Skip to main content
x
አንበሳ ባንክ የወኪል ባንክ ተጠቃሚዎችን 100 ሺሕ አደረስኩ አለ

አንበሳ ባንክ የወኪል ባንክ ተጠቃሚዎችን 100 ሺሕ አደረስኩ አለ

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ የወኪል ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎቹን ቁጥር ከ100 ሺሕ በላይ ማድረሱንና ከ25.6 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር መፈጸሙን ገለጸ፡፡

ባንኩ የወኪል ባንክ አገልግሎቱን ተጠቃሚዎች እዚህ ደረጃ ማድረስ የቻለው ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት መስጫ ሲስተም ጋር በማስተሳሰር በጀመረው አሠራር መሆኑ ተገልጿል፡፡ ባንኩ ከ1,600 በላይ ወኪሎችና ክፍያ ከሚቀበሉ ከ300 በላይ ተቋማት ጋር አገልግሎቱን በማስተሳሰር የተሳካ ሥራ በመሥራቱ የተገኘ ውጤት መሆኑን አመልክቷል፡፡

ከእነዚህ ወኪሎችና በአንበሳ ሄሎ ካሽ አማካይነት ክፍያ የሚቀበሉ የንግድ ተቋማት ውስጥ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ሰላም ባስ፣ ኤድናሞል ሲኒማና መኪና ኔት እንደሚገኙበት አገልግሎቱን በተመለከተ ባንኩ ያወጣው መግለጫ ያስረዳል፡፡

አንበሳ መደበኛ የባንክ አገልግሎቱን ከሄሎ ካሽ አገልግሎት ጋር የማስተሳሰሩ ሥራ በባንኩ የተጀመረ መሆኑን የሚያመለከተው መረጃ፣ ደንበኞች የባንኩ ቅርንጫፍ ወይም ወኪል ጋር መሄድ ሳይጠበቅባቸው ከመደበኛ የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ሒሳባቸው ወደ አንበሳ ሄሎ ካሽ አካውንታቸው እንዲሁም ከአንበሳ ሄሎ ካሽ ሒሳባቸው ወደ መደበኛ የባንክ ሒሳባቸው በቀጥታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል አሠራር እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት የአንበሳ የወኪል ባንክ አገልግሎት መስጫ ሲስተም ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት መስጫ ሲስተም ጋር በመተሳሰሩ ምክንያት የባንኩ ቅርንጫፍ  ወኪሎች በሌሉበት አካባቢ ወይም ከሥራ ሰዓት ውጪ ሒሳባቸውን ማንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን ዕድል የፈጠረ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ የባንኩ የመደበኛ ሒሳብ ተጠቃሚዎችና የወኪል ባንክ ተጠቃሚዎች በባንኩም ሆነ በሌሎች ባንኮች የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች አማካይነት ወጪ ማድረግ የሚችሉበት አሠራርን የሚከተል በመሆኑ፣ በወኪል የባንክ አገልግሎት በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ተችሏል ብሏል፡፡

በአንበሳ ሄሎ ካሽ አገልግሎት በኩል የባንኩ ደንበኞች አቅራቢያቸው በሚገኝ የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ቅርንጫፍ ወይም ወኪል አማካይነት የሞባይል ሒሳብ በመክፈት ገንዘብ ገቢና ወጪ ማድረግ ይችላሉ፡፡ የአንበሳ ሄሎ ካሽ ላለውም ሆነ ለሌለው ሰው ገንዘብ ማስተላለፍ የሚያስችል አገልግሎትን ጭምር ያጠቃለለ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የባንኩ ደንበኞች ገንዘብ መቀበልና ማስተላለፍ፣ የአውሮፕላን ትኬት መቁረጥ፣ የባስ ትኬት መቁረጥ፣ የሲኒማ ትኬት መቁረጥና የሞባይል ካርድ መሙላት የሚችሉ ሲሆን፣ ከጎግል ፕሌይ የሄሎ ካሽ አፕልኬሽን በማውረድ ሙሉውን የአንበሳ ሄሎ ካሽ አገልግሎት መተግበሪያ ማግኘት ከሚያስችል አሠራር ጋር መተሳሰሩ አማራጭ የባንክ  አገልግሎትን ለማስፋት ይረዳል ተብሏል፡፡

 አንበሳ ባንክ ከዚህ ቀደም የባንክ አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ጊዜና ቦታ ሳይገድባቸው የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል የራሴን አስተዋፅኦ እያበረከትኩ ነው ብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአንበሳ ባንክ ሌላ ሕብረት፣ ዳሸን፣ ኦሮሚያ ሕብረት ሥራና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህን የባንክ አገልግሎት ሥራ ላይ አውለውታል፡፡

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በ1999 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ በአሁን ወቅት ከ180 በላይ ቅርንጫፎችን ያሉት ነው፡፡