Skip to main content
x
የሰሜን ወሎ ከተሞች ግጭት አልረገበም
በወልድያ ከተማ ጉዳት ከደረሰባቸው የንግድ ህንፃዋች አንዱ፡፡ ከመርሳ ወልደያ የሚወስደው መንገድ ለትራንስፖርት አገልግሎት ዝግ የነበረ ሲሆን በምስሉ ላይ እንደሚታየው በድንጋይ ተዘግቶ ይገኛል፡፡

የሰሜን ወሎ ከተሞች ግጭት አልረገበም

በጥምቀት በዓል ማግሥት የቃና ዘገሊላን በዓል አስታኮ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በወልዲያ ከተማ የተከሰተው ግጭት ወደ ሌሎች የዞኑ አካባቢዎች እየተዛመተ ከመሆኑም በላይ፣ በአብዛኛው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥራ አለመጀመራቸው ታውቋል፡፡ በወልዲያ ከተማ ሰኞ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሦስት ቀናት የሚቆይ የሥራ አድማ መጠራቱን ሪፖርተር በሥፍራው ተገኝቶ አረጋግጧል፡፡

ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት የስድስት ዜጎች፣ እንዲሁም የአንድ የፀጥታ ኃይል ባልደረባ ሕይወት ከጠፋ በኋላ፣ ችግሩ ወደ ሕዝባዊ አመፅና ግርግር መቀየሩን  በዞኑ በመገኘት ለመታዘብ ተችሏል፡፡

በመርሳ፣ በሲሪንቃ፣ በመሀል አምባ፣ በኡርጌሳ፣ እንዲሁም በቆቦ ከተሞች አመፁና የፀጥታ መደፍረስ ከተስፋፋ በኋላ አሁን የፀጥታው ሁኔታ የተረጋጋ ቢመስልም፣ ለመገመት አስቸጋሪ የሆነ አሥጊ ሁኔታ እንዳለ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በተጠቀሱት ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴ ሲገታ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አሁንም ሥራ አልጀመሩም፡፡

ያጋጠመውን ክስተት ለመዘገብ ወደ አካባቢው ቅዳሜ ጥር 19 ቀን 2010 ዓ.ም. የተጓዘው የሪፖርተር የጋዜጠኞች ቡድን ከደሴ ወልዲያ በሕዝብ ትራንስፖርት ቦታው ለመድረስ የሞከረ ቢሆንም፣ በነበረው የፀጥታ ችግር መንገዶች በመዘጋታቸው መሀል አምባ ድረስ ብቻ ለትራንስፖርት ክፍት ነበረ፡፡ እስከ ወልዲያ ድረስ ያለው ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነው መንገድ ግን ዝግ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት እስከ ወልዲያ ያለውን መንገድ በእግር መጓዝ ግዴታ ነበር፡፡ ከደሴ እስከ መሀል አምባ በነበረው ጉዞ የሚኒባስ ትራንስፖርት ማግኘት ቢቻልም፣ መደበኛው የትራንስፖርት አገልግሎት ግን ተቋርጦ ነበር፡፡

የጋዜጠኛው ቡድን ወልዲያ ደርሶ ስለነበረው ሁኔታ መዘገብ ስለነበረበት ከሌሎች መደበኛ መንገደኞች ጋር በሚኒባስ ወደ ወልዲያ እሑድ ጥር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በሁለት ሰዓት አካባቢ ጉዞ ተደርጓል፡፡ በሰላሙ ጊዜ እስከ 50 ብር ብቻ የሚያስወጣው መንገድ አሁን 100 ብር ለመክፈል በመስማማት ጉዞ ተጀመረ፡፡ ሁለተኛ ሚኒባስም በዚህ መሠረት ከደሴ ከተማ መናኸሪያ ጉዞውን ወደ ወልዲያ አድርጓል፡፡

በጉዞ ላይ የሚኒባሱ አሽከርካሪ ወልዲያ ካሉት ዘመዶቹ መንገድ ላይ ስላለው የፀጥታ ሁኔታ እየደወለ ሲያጣራና መንገድ ላይ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር እንደማያጋጥም ለተሳፋሪዎች ሲናገር ነበር፡፡

ከደሴ ከተማ ወደ ወልዲያ ጉዞ በተጀመረበት ወቅት ከተጠቀሱት ሁለት ሚኒባሶች ውጪ መደበኛ ትራንስፖርት ቆሞ እንደነበር ለመገንዘብ ችሏል፡፡

በጉዞው እንደ ሐይቅ፣ ውጫሌ፣ መሀል አምባ እንዲሁም ኡርጌሳ የተባሉ ከተሞች ሰላማዊ ነበሩ፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ከሁለት ዓመት በፊት በአማራ ክልል ሌሎች አካባቢዎች ማለትም በጎንደርና በጎጃም ሕዝባዊ አመፅና የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም፣ በአንፃራዊነት ሰላማዊ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ይኼ አካባቢ በተለይም በቅርቡ ወልዲያ ከተማ ላይ ተፈጥሮ ከነበረው  የዜጎች በፀጥታ ኃይሎች መገደል ጋር ተያይዞ የፀጥታ መደፍረሱ ቅርጹን በመቀየር፣ ወደ ሕዝባዊ አመፅና መንግሥትን ወደ መቃወም አድጎ በዞኑ የተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች ላይ ሊስፋፋ ችሏል፡፡

በዚህም ሳቢያ ወልዲያ ከተማ ከተገደሉት በተጨማሪ እስካሁን ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎች መሞታቸውን እየተገለጸ ነው፡፡

ከደሴ ወልዲያ በነበረው ጉዞ መንገደኞች መታወቂያ መያዛቸውን በሾፌሩ አማካይነት መጠየቃቸውን ማየት የተቻለ ሲሆን፣ ሾፌሩም መንገደኞችን መታወቂያ ከያዘ ምንም ዓይነት ችግር እንደማይገጥማቸው ሲናገር ተደምጧል፡፡

ነገር ግን ሚኒባሱ መሀል አምባ የምትባል ከተማ መቃረብ ሲጀምሩ ሾፌሩ ሐሳቡን በመቀየር፣ ተሳፋሪዎቹ የብሔር ተኮር ጥቃት ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲነገር ተደምጧል፡፡

በዞኑ የተከሰተው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት እንደነበር፣ የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለመንግሥት ሚዲያዎች መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

‹‹የአማራ ሕዝብ ሌሎችንም የማያቅፍ፣ የማያከብርና አብሮ የመኖር ባህል የሌለው ለማስመሰል ግጭቶችን የማስቀየር ሥራ እየተከናወነ ነው፤›› ያሉት አቶ ንጉሡ፣ ‹‹ዜጎችን ማንነታቸውን ብቻ መሠረት በማድረግ ጥቃት ሲደርስባቸው ተስተውሏል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይኼ አሳፋሪና አሳዛኝ ነው›› ሲሉ አቶ ንጉሡ ለጋዜጠኞቹ ተናግረዋል፡፡

 እንደ መርሳ በመሳሰሉ ከተሞች ደግሞ ግጭቱ ቅዳሜ ጥር 19 ቀን 2010 ዓ.ም. አገርሽቶ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ግጭት ከሰዎች ሞት በተጨማሪ ብዛት ያላቸው የንግድ ተቋማትና ቤቶች ጨምሮ ቃጠሎ ደርሶባቸዋል፡፡

ሪፖርተር በቦታው ጥር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ተገኝቶ እንደተመለከተው፣ ሆቴሎችና ሱቆች በቃጠሎ ጋይተዋል፡፡ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የመገልገያ ቁሳቁሶችም ወድመዋል፡፡

በግጭቱ ከግለሰቦች በተጨማሪ የከተማው ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ይሠሩ የነበሩ ግለሰብ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የከተማው ፍርድ ቤት የቃጠሎው ሰለባ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር በከተማዋ በደረሰ ጊዜ በአብዛኛው በመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በፌዴራል ፖሊስና በጥቂት የክልሉ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ከፍተኛ ጥበቃ ሲደረግ ተመልክቷል፡፡

‹‹ወጣቶቹ እንዲያቆሙ ብንነግራቸው ሊሰሙን አልቻሉም፤›› ያሉ ዕድሜያቸው 70 የሚጠጋ አንድ አዛውንት፣ በግጭቱ ወጣቶች መገደላቸውንና ሌላው ቢቀር የሚያነሳው ያጣ የአንድ ወጣት አስከሬን ወድቆ እንደሚገኝ ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

በከተማዋ ወጣ ብለው በሚገኙና የፀጥታ አካላት በብዛት በማይታዩባቸው ቦታዎች፣ ወጣቶች ትራንስፖርት አጥተው በእግራቸው ወደ ወልዲያ የሚጓዙ መንገደኞችን የየት ክልል ተወላጆች እንደሆኑና መታወቂያ እንዲያሳዩ ሲጠይቁ ለማስተዋል ተችሏል፡፡

ከመርሳ ወጣ ብሎ በሚገኝ ገጠራማ አካባቢም አንድ የጭነት መኪና እሑድ ጥር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ተቃጥሎ እየነደደ፣ ዙሪያውን ወጣቶች ከበው ሲመለከቱ ነበር፡፡

ከወልዲያ ከተማ በኋላ ወደ ቆቦና ሮቢት የተዛመተው ይኼ የዞኑ አለመረጋጋት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ውድመት አስከትሏል፡፡

አሁንም ቢሆን የሮቢት የገጠርና የቆቦ ወረዳ ከተሞች የፀጥታ ሁኔታ እንደለየለትና በዋናነት የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ሠፍረው እንደሚገኙ፣ ሪፖርተር በስልክ ማክሰኞ ጥር 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ያነጋገራቸው የሮቢት ከተማ ነዋሪ ገልጸዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች በፍርኃት ቤት ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት እኚሁ የሮቢት ነዋሪ፣ ችግሩን ለመፍታት የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለምነው መኰንን የቆቦ ከተማን፣ እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ የሮቢትን ነዋሪዎች ስለችግሩ ለማወያየት የሞከሩ ቢሆንም ስብሰባው ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል ብለዋል፡፡

የሮቢቱን ስብሰባ ለመሳተፍ ሄደው እንደነበር የተናገሩት እኚሁ ነዋሪ፣ ተሰብሳቢዎች አቶ ያለውን ሳይሆን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ነው የምንፈልገው በማለታቸው ስብሰባው ሳይካሄድ እንደቀረ አስረድተዋል፡፡ በዋናነት ነዋሪዎች የመልካም አስተዳደር፣ የመሬትና የልማት ጥያቄ እንዳላቸው የተናገሩት የሮቢት ነዋሪ፣ ‹‹ለምሳሌ የሮቢት መሥሪያ ቤቶች ያሉት ቆቦ ነው፣ ይኼ ደግሞ የወረዳው ባለሥልጣናት ሆን ብለው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን በተሻለ ሁኔታ ቆቦ ከተማ ለማኖር እንዲመቻቸው ነው ሲሉ ነዋሪው ይወቅሳሉ፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በመካከላቸው 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ያላቸው ሮቢትና ቆቦ፣ ሮቢት የገጠር ወረዳ ስትሆን ቆቦ ደግሞ አነስተኛ ከተማ ናት፡፡

ሮቢት በነበረው ግጭት ሦስት ሰዎች መቁሰላቸውንና ከእነዚህም ውስጥ አንድ ሰው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ወደ ወልዲያ ሆስፒታል መላኩን እኚሁ ግለሰብ ገልጸዋል፡፡

ገና ለይቶ ያልወጣለት የሰሜን ወሎ ሕዝባዊ አመፅና የሰላም መደፍረስ ሰኞ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ወልዲያ ከተማ ላይ እንደገና አገርሽቶ የባለሥልጣናትን ቤት ለማቃጠል የተሞከረ ሲሆን፣ በተጨማሪም ለሦስት ቀናት የሚቆይ የሥራ ማቆም አድማ መጠራቱን የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ወልዲያ የሚኖሩ የመንግሥት ሠራተኛ፣ በዚህም ምክንያት ሰኞ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ሊሰጥ የነበረው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የመጀመርያ መንፈቅ ዓመት አጠቃላይ ፈተናም እንዲቆም ተደርጓል ብለዋል፡፡