Skip to main content
x
የወልድያ እግር ኳስ ክለብ መበተኑ ተሰማ
የወልድያ እግር ኳስ ክለብ

የወልድያ እግር ኳስ ክለብ መበተኑ ተሰማ

  • ‹‹ቡድኑ እንዲበተን መመርያም ሆነ ትዕዛዝ የሰጠ አካል የለም››

አቶ ገረመው ካሳ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተወዳደረ የሚገኘው የወልድያ እግር ኳስ ክለብ በፀጥታ ችግሮች ምክንያት የቡድኑ አሠልጣኝና ተጨዋቾች ሆቴል ለቀው በመውጣታቸው ቡድኑ በጊዜያዊነት መበተኑ ተሰማ፡፡ የክለቡ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ ቡድኑ በወልድያ ካረፈበት ላል ሆቴል እንዲወጣም ሆነ በጊዜያዊነት ዝግጅት እንዲያቆም ትዕዛዝም ሆነ መመርያ የሰጠ አካል እንደሌለ ይናገራሉ፡፡

ለደኅንነታቸው ሲሉ ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንዳንድ የክለቡ ተጨዋቾች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ በወልድያ ከተማ ባለው ሁኔታ አሠልጣኙን ጨምሮ ብዙዎቹ ተጨዋቾች መደበኛ ዝግጅት ለመሥራትም ሆነ ሆቴል ውስጥ ተረጋግቶ ለመቀመጥ እንኳ የሚያስችል ነገር የለም፡፡ በዚህም ሆቴሉ ለቀው መውጣታቸውን ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ቡድኑ እንዲበተን የደረሳቸው አንዳችም መመርያ እንደሌለ ነው ያስረዱት፡፡

የወልድያ እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገረመው ካሳ ጉዳዩን አስመልክቶ ከሪፖርተር ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ቡድኑ ከነበረበት ላል ሆቴል ወጥቶ እንዲበተንም ሆነ ዝግጅት እንዲያቋርጥ የተላለፈ አንዳችም መመርያ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

‹‹ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ከጅማ አባጅፋር ጋር ጨዋታውን አድርጎ ወደ ወልድያ ከተመለሰ በኋላ በቀጥታ እንዲቀመጥ የተደረገው ላል በተባለው ሆቴል ነው፡፡ ይሁንና የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ግን አሠልጣኙና አንዳንድ ተጨዋቾች ሆቴል ለቀው ወጥተዋል፤›› ብለዋል፡፡

ቀጣይ የክለቡን ዕጣ ፈንታ አስመልክቶ አቶ ገረመው፣ ‹‹ክለቡ አሁን ባለው ሁኔታ ከሌሎች አቻ ክለቦች ጋር ተፎካካሪ ሆኖ ለመጫወት የሚያስችለው የተረጋጋ ነገር ስለሌለው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቀሪውን አራት ጨዋታዎች እንዲያራዝምለት ጠይቋል፡፡ ይሁንታም አግኝቷል፤›› ብለው፣ አሠልጣኙንና ተጨዋቾችን አስመልክቶም ወደ መደበኛ ልምምዳቸው እንዲመለሱ ክለቡ ጥሪ እያደረገ ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡

አሠልጣኙም ሆነ ተጨዋቾች ከክለቡ ዕውቅና ውጪ ሆቴል ለቀው በመውጣታቸው ሊደርስባቸው የሚችል የዲሲፕሊን ዕርምጃ ይኖር ይሆን? ለሚለው አቶ ገረመው፣ ‹‹በፍፁም›› ብለው፣ ባለው ሁኔታ ለደኅንነታቸው በመሥጋት ያደረጉት በመሆኑ በዚህ በኩል ምንም ዓይነት ሥጋት ሊገባቸው አይገባም ሲሉ መልዕክታቸውን ጭምር አስተላልፈዋል፡፡

የወልድያ እግር ኳስ ክለብ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ11 ጨዋታ፣ 12 ነጥብ ሰብስቦ በደረጃ ሰንጠረዥ 12ኛ ላይ ይገኛል፡፡