Skip to main content
x
ታላቁ የዓደዋ ድል ሲዘከር የኢትዮጵያዊነት ስሜትም ያንሰራራ!

ታላቁ የዓደዋ ድል ሲዘከር የኢትዮጵያዊነት ስሜትም ያንሰራራ!

የዛሬ 122 ዓመት የአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶችን አንገት ያስደፋ፣ የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦችን አንገት ደግሞ በኩራት ቀና ያደረገ ታሪክ የተሠራው በጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ወደር የሌለው ተጋድሎ ነበር፡፡ ታላቁ የዓደዋ ድል የአይበገሬነት ፅናትንና የእናት አገር ጥልቅ ፍቅርን ተምሳሌታዊነት ያረጋገጠ የመስዕዋትነት ውጤት ነው፡፡ ከአራቱም ማዕዘናት እንደ ንብ በመትመም የጣሊያንን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች የታጠቀ የሠለጠነ ሠራዊት አከርካሪውን የሰበረው ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ምንም እንኳ እዚህ ግባ የሚባል ትጥቅ ባይኖረውም ለእናት አገሩ የነበረው ወደር የሌለው ፍቅር ግን አንፀባራቂ ታሪክ ሠርቷል፡፡ ከምንም ነገር በላይ ኢትዮጵያዊነት የሚባለውን ታላቅ የአንድነቱ ማሰሪያ ገመድ በመታጠቅ፣ ውድ ሕይወቱን ሰውቶ ቅኝ ገዥውን ኃይል አንበርክኳል፡፡ ይኼ ህያው ታሪክ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ በመናኘት ኢትዮጵያችንን የነፃነት አኩሪ ኮከብ አድርጓታል፡፡ ጀግኖቹ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ከመኖሪያ ቀዬአቸው እስከ አገር አቀፍ ድረስ በወቅቱ በነበረው ሥርዓት ይንገላቱ የነበሩ ቢሆንም እንኳ፣ ከአገር ህልውና በላይ ያስቀደሙት አንዳችም ነገር ባለመኖሩ ለአገራቸው በአንድነት ተሠልፈው አንፀባራቂ ታሪክ ሠርተው አልፈዋል፡፡ ከውስጥ ሽኩቻና ፍልሚያ በላይ ለሆነች ታላቅ አገር በፍቅር መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ታላቁን የዓደዋ ድል ስንዘክር ይህንን ህያው የአገር ፍቅር መቼም ቢሆን አንረሳውም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ታላቁ የሕዝባችን ምሥል ስለሆነ፡፡

በታላቁ የዓደዋ ድል በዓል መታሰቢያ ዋዜማ ላይ ሆነን ይህን የኢትዮጵያዊነት ግርማ በተለያዩ መገለጫዎቹ ማውሳት ይገባናል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ክብር ያገኘችው በዓደዋ ድል ምክንያት ነው፡፡ የቀድሞውን ሊግ ኦፍ ኔሽንስም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን፣ እንዲሁም ታዋቂ ዓለም አቀፍ ተቋማትን መሥራች መሆን የቻለችው በዓደዋ ድል ምክንያት ነው፡፡ አፍሪካውያንም ሆኑ ሌሎች የአርነት ግንባሮች ኢትዮጵያን አርዓያ ያደረጉት በዓደዋ ድል ምክንያት ነው፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መጀመርያና ዕውን መሆን ምክንያት የሆነው የዓደዋ ድል ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ የሆነው የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው በዓደዋ ድል ምክንያት ነው፡፡ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ጥልቅ ኢትዮጵያዊነት የፈጠረው ታላቁ የዓደዋ ድል ሲዘከር፣ ኢትዮጵያዊነትን ምን ያህል ትልቅ ዋጋ የተከፈለበት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ጀግናው፣ ጨዋው፣ አስተዋዩና አይበገሬው ሕዝባችን ኢትዮጵያዊነት ሲገነባ የኖረው ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ የአገር ፍቅር ስሜት ነው ኢትዮጵያ አገራችንን ቅኝ ያልተገዛች የነፃነት ተምሳሌት ያደረጋት፡፡ ይህ ተረት ሳይሆን በደም የደመቀ ታሪክ ነው፡፡

የጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን በዓለም ያስተጋባ የጀግንነት ታሪክ ሲዘከር፣ የእዚህ ዘመን ትውልድ ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ በተለይ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፣ በተለያዩ መስኮች የተሠማሩ ዜጎች፣ ወዘተ. ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ስላላቸው ዕይታ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ አገር ከምንም ነገር በላይ ለመሆኗ፣ ለዚህም ሲባል ውድ ልጆቿ የሕይወትና የአካል መስዕዋትነት ሲከፍሉ መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአስተዋይነትና የጨዋነት ፀጋ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምስክር ነው፡፡ አሁን ባልበሰለ የፖለቲካ አተያይ ምክንያት የተፈጠሩ ውዝግቦችና ውዥንብሮች አገሪቱን መልህቅ እንደሌላት መርከብ ሲንጧት የምናየው፣ ስክነትና ለአገር ማሰብ በመጥፋቱ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት ታላቁ ምሥል እየጠፋ በመንደርተኝነት መቧደንና መጠፋፋት ውስጥ የተገባው፣ ለሰከነና ጨዋነት ለተላበሰ የፖለቲካ ግንኙነት ዕውቅና በመነፈጉ ነው፡፡ ከአገር በላይ ግላዊና ቡድናዊ ጥቅም እየበለጠ ኢትዮጵያዊነት ደብዝዟል፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በዓለም አደባባይ ያላኮራና አንፀባራቂ ታሪክ ያላሠራ ይመስል፣ በዚህ ዘመን ብሔር ተኮር ግጭት መቀስቀሱ ያሳፍራል፡፡ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው፣ ተፋቅረውና ተዋልደው በኖሩባት ታሪካዊ አገር ውስጥ ጠባብነት አገር እስኪያፈርስ ድረስ መቀንቀኑ ያሳምማል፡፡

በሌላ በኩል ኢሕአዴግም ሆነ በዙሪያው የተሰባሰቡ ኃይሎች ኢትዮጵያዊነትን በማሳነስ የፈጸሙት ስህተት ዛሬ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ በተቃውሞው ጎራ ውስጥ ያሉ ኃይሎች የፈጸሙት ደባ ታላቅ ኪሳራ አድርሷል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ማንነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ የብሔር ቆጥ ላይ ብቻ መሥፈር ያመጣው ጣጣ የንፁኃንን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ በማንነታቸው ምክንያት የጥቃት ሰለባ የሆኑ ብዙ ናቸው፡፡ ጥረው ግረው ያፈሩትን ሀብት የተነጠቁትንም ሆነ የወደመባቸውን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ የኢትዮጵያ ጨዋ ሕዝብ ግን በእዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ድርጊት አይታወቅም፡፡ ይልቁንም በእርስ በርስ መስተጋብሩ አማካይነት ኢትዮጵያዊነትን ለዘመናት እያደመቀ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ተምሳሌቱ ነው የሚታወቀው፡፡ ከአገሩ በላይ የሚያሳስበው የግል ጥቅምና ፍላጎት የሌለው ጨዋውና አስተዋዩ ሕዝብ፣ በዚህ ዘመን ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት ቡድናዊ ግጭት ሰለባ ሲሆን ያሳዝናል፣ ያሳፍራል፡፡ ይህ የተከበረ ሕዝብ ያሉትን ፀጋዎች በመጠቀም አገሪቱን ወደ ታላቅነቷ መመለስ ሲገባ፣ አዘቅት ውስጥ እንድትገባ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ቅብዝብዞች አሉ፡፡ ለእነሱ አገር ማለት የግል ዝና፣ ክብር፣ ሀብትና ሥልጣን ስለሆኑ ለሕዝብ አይጨነቁም፡፡ ኢትዮጵያዊነት እየጠፋ ያለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

አገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ በቆመችበት በዚህ አሳሳቢ ጊዜ ቆም ብሎ በሰከነ መንገድ ችግሮችን መፍታት ካልተቻለ፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲያንሰራራ ብርቱ ጥረት ካልተደረገና ሁሉም በየጎራው ተሠልፎ ከተፋጠጠ የዓለም መሳለቂያ ከመሆን ውጪ ዕርባና የለውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ምትክ የሚሰየመውን ተሿሚ ሥርዓት ባለው መንገድ ለሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ሲባል ማምጣት አለመቻል፣ ቀውሱን ያባብሳል እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ ለሥልጣን ብቻ ሲባል የሕዝብ ፍላጎትን አለማካተት አገሪቱን ቀውስ ውስጥ ከመክተት ውጪ የሚያመጣው ትሩፋት የለም፡፡ በፖለቲከኞች መካከል ከሚካሄደው አሰልቺ ትንቅንቅ በተጨማሪ፣ በማኅበራዊ ሚዲያው የሚሰማው እንቶ ፈንቶ ቀውሱን ለማባባስ በጥሬ ዕቃነት እያገለገለ ነው፡፡ ሥልጣን በዕውቀት፣ በልምድ፣ በአገር ፍቅር ስሜት፣ በሥነ ምግባርና በመሳሰሉት መሥፈርቶች መገኘት ሲገባው ማስፈራራት ውስጥ የሚገባው ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ሲፀናወት ነው፡፡ ለአገር ማሰብ ሲነጥፍ ነው፡፡ በሥልጡን ድርድርና በዴሞክራሲያዊ አግባብ ችግሮችን በመፍታት የጋራ ውሳኔ ላይ መድረስ መቻል ሲገባ፣ እጅ ጥምዘዛ ውስጥ እየተገባ አቧራ ማስነሳት ለኢትዮጵያችን አይጠቅማትም፡፡ ኢትዮጵያን የሚጠቅማት ሕዝቧን በተቻለ መጠን የሚያግባባ ሥራ ሲከናወን ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት የሚጎለብተው ከሥልጣን በላይ አገር እንደምትቀድም ማስተማመኛ ሲገኝ ነው፡፡ በአፍ ከሚነገረው በላይ ለሕዝብ ሲታሰብ ነው፡፡ በሰከነ መንፈስ ለመነጋገርና ለመደራደር መቀራረብ መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ ሕዝብን በአግባቡ በማዳመጥ ምላሽ ለመስጠት ተነሳሽነት ሲኖር ነው፡፡ ከኋላ ቀርና አሮጌ አስተሳሰቦች በመላቀቅ የዘመኑን ትውልድ ፍላጎቶች የሚወክሉ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ሲቻል ነው፡፡ ታላቁን የዓደዋ ድል ተምሳሌታዊነት በማረጋገጥ ድሉን ከምንም ነገር በላይ በመዘከር ነው፡፡ ይኼ ታሪካዊና አንፀባራቂ ድል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ቁርጠኝነት በመፍጠር ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ለኢትዮጵያዊነት ትልቁ ምሥል ከፍተኛ አክብሮት በመስጠት ነው፡፡ አሁን ያጋጠሙ ችግሮችን ለመሻገር የሚያስችሉ አስተማማኝ የጋራ መፍትሔዎች መገኘት የሚችሉት፣ በዚህ መንፈስ ማሰብና መግባባት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሲፈልጉ የሚለብሱት፣ ሳይፈልጉ የሚያወልቁት ሸማ ሳይሆን ትውልዶች መስዕዋትነት የከፈሉለት ህያው አገራዊ መገለጫ ነው፡፡ ይህንን ታላቅ እሴት ማስቀጠል የሚቻለው ደግሞ በጥልቅ የአገር ፍቅር ስሜት ነው፡፡ በታላቁ የዓደዋ ድልም ሆነ በተለያዩ ዓውደ ግንባሮች ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን የገበሩትና አጥንታቸውን የከሰከሱት፣ ለውዲቷ አገራቸው በነበራቸው ወደር የሌለው ፍቅር ነው፡፡ ታላቁ የዓደዋ ድል ሲዘከር የኢትዮጵያዊነት ስሜት ማንሰራራት ያለበትም በዚህ ምክንያት ነው!