Skip to main content
x
የቀንጢቻ የታንታለም ማዕድን ማውጫን በጋራ ለማልማት ጨረታ ወጣ

የቀንጢቻ የታንታለም ማዕድን ማውጫን በጋራ ለማልማት ጨረታ ወጣ

የመንግሥት ልማት ድርጀቶች ሚኒስቴር በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የሚገኘውን የቀንጢቻ ታንታለም ማዕድን ማውጫ፣ ከመንግሥት ጋር በጋራ ማልማት ለሚፈልጉ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በድጋሚ ጨረታ አወጣ፡፡

ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም ሦስት ጊዜ ጨረታ ቢያወጣም ሒደቱ መሳካት ባለመቻሉ፣ ጨረታውን በመተው ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር ድርድር ሲያደርግ ቆይቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ድርድሩ አሁንም ባለመሳካቱ በድጋሚ ጥር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ጨረታ ያወጣ ሲሆን፣ ጨረታው ሚያዝያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሚከፈት ተገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ ባወጣው ጨረታ በ40/60 ሒሳባዊ ሥሌት የማዕድን ማውጫውን የሚያለማ፣ አሁን ካለበት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሳድግና የሚያስፋፋ ኩባንያ በውድድሩ እንዲሳተፍ ጋብዟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በጨረታ ሰነዱ ላይ እንደተገለጸው ቢያንስ በታንታለም፣ በሊትየምና በመሳሰሉት ዘርፎች የአምስት ዓመት ልምድ ያለው፣ ከዚህ በተጨማሪ ተወዳዳሪው ኩባንያ የቴክኒክ ዕውቀት፣ የማስተዳደር ብቃት፣ ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ የመግባትና የፋይናንስ አቅም ያለው መሆን ይኖርበታል ብሏል፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከዚህ በፊት ጨረታ ወጥቶ የኩባንያውን አክሲዮን ለማስተላለፍ ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም አልተሳካም፡፡ ‹‹ከዚያ በኋላ ፍላጎታቸውን የሚገልጹ ኩባንያዎች በየጊዜው ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን ይፋዊ ድርድር አላደረግንም፡፡ ለድርድር የምናደርገው በይፋ ኩባንያዎችን ጋብዘን ነው፤›› ሲሉ አቶ ወንድአፍራሽ ገልጸዋል፡፡

ከታንታለም ማዕድን ጋር ሊትየምናና ዩራኒየም ጨምሮ 23 ያህል ማዕድናት ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የቀንጢቻ ማዕድን ሥፍራ በተገቢው መንገድ መልማት ባለመቻሉና በካይ እየሆነ በመምጣቱ፣ በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን አግዶታል፡፡

የኦሮሚያ ክልል አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ኃላፊ ሐሰን የሱፍ (ዶ/ር) የፌዴራል መንግሥት የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን የታንታለም ማዕድንን ለማጥራት የሚጠቀምበት ውኃ ያቆረ ግዙፍ ግድብ ሞልቶ በመደርመሱ፣ በአካባቢና በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል በሚል ሥጋት መታገዱን በቅርቡ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም ግድቡ ሞልቶ የሰውና የእንስሳት ሕይወት ጠፍቷል፡፡ አሁንም የተደቀነውን ሥጋት ለማስወገድ ኮርፖሬሽኑ የገንዘብ አቅም እንደሌለው ግልጽ በማድረጉ ዕርምጃው ተወስዷል፤›› ሲሉ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ለኢንዱስትሪው ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቀንጢቻ  ታንታለም የያዘው የዩራኒየም መጠን ከፍተኛ በመሆኑ አካባቢው በጥንቃቄ ሊያዝ ይገባል፡፡

ከኢኮኖሚ አንፃርም መንግሥት በዚህ ጨረታ ለተጨማሪ እሴት ብዙም ትኩረት አልሰጠም፡፡ ትኩረት የሰጠው ታንታለምንና ሊትየምን ለያይቶ ኤክስፖርት ለማድረግ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለይ ሊቲየም በዓለም ገበያ ተፈላጊ ማዕድን በመሆኑ መንግሥት እስከ ፋብሪካ ድረስ ሊያስብ እንደሚገባ ባለሙያዎች አሳስበዋል፡፡