Skip to main content
x
የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ተቃውሞ ገጠመው
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፈቂ፣ ሊቀመንበሩ ፖል ካጋሜና የቶጎ ፕሬዚዳንት ፋውሬ ናሲንግቤ ለአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ምሥረታ መታወሻ የተቀመጠውን የማዕዘን ድንጋይ መርቀው ሲከፍቱ

የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ተቃውሞ ገጠመው

የአፍሪካን የአየር ትራንስፖርት አውታር ወደፊት እንደሚያራምድ የታመነበት የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ምሥረታ ተቃውሞ ገጠመው፡፡

የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ በክልከላ የተተበተበ በመሆኑ የአፍሪካ የአየር መንገዶች ዕድገት ፈታኝ እንዳደረገው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የገበያ ክልከላን በማስቀረት የአፍሪካ አየር መንገዶች አፍሪካ ውስጥ በነፃነት ከአገር አገር እንዲበሩ የሚያስችል የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ምሥረታ፣ ጥር 20 እና 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተካሄደው 30ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ በይፋ አውጇል፡፡ ሰኞ ጥር 21 ቀን በተካሄደው የመሪዎች ጉባዔ የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ መመሥረቱን ያወጁት አዲሱ የኅብረቱ ሊቀመንበር የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ናቸው፡፡ ፖል ካጋሜ የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ምሥረታ ለአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ዕድገት ትልቅ ዕርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ፖል ካጋሜ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፈቂ ማሃማትና የቶጎ ፕሬዚዳንት ፋውሬ ናሲንግቤ ለጋራ ገበያው ምሥረታ የተቀመጠውን የማስታወሻ ድንጋይ መርቀው ከፍተዋል፡፡

በጉባዔው መክፈቻ ላይ ፖል ካጋሜ የጋራ ገበያ ምሥረታውን አስመልክተው ንግግር ካደረጉ በኋላ፣ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አስተያየት ለመስጠት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ሊቀመንበሩ ፖል ካጋሜ በጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ላይ ማንኛውም መሪ አስተያየት እንዲሰጥ በፕሮግራሙ ላይ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም፣ ለፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ ዕድሉን ሰጥቷቸዋል፡፡፡

ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ምሥረታ ላይ ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የጋራ ገበያ ምሥረታው የሚጠቅመው የተወሰኑ የአፍሪካ አየር መንገዶችን እንደሆነ የገለጹት ሙሴቬኒ፣ እነዚህ የአፍሪካን ሰማይ የተቆጣጠሩት አየር መንገዶች ወደፊትም የአፍሪካን ገበያ እንዲቆጣጠሩ የሚፈቀድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ ጥሩ አይደለም›› ያሉት ሙሴቬኒ፣ ገበያውን ክፍት ከማድረግ በፊት የአፍሪካ አገሮች በየክልላቸው የጋራ አየር መንገድ ቢያቋቋሙ ተመራጭ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የሙሴቬኒ ንግግር በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ ነው፡፡ ‹‹ኡጋንዳ ገበያዋን ለአፍሪካና ለሌሎች አየር መንገዶች ክፍት ያደረገች አገር ናት፡፡ ወደ ኢንቴቤ የማይበር አየር መንገድ የለም፡፡ ሙሴቬኒ በጉባዔው ያንፀባረቁት ሐሳብ ግር የሚያሰኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሙሴቬኒ ተቃውሞ ላይ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የቀድሞ የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር ሊቀመንበርና የአፍሪካ አቪዬሽን ሰርቪስስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ኒክ ፋዱግባ፣ የአፍሪካ አገሮች እ.ኤ.አ. በ1999 የአፍሪካን የአየር ትራንስፖርት ገበያ ክፍት ለማድረግ የያማሱክሮ ውሳኔ በመባል የሚታወቀውን ሰነድ ያፀደቁ መሆኑን አስታውሰው፣ የአፍሪካ አገሮች የማይተገበሩትን ውል ለምን ይፈርማሉ ሲሉ ተችተዋል፡፡

የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ምሥረታን የተቃወሙት ሙሴቬኒ ብቻ አይደሉም፡፡ በናይጄሪያ የሚገኙ የግል አየር መንገዶችም ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ የናይጄሪያ አየር መንገዶች በማኅበራቸው አማካይነት ባወጡት መግለጫ ናይጄሪያ ለጋራ ገበያ ምሥረታው ዝግጁ አለመሆኗን በመግለጽ፣ መንግሥታቸው ውሉን ተግባራዊ እንዳያደርግ ጠይቀዋል፡፡

አንዳንድ የአፍሪካ አየር መንገዶች የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ መመሥረት የሚጠቅመው እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያና ኢትዮጵያ ላሉ ትልልቅ አየር መንገዶችን እንደሆነ በመግለጽ ትንንሽና ደካማ አየር መንገዶችን እንደሚጎዳ ያላቸውን ሥጋት ይገልጻሉ፡፡

የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት የተሰነዘረውን ተቃውሞ አጣጥለውታል፡፡ የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሚስስ ሶሶና ኢያቦ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያው የሚጠቅመው ትልልቅ አየር መንገዶችን ብቻ ነው የሚለው የተሳሳተ አስተያየት ነው፡፡ የጋራ ገበያው ትልቅ ትንሽ ሳይል ሁሉንም አየር መንገዶችና አገሮች የሚጠቅም እንደሆነ የገለጹት ሚስስ ሶስና አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት በማስተሳሰር፣ የመንገደኞች ቁጥር በመጨመር፣ የአቪዬሽንና ተያያዥ ዘርፎችን ሁሉ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

‹‹በፍርኃት ውስጥ የምትኖር ከሆነ ለውጥ ማምጣት አትችልም፡፡ እነዚህ አየር መንገዶች ከፍርኃት ተላቀው የጋራ ገበያ ምሥረታው የሚያመጣውን ዕድሎች ተመልክተው በዕድሎቹ ለመጠቀም መሥራት ይኖርባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

ናይጄሪያዊቷ ሚስስ ሶስና ናይጄሪያ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ምሥረታ ካፀደቁት የመጀመርያ አሥራ አንድ አገሮች አንዷ መሆኗን ጠቁመው፣ የናይጄሪያ መንግሥት ማየት የቻለውን የጋራ ገበያው የሚፈጥረውን ዕድል የናይጄሪያ አየር መንገዶች ገና ማየት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሚስተር አብዱራህማን በርቴ በበኩላቸው፣ ትንንሽ አየር መንገዶች በትልልቅ አየር መንገዶች እንዋጣለን የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ አነስተኛ የሆኑ የአፍሪካ አየር መንገዶች ከትልልቅ የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር መተባበር እንዳለባቸው ሚስተር አብዱራህማን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ትልልቆቹ አየር መንገዶች ሁሉም ቦታ መብረር አይችሉም፡፡ ትልቅ የሚባሉት አየር መንገዶች ረዥም በረራዎች ሲሸፍኑ አነስተኛ አየር መንገዶች አጭር በረራዎችን ማካሄድ ይችላሉ፡፡ መፍትሔው ተባባሮ መሥራት ነው፤›› ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ የጋራ ገበያው የሚመራበት ሕግና ሥርዓት ያለው በመሆኑ አየር መንገዶች ፍርኃት ሊሰማቸው አይገባም ብለዋል፡፡

‹‹የለውጥ ባቡር በመገስገስ ላይ ነው፡፡ ማስቆም አይቻልም፡፡ የሚሻለው ተባብሮ መሥራት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሚስተር ኒክ ፋዱግባ በበኩላቸው፣ ገበያ ሲከፈት አሸናፊና ተሸናፊ እንደሚኖር ጠቁመው፣ ‹‹ስኬታማ የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመውቀስ ይልቅ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ቶጎ፣ ማላዊና አሁን ደግሞ ዛምቢያ እንዳደረጉት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በሽርክና መሥራት ይጠቅማል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም አፍሪካ ውስጥ ትንሽና ትልቅ የሚባል አየር መንገድ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሁላችንም ትንሽ ነን፡፡ አሁን የተባለው ነገር ሁለት ራሰ በረሃ ሰዎች ለማበጠሪያ እንደሚሻሙት ዓይነት ነገር ነው፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ የጋራ ገበያው ለአፍሪካ አየር መንገዶች ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን አገሮች እርስ በርስ ግንኙነት በማጠናከር ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም በማስፋፋት የሚኖረውን ጠቀሜታ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ምሥረታ የአፍሪካ ኅብረት 2063 የልማት አጀንዳ አንዱ አካል ሲሆን፣ 23 አገሮች በፊርማቸው ሲያፀደቁ አራት አገሮች ግን በሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡ አቪዬሽን አፍሪካ ውስጥ ስምንት ሚሊዮን የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ ለአኅጉሪቱ አጠቃላይ ብሔራዊ ምርት 80 ቢሊዮን ዶላር አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡