Skip to main content
x

የፀረ ሙስና ትግልን ለማጠናከር በቅርቡ የተገባው ቃል በትክክል መጠበቅ አለበት

 በኪሮስ ሙሉነህ

የአገራችን ከፍታ ዕውን ለማድረግ የሚደረገውን ርብርብ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያደናቅፈው  ሙስና መሆኑን የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ መንግሥትም ይህንኑ በተለያዩ መድረኮችና ሚዲያዎች ላይ ገልጿል፡፡  ከፍተኛ ሙስና እየተፈጸመ ያለው በመንግሥት ኃላፊዎች መሆኑን ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት የሙስና ወንጀል ምርመራ መዝገቦች ማሳያዎች ናቸው፡፡ ከፍተኛ የሙስና ወንጀል እንዲሠራ ምንጭ የሚሆኑት ደግሞ በአቋራጭ ለመበልፀግ አልመው የሚንቀሰቀሱ ጥገኛ ባለሀብቶች መሆናቸው ነው፡፡  ጥቃቅን ሙስና የሚሠሩት ደግሞ በየዕለቱ ከተገልጋይ ኅብረተሰብ ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው፡፡ ስለሆነም ለጥቃቅን ሙስና ምንጭ የሚሆነው ደግሞ ተገልጋዩ ኅብረተሰብ ራሱ ነው፡፡ ተገልጋይ ኅብረተሰብ የመንግሥት አገልግሎት ፈልጎ ያላሟላቸው ነገሮች ሲያገጥሙት ወይም በሕጋዊ መንገድ ሊያገኝ የማይችለው ጉዳይ ሲያገጥም ጉዳዩን በሕገወጥ መንገድ ለማስፈጸም ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር የግድ ይደራደራል፡፡ እነዚህ ከተገልጋይ ኅብረተሰብ ጋር በመመሳጠር ሙስና ሲሠሩ የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞች በተለያየ አጋጣሚም ሆነ በወቅታዊ ግምገማ ወይም ተደርሶባቸው  ከቦታቸው እንዲነሱ ሲደረጉ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሙስና ወንጀል ጠቋሚ ይሆናሉ ወይም የመንግሥት ቀንደኛ ጠለት ሆነው እንቅስቃሴ ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡ ከጥገኛ ባለሀብት ጋር ሲሞዳሞድ የቆየው የመንግሥት የሥራ ኃላፊም ከቦታው እንዲነሳ ሲደረግ የመንግሥት ጠላት ይሆናል ወይም በተወለደበት አካባቢ በሆነው ባልሆነው ሕዝብን በመንግሥት ላይ ለማነሳሳት ጠንክሮ ይሠራል፡፡ ካልሆነም ከአገር ወጥቶ የተለያዩ ሚዲያዎች በመጠቀም በመንግሥት ላይ የጥላቻ መግለጫዎችን ሊያስተጋባ ይችላል፡፡ 

ታዲያ ሙስናን የሚታገለውም ሆነ የሚሠራው የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ከሆኑ እንዴት ተደርጎ ነው በአገር ደረጃ ሙስና መቀነስ የሚቻለው? በኅብረተሰቡ ውስጥም በሕገወጥ መንገድ ጥቅም ያገኙ ወይም ጉዳይ ያስፈጸሙ ተደርሶባቸው እንዲከሽፍ የተደረገባቸው ሰዎች እንዴትስ የአገሪቱ የሙስና ወንጀል መከላከል ተባባሪና አጋር ሊሆኑ ይችላሉ?  የመንግሥት ሥራ ኃላፊን ከጎኑ አሠልፎ በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚንቀሳቀስ ጥገኛ ባለሀብት ተደርሶበት ሸቤ የገባ ወይም ከአገር የኮበለለ እንዴት ሆኖ ነው ሙስና እንዲጠፋ ተባባሪና አጋር የሚሆነው? በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መፍትሔ ከማስቀመጥ በፊት በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣውን ሙስና ወንጀል ለመከላከል በቅድሚያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በትክክል መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሙስና በማንና እንዴት ይሠራል የሚለውን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሙስና ወንጀል የሚፈጸመው ከግብር ሰብሳቢው ዜጋ ተሰብስቦ በልማት ሥራ ላይ እንዲውል ለመንግሥት ተቋም ከተፈቀደው በጀት ላይ ነው፡፡ የሀብትና ንብረት ዝርፊያ፣ ስርቆትና ማጭበርበርም የሚፈጸመው ከዚሁ ለመንግሥት ተቋም ከተፈቀደው በጀት ከተፈጸመው ንብረት ላይ ነው፡፡ ሰዎች የማይገባቸውን ጥቅም በሕገወጥ መንገድ ለማግኘት ሲሉ አገልግሎቱን የሚሰጡ ሰዎችን በደላላ አማካይነት፣ በዘመድ አዝማድ አማላጅነት ወይም ጥቅም (ጉቦ) በመስጠት ይቀርባሉ፡፡ የሚያጭበረብረው ወይም የሚዘርፈው ወይም የሚሰርቀው ደግሞ በንብረት ላይ ማዘዝ የሚችልበት ሁኔታ ከተመቻቸለት ወይም ያለው ንብረት ሊፈጸም ለታሰበው ሙስና ወንጀል አመቺ መሆኑን ሲያረጋገጥ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ተግባር መጠኑ ይነስ ወይም ይብዛ እንጂ የማይፈጸምበት የመንግሥት ተቋም ወይም ዘርፍ የለም፡፡ ሁሉም ጋ አለ፡፡ በሀብት እንቅስቃሴ ላይ የማዘዝ ሥልጣን ያላቸው የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በስርቆት ወይም በማጭበርበር ሙስና ይሠራሉ፡፡ በአጠቃላይ ውኃ ውስጥ ያለው ዓሳ ውኃ አይጠጣም ወይ የማለት ዓይነት፡፡ ሙስና በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትና በሃይማኖት ተቋማት ጭምር ወዘተ. በስፋት ይፈጸማል፡፡ የሙስና ወንጀል በሁሉም ተቋማትና ዘርፎች ተደራሽ ከመሆን አኳያ ሲታይ ግንባር ቀደም ነው፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚፈጸም ሙስና ውስብስብና መጠኑ ከፍተኛ ነው፡፡ በአብዛኛው የኅብረተሰብ አካላት ዘንድ የሙስና የወንጀል ተጠቂ ብቸኛው መንግሥት ነው ተብሎ ይወሰዳል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመንግሥት ተቋማት ብቻ የሚሠሩ ሙስናዎችን እንዴት እንከላከል? የሚለውን በጥልቀት ማየት ያስፈልጋል፡፡ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥት በየመድረኩ እኔን ያስቸገረኝ ኪራይ ሰብሳቢነትና የእሱ መገለጫ የሆነው ሙስና ነው እያለ ነው፡፡ እንዲህ ሲል በመድረክ ከመናገር ውጪ ጠንካራ የሙስና መከላከያ ሥርዓት ዘርግቶ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ በቅድሚያ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል፡፡ 

መንግሥት በስብስባ መድረኮችና ሚዲያዎች ላይ የሚባለውን በተግባር ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በትክክል መንግሥት የፀረ ሙስና ትግል እየደገፈ ነው ወይ? የዚህ ጽሐፍ አቅራቢ አይደለም ነው መልሱ፡፡ በርግጥ የአራቱም ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በ16 ቀን ግምገማ በተደረሰው ድምዳሜ ላይ መግለጫ ሲሰጡ ዴሞክራቲክ ተቋማትን ጨምሮ የፀረ ሙስና ትግሉን በኃላፊነት ስሜት አለመምራታቸውንና አለማገዛቸውን ማመናቸው በጣም ቢያስደስተኝም በእርግጥ በገቡት ቃል መሠረት ያጠናክሩታል ወይ? የሚለውን ምላሽ ለማግኘት ብዙ መንገዶችን መሄድ ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርም እኮ በአንድ ወቅት ለተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ሲያቀርቡ የዴሞክራቲክ ተቋማትን እናጠናክራለን ብለው ቃል ገብተው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ማጠናከር ለኔ የሚመስለኝ ለሥራ በቂ በጀት መመደብ፣ አፈጻጸሙን መከታተልና መገምገም፣ ተቋሙ ለሚገጥመው ችግር ወቅታዊ የመፍትሔ ምላሽ መስጠት ነው፡፡

በተለይም ከአራቱ ሊቃነ መናብርት አንዱ ሊቀመንበር በአንድ ወቅት የክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ ትግሉን ስለመሩ የፀረ ሙስና ትግል የሚያስተባብረው ተቋም የሚገጥመውን ችግር ከሌሎች በሚገባ ይረዱታል የሚል ድምዳሜ ነበረኝ፡፡ አሁን ደግሞ እሳቸው ውስጥ አዋቂ መንግሥት ሆነው ሳሉ በአገሪቱ በፌዴራልና በክልል በሁለት ዓይነት አደረጃጀት የፀረ ሙስና ትግል እየተካሄደ ነው፡፡ ፌዴራል የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና ወንጀል ጥቆማ ተቀብሎ የምርመራ ሥራ እንዳይሠራ ተደርጓል፡፡ የክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ደግሞ የምርመራ ዓቃቤ ሕግ ሥራዎች በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ስለሆነም ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው የፌዴራልና የክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የፀረ ሙስና ትግሉን እርስ በርሳቸው ተናበው እየሠሩ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ፌዴራል የራሱ ችግር ስላለበት ክልሎችን እየደገፈ አይደለም፡፡ በሪፖርት አቀራረብ ላይ የተለያዩ ናቸው፡፡

በእርግጥ የተለያየ አደረጃጀት ቢኖራቸውም የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት የየራሳቸው የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖችን አደራጅተው ትግሉን እየመሩት እንደሆነ ጸሐፊው ይረዳል፡፡ በክልል ደረጃ ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱት የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ውስጥ በጣም ጥቂቶቹ በሰው ኃይል አቅም ያላቸውና ውጤታማ ተግባራትን በማከናወን እንደሚገኙ ጸሐፊው በተለያየ አጋጣሚ ያገኛቸው መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ግን በሰው ኃይልና በበጀት እጥረት እንዲሁም በሙያ ዕውቀትና ክህሎት በጣም ችግር ያለባቸውና አቅም የሚያንሳቸው ናቸው፡፡ በፌዴራል ደረጃም መንግሥት የምርመራ ሥራ እንዲቀነስ ካደረገ በኋላ የተጠናከረ የሙስና መታገያ ተቋም አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ለሙስና መታገያ በአዋጅ ቁጥር 235/93 (በአዋጅ ቁጥር 883/2008 እንደተሻሻለው) የተቋቋመው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሥልጣንና ተግባርን በአዋጅ ቁጥር 943/2008 ያሽመደመደው መንግሥት ራሱ ነው፡፡ በሚያዝያ ወር 2008 ዓ.ም. በቁጥር 883/2008 የተሻሻለው አዋጅ ልክ በዓመቱ መጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. በቁጥር 943/2008 እንዲሻር ተደርጓል፡፡ መንግሥት አዋጅ ቁጥር 943/2008 ሲያወጣ ተበታትኖ ሲሰጥ የነበረውን የፍትሕ ዘርፍ አገልግሎት በአንድ ቦታ ላይ በማድረግ አገልግሎት በመስጠት ሕዝቡን ለማስደሰት በተለይም በፍትሕ ዘርፍ አገልግሎት ዙሪያ የዜጎች አመኔታን ለማግኘት ይበል እንጂ እውነት የተባለውን አመኔታ ለመምጣት ያስችላል ወይ? እንዴት አዋጅ አንድ ዓመት በትክክል ሳይፈተሽ እንዲቀየር ተደረገ? የሚሉትና ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑት ጥያቄዎች ላይ ወደፊት በዝርዝር እመለሳለሁ፡፡

አዋጅ 943/2008 ከወጣ በኋላ የተከናወነውንና ከአዋጁ መውጣት በኋላ የተከናወነውን ሥራ በማነፃፀር እኮ ለውጡን ማየት ይቻላል፡፡ የፍትሕ ሥርዓት ችግር ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ እንደሆነ እንጂ የመጣው ለውጥ አይታይም፡፡ ድሮ ሰው በፍትሕ ሥርዓት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለቅሳል፣ አሁንም እያለቀሰ ነው፡፡ እኔ ባጋጠመኝ ጉዳይ ከ2009 እስከ 2010 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ድረስ በፍርድ ቤት የደረሰብኝ የቀጠሮ ብዛት (ለትንሽ ጉዳይ ከአሥር በላይ የቀጠሮ ምልልስ መኖር) እና በመጨረሻም በፍርድ ቤት በእውነታ ላይ ያልተመሠረተውና ሚዛናዊ ያልሆነ ውሳኔ መስጠት ራሱ በቂ መረጃ ነው፡፡ የማይካደው ሀቅ ቢኖር ለሰዎች የሥልጣን ክምር ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለዓቃቤ ሕግ ሰዎች የደመወዝ ጭማሪ አስገኝቶላቸዋል፡፡ የሥልጣን ክምር ያገኙ ሰዎች በየጊዜው ሚዲያዎች ላይ እንዲታዩ አድርጎላቸዋል፣ በአጠቃላይ ታዋቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ጥሩ ሥራ ነው ከተባለ ጥሩ ነው፣ ለኔ ግን ጥሩ አይደለም፡፡ ሰዎችን ያለበቂ ማስረጃ አላግባብ የመከሰስና ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ የማድረግ፣ ለጥፋቱ ማስረጃ እያለ ያለፍርድ ቤት ውሳኔ ጭምር ሰዎች ከእስር ቤት እንዲለቀቁ ማድረግ፣ ሰዎች ፍትሕ ለማግኘት መንከራተት፣ የፍርድ ቤት ቀጠሮ መብዛትና ፍርደ ገምድል ውሳኔዎችን መስጠት ድሮም ነበሩ፡፡ አሁንም አለ፡፡ ወደፊትም ይኖራል፡፡

ከአዋጁ መውጣት በኋላ የኮንትሮባንድ ንግድ ስለተባባሰ መንግሥት ልዩ ግብረ ኃይል በመሰየም በዘመቻ የመከላከል ሥራ እየሠራ እንደሆነ ጸሐፊው ይረዳል፡፡ አዋጁ ሲወጣ ይቀረፋል የተባለው እንግልት በፊት ከነበረው እንግልት ለውጥ ካለ እስኪ ጉዳዩ በመረጃ ተደግፎ ለሕዝብ ይቅረብና እንወያይበት፡፡ መሬት ላይ የሚታየው ችግሮች እየተባበሱ እንደሆነ እንጅ እየቀነሱ አይደለም፡፡ የአዋጁ መውጣት የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት ይባል እንጂ የቀድሞ የፍትሕ ሚኒስቴር ሲሰጥ ከነበረው አገልግሎት ሚዲያ ላይ መታየት ካልሆነ በስተቀር የተለየ ለውጥ አይታይም፡፡  ስለሆነም አዋጁ የማይመሳሰሉትን ወደ ማይገባ አደረጃጀት እንዲደራጅ የተደረገው የኅብረሰተብ አመኔታ ለመምጣት ታስቦ ሳይሆን ጥቂት ግለሰቦች መንግሥትን ማታለላቸውን ጸሐፊው ይገነዘባል፡፡ አዋጁ ከወጣ ዓመት ባልሞላ ጊዜ እኮ ነው የዓቃቤ ሕግ ባለሙያዎች አምስት ሚሊዮን ብር ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ የተያዙት፡፡ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲባባስ አድርጓል፡፡ የገቢ መሰብሰብ ዕቅዱ አልተሳካም፡፡ የፍትሕ ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሩ ከበፊቱ በጣም እየባሰበት እንደሆነ እንጂ የተባለውን አመኔታ እያመጣ አይደለም፡፡ መንግሥትም የተሻሻለውን አዋጅ ዓመት እንኳን ሳይሞላው እንዲለወጥ ሲያደርግ ምክንያቱን በግልጽ ለዜጎች አልነገረንም፡፡

በእርግጥ የማይካደው የግለሰቦች ፍላጎት በሚዲያ ላይ ጭምር የኮሚሽኑ ሥራ ላይ ጥላሸት ለመቀባት ሲጣጣሩና በተደጋገሚ በትዕዛዝ ጭምር ሲያጮሁት እንደነበር አስታውለሁ፡፡ በተለይ የመንግሥት ሚዲያዎችም የኮሚሽኑን ዓላማ አስፈጻሚነት ላይ አፍራሽ የሆኑ ቃላትን በተደጋገሚ ያስተላልፉ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እንዲያውም አንድ ግለሰብ መንግሥት ራሱ በሕግ ለኮሚሽኑ የሰጠውን ሥልጣንና ተግባር በመርሳት፣ ኮሚሽኑ ራሱ መርማሪ ራሱ ከሳሽ ያለውን ነበር በተደጋጋሚ በመንግሥት ሚዲያ ላይ እንዲተላለፍ አድርጎ የነበረው፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን  የማስፈጸም ችግር ካለበት በአዋጅ የሚያከናውነውን ሥልጣንና ተግባርን ለሌላ ከመስጠት ይልቅ የነበረውን አመራር በአዲስ በመቀየር የማጠናከር ዕድሉ የራሱ  የመንግሥት ነበር፡፡ የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ሲባል ተፈብርኮ ከሚወራው ወሬና አሉባልታዎች ካልሆነ በስተቀር አመራሩና ሠራተኛ ችግር አለበት ለማለት ተጨባጭ ችግር ይዞ የቀረበ ማንም ዜጋ የለም፡፡ እንደማንም ዜጋ ሙስና ሠርተው ከሆነ ተጨባጭ መረጃ ቀርቦ መከሰስ ይገባቸው ነበር፡፡ መረሣት የሌለበት በኮሚሽኑ ላይ የሚያስወሩት ሙስና መሥራትን የሚፈልጉ ወይም ሙስና ሠርተው የተከሰሱና ያልተከሰሱ ወይም ሙስና የሠሩ ሰዎችም አልተሠሩም ብለው የሚያስቡ ሰዎች መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡

መንግሥትም የኮሚሽኑን የመመርመርና የመክሰስ ሥልጣን ለሌላ ሲሰጥ ይህን አላረጋገጠም፡፡ እንዲያውም ኮሚሽኑ በሥራ አፈጻጸም ድክመት አልተከሰሰም ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኅብረተሰቡ ቢያንስ የሙስና ወንጀል ሥራ የተጠናወታቸው ወይም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ያላቸው የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የሚያደርሱትን እንግልት ላይ ጩኸቱን የሚያሰማበት፣ ተቋሙ ከነችግሩም የደሃውን ዜጋ ድምፅ የሚያዳምጥ ተቋም መሆኑ መንግሥት ጠፍቶት ሳይሆን ጥቂት የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ከጥገኛ ባለሀብቶች ጋር ያሴሩት ሴራ እንደነበር ጸሐፊውን ጨምሮ ብዙ ዜጎች ይስማሙበታል፡፡ መንግሥት የተሳሳተው የሕዝብን የልብ ትርታ ሳያዳምጥ በመርሳት እነዚህን ጥቂት ግለሰቦችና ጥገኛ ባለሀብቶች ሥውር ሴራ መስማቱና ቦታ መስጠቱ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ለመንግሥት ኮሚሽኑ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሕዝብን ሰብስቦ ቢጠየቅና ቢያደምጥ ኖሮ ምነኛ በተወደደ ነበር፡፡ አመኔታውም በዚያው ልክ ይሆን ነበር፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የተቋሙን ሥልጣንና ተግባር በሚያሳጣው አዋጅ ረቂቅ ሰነድ ላይ  ባዘጋጀው የሕዝብ ውይይት መድረክ ላይ ጸሐፊው ተገኝቶ ነበር፡፡ የሆነው ኮሚሽኑ በሙስና ወንጀል ተከሰውና አስፈርዶበቸው ቅጣታቸውን የጨረሱ ሰዎች ስብስብ ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡ መንግሥት ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀል ጥቆማ የመቀበል፣ የመመርመርና የመክሰስ ሥራዎችን እንዳይሠራ እንዲያደርግ ነበር በቁጭት ስሜት ሲያወሩና አስተያየት ሲሰጡ ነበር ያየው፡፡ ይህ ለመንግሥት አስበው ሳይሆን ቁጭታቸውን ለመወጣት ነበር በዘመቻ ሲንቀሳቀሱ የነበረው፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ያካበተውን ልምድ በመጠቀም በጥገኛ ባለሀብቶች እንዲሁም ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ባላቸው የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ላይ የተጠናከረ በትሩን ማሳረፍ ሲጀምር በእነዚህ ጥገኛ በሆኑ በባለሀብቶች አዕምሮ የተመሩት አንዳንድ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ርብርብ የተቋሙን ሥራ አሽመድምደውታል፡፡ በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ጥናት ጭምር በአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይሠራበታል ለተባለው ተቋም የሙስና ወንጀል እንዲመረምር ሥልጣን ተሰጠው፡፡ የተቋሙን ሥልጣንና ተግባር በማሽመድመድ ብቻ አላበቁም፣ ይባስ ብለው ደግሞ የሚሠራበትን ለገሐር ከሚገኘው ሕንፃ አስለቀቁት፡፡ የሚገርመው ሕንፃውን እንዲለቅ ደብዳቤ የጻፉት የቤቶች ኮርፖሬሽን የበላይ ጠባቂ መሆናቸው ነው፡፡ የጥቅም ግጭት ይሉሃል እንደዚህ ነው፡፡ አንድ የመንግሥት ኃላፊ እንዴት ከሕዝብ የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ ለራሱ የሚመቸውን ውሳኔ ይወስናል? ደግሞስ ማን ይጠይቃል? ጊዜ ሲደርስ የዚያ ሰው ይበለን፡፡  ሕዝብ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ተጨባጭ ስለመሆኑ በቂ ማረጋገጫ ባይያዝም በአንድ ወቅት ሰውዬው ኃላፊ በነበሩበት መሥሪያ ቤት ውስጥ ኮሚሽኑ የሙስና ተጠርጣሪዎችን በማሰሩ ይህን ለመበቀል የወሰዱት ዕርምጃ ነው ሲባል ጸሐፊው ሰምቷል፡፡ ኮሚሽኑም የአልሞት ባይ ተገዳይነት ለማሳየት ብቻ በሁለት ቦታ የተከፋፈለ ተቋም ሆኖ ሥራውን ለመጀመር ሲጣጣርና ሲዳክር ይታያል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ ከኢሲኤ ጀርባ በተለምዶ ሳልኮስት (በመኖሪያ ቤቶች የተከበበና መጥፎ ሽታ ያለበት ስለሆነ ለሥራ አመቺ አይደለም) እና ካዛንቺስ የተለያየ ቦታ ቢሮ ተሰጥቶት ሥራውን ለማሠራት፣ ለመቆጣጠርና ለመምራት በማያመች ሁኔታ መደረጉ መንግሥት ሙስና ወንጀል ላይ የሚነገረውና የሚተገብረው ፍየል ወዲህና ቅዝምዝም ዓይነት የተለያዩ እንዲሆኑ አድርጎታል፡፡  የሙስና ወንጀል ምርመራና ዓቃቤ ሕግ ሥራ ለሌላ አካላት ሲሰጥ የኮሚሽኑ ቀሪ ሥራዎች ሙስና ወንጀልና ብልሹ አሠራር መከላከልና የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትምህርቶችን ማስፋፋት ነው፡፡ የሙስናን ወንጀል ለመከላከል ከሚያከናውናቸው ሥራዎች አንዱ ሊፈጸም የታሰበውን የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን በማግኘት ማስቆም ይጠበቅበታል፡፡ ኮሚሽኑ ይህን ጥቆማ የሚያገኘውና የሚያስቆመው በአሁኑ አደረጃጀት ከፌዴራል ፖሊስ ሊሆን ነው፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ቸር ከሆነ ሊልክለት ይችላል፡፡ አለመላክም መብቱ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ደግሞ በዚህ ዙሪያ ይህን በተገቢው መንገድ ለማከናወን ጉልበት ያለው አይደለም፣ የጥቆማ መቀበያ ሥርዓትም የለውም፡፡ በተጨማሪ ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለው ተቋማት በራሳቸው ሙስና እንዲከላከሉ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ሥራ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ሰነድ አዘጋጅቻለሁ እያለ ነው፡፡ በሙስና መከላከል ስትራቴጂ ለተቋማት ኃላፊዎች ሥልጠና በመስጠት ወደ ተግባር ገብቻለሁ ይበል እንጅ በ2009 እና በ2010 ዓ.ም.  የመጀመርያ ስድስት ወር አፈጻጸም ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ መምጣት አልቻለም፡፡

ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶች ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የመጀመርያው ራሱ ኮሚሽኑ በስትራቴጂው ላይ የያዘው ዕውቀትና ክህሎት ግልጽነት የሚጎለው መሆን ሲሆን፣ ሰነዱን በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሊያስተግብር የሚችል በቂ ልምድ፣ ክህሎትና ዕውቀት ያለው የሰው ኃይል አለመኖሩ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ሁለተኛውና በጣም አነጋጋሪ የሆነው የማይተገበሩ የመንግሥት ተቋማት በብዛት መኖር ነው፡፡ ከፍተኛ ሀብትና ንብረት የሚያንቀሳቅሱና የክትትልና የቁጥጥር ሥራ የሚያከናወኑ ተቋማት ጭምር ስትራቴጂውን ለመተግበር ፈቃደኛ አለመሆናቸው አሳሳቢ ችግር ነው፡፡

ኮሚሽኑ ይህን ይበል እንጂ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር በአገሪቱ የሰው ኃይል ልማት ሥራውን ወደ ጎን በመተው የኮሚሽኑን ሥራ ለመሥራት መፍጨርጨር ይህች አገር ወዴት እየሄደች ነው እንዲባል አድርጎታል፡፡ ኮሚሽኑ በሙስና መከላከል ስትራቴጂ መሠረት ተቋማት በራሳቸው ሙስናን እንዲከላከሉ ሲሠራ፣ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ደግሞ ተቋማት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ማክሰሚያ ዕቅድ በማቀድ እንዲተገብሩ ሲያስገድድ ይታያል፡፡ በሕግ ያልተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር ማስተግበር ማለት ይህ ነው እንግዲህ፡፡ ሁለቱም ተቋማት የሚሠሩት አንድ ዓይነት ተግባራትን ለማስተግበር ተቋማትን በር ማንኳኳታቸው በእኔ አመለካከት ብክነት ነው፡፡ ሌላው የኮሚሽኑ የሥነ ምግባር መርሆዎች የነበሩትን በቃላት አሰማምሮ የሥነ ምግባር ኮድ በማለት መመርያ ያወጣው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ነው፡፡ የሥነ ምግባር ትምህርት ማስተማር፣ የሥነ ምግባር መመርያ ማውጣት ወይም ተቋማት እንዲያወጡ ማድረግ በአዋጅ ቁጥር 434/1997 ለኮሚሽኑ የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ሆኖ እያለ እንደገና በአዋጅ ቁጥር 986/2008 ለፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ይህንኑ ሥልጣንና ተግባር የሰጠው የተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የሚገርም ነው፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው የአገሪቱ ሕግ አወጣጥ ምን ያህል ጥንቃቄ እንደሚጎለው ነው፡፡ ሚኒስቴሩ በአዋጅ የተሰጠውን ሥልጣን በመጠቀም በአሁኑ ጊዜ የሥነ ምግባር መርሆዎችን ለማስተማር ሲዳክር ይታያል፡፡ ይህ የመንግሥት ያለህ የሚያስብል ነውና ሊታይ ይገባል፡፡ የመርሆዎች ተፈጻሚነትን እንደሚከታተልም ሲያስተምረን ነበር፡፡

እንግዲህ የተገለጹት ቱባ ቱባ የሆኑ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ላይ እንዴት ሆኖ ነው በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚፈጸመው ሙስና ሊቀንስ የሚችለው፣ የመንግሥት ድጋፍ ሳይኖረው ኮሚሽኑ በምን አቅሙ ነው ሙስና በትክክል መከላከል የሚቻለው? በሕግ የተሰጠው ሥልጣንና ተግባራት ለተለያዩ ተቋማት እየተቦጨቀ እየተሰጠ ነው፡፡ ተቋሙ ስትራቴጂውን ማስፈጸም የማይችል ከሆነ የመንግሥት ተቋማትን ሙስና ወንጀል እንዴት መከላከል ይቻላል? አቅም የሌለውን ተቋም አስቀምጦ ውጤት መጠበቅ ሕዝብ ማታለል አይሆንም ወይ? የጸሐፊው ጥያቄ፡፡  ዋናውን ሥራ በጠራራ ፀሐይ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር እየወሰደ ቢሆንም ኮሚሽኑ በሥነ ምግባር ትምህርት የሰውን አመለካከት ለመለወጥ ይሠራል፡፡ ሥነ ምግባር ትምህርትን ለማስረጽ  የሚያስችል ብቃትና ክህሎት አቅም ውስንነት በኮሚሽኑ መኖሩ እንዳለ፣ ይህን ሥራ ለመሥራት የሚያስችል አዳራሽ እንኳን የለውም፡፡ አለ የተባለውና የተሰጠው አዳራሽ ሥልጠናው ለሚሰጣቸው ሰዎች  የሚመች አይደለም፡፡ በመኖሪያ ቤቶች መካከል የተወሸቀ አዳራሽ ነው የተሰጠው፡፡ ሠልጣኝ የሚሰጠውን ሥልጠና ዘና ብሎ  ለመውሰድ የሚያመች አይደለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኮሚሽኑ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዴት አድርጎ ነው መወጣት የሚችለው? የሚለውን ፍርድ ለራሱ ለመንግሥት እተዋለሁ፡፡

የመንግሥት ተቋማት በሙስና መከላከል ላይ ያላቸው ዳተኝነት ሌላው መሰናክል ነው፡፡ የመንግሥት ተቋማትን የሚመሩት በአብዛኛው በሹመት የተሰየሙ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰዎቹ የተሾሙት ባላቸው የትምህርት ዝግጅትና ታማኝነት ነው፡፡ ተቋሙ ውስጥ የፖለቲካ አመራር ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ይህን ቃል የተጠቀምኩት በአንድ ወቅት አንድ የመንግሥት ኃላፊ በሚዲያ ያሉትን ሰምቼ ነው፡፡ ፖለቲካው ሙስና የአገሪቱ ልማት እንቅፋት ነው እያለ ነው፡፡ እንግዲህ መንግሥት እምነት ጥሎበት የሾመው የመንግሥት ኃላፊ ግን ይህን ከልቡ እያዳመጠና እያስተገበረ አይደለም፡፡ በተቋሙ ውስጥ ለኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በመለየትና መፍትሔ በማስቀመጥ የትግበራ ዕቅድ እንዲያቅድ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ይጠይቃል፣ አቅዶ ይልካል፡፡ በየወሩ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሚኒስቴሩ ይልካል፣ ግብረ መልስ ይወስዳል፡፡ ነገር ግን በተቋሙ ሙስና ይሠራል፡፡  የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ በተቋም እንዲተገበር የሚፈልገው የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ነው፡፡ ይህ ስትራቴጂ ተቋሙ ይህን የሚያስፈጽም ኮሚቴ በማዋቀር፣ የመነሻ ሰነድ በማዘጋጀት፣ በመነሻ ሰነዱ መሠረት በተቋሙ ውስጥ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ የሥጋት አካባቢዎችን በመለየት የሙስና መከላከል ስትራቴጂ እንዲታቀድና እንዲተገበር፣ የሥጋት አካባቢዎችን የመለየት ሥራው ደግሞ የተቋሙ ሠራተኞች፣ የባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ ያስፈልጋል ይላል የኮሚሽኑ ስትራቴጂ ሰነድ፡፡ የሙስና መከላከል ስትራቴጂክ ዕቅድ ትግበራ ሒደቱ በኮሚሽኑ ክትትል የሚደረግበት ሲሆን፣ ተቋማት ይህን ለመተግበር ያላቸው ዳተኛነት ለዚያውም የመንግሥት ታማኝና ሹመኛ ኃላፊ ያለበት ተቋም መሆኑ በጣም የሚገርም ነው፡፡

በኅብረተሰቡ ዘንድ በሙስና ወንጀል መከላከል ዕይታ ላይ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በሙስና ወንጀል ተጎጂ ወዲያው ስለማይታወቅ ኅብረተሰቡ ዘንድ ሙስናን በቁርጠኝነት ለመታገል ያለው ዝግጁነት ብዙ መሥራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ የሙስና ወንጀል ጎጂነት ላይ በቂ ግንዛቤ ያልያዙ ሰዎች በአገራችን በብዛት አሉ፡፡ መንግሥትን ዘረፈ እንጂ እኔን ምንም አላደረገም የሚሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ የሙስና ወንጀል የሚፈጸመው በሕዝብ ሀብት ላይ ስለመሆኑ ገና በቅጡ አልታወቀም፡፡ በራስ ላይ ካልደረሰ በስተቀር ሙስናን ለመታገል በቁርጠኝነት የሚንቀሳቀስ አካል በጣም ውስን ነው፡፡ ኮሚሽኑ የተለያዩ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም በሙስና ጎጅነት ላይ ሲያስተምር ይስተዋላል፡፡ ግን ገና ጥልቅ ግንዛቤ ያልተያዘበት ጉዳይ በመሆኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሙስናን በቁርጠኝነት ለመዋጋት ያለው ዝግጁነት ብዙ የሚቀር ቢሆንም አሁን አሁን በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ሆነው የተለያዩ ጥቅም ሲያገኙ የነበሩ ሰዎች ከቦታው እንዲነሱ በመደረጋቸው ሕዝቡን ሲያምሱ ይስተዋላሉ፣ ቁጭታቸውን ሕዝብን በመንግሥት ላይ በማስነሳት ለመወጣት ሲፍጨረጨሩ በግልጽ እያየን ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይህን ጉዳይ ለሕዝብ በግልጽ ግንዛቤ ለማስጨበጥ መሥራት ይጠበቅበል፡፡ በአደባባይ ላይ ብቻ አገሪቱ እንድትታመስ እያደረጉ ያሉት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የተጠናወታቸውና ሙስና ለመሥራት ፍላጎት ያለቸው ሰዎች ናቸው ማለት ለኔ በቂ አይደለም፡፡ በሙስና ከኃላፊነት እንዲነሱ የተደረጉት እከሌና እከሌ ናቸው፣ ይህን ያህል ገንዘብ መዝረፋቸውን መረጃ አለኝ ያውላችሁ ማለት ይኖርበታል፡፡ ያልሆነውን አንዱን ጅብ አንስቶ ሌለውን ጅብ መተካት ትርጉም የለውም፡፡ ቀደም ሲል የበላውን ጅብ ማቆየትና በድጋሚ እንዳይበላ መከታተልና መቆጣጠር በቂ ይመስለኛል፡፡

የፍትሕ ዘርፉ ለሙስና ወንጀል ያለው ዝግጁነት ሌለው መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ፍትሕ ዘርፍ በተለይም ፍርድ ቤቶች በሙስናና በደረቅ ወንጀሎች ላይ በዕውቀትና በክህሎት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ይሰጣሉ ለማለት ያስቸገራል፡፡ የቀረቡትን ሰነዶችና ጉዳዮችን በትክክል በመተንተን ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ ወደ አንዱ ወገን ያጋደለ ውሳኔ ሲሰጡ ይታያል፡፡ በተለይም በደረቅ ወንጀል ለዓቃቤ ሕግ ያጋደለ ብይን ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ሕዝብ በፍርድ ቤቶች አሠራር ላይ በጣም እየተማረረ ነው፡፡ በዕድሜያቸው በጣም ወጣት ሆነው ግብታዊ ውሳኔ ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ዳኛ የሚሆን ሰው በዕድሜ በሳል ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ ይህ ተግባራቸው ሕዝብ በመንግሥት ላይ ጥላቻን እያሳደረ ነው፡፡ መንግሥት ይህን በጥልቀት ማየት አለበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሙስና ወንጀል ላይ የሚሰጥ ውሳኔ በጣም የሚገርም ነው፡፡ በሙስና ብዙ ያካበተውን  የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ አስረድቷል ብለው፣ በጥቂት የእስራት ዓመታት ውሳኔ ሲሰጡ ደሃው ለፈጸመው ጥቃቅን ሙስና በተቃራኒ የብዙ ዓመታት እስራት ብይን ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ደሃ ላይ  እስራት የማከናነብ ሁኔታ መኖሩን ግልጽ የውይይት መድረክ ቢኖር በተጨባጭ መረጃ ማቅረብ ይቻል ነበር፡፡ ደሃው ሁሌም በፍርድ ቤት ውሳኔ ተጠቂ እንደሆነ ማንም ሰው ይረዳል፡፡ ሀብታም ማረፊያ/እስር ቤት አያድርም፡፡ ማታ ወደ ቤቱ የሚሄድበት ሁኔታ መኖሩን በመረጃ ጭምር ማሳየት ይቻላል፡፡ ጠዋት ለማስመሰል ይመጣና ከፖሊሶች ጋር ተቀምጦ እያወራና እያስወራ ይውላል፡፡ ጸሐፊውን ይህን እውነታ አንድ ባለሀብት ታስሮ ይህን ሲተገብር በግልጽ ለማየት ችሏል፡፡ ፍርድ ቤቶችም ለደሃውና ሀብታም እኩል እየዳኙ አይደለም፡፡ ሀብታም በፍርድ ቤትም ሀብታም ነው፡፡ ደሃ ሁሌም እየተበደለ ነው፡፡

ስለዚህ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በስፋት ተንሰራፍቷል እየተባለ ያለውን የሙስና ወንጀል መጠን በመቀነስ፣ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን፣ የተጀመረው ህዳሴ ዕውን እንዲሆን መንግሥት በፀረ ሙስና ትግል ላይ ቁርጠኛ አቋም መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ይህንንም በተግባር ሊያሳይ ይገባል፡፡ ጸሐፊውና ሕዝቡ ይህን በግልጽ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ በሚዲያዎችና በተለያዩ መድረኮች ላይ ብቻ የችግሩን አሳሳቢነት እንዲነገር ከማድረግ በተጨማሪ በተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ተግባራትን በማከናወን ማሳየት ከመንግሥት የሚጠበቅ ነው፡፡ ማለትም የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሠራ ማድረግ አለበት፡፡ ተጨባጭ ውጤት የሚታየው ደግሞ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቅም ማሳደግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ የዓቃቤ ሕግ ለኮሚሽኑ ይመለስለት የሚል እምነት የለኝም፡፡ መመለስም የለበትም፡፡ ምክንያቱ የሌሎች አገሮች የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች አደረጃጀት በአብዛኛው ዓቃቤ ሕግን ያካተተ አይደለም፡፡ የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራ የፖሊስ ሳይሆን የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሥራ መሆኑን በትክክል ማመን አለበት፡፡ ይህን ተግባራዊ ማድረግ በአገሪቱ አንድ ዕርምጃ ለውጥ ያመጣል፡፡ መንግሥት የተቋማት የሥራ ድርርቦሽን መቀነስ ይኖርበታል፡፡ ያለበቂ ጥናት የተደራጁ ተቋማትን ለአላስፈላጊ ወጪ ስለሚዳርጉ በጥናት በመለየት መዝጋት ወይም ወደ አንድ እንዲጠቃለሉ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ተመሳሳይ ሥራ በተለያየ ቦታ እየተከናወነ ሀብት መባከን የለበትም፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር የኮሚሽኑን ሥራ ከመሥራት ይልቅ በለውጥ መሣሪያዎች ትግበራና የሰው ሀብት ልማት ሥራ ላይ ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው፡፡ በአገራችን ከሙስና ችግር የማይተናነሰው የማስፈጸም አቅም ማነስ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ይህን የማስፈጸም አቅም ለማጎልበት ተግቶ ሊሠራ ይገባል፡፡

በኮሚሽኑ ሥራ ላይ መሻማትን መተው ይኖርበታል፡፡ ኮሚሽኑ የመፈጸም አቅም ካነሰው አቅሙን የሚያጎለብት ክትትልና ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል፡፡ መንግሥታችን የተግባር መንግሥት ሊሆን ይገባል፡፡ በአሁን ዘመን ያለው ሕዝብ የሠለጠነና ሁሉንም ነገር በቀላሉ ሊረዳ የሚችል ነው፡፡ መንግሥትም በዚያው ልክ የራሱን አቅም ማጎልበት ይጠበቅበታል፡፡ ሕዝብ ከመሪው ፊት ከቀደመ በትክክል ለመምራት በጣም ይቸገራል፡፡ በምንም ተዓምር መሪ ከፊት መቅደም ይኖርበታል፡፡ የሚያወጣቸው ሕጎች ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ድግግሞሽ መኖር የለበትም፡፡ መንግሥትን የሚያሳስቱ ሰዎችን የሚለይበት አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ በመንግሥት ውስጥ ሆነው ሕዝብና መንግሥትን የሚያቃቅሩ ሥራዎችን የሚሠሩ ሰዎችን በየጊዜው በማጥራት በአፋጣኝ ሊያስወግድ የሚችልበትን አሠራር በጥንቃቄ መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ይህ ከሆነ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እምነት ያሳድራል፡፡ ከጎኑ ይቆማል፡፡ በሁሉም ርብርብ ሙስና መከላከል ብቻ ሳይሆን ተራራም መናድ ይቻላል፡፡ መንግሥት በትክክል ሊያደምጠን ይገባል፡፡ ኅብረተሰቡም ሙስና በሚያስከትለው ጉዳት ላይ ግልጽ ግንዛቤ መያዝ እንዲችል የመንግሥት ሚዲያዎች ላይ ትምህርቱ በስፋት ሊሰጥ ይገባል፡፡ የመንግሥት ሚዲያ ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች በሥነ ምግባር ታንፀው፣ ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ተክነው ሥራቸውን እንዲያከናወኑ በተለይ በሙስና ወንጀል ላይ የአመለካከት ለውጥ አድርገው በተገቢው እንዲንቀሳቀሱና ሕዝቡን የማነሳሳት ሥራ እንዲሠሩ ሊደረግ ይገባል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በ2018 በአገሪቱ ውጤታማ የሆነ የፀረ ሙስና ትግል ሊያካሄድ ያቀደው ዕቅድ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ ስለሆነ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣውን ዕቅድ በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በኩል በማቀድ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቸር ይግጠመን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡