Skip to main content
x
ከ64 በመቶ በላይ ልኳንዳ ቤቶች ሚዛኖች ችግር እንዳለባቸው ተገለጸ
የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የጥናት ምርምር ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ለማ ማብራሪያ ሲሰጡ

ከ64 በመቶ በላይ ልኳንዳ ቤቶች ሚዛኖች ችግር እንዳለባቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ ለተለያዩ ግብይቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ የልኬት መሣሪያዎች (ሚዛኖች) በስፋት ችግር እንዳለባቸው፣ በተለይ 64 በመቶ የሚሆኑ ልኳንዳ ቤቶች የልኬት መሣሪያዎች ላይ ደግሞ ችግሩ ጎልቶ እንደሚታይ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን በአዲስ አበባ ከተማ የልኬት መሣሪያዎች ችግር ላይ በተመረጡ የከተማዋ ልኳንዳ ቤቶችና የችርቻሮ መደብሮች ላይ ያካሄደው ይኸው ጥናት፣ አብዛኞቹ ሥጋ ቤቶች የሚጠቀሙባቸው ሚዛኖች ጉድለት ያለባቸውና አጠራጣሪ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ማክሰኞ ጥር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል ይፋ የሆነውን ጥናት ያቀረቡት የባለሥልጣኑ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ለማ እንደገለጹት፣ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ የግልና የሸማቾች ማኅበራት ልኳንዳ ቤቶች ከ64 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሚዛኖቻቸው ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ በተለይ ችግሩ በሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ልኳንዳ ቤቶች ላይ ጎልቶ ታይቷል ብለዋል፡፡

ምልከታ ከተደረገባቸው 12 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ልኳንዳ ቤቶች መካከል የሚዛን ልኬት ችግር ያልታየባቸው ሁለቱ ብቻ ናቸው፡፡ 83 በመቶ የሚሆኑት ወይም አሥሩ ደግሞ በተለያየ ደረጃ የልኬት ችግሮች ያለባቸው ሆነው እንደተገኙ አመልክተዋል፡፡ ይህም ማለት በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ልኳንዳ ቤቶች ላይ የሚዛን የልኬት ችግር በስፋት እንዳለ የሚጠቁም ነው ተብሏል፡፡

ከሚዛን ልኬት ጋር በተያያዘም ምልከታ ከተደረገባቸው 33 የግልና የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ልኳንዳ ቤቶች ውስጥ፣ ሃያ አንዱ ወይም 64 በመቶ የሚሆኑት ሥጋ ቤቶች ላይ በተለያየ መጠን የሥጋ ክብደት የልኬት ችግሮች ታይተዋል፡፡ አሥራ ሁለቱ ወይም 36 በመቶዎቹ ደግሞ ከልኬት ጋር በተያያዘ ሸማቹን የሚጎዳ ችግር እንደሌለባቸው ጥናቱ ያመለክታል፡፡ የዚህ የዳሰሳ ጥናት ግኝት እንደሚያመለክተው በሥጋ ቤቶች ላይ  የሚዛን የክብደት ልኬት ችግሮች በሰፊው እንደሚታዩ የሚጠቁም ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ደግሞ ሸማቹ በከፈለው ገንዘብ መጠን ሥጋ እንዳያገኝ የሚያደርግና ለብዝበዛ የሚያጋልጥ የአለካክ ሥርዓት መኖሩን ያሳያል በማለት ጥናት አቅራቢው ተናግረዋል፡፡

83 በመቶ ከሚሆኑትና ችግሩ ከታየባቸው የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ልኳንዳ ቤቶች መካከል፣ ከአንድ ኪሎ ሥጋ ላይ እስከ 143 ግራም የሆነ የልኬት መጓደሎች መታየቱ ተገልጿል፡፡

በተለይ 143 ግራም፣ 135 ግራም፣ 120 ግራም እንዲሁም 90 ግራም ጉድለት የተገኘባቸው ልኳንዳ ቤቶች፣ የጉድለት መጠናቸው ከፍተኛ የሚባል ደረጃ በመሆኑ፣ ሸማቹን ለከፍተኛ ብዝብዛ የሚያጋልጡበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንዲህ ያለው ጉድለት እያስከተለ ያለውን ጉዳት ሲያብራሩም፣ አብዛኛዎቹ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ልኳንዳ ቤቶች አንድ ኪሎ የሥጋ ምርት ውጤት በ80 ብር ዋጋ ለሸማቹ የሚሸጡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ልኳንዳ ቤቶች መካከል በአንዱ ብቻ በቀላሉ 100 ኪሎ ግራም ሥጋ ለሸማቹ ለሽያጭ አገልግሎት ቢቀርብና ከአንድ ኪሎ 143 ግራም ቢጎድል፣ ይህ ልኳንዳ ቤት 14 ኪሎ ከ300 ግራም ያጭበረብራል ማለት ነው ብለዋል፡፡  ይህም 1,144 ብር የሚደርስ የገንዘብ መጠን ሸማቹ ላልተገባ ብዝበዛ የሚዳርግ ሲሆን፣ በዚያው ልክ ደግሞ ለእነዚህ ሕገወጥ ልኳንዳ ቤቶች ከፍተኛ የሆነ ያልተገባ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸውም ጥናቱ ማሳየቱ ተጠቁሟል፡፡

በዚህ የዳሰሳ ጥናት ምልከታ ከተደረገባቸው ልኳንዳ ቤቶች ውስጥ 21 ያህሉ የግል መሆናቸውን የገለጹት አቶ መንግሥቱ፣ ከእነዚህ ልኳንዳ ቤቶች አሥራ አንዱ ወይም 52 በመቶ የሚሆኑት የግል መሆናቸውንና በተለያየ መጠን የሚዛን ጉድለት ችግሮች እንዳሉባቸው ለማየት መቻሉን አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ የግል ልኳንዳ ቤቶች አሥር ወይም 48 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከሚዛን ልኬት ጋር በተያያዘ ሸማቹን ኅብረተሰብ ሊጎዳ የሚችል የልኬት ችግር እንደሌለባቸው ለመገንዘብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ከግል ልኳንዳ ቤቶች ጋር በተያያዘ ሸማቹ በገንዘብ ደረጃ የሚደርስበትን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በተመለከተ የተሰጠው ማብራሪያ፣ በአብዛኛው የግል ልኳንዳ ቤቶች በአማካይ የአንድ ኪሎ የሥጋ ምርት ውጤትን 160 ብር በሆነ ዋጋ ያቀርባሉ የሚለውን በመያዝ ነው፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት ከአንድ ኪሎ እስከ 123 ግራም የሚያጎድሉት ልኳንዳ ቤቶች ብቻ 100 ኪሎ ግራም ሥጋ ቢያቀርቡ ከመቶ ኪሎ ሥጋ ሽያጩ 12 ኪሎ ከ300 ግራም የሆነ ሥጋ ሸማቹ ያጣል፡፡ ይህም የጉድለት መጠን ደግሞ በገንዘብ ሲተመን 1,968 ብር ነው ተብሏል፡፡

ከሥጋ ውጪ የግል የችርቻሮ ሱቆችና  የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሱቆች ላይ በተደረገ ጥናት፣ ከልኳንዳ ቤቶች ያነሰ ችግር የታየ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ምልከታ ከተደረገባቸው 75 የግል ሱቆች 49 ወይም 65.3 በመቶ የሚሆኑት የልኬት ችግር የሌለባቸው ናቸው ተብሏል፡፡

ይህ የዳሰሳ ጥናት አብዛኛዎቹ የችርቻሮ ሱቆች ላይ ከልኬት ጋር የተያዘ የጎላ ችግር እንደሌለ ቢገልጽም፣ አንዳንዶች ላይ ከፍ ያለ ጉድለት እንዳለ ግን ያመለክታል፡፡ ሌላው እንደ ችግር የታየው የመለኪያ መሣሪያዎች ትክክለኛነትን የሚያሳይ ማረጋገጫ ያልተለጠፈባቸው ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ ከ75 ሱቆች 38 ወይም 50.7 በመቶዎች የልኬት መሣሪያ ማረጋገጫ የተለፈጠፈባቸው ሲሆን፣ 25.3 በመቶዎቹ ማረጋገጫ ያልተለጠፈባቸው፣ 24 በመቶዎቹ ደግሞ ማረጋገጫቸው የማይታይ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

የመሥፈሪያ መሣሪያዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥን በተመለከተ ነጋዴው በዓመት አንድ ጊዜ የሚጠቀምበትን ሚዛን ንግድ ጽሕፈት ቤት ቀርቦ ማስመርመርና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ያለበት ቢሆንም፣ ይህንን አለማድረጉ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ እንዲሁም የንግዱ ማኅበረሰብ አዲስ ሚዛኖች በሚገዛበት ወቅትም ሆነ ወደ ንግዱ ዓለም በሚቀላቀልበት ወቅት የመሥፈሪያ መሣሪያዎች ትክክለኛነት ተረገጋግጦ ወደ ሥራ መግባት ሲኖርበት፣ ሳይመረመር አገልግሎት እየሰጠ በተገኘ የመሥፈሪያ መሣሪያ ባለቤቱ ተጠያቂ የሚሆንበት ሕግ ቢኖርም ይህ አለመተግበሩም እንደ ችግር ተወስቷል፡፡ ጥናቱ መፍትሔ ይሆናሉ ብሎ ያነሳቸው ሐሳቦችም የተካተቱበት ነው፡፡ በተለይ ከልኬት መሣሪያዎች ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመቅረፍ፣ ዲጂታል መለኪያዎችን መጠቀም አንዱ አማራጭ ነው ተብሏል፡፡