Skip to main content
x
‹‹ፖለቲካዊ ችግሩ በአፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያገኝ ተስፋ እናደርጋለን››

‹‹ፖለቲካዊ ችግሩ በአፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያገኝ ተስፋ እናደርጋለን››

አቶ ሀዲስ ታደሰ፣ የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር

ከጥቂት ቀናት በፊት የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን፣ የተቋሙን ዓመታዊ መጽሔት ይፋ ሲያደርግ ጥንዶቹ የዓለም ቢሊየነሮች በየአጋጣሚው ከሚቀርቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች ውስጥ አሥር ከባድ ጥያቄዎች ባሏቸው ላይ የሰጧቸውን ምላሾች በመጽሔቱ አስነብበዋል፡፡ ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር፣ እንዲሁም የተቋሙ የአፍሪካ ተጠሪ የሆኑት አቶ ሀዲስ ታደሰ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንን ከመሥራት ጀምሮ በዋና ዳይሬክተርነት ላለፉት ሰባት ዓመታት እየመሩ የሚገኙት አቶ ሀዲስ ለጥንዶቹ ስለሚቀርቡት ጥያቄዎች፣ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ ስለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች፣ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ድርቅ ፋውንዴሽኑ ስለነበረው ሚና፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ስለገባችበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ስለሚያስከትላቸው ችግሮችና ስለሌሎችም ጉዳዮች ብርሃኑ ፈቃደ አቶ ሀዲስን አነጋግሮ የሚከተለውን አጠናቅሯል፡፡   

ሪፖርተር፡- ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ በቅርቡ ይፋ በተደረገው የፋውንዴሽኑ ዓመታዊ መጽሔት ውስጥ አሥር ከባድ ላሏቸው ጥያቄዎች የሰጧቸውን ምላሾች አስነብበዋል፡፡ ከተጠየቁት ጥያቄዎች መካከል ለሌሎች አገሮች ከሚሰጡት ዕርዳታ አኳያ ለአሜሪካ ለምን እንደማይሰጡ፣ የፋይናንስ ድጋፎች እንዴት እንደሚለቀቁ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ለመሆኑ ፋይናንስ ለምታደርጓቸው ፕሮጀክቶች ቅድሚያ የምትሰጡት እንዴት ነው?  

አቶ ሀዲስ፡- ሰዎች ይጠይቋቸዋል፡፡ ለምን ለአሜሪካ ብዙ አትሰጡም ይሏቸዋል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ለትምህርት ቅድሚያ ቢሰጡም በየዓመቱ እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር በአሜሪካ ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ የቀረውንም በመላው ዓለም ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ ይህም የራሱ ምክንያት ስላለው ነው፡፡ በዓለም ላይ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ለማየት ሞክረናል፡፡ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከልም ትልልቅ የሚባሉትን መርጠን እነሱ ላይ ኢንቨስት እየደረግን ነው፡፡ እናቶች በወሊድ ወቅት ይሞታሉ፡፡ በርካታ ሕፃናት ከተወለዱ በኋላ አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ይሞታሉ፡፡ እንደ ወባ፣ የሳንባ በሽታና ኤችአይቪ/ኤድስ ያሉ መከላከል የሚቻሉ በሽታዎች በርካታዎችን ለሕልፈት የሚዳርጉት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ነው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ፋውንዴሽኑ የበርካቶችን ሕይወት መታደግን ምርጫው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ እነዚህን ፈታኝ ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችል ኢንቨስትመንት እያካሄድን እንገኛለን፡፡ በአሜሪካ ኢንቨስት የምናደርገው አነስተኛ የሆነው በአሜሪካ ያለው የበሽታ ብዛትና ጫና ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ያለው ሀብትም በታዳጊ አገሮች ካለው አኳያ የላቀ በመሆኑ ትኩረታችንን ወደ እነዚህ መስኮች አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በመላው አፍሪካ ደረጃ ፋውንዴሽኑን በመወከል ለአፍሪካ ኅብረት ተጠሪ ነዎት፡፡ ለእርስዎም ከባድ የተባሉ ጥያቄዎች ይቀርቡልዎታል?

አቶ ሀዲስ፡- በርካታ ጥያቄዎችን እናስተናግዳለን፡፡ አንዳንዶቹ በቀላሉ የሚመለሱ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ከበድ ይላሉ፡፡ አንዳንድ ጥያቄዎች ጊዜ ወስዶ መመለስን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ፋውንዴሽኑን በአፍሪካ ደረጃ እንደ መወከሌ የሚቀርቡልን ጥያቄዎች በርካታ ናቸው፡፡ ከጥያቄዎች ውስጥ ለምን እንዲህ ካለው አገር መንግሥት ጋር ትሠራላችሁ የሚሉትን ጨምሮ የዘረመል ምርቶችን ትደግፋላችሁ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ለምን የግል ኩባንያዎችን ትደግፋላችሁ የሚሉንም አሉ፡፡ አንዳንዶችም ቢል ጌትስ ገንዘብ የሚሰጠው በሌላ መንገድ ብዙ ገንዘብ ለማግኘት ነው ይላሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ይመጣሉ፡፡ በተቻለኝ አቅም እውነታውን ሁሉ በመናገር፣ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ በምንሠራቸው ሥራዎች አማካይነት የገንዘብ ጥቅም የማግኘት ዓላማ የለንም፡፡ የቢል ጌትስ ቤተሰብ በዚህ ረገድ ከሚገመተው በላይ ብዙ ያካበተ ነው፡፡ እነሱ የሚፈልጉት ለሁላችንም በምትመች ዓለም ውስጥ እንድንኖር ማድረግ ነው፡፡ ገንዘባቸውን ለምን እንደሚሰጡ የሚጠይቅ አንድ ጥያቄም ተነስቶ ነበር፡፡ ለዚህ ሦስት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡

አንደኛው በሚሠሩት ሥራ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ በማበርከት ለዓለም ማኅበረሰብ ጥሩና ምቹ ነገር መፍጠር ነው፡፡ መስጠት ስላለው ዋጋ ልጆቻቸው እንዲገነዘቡና የእነሱን አርዓያ እንዲከተሉ ይፈልጋሉ፡፡ በሚሠሩት ሥራም ደስተኞች ናቸው፡፡ ሰዎችን ማገዝና መርዳት ያስደስታቸዋል፡፡ በተጨማሪም አዳዲስ ነገሮችን መማርና ማወቅ ይወዳሉ፡፡ በሶፍትዌር ማበልፀግ የካበተ ልምድ አላቸው፡፡ ሚስተር ቢል ጌትስ ማይክሮሶፍት ኩባንያን ለበርካታ ዓመታት መርተዋል፡፡ አብዛኛውን ዕድሜያቸውንም በዚሁ ኩባንያ አሳልፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስለግብርና፣ ስለፋይናንስ አገልግሎቶች፣ እንዲሁም በአፍሪካ ስላሉ የጤና አገልግሎቶች ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ እንደ ቢልና ሜሊንዳ ያሉ ሰዎች አዳዲስ ነገሮችን በመማርና በማወቅ ይደሰታሉ፡፡ የእነዚህ ነገሮች ድምር ነው ካላቸው ለመስጠት እንዲነሳሱ የሚያደርጋቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሚስተር ቢል ጌትስ ከሚወዷቸው ነገሮች ውስጥ ማንበብም ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ከፍተኛ የማንበብ ፍቅር ያደረባቸው ሰው ናቸው ሊባሉ ይችላሉ?

አቶ ሀዲስ፡- ከፍተኛ የማንበብ ፍቅር ያደረባቸው ከመሆናቸው የተነሳ ማንም አይወዳደራቸውም፡፡ (www.gatesnotes.com/books) በተሰኘው ድረ ገጻቸው የሚወዷቸው መጻሕፍት አስፍረዋል፡፡ ማንበብ የሚፈልጉ ሰዎች ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ቢል ጌትስ በለጋስነታቸው ስለሚያደርጓቸው ድጋፎች በርካቶች የሚደግፏቸውን ያህል የሚወቅሷቸውም አሉ፡፡ በሳይንስና ፈጠራ መስክ፣ በዘረመል ምሕንድስና፣ እንዲሁም በክትባት መድኃኒቶች መስክ ባላቸው አቋም የሚተቹባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የእስርዎ ምላሽ ምንድነው?

አቶ ሀዲስ፡- ለእኔ ጥያቄው መሆን ያለበት የትኛውን ችግር ለመቅረፍ እየሞከርን ነው የሚለው ነው፡፡ ኤችአይቪ/ኤድስ ወይም የግብርና ምርታማነት ወይም ሥነ ምግብ ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ በምን ዓይነት ጉዳይ ማተኮር እንደሚገባን ከለየን በኋላ፣ ቀጣዩ ጥያቄ ይህንን ችግር የመቅረፍ አቅምና ብቃት ያለው ማን እንደሆነ ወደ መለየቱ እንሄዳለን፡፡ የትኞቹ ችግሮች መፈታት አለባቸው ብለህ ስትነሳም ትተቻለህ፡፡ ለምሳሌ እኛ ካንሰር ላይ አንሠራም፡፡ ካንሰር በአሁኑ ወቅት የታዳጊ አገሮች ችግር እየሆነ መጥቷል፡፡ እኛ ደግሞ በኤችአይቪ፣ በወባ ወይም በሳንባ በሽታ ላይ በማተኮራችን ወቀሳ ይቀርብብናል፡፡ ለምን በካንሰር ላይ አትሠሩም እንባላለን፡፡ ምላሹ ግን የቱንም ያህል ትልቅ ብንሆን እኛም የሀብት ውስንነት አለብን፡፡ በመሆኑም ለውጥ ማምጣት የምንችልባቸውን መስኮች በመምረጥ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ መፍትሔ ያስፈልገዋል ብለን ለመረጥነው ችግር ማን ጥሩ አቅም አለው? ችግሩን ለመቅረፍ የሚችል መፍትሔ ሊሰጠን የሚችለው ማን ነው? ብለን ስንነሳም ወቀሳዎች አይጠፉም፡፡

ከባድ የሚባሉትን ችግሮችን ለመቅረፍ ስትነሳ እነዚህን ችግሮች ሊቀርፉ የሚችሉ እነማን እንደሆኑ መለየት አለብህ፡፡ አንዳንዴ ወደ መንግሥታት ልንሄድ እንችላለን፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን ከዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ጋር በመሆን ችግሮችን ለመፍታት እንሠራለን፡፡ ከአገር ውስጥና ከውጭ ኩባንያዎች ጋርም እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ የክትባት መድኃኒቶችን ለማምረት አብዛኞቹ መንግሥታት አቅሙም ቴክኖሎጂውም አይኖራቸውም፡፡ ለኤችአይቪ/ኤድስ ክትባት ለሚደረግ ምርምር የሚውል ሀብትና አቅም ላይኖራቸው ይችላል፡፡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችም እንደዚሁ፡፡ ሆኖም ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የቴክኒክ ብቃቱና አቅሙ አላቸው፡፡ ለመፍታት እንደምንሞክረው ችግር ዓይነት አቅሙና ተፈላጊው ብቃት ወዳላቸው ዘንድ በመሄድ መፍትሔ እናፈላልጋለን፡፡ ይህን የምናደርገው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ይበልጥ ትርፋማ እንዲሆኑ ለማድረግ አይደለም፡፡ ለመፍታት የምንፈልገው ችግር ነው ወደ እነዚህ ኩባንያዎች የሚወስደን፡፡ አቅሙ ስላላቸው እንዲረዱን በማሰብ ነው ወደ እነሱ የምንሄደው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከስድስት ወራት በፊት እ.ኤ.አ. በ2030 ላይ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች በኤችአይቪ ሳቢያ ሊሞቱ እንደሚችሉ ገልጸው ነበር፡፡ እስካሁንም 35 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ለሕልፈት መብቃታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ይፋ ካደረገ ወዲህ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ሀዲስ፡- በሒደት ላይ ያለ ነገር ነው፡፡ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ በበሽታው ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ኢትዮጵያ ነች፡፡ በኢትዮጵያ ኤችአይቪ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ማግኘት የሚገባቸው ሕክምና ማግኘት እንዲችሉ ከማድረግ ጎን ለጎን፣ ለበሽታው ፈውስ ለማግኘት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ እንሳተፋለን፡፡ ለኤችአይቪ መከላከያ ክትባት መሥራት ከተቻለ ትልቅ ዕፎይታ ነው፡፡ በርካታ ሙከራዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ሙከራዎች በአሁኑ ወቅት የሚገኙበትን ደረጃ መናገር ባልችልም፣ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ አውቃለሁ፡፡ የወባ በሽታ የክትባት መድኃኒት የለውም፡፡ እንዲህ ባሉት መስኮች ላይ ጥሩ ውጤቶችን ለማምጣት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያካሄድን ነው፡፡ እየተካሄዱ ከሚገኙት ሙከራዎች በመጪዎቹ ዓመታት ውስጥ ጥሩ ውጤት እንደምናገኝ አልጠራጠርም፡፡

ሪፖርተር፡- ሜሊንዳና ቢል ጌትስ ባለፉት 18 ዓመታት ውስጥ 50 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ኢትዮጵያ ምን ያህል ደርሷታል?

አቶ ሀዲስ፡- ባለፉት 17 ወይም 18 ዓመታት ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንደተደረገ በትክክል መናገር ከባድ ነው፡፡ ሆኖም በግርድፉ 600 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት 200 ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ እናደርጋለን፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ቅድሚያ ከምንሰጣቸው አገሮች አንዷ ነች፡፡ በትንሹ ብንጀምርም በሒደት ኢንቨስትመንታችንን አስፋፍተናል፡፡ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የምናካሂድባቸው ዋነኛ አገሮች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሆኖም ከስድስት ወራት በፊት የዘላቂ ልማት ግቦችንና የቀደሙትን የሚሊኒየሙ የልማት ግቦችን የዳሰሰውን ሪፖርት ፋንዴሽኑ ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለኢትዮጵያ መመደቡን ገልጸው ነበር፡፡

አቶ ሀዲስ፡- በወቅቱ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ እስካሁን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ተደርጓል ነበር ያልኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ቃል የተገባው ምን ያህል ገንዘብ እንደሆነስ ሊጠቅሱ ይችላሉ?

አቶ ሀዲስ፡- ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት እስካሁን 600 ሚሊዮን ዶላር ያህል ኢንቨስት አድርገናል፡፡ የኢንቨስትመንት መጠኑም ከዚህ በላይ እየጨመረ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ምን ያህል ቃል ተገብቷል ለሚለው ጥያቄ እንዲህ ነው ብሎ መግለጽ ይከብዳል፡፡ እንደተመረጠው ፕሮጀክት፣ እንደ ፕሮጀክቱ ዓይነትና መጠን ኢንቨስት የሚደረገው የገንዘብ መጠን ይለያያል፡፡ በአዲስ ፕሮጀክት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ከወሰንን፣ ኢንቨስት የምናደርገውን ገንዘብ መጠንም እንጨምራለን፡፡ በየዓመቱ ምናልባት ከ150 እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ፋውንዴሽኑ የፋይናንስ ድጋፍ ከሚጣቸው ተቋማት አንዱ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ነው፡፡ የተቋሙን ውጤታማነት እንዴት ነው የምትመዝኑት? የምትጠብቁትን ውጤት እያስገኘ ነው?

አቶ ሀዲስ፡- ግብርና ዋናው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡ ለአገሪቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሳካት ሰፊ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አብዛኛው የወጪ ንግድ ሸቀጦች የሚመነጩትም ከግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግብርናዋን ለመቀየር ግልጽ ፍላጎት አላት፡፡ ኤጀንሲውም የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ በመለወጥ ሒደት ውስጥ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በማሰብ እኛ ብቻም ሳንሆን በርካታ ድጋፍ የሚሰጡት አካላት አሉ፡፡ ለውጥን እንዴት እንመዝናለን ካልን የረዥም ጊዜ ሒደት ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ በመዋቅራዊ ደረጃ ለመቀየር ሲፈለግ፣ እንደ ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሥነ ምኅዳርና የፖለቲካ ሁኔታ ባለው አገር ውስጥ የለውጥ ሒደቱ ውስብስብ ይሆናል፡፡ በረዥም ጊዜ ሒደት ውስጥ የሚመጣውን ለውጥ ለማሳካት የሚያስችሉ መነሻዎችን መጀመር ያስፈልጋል፡፡

ለምሳሌ ጤፍን በመስመር በመዝራት በኩል የሠሩት ሥራ፣ የአገሪቱን የአፈር ዓይነት በመለየት ዲጂታላይዝ ማድረጋቸው ምሳሌያዊ ተግባር ነው፡፡ እንዲህ ያሉትን የኤጀንሲውን ሥራዎች እየደገፍን እንገኛለን፡፡ በአሁኑ ወቅትም የክላስተር ስትራቴጂን በመከተል የትኞቹ የምርት ዓይነቶች የት አካባቢ መመረት እንዳለባቸው የሚጠቁም ሥራ እያካሄዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ምርቶች የት እንደተመረቱና እንዴት ወደ ገበያ እንደሚደርሱ፣ እንዲሁም ገበሬዎች በምን አግባብ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ለማወቅ የሚያስችለን አሠራር ነው፡፡ ይህ ሲደረግ ተፈላጊውን ፖሊሲ በመቅረፅ የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡ ሆኖም ለእኛ ስኬት ማለት ገበሬዎች፣ የገበሬዎች ማኅበራት፣ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ሥራዎች ተጠቃሚ መሆን ሲችሉ ማየት ነው፡፡ የውጤት መለኪያችንም ሁልጊዜ የሚያያዘው የገበሬዎች ሕይወት ላይ መታየት በቻለው ውጤት ልክ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት ይፋ በተደረጉ አኃዞች መሠረት በኢትዮጵያ 7.8 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ይታወቃል፡፡ በእንዲህ ያለው ወቅት የፋውንዴሽኑ ሚና ምን ነበር?

አቶ ሀዲስ፡-  ዝቅተኛ የመስኖ እርሻ በሚታይበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ዝናብ ተኮር ግብርና፣ የዝናብ መጠን በተዛባ ቁጥር በድርቅ መመታታችን የማይቀር ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚያሳየን ነው፡፡ ካቻምናም ዓምናም አስከፊ የሚባለውንና የግብርናው ዘርፍ የሚፈታተን ድርቅ ዓይተናል፡፡ ምንም እንኳ አንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ድርቁን ለማካካስ የሚረዳ ምርት ቢያመርቱም ችግሩ ሰፊ ነበር፡፡ በዚህ ሳቢያም ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለምግብ ዕርዳታ ተዳርገው ነበር፡፡ አዲስ የመስክ ዳሰሳ ጥናት ተደርጎ በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታ ለማየት ተሞክሯል፡፡ በቅርቡ ይፋ ሊደረግ ይችላል፡፡ የድርቁን መከሰት ካየን በኋላ እየተከናወኑ የነበሩ ፕሮጀክቶች እንዳይቋረጡ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ለዘርፉ የምናደርገውን ድጋፍ በማጠናከር ወደ ፊት ድርቅ ቢከሰት እንኳ ገበሬዎች አይበገሬነትን እንዲያጎለብቱ ለማገዝ ሞክረናል፡፡ የረዥምና የአጭር ጊዜ ፈታኝ ሁኔታዎችንም ለመመልከት ሞክረናል፡፡ በአብዛኛው የእኛ ኢንቨስትመንት ለረዥም ጊዜ አስቸጋሪ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ለአጭር ጊዜ በሚቆዩ አስቸጋሪ ጉዳዮችም ላይ እንሳተፋለን፡፡ መንግሥት በተለይም የብሔራዊ አደጋ መከላከልና ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለሚያስተባብረው አገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ሞክረናል፡፡ የፋይናንስ ድጋፍ አድርገናል፡፡፡ ለረዥም ጊዜ በሚረዱ የመፍትሔ ተግባራት ላይ ጥሩ ልምድ አለን፡፡ በተመሳሳይ መንገድ አስቸኳይ ጉዳይ ሲከሰትም ቶሎ በመድረስ የቴክኒክም ሆነ የፋይናንስ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከድርቁ ባሻገር የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ አጋጥሟል፡፡ በዚህ ሳቢያ በፋውንዴሽኑ ሥራዎች ላይ መስተጓጎል አጋጥሟል?

አቶ ሀዲስ፡- በየትኛውም ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ ማንኛውም ዓይነት ችግር ሲያጋጥም ልማት መጎዳቱ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይም ችግር ባጋጠመበት አካባቢ የተለመደውን ሥራ እንደ ወትሮው ማከናወን ከባድ ይሆናል፡፡ ተፅዕኖው ግን ከዚህም በላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላ አገር በንግድ እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ኢንቨስትመንትን ይጎዳል፡፡ ኢንቨስተሮች በልበ ሙሉነት እንዳይሠሩ ያደርጋል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴም ሆነ ኤክስፖርት ሲቀዛቀዝ አገሪቱ በእጅጉ የሚያስፈልጋት የውጭ ምንዛሪ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ በፖለቲካዊ ቀውሱ ሳቢያ ፋውንዴሽናችን ያን ያህል ተፅዕኖ ውስጥ አልወደቀም፡፡ ሆኖም ከባቢው አየር ችግር ውስጥ ከወደቀ የጤናና የግብርና ልማትን መጎተቱ አይቀርም፡፡ ሁኔታው በልማት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ግልጽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለመሥራታችን አንዱ ምክንያት ከመንግሥት ጋር ያለን ጠንካራ አጋርነት ነው፡፡ ይህ መንግሥት ደሃ ተኮር የልማት አጀንዳዎችን ያራምዳል፡፡ በመሆኑም እንዳሁኑ ያለ ፖለቲካዊ ችግር፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዘርፉን የሚመሩ ሰዎችን ከልማት ሥራ እንዲዘናጉ ያስገድዳቸዋል፡፡ እነሱንም ሆነ ለልማት የሚፈለገውን ወሳኝ ጥሪት መሻማቱ አይቀሬ ነው፡፡ ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውለው ጥሪት ቀውሱን ለማረጋጋት ሲባል ፕሮጀክቶች ታጥፈው ሊወሰድ ይችላል፡፡ ተስፋ የምናደርገው ፖለቲካዊ ችግሩ በአፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያገኝ ነው፡፡ ችግሩ የተፈጠረው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በምናሳድግበትና የእያንዳንዱን ኢትዮጵያ ሕይወት ለማሻሻል በምንጣጣርበት ወቅት በመሆኑ የሚያስከትለው ጉዳት በጣም ከባድ ነው፡፡