Skip to main content
x
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለ20 ኤጀንሲዎች ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለ20 ኤጀንሲዎች ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ለመሠማራት ፈቃድ የሰጣቸው የአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች 20 ብቻ ናቸው አለ፡፡ ይህ የተባለው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋናው አድማሱ፣ የሰው ኃይል ጥናትና ሥምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አበበ ኃይሌና የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

ምንም እንኳን ለኤጀንሲነት ምዝገባ 923 ድርጅቶች ማመልከቻ ያስገቡ ቢሆንም፣ መሥፈርቱን አሟልተው ፈቃድ ማግኘት የቻሉት ግን 20 ብቻ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

ፈቃድ ተሰጥቷቸው በውጭ አገር የሥራ ሥምሪት የሚሠማሩ ድርጅቶች 100 ሺሕ ዶላር ማስያዝ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች ይህንን መስፈርት ያሟሉ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በእነዚህ 20 ድርጅቶች የሚጀመረው የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ወደ ኳታር፣ ኩዌትና ጆርዳን መሆኑ በመግለጫው የተነገረ ሲሆን፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር የሠራተኞች ሥምሪት ስምምነት ቢኖርም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስላልፀደቀ ለጊዜው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚደረግ የሥራ ሥምሪት እንደማይኖር ተገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ ፈቃድ ከመስጠት ባለፈም ከሦስት ጊዜ በላይ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውን 97 የአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ድርጅቶች ፈቃድ መሰረዙንም አስታውቋል፡፡

ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ሠራተኞችንም ለማሠልጠን በሁሉም ክልሎች 40 የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት መመረጣቸውም ታውቋል፡፡