Skip to main content
x

የውድቀት አመቻቾቹ ሐሰተኛ “ምሁራን” ምን ይደረጉ?

በልዑል ዘሩ

በዓለም አቀፍ እሳቤም ሆነ በእኛ አገር የምንስማማበት ብያኔ ምሁርነት በእውቀት መላቅ፣ በእውቀት መምጠቅና የባህሪ ለውጥ ማምጣት የሚለውን አባባል የሚገልጸው ነው፡፡ በእወቀት ላይ የተመሠረተ ተግባርም የምሁርነት ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡ ምሁርነት የሙያ አድማስን ማስፋት፣ በእውቀትም ላይ እውቀት እየጨመሩና  እየበቁ መሄድ ነው፡፡ ለዚህም ነው አንድ ሰው ምሁር ሆነ ማለት ተማረ፣ አወቀ፣ ተመራመረ፣ በእውቀት ገበያው ላይ በሰፊው ገበያ ሸመተ፣ አተረፈ፣ አገኘ ማለት የሚሆነውና ከግል አልፎ ለማኅበረሰብና ለአገር የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው፡፡

አንድ ቤተሰብ ልጁን በሥነ ምግባር አንጾና አስተምሮ ለምሁርነት ሲያበቃው ለራሱ የበቃ፣  ለአገሩና  ለሕዝቡ ሁነኛ መድኃኒት አመንጪ እንዲሆን ነው፡፡ አንድ ክቡር ዜጋ  ችግር ፈቺ መፍትሔና መላ አመንጪ ሰብዕናን ለመገንባት የሚያስችለው ትክክለኛው  የምሁራን ተሳትፎ ነው መባሉም ለዚሁ ነው፡፡ አሁን ያለችዋን ዓለም በብዙ መንገድ ቀይረው እዚህ ያደረሱ ምሁራንና ተመራማሪዎች መሆናቸውም ሊሸሸግ የሚችል አይደለም፡፡

በአገራችንም በአሁኑ ወቅት ምሁርነትና ተመራማሪነት እንደ ጨው ከመርከሱ በፊት  ለፍቶና ግሮ እውነተኛ እውቀት ለመጨበጥና ለማግኘት መታገል የላቀ ተግባር ሆኖ ቆይቷል፡፡ የመንግሥት ሠራተኝነትም (ፖለቲከኛውን ጨምሮ) ቢሆን ቢያንስ ክብርን ጠብቆ ሥርዓቶቹን ማገልገሉ ባይሸሸግም፣ በበቂ የትምህርት ዝግጅትና ብቃት የሚገኝ የላቀ ኃላፊነት ነበር፡፡ ፍትሐዊ ባልነበሩ የፖለቲካ ሥርዓቶች ሳይቀር እንደ መርፌ ክር በጠበበ ዕድል ተጠቅመው ብዙዎች በትምህርት ከዳር መድረስ የቻሉትም፣ ለእነዚህ ዓላማዎች በመሠለፍ እንደነበር ማስተባበል ያዳግታል፡፡

ዛሬ ከአገራችን አልፎ በተለያዩ ስመጥር አገሮችም አንቱ የተባሉ ኢትዮጵያዊያን ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች በከፍተኛ ባለሙያነት እያገለገሉ ያሉት የዚያ ትውልድ ውጤቶች በመሆናቸው ነው፡፡ እውነት ለመናገር የ1950/60ዎቹ አብዮት ናፋቂ ትውልድም ቢሆን የሄደበት መንገድ ወጣ ገባነትና ያስገኘው የመፋጀት እኩይ ፍሬ ቢያሳዝንም፣ የሚያማልለው ለውጥና የሕዝቦች ጥቅም ከምሁራዊ ወኔ የሚመነጭ እንደነበር አይታበልም፡፡

በመሠረቱ በያኔው ትውልድ አጥብቆ መማር፣ ተምሮም በብዙ ድካም ለምሁርነት መብቃት ግለሰቡን፣ ቤተሰብንና አገርንም በአያሌው ያኮራል፣ ያስከብራል፡፡ የቀድሞ ተማሪዎች አንዱ መለያ ለእውቀት ከፍተኛ ረሃብ የነበራቸው የመሆኑ ቁም ነገር መነሻም ይኼው ነበር፡፡ መደበኛ ትምህርታቸውን በትጋት መከታተል፣ ማጥናት፣  በእውቀት ላይ የተመሠረተ ክርክር፣ የእውቀት ፉክክር ማድረግ እንደ ዛሬው መጻሕፍት እንደ ልብ በማይገኙበት ዘመን አንድን የተገኘ መጽሐፍ በላብ እስኪቀደድ ድረስ እየተዋዋሱ ማንበብ፣ የበረቱት ደግሞ መጽሐፉን ራሱን በእጅ ጽሑፍ እስከ መገልበጥ  መድከም የተለመደ ተግባር ሆኖም ቆይቷል፡፡ አገላላጹ ድሮን ናፋቂ እንዳያስብለኝ እንጂ፡፡

እውነት ለመናገር የቀደመው ትውልድ አባላት በፖለቲካዊ ሴራ ቢታሙም፣ በተሰማሩበት የሥራ መስክ በእውቀት የማይታሙና የተከበሩ ናቸው፡፡ ይነስም ይብዛም በሥነ ጽሑፍና በኪነ ጥበብ መስክ እንኳን ብዙዎቹ ወጥና “ክላሲካል” የሚባሉ የአገራችን የጥበብ ሥራዎች የሚጠቀሱት ከዚያኛው ትውልድ አሻራ አይደለምን!? ያም ሆኖ በዚያኛው ትውልድም  ቢሆን መጠኑ ባይበዛም  ሐሰተኛ ምሁራን፣ በተወናበደ የትምህርት መረጃ የሚያምታቱና ለአገር ደንታ የሌላቸው  አንዳንድ ስግብግብ ፍጡራን አይገኙም ለማለት አዳጋች ነው፡፡ በየትውልዱ የመከነ ኃይል እንደማይጠፋው ሁሉ፡፡

አሁን ባለው ትውልድም ቢሆን የቀደመውን ጠንካራ ፈልግ በመከተል ድንቅ ውጤት ያስመዘገቡና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የቻሉ ወጣቶች እንዳሉ ጥርጥር የለም፡፡ እውቀት በወረቀት መያዝ ብቻ አይገለጥም ብለው በፈጠራና በምርምር የታጀበ ፍሬ ማፍራት የቻሉ እንዳሉም ታዝበናል፡፡ ዛሬም ቁጥራቸው መብዛቱ ላይ ቢያጠራጥርም የእውቀት ጥማትና ፍለጋ ላይ የሚዋትቱ ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣቶችም አይጠፉም፡፡ ለዚህ ደግሞ ከቦታ ቦታ ቢለያይም የክልል መንግሥታት የሚያደርጉት ድጋፍ፣ የወላጆች እገዛና የዓለም አቀፉ ሉላዊ የመረጃ ሁኔታ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይታመናል፡፡ 

የዚያንም ያህል በአሁኑ ዘመን ያለው የሐሰተኛ ምሁርነት መብዛትና የቀለም ቀንዲል የመስበር ልክፍት አገርን ገደል እስከ መክተት የሚያደርስ ነው፡፡ በትምህርት ጥራት ላይ ብቻ እየተሳበበ ግን በዘርፉ ሥር እየሰደደ የመጣው የትምህርት ወሮበላነት፣  አገርና ትውልድ ገዳይ አዲስ አስከፊ ወረርሽኝና አገራዊ በሽታ ሆኖ ተጣብቶናል፡፡ የሌላውን ዓለም ባህልና ልማድ በወረርሽኝ መልክ ቀርጥፎ የሚበላ፣ በራሱ ማንነት (በተለይ ብሔራዊ ስሜት) የማይተማመን፣ በመንደርተኝነትና በጠንካራ አገራዊ አንድነት አልባ  ጀልባ ቀን ከሌሊት የሚቀዝፍ “ትውልድ” የመበርከቱ አንዱ መነሻም ከዚህ የሚመነጭ  ነው፡፡ ከአድርባይነት የተነሳም ይባል ተራ የፖለቲካ ፍርፋሪ ለማትረፍ የዳሽን ተራራን ወይም ላሊበላን ያህል ትልልቅ ቅርሶች ቦታ እየቀየረ መጽሐፍ የሚያትም፣ ሲያውቀውም ፈጥኖ የማያርም እንዝህላል ትውልድ የትምህርት ሥነ ምኅዳሩን ወሮታል፡፡ ሕዝብን በአገራዊ ትልቁ ምሥል ውስጥ ከማሰባሰብ ይልቅ፣ በጥላቻና በጥገኛ መንገድ የተለጠጠ ብሔርተኝነትን ማቀንቀንም የድንቁርና መገለጫ ነው፡፡

ለዚህ ዓይነቱ ዝንፈት የሚያጋለጥው ታዲያ የተሟላና ዓለም አቀፋዊ የምሁርነት ብስለት ያለማስፋፋት ችግር ነው፡፡ ለአብነት ያህል አሁን ባለችው አገራችን ያለ ብቃት ኮርጆና አምታትቶ ባለ ዲግሪ መሆን፣ ምንም ሳይሞክር ወረቀት ገዝቶ ዲግሪ አለኝ ከሚለው ስለሚሻል ብዙም የማይደንቅ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ ብቻ ሳይሆን ማስትሬት ዲግሪም ይዞ ሥራ አጥና ተቀማጭ መሆን የማይገርም የተለመደ እውነታ ነው፡፡ በየአካባቢው ፎርጅድ ምሁራን በገፍ ተቀፍቅፈዋል፡፡ የወረቀትና የስም ፍቅር እንጂ እውቀት አልቦዎች ያለፉበትንና ያልደከሙበትን የትምህርት ማዕረግ በግዥ የሚሰበስቡ ጉዶች እየበረከቱ ነው፡፡ አሳፋሪው እውነታ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ቀጣፊዎች በመንግሥት ኃላፊነትና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመምህርነትም የሞሉ መሆናቸው ነው (በቅርቡ በአገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ በተደረገ መጀመሪያ ዙር መረጃ የማጥራት ዕርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለፎርጅድ የትምህርት መረጃ ሠራተኞችና ተሿሚዎች መገኘታቸውን ልብ ይላል)፡፡ ‹‹ከእጅ አይሻል ዶማ›› ይሉታል ይህንን ነው፡፡

በእርግጥ በመርህ ደረጃም ቢሆን መንግሥት የሚሠራው በእውቀት ላይ የተገነባ   ትውልድ፣ በፈጠራ የታገዘና ኮርጆም ቢሆን አዲስ ነገር ለመሥራት የሚታትር የቴክኒክ ሰው እንዲፈጠር ነው፡፡ ለዚህም ነው በአገሪቱ እስከ 41 የሚደርሱ ዩኒቨርሲቲዎች በመንግሥት ተከፍተው፣ ከ1,250 በላይ የቴክኒክ ትምህርት ቤቶችና የግል ኮሌጆች ሥራ ላይ ውለው የሚገኙት፡፡ ለነገሩማ በአገር ደረጃ እስከ 18,800 የሚደርሱ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችስ ከ25 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችንና መምህራንን አቅፈው  በየዕለቱ  በተሟሟቀ ሥራ ላይ የሚገኙት በዚሁ ዓላማ ላይ ተመሥርተው አይደለምን? ነገር ግን የዚህን ሰፊ ድካም ያህል ከሐሰተኛና ከወላዋይ ምሁራን የፀዳ፣ ለአገርና ሕዝብ የሚቆረቆርና ብሔራዊ አንድነትን የሚያስብ ትውልድ እንዲገነባ እስካሁን እያጋጠሙ የነበሩ አሳሳቢ ችግሮችን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ እየታዩ ካሉ ችግሮች ቀዳሚው የሐሰተኛ ማስረጃ (ፎርጅድ) እና የማደናገሪያ የትምህርት ማስረጃን የመጠቀም ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳዳሮች ያለ በቂ የቁጥጥር ሥርዓት ከፌዴራል መንግሥት ጋርም ባልተናነሰ ሁኔታ የትምህርት መረጃ ሰጭም፣ ተቀባይም መሆናቸው  አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገመታል፡፡ ለአብነት ያህል ከወራት በፊት የጋምቤላ ክልል 50 በመቶ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የትምህርት መረጃ ሐሰተኛ መሆኑ አንድ ማሳያ ነው፡፡ የዚሁ ተመሳሳይ በአፋር፣ በሶማሌና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ቢኖርም ሐሰተኛ መረጃን ይዞ በመንግሥት ቤት መቀጠር ወይም መሾም በተለይ በታዳጊ በክልሎች የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችን እንደ ማበረታታት ተወስዶ ለዓመታት ሲድበሰበስ የመቆየቱ ውጤት ነው፡፡ በታሪክ አጋጣሚ በትምህርት ወደኋላ የቀሩ ወገኖች ተገቢው ድጋፍ ተደርጎላቸው በፍጥነት እንዲማሩ ማድረግ ሲገባ፣ ከሶማሊያና ከደቡብ ሱዳን በመጣ የተወናበደ መረጃ ጭምር አገር (ክልል) እንዲመሩ ማድረግ በአገር እንደመቀለድ የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ችግሩ በተለይ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎችም የገነነ መሆኑ ሲታይ አገራዊ አንድምታውን የሚያሳይ ነው፡፡

ሐሰተኛ የትምህርት መረጃ በተለያዩ የውሸት ብቃት ማረጋገጫዎችም ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋጋጫን ብንወስድ በተለይ በታዳጊ ክልሎችና በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች በቀጥታ ክፍያ (ያለ ሥልጠናና ፈተና) ከመንገድ ትራንስፖርት ፋይል ተከፍቶለት የመንጃ ፈቃዱ ቤት ድረስ እንደሚመጣ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በቅርቡ በመንግሥታዊዎቹ የመገናኛ ብዙኃን በቀረበው ዘገባ መሠረት የፎርጅድ መንጃ ፈቃዶችን ቀድሞ መፈተሽ የጀመረው የሶማሌ ክልል በአንድ ወር ውስጥ ብቻ 1,500 ሐሰተኛ መረጃዎችን ማግኘቱ ተገልጿል፡፡ እንግዲህ ይህ ችግር በሁሉም አካባቢ ቢፈተሽ ምን ያህል ለትራፊክ አደጋ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን መገንዘብ ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም የሚቀለው በትራፊክ አደጋ የሚወድቀውን ሬሳ መቁጠር እንጂ ሕገወጥነትን አመርሮ መታገል አልሆነም፡፡

በግሌ የማውቃቸው በርከት ያሉ ባለሀብቶች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና አርቲስቶች ሳይቀሩ አዲስ አበባ ተቀምጠው በክልል ፎርጅድና ሐሰተኛ የማሽከርከሪያ ብቃት መለኪያ ፈቃድ እንደሚጠቀሙ ታዝቤያለሁ፡፡ የትራፊክ ፖሊሶች ሲነቁባቸውም በ100 ብር (እንደ አደጋው ሁኔታ ጉቦውም እንደሚጨምር ግልጽ ነው) እያለፉ እነሆ ቀጥለዋል፡፡ የሐሰተኛ ችሎታ ዘመን አንዱ ማሳያ መሆኑ ይሆን!?

እንደ አገር የትምህርትና የሥልጠና ዘርፉ እንዲስፋፋም ሆነ ዜጎች አማራጭ ዕድል እንዲያገኙ እስካሁን የግል ማሠልጠኛዎችና ኮሌጆች የራሳቸውን በጎ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በዚያው ልክ አንዳንዶቹ ሰርተፊኬት በገንዘብ በመሸጥና ሐሰተኛ  ትምህርት መረጃን በማደል ወደር የማይገኝላቸውም ናቸው፡፡ ይህንን የምለው ከመሬት በመነሳት ሳይሆን አንድ ስሙን የማልጠቅሰው የግል ተቋም ዲፕሎማ በ30 ሺሕ ብር፣ ዲግሪ በ60 ሺሕ ብር ይሸጥ እንደነበር በተጨባጭ መረጃ ደርሸበት ለሚመለከተው አካል እስከ መጠቆም ደርሼ ስለነበር ነው፡፡ ወደ ኋላ ላይ መንግሥት በየዘርፉ የብቃት ማረጋጋጫ ፈተና ሥርዓትን በማምጣት ችግሩን ለመመከት መሞከሩ ባይካድም (እሱም ቢሆን ዋነኛው የሙስና ገቢ ደራበት)፣ የትምህርት ማስረጃዎች ግን ወደ ውጭ ለሚሄዱ ሰዎች ሳይቀር በሐሰት መሸጣቸው አሁንም አልቆመም፡፡

በአንዳንድ የግል ተቋማት በኩል ሐሰተኛ ምሁራንን ለመቀፍቀፍ የሚበረታታው ሌላው ችግር በትምህርት ጥራት ላይ የሚታየው መዝረክረክ ነው፡፡ ገና ከቅበላ አንስቶ ወደ በኮሌጅ ማለፊያ ውጤታቸው የወደቁ ተማሪዎችን በመቀበል ገንዘብ ተኮር የትምህርት አሰጣጥና የፈተና ዘዴን በመከተል፣ የትውልድ ውድቀትን የማያጤኑ ብዙ ስግብግቦች ያሉባት አገር ሆናለች ኢትዮጵያችን፡፡ አንዳንዶቹን አወናባጆች ቢዘገይም አሁን መንግሥት በሙስና ወንጅሎ እየተቆጣጠራቸው ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ግን አሁንም እንደ ክረምት አይጥ በጉድጓዳቸው መሽገው ቀኑን ለማሳለፍ እየሞከሩ ነው፡፡

የኮሌጆቹና የማሠልጠኛዎቹ የትምህርት አሰጣጥ የጥራት ችግር፣ ከመምህራን እጥረትና ብቃት መጓደል፣ ከመርጃ መሣሪያ ማጣት፣ ከተቋማት የብቃት መጓደልና መሰል ጉዳዮች ጋር እንደሚያያዝም ይታወቃል፡፡ ይህ ችግር ግን በግል ኮሌጆች ብቻ ያለ ነው እንዳይባል በብዙዎቹ አዳዲስ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችም ጎልቶ በመታየት ላይ ነው፡፡ አንዱም ይህ ነው እንግዲህ አስመሳይና ሐሰተኛ ምሁራንና ብቃት የለሽ ባለ ዲግሪዎች በየመንደሩ እየተቀፈቀፉ እንዲቀጥሉ በማድረግ ላይ የሚገኘው የሚል እምነት አለኝ፡፡

እዚህ ላይ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚሠራ እንግሊዛዊ በተረብ መልክ፣ ‹‹በእንግሊዝኛ ቋንቋ ራሳቸውን በአግባቡ የማይገልጹ ባለ ዲግሪዎች የሞሉባት አፍሪካዊት አገር›› (ምንም እንኳን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ እውቀት ባይለካም፣ ትምህርቱን በዚሁ ዓለም አቀፍ መግባቢያ ሲወስድ ከርሞ አለመቻል የውድቀት ማሳያ መሆኑን እስማማበታለሁ) ያለንን አልረሳውም፡፡

ይህንንም ክፍተት ለመሙላት በየጊዜው የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና መሰጠቱ ተገቢ ሲሆን ዘላቂነቱ ላይ ሊጠናከር የሚገባው ነው፡፡ በዚህ ላይ የፌዴራል ሥርዓቱን ወጥነት ያሳጣው የክልሎች የትምህርት ፖሊሲ፣ የሥነ ትምህርት መመሪያና መርሐ ግብር፣ እንዲሁም የመጻሕፍት ዝግጅት፣ የመምህራን ምለመላ፣ ሥልጠና፣ ምደባ፣ ወዘተ በጥልቀት ሊጠና የሚገባው ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ውሳኔን የሚፈልግ ትውልድ የመቅረፅ ዕርምጃ የትምህርት ጥራትን በወጥነት በአገር ደረጃ ለማስፈን ከመርዳቱ ባሻገር፣ ሐሰተኛና አቅመ ቢስ ምሁር ተብዬዎችን ከመቀፍቀፍ የሚያድን ይሆናል፡፡

አሁን በምንገኝበት ደረጃ መንግሥት ውስጡን የመፈተሽ ተግባር ላይ እንደሆነ ሲናገር ይደመጣል፡፡ በዚህ ረገድ በሙስናና በፖለቲካ ብልሽት ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ በርካታ ሰዎች ከኃላፊነታቸው እየተነሱ፣ እንደ ጥፋታቸው ክብደትም በሕግ እየተጠየቁ (በተሟላ መንገድ ባይሆንም) መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ትግሉም ተጀመረ እንጂ ገና እንዳልተነካ ሲነገር ይደመጣል፡፡ ይሁንና በትምህርት ጥራት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ተወዳዳሪነትና ፈጠራን ሆን ብለው ችግር የፈጠሩ ጥፋተኞችና በሐሰት የምሁርነት ታፔላ ለጥፈው ሲያወናብዱ የነበሩ ሐሰተኛ ምሁራን ላይ የተወሰደ ዕርምጃ እምብዛም ትርጉም ያለው አልሆነም፣ ጎልቶም አልተሰማም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በፎርጅድና በሐሰተኛ የትምህርት ማሰረጃ ሲሠሩ ቆይተው ይቅርታ ከጠየቁ በይቅርታ ይታለፋሉ መባሉም መሳቂያና መሳለቂያ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም በአገራችን ምሁራንን የምናይበት አተያይና የምሁራን አገራዊ ፍቅርና ተነሳሽነት ጉዳይም በጥልቀት መፈተሽ ያለበት መሆኑን መጥቀስ ይገባል ባይ ነኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡