Skip to main content
x
ለነዳጅ ታሪፍ ጭማሪ የዘገየው የመንግሥት ምላሽ አንድምታ

ለነዳጅ ታሪፍ ጭማሪ የዘገየው የመንግሥት ምላሽ አንድምታ

የነዳጅ ትርፍ ህዳግ (ታሪፍ) ለዓመታት ባለመስተካከሉና የዘርፉ ቢሮክራሲ ከመቃናት ይልቅ እየተወሳሰበ በመቀጠሉ፣ በርካታ የነዳጅ ማመላለሻ ትራንስፖርት ባለቤቶች እንዲሁም የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ሥራ ማቆምን አማራጭ አድርገው ማሰብ ጀምረዋል፡፡

ነዳጅ ለኢትዮጵያ ዋነኛው ስትራቴጂክ ሸቀጥ ቢሆንም፣ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመንፈጉ የነዳጅ ዘርፍ ነጋዴዎች ለኪሳራ በመዳረጋቸው ኪሳራውን መሸከም የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን አበክረው እያሳወቁ ነው፡፡ በመንግሥት ቸልተኝነት እያዘኑ ከሚገኙ ዋነኛ የነዳጅ ዘርፍ ተዋናዮች መካከል አቶ ፀጋ አሳመረ ይገኙበታል፡፡ የ77 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋው አቶ ፀጋ፣ በኢትዮጵያ የነዳጅ ማመላለሻ ትራንስፖርት፣ በነዳጅ ማደያ ዘርፍ እንዲሁም በነዳጅ ማከፋፈል ዘርፍ ውስጥ ለ56 ዓመታት ጉልህ ሥፍራ ይዘው ቆይተዋል፡፡

ፀጋ አሳመረና ቤተሰቡ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በነዳጅ ማመላለሻ ትራንስፖርት ዘርፍ፣ በከባድ ተሽከርካሪዎች መለዋወጫ አቅርቦት ዘርፍ፣ በነዳጅ ማደያ ዘርፍና በመሳሰሉት ሥራዎች የተሰማራ የንግድ ድርጅት ነው፡፡ ባለቤቱ አቶ ፀጋም በኢትዮጵያ የመጀመርያውና በኢትዮጵያውያን የተቋቋመውን የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም አክሲዮን ማኅበርን ከወዳጆቻቸው ጋር የመሠረቱና ማኅበሩንም ለረዥም ዓመታት የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የመሩ ናቸው፡፡

አቶ ፀጋ ሌላው ከሚታወቁባቸው ሥራዎች መካከል በነዳጅ ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከመንግሥት ጋር የሚሟገቱ መሆናቸው ተጠቃሽ ሲሆን፣ ከምርጫ 97 ቀውስ በኋላ በአገሪቱ ሰላማዊ ሠልፍ ማካሄድ ተከልክሎ ሲፈቀድ በኢትዮጵያ ምናልባትም ከ30 ዓመታት ወዲህ ብቸኛውን የኢኮኖሚ ጥያቄ በሰላማዊ ሠልፍ መጠየቃቸው ይገኝበታል፡፡

አቶ ፀጋ ከነዳጅ ዘርፍ ተዋናይ ወዳጆቸው ጋር በመሆን ከመስቀል አደባባይ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ ሰላማዊ ሠልፍ በማካሄድ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በመነጋገር በወቅቱ ለተከሰተው ችግር መፍትሔ አስገኝተዋል፡፡ በአስቸጋሪ መንገዶች ወስጥ አልፈው ዛሬ ላይ የደረሱት ባለፀጋው አቶ ፀጋ ‹‹አሁን ታከተኝ›› ሲሉ በአጠቃላይ ባለፉት 56 ዓመታት ከቆዩበት ነዳጅ ዘርፍ ሊወጡ እንደሚችሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ለአቶ ፀጋና ለነዳጅ ዘርፍ ዋነኛ ተዋናዮች ከሥራ እስከመውጣት ድረስ እንዲያስቡ እያደረጉ ካሉ ችግሮች መካከል መንግሥት ለዓመታት በነዳጅ ዘርፍ የትርፍ ህዳግ ጭማሪ አለማድረጉ፣ የተወሰኑ የነዳጅ ኩባንያዎች ከአሥር ዓመት በላይ ያገለገሉ ከባድ ተሽከርካሪዎችን አንቀበልም ማለት መጀመራቸውና በንግድ ሚኒስቴር የሚመራው ሕጋዊ ሥነ ልክ ቡድን አሠራር ደካማ መሆን ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ ኩባንያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ የነዳጅ አዳዮች አሠሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው መሸሻና የነዳጅ አጓጓዦች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ይስሃቅ አብዱላሂ ኅዳር 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዲያነጋግሯቸው በጋራ ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡

‹‹የነዳጅ ትርፍ ህዳግና የነዳጅ ማጓጓዧ ታሪፍን በተመለከተ ለመወያየት የስብሰባ ጊዜ ስለመጠየቅ›› በሚል ዓብይ ጉዳይ በተጻፈው ደብዳቤ እንደተገለጸው፣ የነዳጅ ሥራን በጥራትና በቅልጥፍና ለማከናወን፣ ለነዳጅ ማከፋፈል ሥራዎችና ማጓጓዣ የሚያስፈልገው የመዋዕለ ንዋይ መጠን እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም፣ በአንፃሩ ለዘርፉ የተመደበው የትርፍ ህዳግና የማጓጓዣ ታሪፍ የሥራ ዘርፉን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገውን ወጪ ከግንዛቤ ያላስገባ ነው፡፡

‹‹ይህንን በተመለከተ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያለው ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት በመቅጠር ጥናት ያስደረግን ሲሆን፣ የጥናቱም ውጤት ለዚህ ዘርፍ የተመደበው የትርፍ ህዳግ ለሥራው ከሚያስፈልጉ ወጪዎችና ከአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን አመላክቷል፤›› የሚለው የነዳጅ ድርጅቶቹ ደብዳቤ፣ ‹‹የትርፍ ህዳግና የማጓጓዧ ታሪፍ ማነስ፣ የግብይት ሥርዓቱ የተሳለጠ እንዳይሆን ዋነኛ ተግዳሮት በመሆኑ ማስተካከያ እንዲደረግበት በዘርፉ ጥናትና ምክረ ሐሳብ ያቀረብን ቢሆንም፣ [ሁለት ዓመት ሆኖታል] እስካሁን መፍትሔ አልተሰጠውም፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት አስቸኳይ ዕርምጃ ካልተወሰደ የሥራ ዘርፉ በኢኮኖሚው ያለውን አስተዋጽኦ በእጅጉ ይጎዳል፤›› በማለት ማኅበራቱ በጻፉት ደብዳቤ ዘርፉ የገጠመውን ፈተና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር እስካሁን ቀጠሮ እንዳልተሰጠ ለማወቅ ተችሏል፡፡ መንግሥት ከዛሬ ነገ ምላሽ ይሰጣል ብለው ቢጠብቁም፣ ምላሹ ግን የውኃ ሽታ ሆኖ እንደቀረ በነዳጅ ሥራ ላይ የሰተማሩ ኩባንያዎች ይናገራሉ፡፡

ለነዳጅ ታሪፍ ጭማሪ የዘገየው የመንግሥት ምላሽ አንድምታ

ዕድገት የፍሳሽ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማኅበር 251 ከባድ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ባለቤት ነው፡፡ የማኅበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይበልጣል ካሳዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዘርፉ የተንሰራፋው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ማኅበሩ የሚያገኘው ገቢ ግን እያሽቆለቆለ ነው፡፡

‹‹የቅርብ ጊዜውን እንኳ ብንመለከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ወዲህ ብር ከዶላር ጋር ያለው ምጣኔ በ15 በመቶ እንዲያንስ ከወሰነ በኋላ የመለዋወጫ ዕቃዎች፣ የተሽከርካሪዎች ሰርቪስ ወጪ በ40 በመቶ ጨምሯል፡፡ ነገር ግን የማጓጓዧ ታሪፍ ላይ ለውጥ ባለመደረጉ ማኅበራችን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቷል፤›› ሲሉ አቶ ይበልጣል ለሪፖርተር ይናገራሉ፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ሦስት ሺሕ አካባቢ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ከብር ምጣኔ ለውጡ በኋላ እስከ አንድ ሺሕ የሚጠጉ ከባድ ተሽከርካሪዎች ዘርፉን ለመቀላቀል እየተዘጋጁ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡

አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ዘርፉን መቀላቀላቸውን ምክንያት በማድረግ የነዳጅ ኩባንያዎች ከአሥር ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን ላለመቀበል አዝማሚያ እያሳዩ መሆኑ አቶ ይበልጣልን፣ አቶ ፀጋንና በዘርፉ ተሰማርተው የቆዩ ባለንብረቶችን በእጅጉ አሳስቧል፡፡

አቶ ይበልጣል እንደሚናገሩት፣ በአስተሳሰብ ደረጃ ሁሉም የነዳጅ ኩባንያዎች አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን የማሠራት ፍላጎት እያሳዩ ነው፡፡ ነገር ግን ከአሥር ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ዕቃ እስከተቀየረላቸው ድረስ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ እየሠሩም ነው፡፡ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ አንፃርም እነዚህን ተሽከርካሪዎች ከሥራ ውጭ ለማድረግ መሞከር ብዙ ኪሳራ የሚያመጣ፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ቤተሰቦች መተዳደሪያም እንደመሆኑ መንግሥት ጉዳዩን ሊያየው ይገባል፡፡

አቶ ፀጋም ተመሳሳይ ሐሳብ አለቸው፡፡ አቶ ፀጋ በ1990ዎቹ መጨረሻ ሰላማዊ ሠልፍ የወጡበትን ምክንያት ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ ቶታል 12 የሚጠጉ ባለሀብቶች ከባንክ ጋር አስተሳስሮ 580 አዳዲስ ነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ለማስገባትና 482 ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ያቀደውን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ፡፡ ይህን የተቃወሙት አቶ ፀጋና የዘርፉ ተዋናዮች ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በመወያየት የቶታል ዕቅድ ተግባራዊ እንዳይደረግ ውሳኔ እንዲተላለፍ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድ ባለሀብት ከአሥር ተሽከርካሪዎች በላይ ይዞ ወደ ሥራ መግባት እንዳለበት ኩባንያዎቹ ያስቀመጡት አሠራር ተቃውሞ ቀስቅሶ፣ በተደረገው ሙግትም አንድም ተሽከርካሪም ቢሆን ይዞ መግባት እንደሚችል መወሰኑ ይታወሳል፡፡

የነዳጅ ዘርፍ ተዋናዮች በወቅቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ከነበሩት አምባሳደር ግርማ ብሩ ጋር ሐሳብ በመለዋወጥ እንዲህ ዓይነት ተዕዕኖ የሚፈጠረው አገር በቀል የነዳጅ ኩባንያ ባለመኖሩ እንደሆነ መተማመን ላይ በመድረሱ፣ እነ አቶ ፀጋ የተባበሩት ብሔራዊ ፔትሮሊየም ድርጅቶችን ሊመሠርቱ በቅተዋል፡፡

አቶ ፀጋ እንደሚናገሩት በመሬት ላይ የሚጓጓዝ ተሽከርካሪ ይቅርና በአየር ላይ የሚበረው አውሮፕላን በቂ ሰርቪስ እስካገኝ ድረስ ከ30 ዓመት በላይ ሊበር ይችላል፡፡ የምድር ተሽከርካሪም እንዲሁ በቂ መለዋወጫ እስካለና እስከተጠገነ ድረስ እስከተፈለገው ጊዜ ድረስ እንደሚሠራ አቶ ፀጋ ገልጸው፣ ዘርፉ በርካታ ሰዎች የዕለት እንጀራቸውን የሚያገኙበት በመሆኑ ይኼንን ጠንቀኛ አስተሳሰብ መንግሥት በጥሞና ሊያየው እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

የትራንስፖርት ባለንብረቶች እንደሚያምኑት፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በነዳጅ ማመላለሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከበቂ በላይ ናቸው፡፡ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ቢሞከርም፣ ሊገኙ ባለመቻላቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡

በተለይ አገር ውስጥ ከበቂ በላይ ተሽከርካሪ ቢኖርም አሁንም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በርካታ ተሽከርካሪዎች እየገቡ መሆኑ፣ በአንፃሩ በነባር ተሽከርካሪ የሚጠየቀው የመለዋወጫ ዕቃዎች ጭማሪ፣ የሠራተኞች ደመወዝ፣ የኢንሹራንስና የጂቡቲ መግቢያ ዋጋ ንረት፣ ከሁለት ዓመት በፊት የተጠናው የታሪፍ ጭማሪ ምላሽ አለማግኘቱ፣ ብር ከዶላር ጋር ያለው ምጣኔ እንዲቀንስ ከተደረገ በኋላ የመለዋወጫ ዋጋ 40 በመቶ መጨመሩ የዘርፉ ተዋናዮችን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እያደረሰ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

‹‹ውድቀታችን እየተፋጠነ በመሄድ ላይ ነው፣ ለመውደቅም ቋፍ ላይ ነን፤›› ሲሉ አቶ ይበልጣል ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ለመፍታት በዋናነት አማራጭ ተደርጎ የተወሰነው መንግሥት ለዓመታት ችላ ብሎት የቆየው የታሪፍ ጭማሪ ጉዳይ ነው፡፡ አቶ ፀጋ እንደሚገልጹት፣ አንድ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በጠቅላላ አምስት ሚሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ ከጂቡቲ አገር ውስጥ 42 ሺሕ ሊትር ነዳጅ ለማጓጓዝ የሚከፈለው 42 ሺሕ ብር ነው፡፡ በዚህ ሒደት ለተሽከርካሪው ነዳጅ 15,760 ብር፣ ለሾፌር አባል አራት ሺሕ ብር፣ ለጭነቱ ኢንሹራንስ 560 ብር፣ ለወርኃዊ ኢንሹራንስ 2,250 ብር ከጥቅም ውጭ ለሚሆን ጎማ በትንሹ 9,037 ብር እና ሌሎችንም ወጪዎች ጨምሮ በድምሩ 31,607 ብር ወጪ ይሆናል፡፡

ከቀሪው 10,393 ብር ላይ ለተለያዩ የሠራተኞች የሚከፈል ደመወዝ፣ የሾፌር አራት ሺሕ ብር ወርኃዊ ደመወዝ፣ የዘይት፣ የመለዋወጫ አገልግሎት የባንክ ብድር ወለድና የቢሮና የቢሮ ሠራተኞች ይወስዱታል፡፡

አምስት ሚሊዮን ብር በወጣበት አንድ ተሽከርካሪ ምንም እየተገኘ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት ከተሠሩ ሥራዎች የተገኘ ገቢንም ጨምሮ እየወሰደ በመሆኑ ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆናቸውን አቶ ፀጋ ይናገራሉ፡፡

በነዳጅ ማመላለሻ ዘርፍ የተሰማሩ ባለንብረቶች ላይ አደጋ የጋረጠው የታሪፍ ጉዳይ የነዳጅ ማደያ ድርጅት ባለቤቶች ላይም ከሥራ እስከመውጣት የሚደርስ አደጋ መጋረጡ ተመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች አሠሪዎች ማኅበር ከተመሠረተ ከ50 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በመላ አገሪቱ ከሚገኙ 700 በላይ ነዳጅ ማደያዎች በየጊዜው ችግር ውስጥ እንደሆኑ ከሥራ ለመውጣትም እየተገፋፉ መሆናቸውን ፊርማ እያሰባሰቡ ጭምር መልዕክት ይልኩለታል፡፡ ማኅበሩ ከአባላቱ የሚቀርብለትን እሮሮ በመግለጽ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እየተፈጠረ ያለውን ችግር በዝርዝር አብራርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች አሠሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው መሸሻ ፊርማ መስከረም 2009 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተላከው ደብዳቤ ‹‹ነዳጅ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ስለሚገኝ የማስተካከል ዕርምጃ በመንግሥት በኩል ብቻ የሚገኝ በመሆኑ፣ ጥያቄያችንን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የምናቀርበው በሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ፍትሕ ባለመግኘታችን ነው፤›› በማለት የሚጀምረው የማኅበሩ ደብዳቤ፣ ‹‹ይኼ የነዳጅ አዳዮች የትርፍ መጠን እንዲስተካከል የምናቀርበው አቤቱታ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በቅርብ የተደረገው መጠነኛ ማሻሻያ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ያለመሆኑና በይበልጥም የማደያዎችን አስተዳደራዊ ወጪዎች ማለትም የሠራተኞችን ወርኃዊ ደመወዝ፣ የመገልገያ ዕቃዎች ግዥ፣ የመብራት፣ የስልክና የውኃ እንዲሁም የፅዳት ወጪዎችንና የነዳጅ ጉድለትና ሌሎችንም ወጪዎች ያላገናዘበ መሆኑን ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም፤›› በማለት ደብዳቤው ያብራራል፡፡

‹‹ለሥራ ማካሄጃና ለትርፍ የተመደበው በሊትር 0.175 ሲሆን፣ ይኼም በመቶኛ ሲሰላ ለቤንዚን 0.43 በመቶ፣ ለናፍጣ 0.5 በመቶና ለኬሮሲን 0.5 በመቶ ነው፡፡ ለሁሉም የነዳጅ ዓይነቶች የተቀመጠው የትርፍ ህዳግ ከአንድ በመቶ በታች ነው፡፡ በዓለም ላይ በዚህ ምጣኔ ተሠርቶበትም ታይቶም አይታወቅም፤›› በማለት የአቶ ጌታቸው ደብዳቤ ገልጾ፣ ‹‹በአካባቢያችን በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች የነዳጅ ትርፍ 7.5 በመቶ ነው፡፡ ይኼን ያህል ይደረግልን ባንልም ግማሹን እንኳ ማለትም 3.75 በመቶ እንዲደረግ መጠየቅ አግባብነት እንዳለው መረዳት ይቻላል፤›› በማለት ማኅበሩ 3.75 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ጠይቋል፡፡

አቶ አፈወርቅ ጥላሁንና አቶ ደምሴ ሺበሺ የነዳጅ አዳዮች አሠሪዎች ማኅበር ቦርድ አባላት ናቸው፡፡ አቶ አፈወርቅ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አንድ የነዳጅ ማደያ 45 ሺሕ ሊትር በ800 ሺሕ ብር ይገዛል፡፡ ከዚህ ነዳጅ አጠቃላይ ሽያጭ የሚገኘው ትርፍ 3,100 ብር ብቻ ነው፡፡

በመጀመርያ ደረጃ በ800 ሺሕ ብር ወጪ 3,100 ብር ትርፍ የትም አገር ላይ የለም፡፡ በነዳጅ ማደያዎች እስከ 50 ሠራተኞች አሉ፡፡ ኤሌክትሪክ፣ ውኃ፣ መብራትና ፅዳት ወጪዎች አሉት፡፡ ይኼ ታሪፍ ስለማይበቃ ኪሳራ ውስጥ ነን ሲሉ አቶ አፈወርቅ ይናገራሉ፡፡

አቶ አፈወርቅ ምሳሌ ጠቅሰው ሲያስረዱ አንድ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ታንከር ሰባት ሊትር ነው፡፡ አንድ ባጃጅ ይኼንን ነዳጅ ሲሞላ ነዳጅ ማደያው 49 ሳንቲም ትርፍ ያገኛል፡፡ የባጃጅ አሽከርካሪ ደረሰኝ ከወሰደ ኪሳራ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ቅጠል ደረሰኝ ማተሚያ ዋጋ አንድ ብር ነው፡፡ ከባጃጅ የተገኘው ደግሞ 49 ሳንቲም በመሆኑ የ51 ሳንቲም ኪሳራ ወዲያውኑ ይመዘገባል በማለት አቶ አፈወርቅ የጉዳዩን አሳሳቢነት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የታሪፍ ጭማሪውን በተመለከተ የንግድ ሚኒስቴርና የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ከነዳጅ ዘርፍ ተዋናዮች ተሳትፎ ተደርጎ የተካሄደው የታሪፍ ጭማሪ ጥናት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል ከተባለ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በርካታ የዘርፉ ተዋናዮች ይኼ የታሪፍ ጭማሪ ተግባራዊ ይሆናል በሚል ተስፋ በኪሳራ እየሠሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይኼ ተስፋ ባይኖር እስካሁንም ከሥራ ሊወጡ የሚችሉባቸው ምክንያቶች ሰፊ እንደሆኑም የሚናገሩ አሉ፡፡

የንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰድ ዚያድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የታሪፍ ጭማሪ ጥናቱ ንግድ ሚኒስቴር ከማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ጋር አዘጋጅተን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቅርበናል፡፡ የታሪፍ ጥናቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቀርቧል ከተባለ ረዥም ጊዜው ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ተግባራዊ ያልተደረገው ለምንድነው? ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አሰድ ሲመልሱ፣ ‹‹መንግሥት ያለበትን ሁኔታ ታውቃላችሁ፡፡ መንግሥት በሌሎች ወቅታዊ ሥራዎች ተጠምዷል፡፡ ሰሞኑን ግን ውይይት ተደርጎበት ምላሽ ያገኛል፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ሌላው ለፍሳሽ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ችግር የሆነው የካሊብሬሽን አሠራር ነው፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ከ2004 ዓ.ም. ወዲህ የፍሳሽ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ካሊብሬሽን የመሥራት፣ በሠራው ካሊብሬሽን መጠንም የነዳጅ ኩባንያዎች እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ መሠረት ንግድ ሚኒስቴር ሕጋዊ ሥነ ልክ ቡድን አቋቁሞ ከደረጃዎች መዳቢ ድርጅት በትውስት ቦታ ወስዶ ልኬት እያካሄደ ይገኛል፡፡

የፍሳሽ ማመላለሻ ባለንብረቶችን ከንግድ ሚኒስቴር ጋር እያቃቃረ የሚገኘው ድርጊት ንግድ ሚኒስቴር የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ ባለመጠቀሙ የነዳጅ ኩባንያዎች የሚኒስቴሩን ሥልጣንና ኃላፊነት እየነጠቁ፣ እንዳሻቸው ማድረጋቸው ነው፡፡ አንድ ተሽከርካሪ ሥነ ልክ ለማሠራትና ሰርተፍኬት ለመያዝ ደረጃ መዳቢ ግቢ ለመግባት ወረፋ ይይዛል፡፡ አንድ ተሽከርካሪ ጠቅላላ ዋጋው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ሲሆን፣ አንድ ቢሊዮን ብር የሚያወጡ 200 ተሽከርካሪዎች ተሠልፈው ተራቸውን ይጠባበቃሉ፡፡ ሕጋዊ ሥነ ልክ ቡድን ከዓመት በፊት በቀን ስድስት ተሽከርካሪዎችን የመለካት አቅም የነበረው ቢሆንም፣ ይህንን አሻሽሎ 15 ተሽከርካሪዎችን የመለካት አቅም ላይ አድርሷል፡፡ ነገር ግን ተራ በያዙት ላይ ሌላ ባለተራ የሚደመር በመሆኑ በየቀኑ ሠልፍ ማየት የተለመደ ነው፡፡ አንድ ተሽከርካሪ ልኬት ለማድረግ ከ15 እስከ 30 ቀን ሊፈጅበት እንደሚችል ተገልጿል፡፡ በዚህ እንግልት ውስጥ አልፎ የተለካ፣ ተለክቶም ሰርተፍኬት የተሰጠው ተሽከርካሪ ወደ የነዳጅ ኩባንያዎች በሚሄድበት ወቅት ኩባንያዎች ልኬቱ ትክክል እንዳልሆነና እንደማይቀበሉ በመግለጽ የሚመልሱ በመሆኑ ችግሩ የተወሳሰበ መሆን ብቻ ሳይሆን ንግድ ሚኒስቴር ሥልጣኑን አሳልፎ ሰጥቷል የሚል ቅሬታ በሰፊው እየተደመጠ ይገኛል፡፡

‹‹የንግድ ሚኒስቴር ሕጋዊ ሥነ ልክ ቡድን አንድን ተሽከርካሪ ልኬት አድርጎ ተሽከርካሪው ይህን ያህል ሊትር መጫን ይችላል ብሎ ሰርተፍኬት ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ኩባንያዎች የራሳቸውን ልኬት አድርገው አይሆንም ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ነው፤›› ሲሉ አቶ ይበልጣል ገልጸው፣ ‹‹ምንም ይሁን ምን ንግድ ሚኒስቴር ሥልጣኑን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ የተሰጠውን ሥልጣን አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ሥልጣኑን ለምን እንደማያስከብር አይገባኝም፤›› ሲሉ አቶ ይበልጣል ይናገራሉ፡፡

አቶ ኢብራሂም ኑር ሁሴን የንግድ ሚኒስቴር ሕጋዊ ሥነ ልክ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ አቶ ኢብራሂም ይህ ችግር መኖሩን ያምናሉ፡፡ አቶ ኢብራሂም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሕጋዊ ሥነ ልክ ቡድን ሥራውን እየሠራ የሚገኘው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ አይደለም፡፡ ‹‹የምንጠቀመው ኋላቀር አሠራር በመሆኑ እኛ በምንሰጠውና በተለይ ኦይል ሊቢያ፣ ቶታል አሁን ለጊዜው አቁሟል እንጂ ኖክ በዘመናዊ መሥሪያ ለክተው በሚሰጡት ቁጥር መካከል ልዩነት ሊገኝ ይችላል፡፡ የዚያኔ በድጋሚ እንዲታይ ይመልሳሉ፤›› ሲሉ አቶ ኢብራሂም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ የሚጭኑባቸው ክፍሎች በተለያዩ ቦርዶች የተከፋፈለ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳ ኦይል ሊቢያ በአንደኛው ክፍል 13 ሊትር፣ በአንደኛው ክፍል 60 ሊትር ጉድለት አለው ሲል በድጋሚ እንዲታይ ወደኛ ልኳል፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ኢብራሂም፣ ለመለካት የሚጠቀሙበት መንገድ ኋላቀር መሆኑ እንደገደባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ንግድ ሚኒስቴር ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመግዛት ጨረታ አውጥቶ በሒደት ላይ ነው፤›› ሲሉ አቶ ኢብራሂም ገልጸዋል፡፡

ሕጋዊ ሥነ ልክ ቡድኑ አንድ ተሽከርካሪን የሚለካው ውኃ ተጠቅሞ፣ በሜትር በመለካት ነው፡፡ አንድ ነዳጅ ቦቴ ተሽከርካሪ ግቢ ውስጥ ከገባ በኋላ ውኃ እስኪሞላ፣ መጠበቅ ውኃ ሞልቶ ከተላከ በኋላ ውኃውን ደፍቶ እስኪወጣ ድረስ መቆየቱ አይቀርም፡፡ ልኬቱ ዘመናዊ ባለመሆኑ የሞላውን ውኃም መልሶ ለመድፋት ቦታ ይዞ መጠበቅ የግድ ነው፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ከዚህ ኃላቀር አሠራር ላይ መገኘቱ ጭምር መንግሥት ነዳጅን እንደ ስትራቴጂክ ጉዳይ ይዞታል ወይ? በማለት የሚጠይቁ፣ ይኼ የልኬት ጉዳይ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ብቻ ሳይሆን በተለይ ለነዳጅ ማደያ ባለንብረቶችም ከባድ ችግር መፍጠሩ ይገለጻል፡፡

ነዳጅ የመለጠጥና የመኮማተር ባህሪ አለው፡፡ ከጂቡቲ ወደብ በሚጫንበት ወቅት በ44 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ታሳቢ ተደርጎ ይጫናል፡፡ አዲስ አበባ ሲደርስ የሙቀት መጠኑ በ20 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሊኮማተር ይችላል ተብሎ ታስቦ ይጫናል፡፡

ነገር ግን አዲስ አበባ ነዳጅ ማደያ ሲደርስ 25 እና 27 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያ መሀል ያለውን ልዩነት የሚጠቀመው አካል ራሱን ያውቃል ይላሉ የማደያ ባለቤቶች፡፡ አቶ ደምሴ ሺበሺ እንደሚናገሩት፣ ልዩነቱ በተለያዩ መንገዶች ሾፌሮች ይወስዱታል፡፡ ‹‹ሾፌሮች ሥራ ያቆሙና አገር ይበጠበጣል ተብሎ ሁሉም አካል ጥፋቱን በጋራ ዝም ብሎታል፤›› ያሉት አቶ ደምሴ፣ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ከጂቡቲ የመጣ ነዳጅ በማደያዎች ታንከር ውስጥ ሲራገፍ እስከ 400 ሊትር ድረስ ሊጎድል እንደሚችል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ በአሥር በመቶ እያደገ የሚገኘው የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎት በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ደርሷል፡፡ ለዚህ ነዳጅ ግዥ 2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ወጪ ያደርጋል፡፡ በመንግሥት ባለቤትነት ተገዝቶ እስከ ወደብና ከደረሰ በኋላ ነባርና አዳዲሶቹን ጨምሮ 18 የነዳጅ ኩባንያዎች ይረከባሉ፡፡ በማሠራጨቱ በኩል ደግሞ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ያላቸው ባለንብረቶች ከኩባንያዎቹ ነዳጅን ተረክበው ያጓጉዛሉ፡፡ 700 የሚጠጉ ነዳጅ ማደያዎች ደግሞ በሥርጭቱ ከፍተኛ ሥራ ይሠራሉ፡፡ እነዚህ ኩባንያዎችና ሠራተኞቻቸው በመሉ የታሪፍ ጭማሪውን በጉጉት በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

አቶ ፀጋና የነዳጅ ዘርፍ ተዋናዮች መንግሥት ለነዳጅ ዘርፍ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ትኩረት መስጠት ያለበት ወቅት መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር ወይም ከዘገየ ግን ወይም ተስፋ አስቆራጭ ክስተት ከታየ በርካታ ነባር የነዳጅ ዘርፍ ተዋናዮች ሥራውን ለመተው የሚገደዱ በመሆኑ፣ የሚመጣው ቀውስ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል በተዋናዮቹ ዘንድ ሥጋት ፈጥሯል፡፡