Skip to main content
x
የፍርድ ቤት ዕግድ የጣሱ የሥራ ኃላፊዎች ወንጀል መፈጸማቸውን ፍርድ ቤት አስታወቀ

የፍርድ ቤት ዕግድ የጣሱ የሥራ ኃላፊዎች ወንጀል መፈጸማቸውን ፍርድ ቤት አስታወቀ

  • ዓቃቤ ሕግ ምርመራ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ተሰጥቷል

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ፍርድ ቤት የሰጠውን የዕግድ ትዕዛዝ በመተላለፍ የግል ይዞታን ‹‹የመንግሥት ይዞታ ነው›› በማለት የባለይዞታዎችን ቤት በማፍረሳቸው ‹‹ወንጀል ፈጽመዋል›› ሲል፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 13ኛ ይግባኝ ሰሚ ፍትሐ ብሔር ችሎት ውሳኔ  ሰጠ፡፡

ፍርድ ቤቱ የአስተዳደር ጽሕፈት ቤቱን ኃላፊዎች ‹‹ወንጀል ፈጽመዋል›› ያላቸው የዘጠኝ ቤተሰቦች የውርስ ሀብት የሆነ 1,045 ካሬ ሜትር ነባር ይዞታ በልማት ምክንያት ተቀናንሶ 783 ካሬ ሜትር መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ካርታ አስተካክሎ መስጠት ሲገባቸው ካርታውን 670 ካሬ ሜትር አድርገውና አሳስተው በመስጠታቸው  በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት በተነሳ የሕግ ጥያቄ ነው፡፡ ወራሾች የተሠራው ካርታ ስህተት መሆኑን በመግለጽ እንዲስተካልላቸው ሲያመለክቱ፣ ‹‹መመርያ እስከሚወጣ ጠብቁ›› ተብለው ሲጠባበቁ መቆየታቸውን የፍርድ ቤቱ ወሳኔ ያሳያል፡፡ ወራሾች መመርያው ወጥቶ ይዞታቸው (783 ካሬ ሜትር) ተስተካክሎ ይሰጠናል በማለት እየተጠባበቁ እያለ፣ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ግንባታ ምክንያት አቅጣጫውን በሳተ ጎርፍ በመጥለቅለቃቸው ቤታቸውና አጥራቸው ፈርሶ ንብረት የወደመባቸው መሆኑን የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች፣ የክፍለ ከተማው ጽሕፈት ቤትና የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ጭምር የሚያውቁት እንደሆነ በክሱ አብራርተው ማቅረባቸውን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያብራራል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በሠራው ስህተት ምክንያት ቤታቸው በጎርፍ መፍረሱንና ለችግር መዳረጋቸውን በመግለጽ ባለሥልጣኑ እንዲሠራላቸው ቢጠይቁም፣ ምላሽ ባለማግኘታቸው በራሳቸው ወጪ ግንብ የነበረውን አጥር በቆርቆሮ ሲያጥሩና የፈረሱትን ቤቶችም ሲገነቡ የወረዳው ጽሕፈት ቤትም ያልተቃወማቸው መሆኑን በክርክር ሒደት ማስረዳታቸውን ውሳኔው ይጠቁማል፡፡፡ የገነቧቸው ቤቶች ለሱቅ አገልግሎት የሚውሉ በመሆናቸው ለሚነግዱት ሰዎች ጽሕፈት ቤቱ የንግድ ፈቃድ መስጠቱንም አክለዋል፡፡ የሠሯቸውን ቤቶች እየነገዱባቸው ባሉበት ወቅት የወረዳው ጽሕፈት ቤት በድንገት ‹‹የተሠሩት ቤቶች በባዶ ቦታና በመንግሥት ይዞታ ላይ የተሠሩ ስለሆነ በ13 ቀናት ውስጥ እንድታፈርሱ፣ ተከራዮችም ዕቃቸውን እንዲያወጡ›› የሚል ትዕዛዝ መስጠቱን ውሳኔው ይገልጻል፡፡

ወራሾች ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በጻፉት ‹‹ሁከት ይወገድልን›› አቤቱታ እንደገለጹት በውርስ ያገኙትና ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ ሲገበርበት የነበረ ሕጋዊ ይዞታቸውን በወረራ እንደያዙት በማስመሰል አፍርሱና ልቀቁ መባላቸው ተገቢ ባለመሆኑ፣ የወረዳው ጽሕፈት ቤት የፈጠረባቸው ሁከት በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1149 መሠረት እንዲወገድላቸው አቅርበዋል፡፡ በወቅቱም ፍርድ ቤቱ ዕግድ መስጠቱን ውሳኔው ያሳያል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ሁለቱን ወገኖች አከራክሮ ወራሾች ሕጋዊ የውርስ ይዞታቸው መሆኑን ያስረዱ ቢሆንም፣ ጽሕፈት ቤቱ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ሁከት ይወገድልኝ ዳኝነት የመስጠት ሥልጣን እንደሌለውና ወራሾች ከተሰጣቸው ይዞታ ውጪ አስፋፍተው የያዙት ይዞታ መሆኑን በመግለጽ ተከራክሮ ሁከት እንዳልሆነ ምላሽ መስጠቱን ውሳኔው ይዘረዝራል፡፡ የሥር ፍርድ ቤትም የወረዳውን ጽሕፈት ቤት ሐሳብ በመቀበል በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1149(1) ሥር የሚወድቅ መሆኑን ጠቁሞ፣ ‹‹ከውል ውጭ ኃላፊነት ሊኖረው ከሚችል በስተቀር ድርጊቱ ሁከት አይደለም›› በማለት ውሳኔ መስጠቱን አስታውቋል፡፡

የውርስ ባለመብቶቹ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ባቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ እንደገለጹት፣ ‹‹ሁከት ይወገድልኝ ባዩ መብት ያለው መሆኑን ማሳየቱ በቂ ነው›› በማለት የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 36645፣ 27506፣ 39940፣ 38228 እና 70801 ላይ የሰጣቸውን ውሳኔዎች በመጥቀስ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን ተቃውመዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1149(1) እና (3)ን የሕግ ትርጉም ዓላማና ግብ ውጪ በመውጣት፣ የአስተዳደር አካላት በሕግ በተሰጣቸው ሥልጣን የሚፈጽሙት ተግባር የሁከት ክስ ሊቀርብበት አይገባም በማለት፣ የሚሠሩት ሥራ ሁሉ ትክክል እንደሆነና አይነኬ እንደሆኑ በማስመሰል የሕግ አውጪውን መንፈስ በመፃረር የሰጠው ውሳኔ እንዲሻር ጠይቀዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የወረዳውን ጽሕፈት ቤት መልስ እንዲሰጥ ሲያዘው የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ስንታየሁ ሀብቴ ቀርበው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የፍርድ ቤት ዕግድ ሳይነሳ አፍርሰናል፡፡ ማፍረሳችን ስህተት ነው፡፡ ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ፡፡ ስህተቱንም እናርማለን፡፡ ወራሾች ይምጡ ችግራቸውን እንፈታለን፤›› ብለው ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ውሳኔው ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ኃላፊው ለፍርድ ቤቱ የእምነት ቃል ሰጥተው ከመሄዳቸው በስተቀር በተግባር ሊፈጽሙ ባለመቻላቸው፣ ወራሾች ቤቱን ያፈረሱት የወረዳው አስተዳደር ኃላፊዎች አቶ ስንታየሁ ሀብቴ፣ ወ/ሮ ሒሩት በቀለ፣ አቶ ተስፋዬ ጨመዳ፣ ምክትል ኮማንደር ኬሪያ ሰዲቅና አቶ ተስፋዬ ደበላ በየግላቸው፣ በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ለደረሰው የንብረት ጉዳት በቡድን ተጠያቂ እንዲሆኑና ኃላፊነት አለባቸው እንዲባልላቸው መጠየቃቸውን አብራርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ እንደገለጸው፣ የሥር ፍርድ ቤት የሁከት ድርጊት አይደለም ብሎ የሰጠው ውሳኔ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው፡፡ ወራሾች ግንቦት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. በደረሰ ድንገተኛ ጎርፍ ሰርቪስ ቤታቸው መፍረሱ ተረጋግጧል፡፡ መንገዶች ባለሥልጣን በሠራው ስህተት ቤቱና አጥሩ መፍረሱ እየታወቀ ራሳቸው መገንባታቸው፣ ‹‹ከተሰጣቸው ይዞታ ውጪ አስፋፍተው በመያዝ ገንብተዋል›› በማለት የተሰጠው ማስጠንቀቂያ የሁከት ተግባር ነው፡፡ የፈረሰው ቤት በጂአይኤስና በላይን ማፕ መረጃ ላይ የነበረ መሆኑንና ከክፍለ ከተማው ከወጣው ማኅደርም ለመረዳት መቻሉን አስረድቷል፡፡

የፍርድ ቤት ዕግድ ትዕዛዝ ሳይነሳ ቤቱንና አጥሩን ያፈረሱ መሆናቸውን በችሎት ቀርበው የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ማመናቸውንና ኃላፊነት መውሰዳቸውን ፍርድ ቤቱ አስታውሶ፣ በካቢኔ ቤቱ በአፍራሽ ግብረ ኃይል እንዲፈርስ ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ስምምነት ላይ መደረሱን የተጻፈ ቃለ ጉባዔ መኖሩን ኃላፊው ለፍርድ ቤት የተናገሩ ቢሆንም፣ በቃለ ጉባዔው ላይ የጻፉት ግን ሰኔ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. መሆኑንና የተምታታ ሥራ መሠራቱን የሚያሳይ መሆኑን ውሳኔው ይገልጻል፡፡ ፍርድ ቤቱ ይዞታው እንዲለካ በሰጠው ትዕዛዝ ሲለካ 783.82 ካሬ ሜትር መሆኑንና አስተዳደሩ ዕግድ ሳይነሳ ያፈረሳቸው ቤቶች ያሉበት ይዞታ ለልማት ተቀናንሶ 796.89 ካሬ ሜትር ካርታ እንዲሠራላቸው መሐንዲስ ሪፖርት ካደረገው ሰነድ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ገልጿል፡፡

ችሎቱም በአካል ሄዶ እንዳረጋገጠው ወራሾች ይዞታው በጎርፍ ሲፈርስባቸው በራሳቸው ወጪ የሠሩት ቤት በ1988 እና 1997 ዓ.ም. የተነሳው ካርታ ላይ የነበረ መሆኑ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ወራሾች ከነበራቸው ይዞታ ላይ ለልማት ተቀንሶ 783.82 ካሬ ሜትር የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ይሠራላቸው ሲባል 670 ካሬ ሜትር መሠራቱ ስህተት መሆኑ እየታወቀ፣ የሥር ፍርድ ቤት ጥያቄውን አልቀበልም ማለቱ የሕግ ስህተት መሆኑን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አረጋግጧል፡፡ ወራሾች ሕጋዊ የይዞታቸው ማረጋገጫ ካርታ ተስተካክሎ እንዲሠራላቸው ጥያቄ ያቀረቡት ወ/ሮ መሰለች ደስታ፣ ወ/ሮ ወሰንየለሽ መንክር፣ አቶ ቀደስ መንክር፣ አቶ አክሊሉ መንክር፣ ወ/ሪት ፎቶ መንክር፣ ወ/ሮ ፀሐይ መንክር፣ ወ/ሮ ሒሩት መንክር፣ አቶ ናርዶስ መንክርና አቶ ነቢዩ መንክር ፍርድ ቤት ቀርበው መብታቸውን ካላስከበሩ የትም ሄደው ማስከበር የማይችሉ በመሆኑ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 መሠረት በፍርድ ቤት የሚታይ ጉዳይ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የወረዳው ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችንም ‹‹ወንጀል ፈጽመዋል›› በማለት የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ውድቅ አድርጓል፡፡ የወራሾች ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በ783.82 ካሬ ሜትር ተስተካክሎ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ጽሕፈት ቤቱ የሠራው ተግባርም ሁከት በመሆኑ ሊወገድ ይገባል ብሏል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም ከላይ ስማቸው በተገለጸው የአስተዳደሩ ጽሕፈት ቤት የተለያዩ ክፍል ኃላፊዎች ላይ ምርመራ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡