቡዌ ውስጥ ተደብቆ በሚኖር ወንበዴ ግለሰብ የተገደሉ ናቸው፡፡

ሌሬንሶ (መብራህቱ) ትዕዛዝ ከንጉሡ ጋር በስደት እንግሊዝ አገር ከነበሩት ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ ራስ ካሳና አባ ሀና ጋር አብረው የነበሩ ከፈረንሣይ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሩቅ ናቸው፡፡ በትውልድ ኤርትራዊ ቢሆኑም ከእኛ ኢትዮጵያዊ ከምንባለው የበለጠ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ከስደት በኋላም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፣ በአክሊሉ ሀብተ ወልድ በሚመራ የልዑካን ቡድን ውስጥ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው ዲፕሎማት ነበሩ፡፡ ሎሬንሶ በራሺያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በመሾማቸው ወደዚያው በማቅናት ላይ እንዳሉ ስቶክሆልም (ሲዊድን) ባረፉበት ሆቴል ሞተው ተገኝተዋል፡፡

ዳጃዝማች በየነ ባራኪና ቢትወደድ አስፍኃ ወልደ ሚካኤል ሁለቱም የኤርትራ ተወላጆች ይሁኑ እንጂ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራትና አንድነቷም ተጠብቆ እንድትኖር የደከሙ ሐውልት ሊቆምላቸው ሲገባ አስተዋፅኦ በማጣት የትም ወድቀው ከቀሩ ዜጎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ማኅበር (ኘውአት) እና ማኅበር ማዕሳ ወይም ቁጭት የሚባል ድርጀት ከረን ውስጥ በማቋቋም በተቃዋሚው ወልደ አብ ወልደ ማርያም ከሚመራው ሊበራል ፕሮግሬሲቭና ከሌሎች ሦስት ድርጅቶች ጋር የፖለቲካና የትጥቅ ትግል አካሂደዋል፡፡ ከዚያም አልፎ በዓለም በተካሄዱ ታላላቅ ጉባዔዎች እየተገኙ የኢትዮጵያን ባህላዊ አለባበስ አንፀባርቀዋል፡፡ እንባቸውን እያፈሰሱ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል የነበረች መሆኗንና ሕዝቦቿም ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ ኤፍሬም ተክለ መድህን (ብላታ) ከንቲባ ኡስማን፣ ዲሚጥሮስ ገብረ ማርያም (ንቡረዕድ) እና ኢብራሂም ሱልጣን የትግል አጋሮቻቸው ነበሩ፡፡ አስፍኃ ወልደ ሚካኤል (ቢትወደድ) በደርግ ዘመን የአንድ ስሙን መለየት ባልቻልኩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ እንዳሉ በጨፍጫፊነቱ ታሪክ የሚያወሳው ደርግ ለአንድ ዓመት ካሰራቸው በኋላ ተፈተው እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በሕመም ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ስለቀሪዎቹ አሟሟት በታሪክ የተደገፈ ነገር አላገኘሁም፡፡

ኢትዮጵያን እንደ አገር ካቆሟት ወታደራዊና ሲቪል ዲፕሎማቶች ውስጥ የጥቂቱን ግለ ታሪክ መዘዤ የጻፍኩት ዝክረ ጃገማ ጊዜያዊ ኮሚቴ ተብየው በቀበሌኛ አመለካከት የታጠረ የግለሰቦች ስብሰባ መሆኑን በማሳየት አገሪቷ በነማን ስትመራ እንደቆየች ለወጣቱ ትውልድ ለማስተዋወቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኮሚቴው አባላት አገራዊ አጀንዳ የሌላቸው በቀደመ ስማቸው የሚንገታገቱ ሌላው ቀርቶ እነ አክሊሉ ሀብተ ወልድን ለመዘከር ቅንነት የጎደላቸው ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ እየሄዱበት ያለው የታሪክ ማዛባት ከፍተኛ አቧራን የሚያስነሳ ተቃውሞ ያስከትላል፡፡ ጊዜውን ጠብቆም ቢሆን በደርግ ጥይት እየተደበደቡ የወደቁ፣ የበረሃው አሞራ የጎተታቸው የአፍ አቤት፣ የናቅፋና የምፅዋ፣ ጀግኖች የሚታወሱበት ፋውንዴሽን መመሥረቱ የፍላጎት ሳይሆን የታሪክ አስገዳድጅነት ይመጣል፡፡ ዝክረ ጃገማ ጊዜያዊ ኮሚቴም ቆም ብሎ የማሰብ ጊዜ ይኖረው ይሆናል፡፡ ብቻ ዕድሜ ይስጠን፡፡

(ውብሸት ተክሌ፣ ከገርጂ)