Skip to main content
x

ጥያቄ እያስነሳ ያለው የዘርፍ ምክር ቤቱ የውክልና አመራር

በመንግሥት ውጥን መሠረት የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ሲከለስና ንግድ ምክር ቤቶችን ከዘርፍ ምክር ቤቶች ጋር በማጣመር እንዲደራጁ ሲወስን፣ እንደ አንድ ዋነኛ ዓላማ ያደረገው የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከፍ ለማድረግ ነው፡፡

በዘርፉ ማኅበራት ምክር ቤት ሥር የተደራጁ አባላትም ኢንዱስትሪ ቀመስ እንዲሆኑ ታስቦ የመጪው ጊዜ የኢንዱስትሪ ዘርፉ መሪ ሆነው እንዲወጡ ለማስቻል ነበር ዓላማው፡፡

በዚህ መነሻነት ንግድ ምክር ቤቶች በሚል ስያሜ ከሰባ ዓመታት በላይ የዘለቁት ተቋማት፣ ከ12 ዓመታት በፊት በወጣው አዋጅ መሠረት በንግድና በዘርፍ የሚጠቀሱ ተቋማትን አጣምረው ከወረዳና ከከተማ ጀምሮ እስከ አገር አቀፍ ድረስ እንዲደራጁ ተደርጎ የተዋቀረ ነው፡፡

እንቅስቃሴያቸው ምን ያህል ውጤታማ ሆኗል የሚለው ላይ በርካታ ጥያቄዎች የሚነሱ ቢሆንም፣ ከንግድ ዘርፉ የበለጠ ጠንካራ ሆኖ ይወጣል የተባለው የዘርፉ ማኅበራት ምክር ቤት ግን የታሰበውን ያህል ሊሆን አልቻለም፡፡ በተለያዩ የዘርፍ ምክር ቤቶች አመራር ሆነው የቆዩትና በአሁኑ ወቅትም የኦሮሚያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ አበበ በንቲ፣ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የተባለውን ያህል ጥንካሬ ባይኖራቸውም ብዙ ለውጥ እያሳዩ ነው ይላሉ፡፡ አባላትንም እያበዙ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አበበ፣ የኦሮሚያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

የዘርፍ ምክር ቤቱ 75 ሺሕ አባላት ማፍራት ችሏል ያሉት አቶ አበበ፣ ይህ ትልቅ ለውጥ ነው ብለዋል፡፡ ከ380 ሺሕ በላይ የንግድ ኅብረተሰብ ባለበት ክልል አሁን ያሉት አባላት በቂ ናቸው ባይባልም ይህንን እያሰፋን እንሄዳለን ብለዋል፡፡

ከመጀመርያው አደረጃጀት ጀምሮ አሁን የደረሰበት ደረጃ ድረስ በርካታ ጉድለቶች የነበሩበት እንደነበር የሚከራከሩ ወገኖች ደግሞ፣ በተለይ ይህንን አገር አቀፍ የዘርፍ ምክር ቤት በበላይነት ይመሩ የነበሩ ጥቂት ግለሰቦች ወደ አሥር ዓመታት ለሚሆን ጊዜ የአመራሩን ቦታ የሙጥኝ ብለው መያዛቸው ለድክመቱ አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ አቶ አበበ እንዲህ ያለው ነገር ለመለወጥ ብዙ መሠራት እንዳለበት አመልክተው፣ ዘርፍ ምክር ቤቶች ከተሰጣቸው ተልዕኮ አንፃር ብዙ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ከዘርፍ ምክር ቤቱ አቋምና ተግባር አንፃር የተለያዩ ሐሳቦች ቢኖሩም፣ ባለፈው ዓመት በኃላፊነት ላይ የነበሩት አመራሮች ከሥልጣን ላለመውረድ ያደጉት ፉክቻ ይታወሳል፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ታክሎበት በአዲስ አመራሮች ተተክተው ውዝግቡ እንዲረጋጋ ተደርጓል ተብሎም ነበር፡፡ ሆኖም አዲሱ አመራር ኃላፊነት በወሰደ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተፈጠረ ሌላው ችግር አገር አቀፉን የዘርፍ ምክር ቤት ስም የሚያስነሳ፣ በንግድም ሆነ በዘርፍ ምክር ቤቶች ያልተስተዋለ ክስተት ተከስቷል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ እያሱ ሞሲሳና ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ልሳኑ በለጠ በብሔራዊ ደረጃ ከተወከለ አንድ የንግድ ልዑካን ጋር ወደ አውስትራሊያ ሄደው መቅረታቸው ነው፡፡ አንድ በአገር አቀፍ ደረጃ የታወቀ የማኅበር በመሪዎች ለሚመሩት ማኅበር አባላት ምንም ሳይተነፍሱ በዚያው መቅረታቸው፣ የዘርፍ ምክር ቤቱንም ሆነ አጠቃላይ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን አንገት ያስደፋ ድርጊት ሆኗል፡፡ የአቶ እያሱ ወጥቶ መቅረት በሚዲያ የሰሙ መሆናቸውን አቶ አበበ አስታውሰው፣ በድርጊቱ መቆጨታቸውን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ኮብላዩን አቶ እያሱን በመተካት እየሠሩም ቢሆኑ በአጭር ጊዜ ፕሬዚዳንቱን የሚተካ ይመረጣል ብለዋል፡፡

የአቶ እያሱ እንዲህ ባለው መንገድ ኃላፊነታቸውን መልቀቅ ብዙ አያስጨንቀንም የሚሉት አቶ አበበ፣ ‹‹ወላድ ውላ ትግባ ለአገር የሚሠሩ ብዙዎች ስላሉ በቅርብ ጊዜ ጠንካራ አመራር አንዲተካ እናደርጋለን፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ አቶ እያሱ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውስጥ የቦርድ አባልና የኦሮሚያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መሆናቸው ጉዳዩን አነጋጋሪ ቢያደርገውም፣ የእርሳቸውና ምክትላቸውን ለመተካት ግን ሕጋዊ አካሄድ ሊኖር ይገባል ተብሏል፡፡

እነዚህን አመራሮች ለመተካት የተወሰነው ውሳኔ ደግሞ እንደገና በዘርፍ ምክር ቤቱ ውስጥ ሌላ መነጋገሪያ ፈጥሯል፡፡፡ የእነዚህ አመራሮች ከአገር ወጥቶ መቅረት ከተረጋገጠ በኋላ የአገር አቀፉ ቀሪ የቦርድ አባላት እነዚህን ለመተካት የወሰኑት ውሳኔ አሁንም የምክር ቤቱን ደንብና መተዳደሪያ ሕግ የጣሰ ነው የሚል አስተያየት እንዲሰነዘር አድርጓል፡፡

አቶ አበበም ይህ አካሄድ ደንብ የጠበቀ ያለመሆኑን ጠቁመው፣ ፕሬዚዳንቱንና ምክትል ፕሬዚዳንት የመረጠው ጠቅላላ ጉባዔው ነውና እነርሱን የሚተካውም ይኸው ጠቅላላ ጉባዔ ነው ብለዋል፡፡

የአንድ ተቋም ከፍተኛ አመራሮች እንዲህ ባለ መንገድ ሲኮበልሉ ተቋሙ ከፍተኛ አመራሩን አጥቷል ማለት ስለሆነ ይህንን ክፍተት ለመድፈን ቀሪው ቦርድ እርስ በርሱ ከመሿሿም በቀጥታ ጠቅላላ ጉባዔውን መጥራት እንደነበረበት ተገልጿል፡፡ አሁን የእነርሱን ቦታ በጊዜያዊነት የተኩት ግለሰቦች ኃላፊነቱን ለጠቅላላ ጉባዔው መስጠት አለባቸው፡፡

በአዋጅ ቁጥር 341/95 ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የመምረጥ ሥልጣን ያለው ጠቅላላ ጉባዔ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አበበ፣ እስካሁን ድረስ እከሌ ተተኪ ወይም ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆኗል እከሌ ምክትል ሆኗል የሚለው መረጃ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ እስካሁን የደረሰን መረጃ በፕሬዚዳንቱና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ከሥራ ገበታቸው ላይ ሳያሳውቁ መቅረታቸውን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡና የሰባት ቀን ገደብ ሰጥቶ እስከዚህ ድረስ ካልመጣችሁ ዕርምጃ እንወስዳለን የሚለው ደብዳቤ ብቻ ነውም ይላሉ፡፡

ስለዚህ ያሉትን የቦርድ አባላት በቦርድ አባልነታቸው ነው የምናውቃቸው ያሉት አቶ አበበ፣ አሁንም መሆን ያለበት ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲወስን ማድረግ ብቻ ነው ይላሉ፡፡

ከአገር አቀፉ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና ከአንዳንድ የቦርድ አባላት ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ፣ በዚህ ጉዳይ ለመወሰን የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ሥር ያሉ ምክር ቤት አባል ምክር ቤቶችን ለስብሰባ ለመጥራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ አባል ምክር ቤቶችም ፕሬዚዳንቱንና ምክትል ፕሬዚዳንቱን ለመተካት ያስችላል የሚለውን ጠቅላላ ጉባዔ እንዴት ይጠራ የሚለው ላይ መክረው ውሳኔ ሊሰጡ ይችላሉ ተብሏል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አሁን ያለው ጊዜያዊ አመራር ሕጋዊ ሊሆን እንደማይችል እየተነገረ ነው፡፡ የዘርፍ ምክር ቤቱን በጊዜያዊነት እንዲመሩ ቦርዱ የሰየማቸው ሐሰን አብዲላሂን (ዶ/ር) እንደሆነ ይታወሳል፡፡