Skip to main content
x
ለውጥን መሸሽ አያዋጣም!

ለውጥን መሸሽ አያዋጣም!

በማያቋርጥ የለውጥ ሒደት ውስጥ በሚገኝ ዓለም መንቀርፈፍ መገኘት ካለበት ጥቅም ጋር ያቆራርጣል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለውጥ በፍጥነት ስለሚከናወን ከበረከቱ መቋደስ የሚቻለው ራስን ከፍጥነቱ ጋር ማስተካከል ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ በረከቶች በየቀኑ በአራቱም የዓለም ማዕዘናት በብርሃን ፍጥነት ከአንዱ ወደ ሌላው መሸጋገር የቻሉት፣ በማያቋርጠው የለውጥ ሒደት ውስጥ በማለፍ ነው፡፡ በሥልጣኔ እየገፋ ያለው የሰው ልጅም ዘመናትን ተሻግሮ እዚህ የደረሰው፣ ዓለምን እንድትመቸው አድርጎ መለወጥ በመቻሉ ነው፡፡ ለውጥን መፍራትና መጠራጠር አንዱ የድክመት ምልክት ሲሆን፣ መቼም ቢሆን ግን ሳይለወጡ በነበሩበት መቀጠል አይቻልም፡፡ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን የለውጥን አስላፈላጊነት ስንነጋገር፣ ለውጥን በመሸሽ እያፈጠጡ ከሚመጡ ችግሮች ማምለጥ እንደማይቻል አስረግጦ መተማመን ይገባል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ70 በመቶ በላይ ወጣት ትውልድ ያላት ኢትዮጵያ ለትውልዱ የሚመጥን ለውጥ ያስፈልጋታል፡፡ ይህ ለውጥ በሥርዓት እየተመራ በጋራ መግባባት ላይ በመመሥረት ሲከናወን፣ ለጥፋትና ለውድመት የሚዳርጉ አላስፈላጊ ድርጊቶች ይገታሉ፡፡ ይልቁንም ለውጥ ተቋማዊና ዘለቄታዊ ሆኖ በሕግ የበላይነት ሥር እንዲከናወን፣ መሠረታዊ ጉዳዮችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ መለወጥ አለበት፡፡ ከአርባ ዓመታት በፊት የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ የትጥቅ ትግል ያደረገ ድርጅት ላለፉት 26 ዓመታት በሥልጣን ላይ አለ፡፡ ቀደም ሲል የተነሳለትን ዓላማ አሳክቶ ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ጊዜያት ላከናወናቸው መልካም ተግባራት የሚመሠገነውን ያህል፣ በሠራቸው ስህተቶችና በፈጸማቸው ድርጊቶች ደግሞ ይወቀሳል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በላይ በአገሪቱ ውስጥ ለተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ጣቱን ሌሎች ላይ ከመጠቆም ተላቆ በቅርቡ ራሱን ተጠያቂ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ምንም እንኳ በተለያዩ ጊዜያት ተሃድሶ እያደረገ ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ቃል ቢገባም፣ ቃልና ተግባር አልገናኝ እያሉ አገሪቱም ሆነች ሕዝቡ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡ ኢሕአዴግ ለለውጥ ያለው ፍላጎት በጣም አናሳ ከመሆኑ የተነሳ፣ ራሱን ከአዲሱ ትውልድ ፍላጎት ጋር ማጣጣም ተስኖታል፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ይህንን ዘመን አይመስሉም፡፡ ፕሮፓጋንዳ ዘመን ያለፈበት አሠራር መሆኑ እየታወቀ፣ አዲሱን ትውልድ ለማጥመድ ሲሞከር የበለጠ ጥላቻ ይፈጠራል፡፡ አንድ ክስተት ሲያጋጥም ኢንተርኔት ወይም ፌስቡክ መዝጋት መፍትሔ እንደማያመጣ፣ ይልቁንም የበለጠ ጥላቻ እንደሚፈጥር በስፋት ይታወቃል፡፡ ክልከላ የዚህ ዘመን መገለጫ አይደለም፡፡ የ20ኛውን ክፍለ ዘመን ታክቲክ በዚህ ዘመን ተግባራዊ ማድረግ፣ ከለውጥ ጋር ያለውን ፀብ ነው የሚያሳየው፡፡

በሃያኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የዘመኑን ፖለቲካ ለመግራት መሞከር ጉም የመዝገን ያህል ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ለዓመታት የሚታየው ትልቁ በሽታ ለውጥን መጥላት ነው፡፡ የ1960ዎቹ የሚባለው ትውልድ አባል የሆነው ኢሕአዴግ ተፎካካሪዎቹን በጠላትነት በመፈረጅ አጠገቡ እንዳይደርሱ ያደርግ የነበረውና የፖለቲካ ምኅዳሩን የዘጋጋው፣ ለዘመኑ የሚመጥን ለውጥ ከውስጡ ሊፈልቅ ባለመቻሉ ነው፡፡ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ተስፋ ከተጣለበት ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የነበረው ውጣ ውረድም ይህንን በግልጽ ያሳያል፡፡ ኢሕአዴግ ራሱን ወደ አውራ ፓርቲነት በማሸጋገር ገዝፎ የወጣው ተፎካካሪዎቹ በሙሉ የደረሰባቸውን ድፍጠጣ መቋቋም ባለመቻላቸው ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከአጋሮቹ ጋር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶችን መቀመጫ ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ መዳፉ ውስጥ ሲያስገባ ለለውጥ የነበረው ግንዛቤ በጣም ደካማ መሆኑን ያሳያል፡፡ ፓርላማው በይፋ ሥራውን በጀመረ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞና ሁከት ለምንነጋገርበት ጉዳይ ማረጋገጫ ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አንድ ፓርቲ የፓርላማ መቀመጫዎችን ጠቅልሎ ያዘ ሲባል ለሰሚውም አስደንጋጭ ነበር፡፡ በጣም ከረፈደ በኋላ የተወሰኑ ማስተካከያዎች ለማድረግ ጅምሮች ቢታዩም፣ አሁንም ለዘመኑ የሚመጥን የለውጥ ዕርምጃ ካልተወሰደ ችግሮች ይቀጥላሉ፡፡ ለውጥን መሣሪያ ማድረግ አለመቻል ለሥርዓተ አልበኝነት ያጋልጣል፡፡

ለውጥ ተቋማዊና ዘለቄታዊ እንዲሆን ሲፈለግ ቅድሚያ የሚሰጠው ለመነጋገርና ለመደማመጥ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በአገሪቱ ለደረሱ ጥፋቶች ኃላፊነት ወስዶ እስረኞችን ሲፈታና የፖለቲካ ምኅዳሩን ለመክፈት ቃል ሲገባ፣ እርስ በርሱም ሆነ ከሕዝብ ጋር በግልጽ መነጋገር አለበት፡፡ ሕዝብ ምንድነው የሚፈልገው? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት የሚቻለው ለለውጥ ያለው ተነሳሽነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ የሚያስፈልገው ይኼ ነው ብሎ ከመደምደም ይልቅ፣ ምን እንደሚፈልግ በግልጽ እንዲናገር ማድረግ የለውጡን ፍኖተ ካርታ (Road Map) ለመንደፍ ይጠቅማል፡፡ ለውጥ የሰዎችን አስተሳሰብ ጨምሮ የተቋማትን ጥንካሬ ለማጎልበት የሚረዳ ከመሆኑም በላይ፣ በግብታዊነት ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስ ወይም ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን በተለመደው መንገድ ለመጓዝ ማሰብ ወይም የነበረውን እንዳለ ለማስቀጠል መሞከር የበለጠ ሁከት ይቀሰቅሳል፡፡ ኢሕአዴግ ከነባሩ የፕሮፓጋንዳ አጠባ ወጥቶ ለዘመኑ የሚመጥን ለውጥ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ለትጥቅ ትግሉ የረዱ አሠራሮች ለዚህ ዘመን ማገልገል እንደማይችሉም ማሰብ ይገባል፡፡ ይኼ ዘመንና የበፊቱ በብዙ ነገሮች ተለያይተዋል፡፡ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ከመጠን በላይ ባደጉበት በዚህ ዘመን የበፊቱ አስተሳሰብ ሥፍራ የለውም፡፡ የሚያዋጣው ለውጥን ተቀብሎ ለአገር እንዲበጅ ማድረግ ነው፡፡ ለአገር የሚያስፈልገውም ይኼው ነው፡፡

ይኼ ማሳሰቢያ ከኢሕአዴግ በተቃራኒ የተሠለፉ ኃይሎችንም ይመለከታል፡፡ በተለይ የ1960ዎቹ ትውልድ ፖለቲከኞችና በእነሱ ዙሪያ የተኮለኮሉ ሁሉ ከዘመነ ፕሮፓጋንዳ አስተሳሰብ መውጣት አለባቸው፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ የተለመደውንና አሰልቺውን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ መርጨት ፋይዳ ቢስ መሆኑን ማመን ይገባቸዋል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በመሆን ወንዝ የማያሻግር እሰጥ አገባ ውስጥ መጣድ የጠቀመው ነገር የለም፡፡ አሁን ተወደደም ተጠላም ወጣቱ ትውልድ ነቅቷል፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትምህርት ላይ ያለው በበርካታ ሚሊዮኖች የሚቆጠረው ወጣቱ ትውልድ፣ ዝም ብሎ በስሜት እየተነዳ ያሰብነውን ያሳካልናል ማለት ተረት የሚሆንበት ጊዜ በጣም ቅርብ ነው፡፡ ወጣቱ መጠየቅና መሞገት እየጀመረ በመሆኑ የማንንም አጀንዳ በደመነፍስ አይሸከምም፡፡ ለዚህ ትውልድ የሚመጥን አጀንዳ ሳይኖር የፖለቲካ ድርጅት እመራለሁ ማለትም አይቻልም፡፡ ይልቁንም የለውጡን ባቡር በመሳፈር ለሰጥቶ መቀበል መርህ ለመገዛት መዘጋጀት የወቅቱ የማይታለፍ ጥያቄ ነው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን የሚገኘው በሕዝብ ወሳኝ ድምፅ ነው በማለት በሕግ የበላይነት ሥር ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲደረግ፣ ሥልጣን በጉልበት ሳይሆን በሥርዓት እንዲያዝ የሚያስችል ለውጥ እንዲመጣ ራስን ማዘጋጀት ግድ ይላል፡፡ በግትርነትና በቂም በቀል ልክፍት ውስጥ ሆኖ ለውጥ አይመጣም፡፡ ጊዜ ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ በዚህ ዘመን አይሠራም፡፡ ከሥልጡን ፖለቲካዊ ግንኙነት ውጪ ያለው መንገድ የትም አያደርስም፡፡ በዚህ መሠረት ራስን ለለውጥ ማዘጋጀት ይሻላል፡፡ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ አለ ከተባለም አያዋጣም፡፡

በአጠቃላይ ለውጥ ለአገርና ለሕዝብ በሚጠቅም መንገድ እንዲከናወን ልዩ ጥንቃቄ ያሻል፡፡ ለዚህም መነጋገርና መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ በብሔራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢ አቋም መኖር አለበት፡፡ ልዩነትን ማክበርና የተሻለ ሐሳብ ይዞ በመቅረብ የሕዝብ ልብ መማረክ ያስፈልጋል፡፡ ለውጥ ተቋማዊና ዘለቄታዊ ሲሆን፣ ሥርዓተ አልበኝነትና ግርግር ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ከጥላቻና ከበቀል ውስጥ በመውጣት በሰከነ መንገድ መነጋገር መቻል ተገቢ ነው፡፡ የሕዝብን የልብ ትርታ እያዳመጡ ለውጥን መግራት መቻል ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ይበጃል፡፡ ከዚህ በተረፈ ለተወሰነ ቡድን ጥቅምና ልዕልና ብቻ የሚደረግ ሸብ ረብ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያው ውስጥ የሚታየው ለአገር የማይጠቅም የግለሰቦች ንትርክና ቧልት፣ ወደ ተጨባጩ የአገር ጉዳይ እየመጣ የበለጠ ቅራኔ እንዲፈጥር ዕድል መስጠትም አይገባም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ህልውና ፋይዳ የሌላቸው ራስ ወዳዶችና አርቆ ማሰብ የተሳናቸው ከንቱዎች ለውጥን እንዳያጨናግፉ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ የምንነጋገረው ስለአገርና ስለሕዝብ ህልውና እስከሆነ ድረስ ቅንነትና ጥንካሬ የግድ ይላል፡፡ በዚህ መንፈስ መነሳሳት ከተቻለ ለውጥን መቀበል አያዳግትም፡፡ ስለሆነም ለውጥን መሸሽ አያዋጣም መባል አለበት!