Skip to main content
x

ታክሲዎች ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸው

በጣም ጨዋና ሰው አክባሪ የታክሲ ሾፌርና ረዳቶች ቢኖሩም የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ይበዛሉ፡፡ በከተማችን ዳርቻ ኮንዶሚኒየሞች አካባቢ ከታሪፍ ውጪ ማስከፈልና መስመር አቆራርጦ መጫን የተለመደ ነው፡፡ መሸት ካለ ያንኑ ሕገወጥ ታሪፍ የሆነ ክፍያንም እጥፍ አርጉልን ይላሉ፡፡ ተጠቃሚው አይከበርም ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ይዋረዳል፡፡ አቅመ ደካሞችና ሴቶች መብታቸው ይገፈፋል፡፡ ይኼ የዕለት ተለት ገጠመኛችን ሲሆን፣ ይህን ለመጻፍ ያነሳሳኝ የገና በዓል ዕለት ያጋጠመኝ አጋጣሚ ነው፡፡ ከሰሚት ኮንዶሚኒየም እስከ መገናኛ ድረስ ታሪፉ 3.75 ብር ሲሆን፣ የታክሲ ሾፌርና ረዳቶች አጽድቀው በተመኑትና ተገልጋዩም አማራጭ አጥቶ መብቱን ማስከበር አቅቶት በውዴታ ግዴታ የተቀበለው አምስት ብር ታክሲ አለመውጣቱን ዓይተው አሥር ብር ክፈሉን አሉ፡፡ አማራጭ አጥተን ብንስማማም ይኼ ሳያንስ በታክሲው ውስጥ ሾፌሩንና ረዳቱን ጨምሮ 23 ሰው እንደሰርዲን ተጠቀጠቀ፡፡ ሒሳብ መሰብሰብ ሲጀምር አንዲት ልጅ የለኝም ብላ በታሪፉ አምስት ብር አውጥታ ስትከፍል፣ ተስማምተሽ ነው የገባሽው ብለው እጅግ የሚሰቀጥጥና ክብረ ነክ የሆነ ፀያፍ ስድብ ሰድበው ሌላ ትራንስፖርት ለማግኘት የማይቻልበት ቦታ ጎትተው አውጥተው ወረወሩዋት፡፡ የዚህን ዓይነቱን ድርጊት በዕለት ተለት የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚነታችን የምናየው አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡

መፍትሔ

  1. የትራንስፖርት ቢሮ እንደማንኛውም የሥራ ዘርፍ የታክሲ ሾፌርነትም ሆነ ረዳትነት የሙያ ፈቃድ ኖሮት የሚቀርቡ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች ሊስተናገዱበት የሚችሉበት አሠራሮች ሊዘረጉ ይገባል፡፡ ዘርፉ በአሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የዕለት እንጀራቸውን የሚያገኙበት እንደሆነ ስለሚታወቅ፣ ግልጽ አሠራር ሊዘረጋበትና የሙያ ሥነ ምግባር ደንብና መመርያ ሊዘጋጅበት ይገባል፡፡ ሥነ ምግባሩን የማያሟሉም ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡
  2. ተሳፋሪዎች የተጠቀሙበትን ብቻ በኪሎ ሜትር ተሠልቶ እንዲከፍሉ ክፍያ በትኬት ወይም በካርድ የሚፈጸምበትን አሠራር በመዘርጋት፣ በታሪፍ የሚፈጠር ግብግብን ከማስቀረቱም በላይ የታክሲን ሥራ ግልጽነት የተሞላበት ያደርገዋል፡፡ ይኼ መደረጉ ለታክሲ ባለንብረቶችም ሆነ ለመንግሥትና ለተጠቃሚውም ጥሩ ነው፡፡
  3. የመንገድ ትራንስፖርት ከታሪፍ ጋር የተያያዙ ችግሮችን መጠቆሚያ አድራሻ በየታክሲዎቹ       (ግማሽ ያህሉ) ላይ እንዲለጠፍ ማድረጉ ያስመሰግነዋል፡፡ ሁሉም ላይ እንዲለጠፍ መቆጣጠር ይገባዋል፡፡ ስልኩ በአብዛኛው የማይነሳ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል፡፡
  4. መንግሥት አደራጅቶ ያሰማራቸው የተራ አስከባሪዎች ቢኖሩም፣ በተራ ገንዘብ ከመሰብሰብ ባለፈ የሚሠሩት ሥራ የለም፡፡ መስመር እንዳይቆራረጥና ከታሪፍ በላይ እንዳይከፈል ከመቀመጫ በላይ እንዳይጫን ሊቆጣጠሩ ይገባል፡፡ አደራጅቶ ፈቃድ የሰጣቸውም አካል ሊቆጣጠራቸው ይገባል፡፡

(ሰሎሞን፣ ከአዲስ አበባ)

***

የፓርላማ ሕንፃውን መቀየር ለምን አስፈለገ?

ለዚህ ጽሑፍ መነሻዬ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ አዲስ የፓርላማ ሕንፃ ለመገንባት በሚል የወጣው ጽሑፍ ነው፡፡

አብዛኛው የዓለም ክፍልን ካየን ጥንታዊ ቤቶችንና ሕንፃዎችን በእንክብካቤ ነው የሚይዙት፡፡ በአዲስ አይተኩም፡፡ የእንግሊዝ ፓርላማን እንደ አብነት ብንወስድ፣ ረዥም ዓመት ዕድሜ ነው ያለው፡፡ ያልቀየሩት ገንዘብ ስለሌላቸው አይደለም፡፡

ዛሬ በአገራችን ከፍተኛ የመሠረት ልማት ችግር እያለብን፣ የሥራ አጥ ቁጥር ከፍተኛ በሆነበት የቀድሞውንና ታሪካዊውን ፓርላማ መቀየር ለምን አስፈለገ? በነገራችን ላይ አሁን ያለውን ፓርላማ በራሳቸው ገንዘብ ያሠሩት ንጉሥ ተፈሪ ንጉሠ ነገሥት ከመሆናቸው በፊት ነበር፡፡

(በላይ፣ ከአዲስ አበባ)