Skip to main content
x
‹‹በኢትዮጵያ የአየር ብክለት ጉዳይ የሰዎችን ትኩረት መሳብ የጀመረው ገና አሁን ነው››

‹‹በኢትዮጵያ የአየር ብክለት ጉዳይ የሰዎችን ትኩረት መሳብ የጀመረው ገና አሁን ነው››

ሳራ ቴሪ፣ በአሜሪካ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ

በአሜሪካ መንግሥት የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አማካይነት የአየር ብክለትና የብክለት ደረጃን የሚለካ ጥራቱን የሚከታተል፣ ‹‹ኤር ኳሊቲ ፕላኒንግ ኤንድ ስታንዳርድስ›› በሚል መጠሪያ የሚንቀሳቀስ ጽሕፈት ቤት አለ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በአሜሪካ ያለውን የአየር ብክለት ደረጃ ከመለካት ባሻገር፣ ለብክለት መንስዔ የሆኑ ምንጮችን በመከታተልና በማጥናት ጭምር ይታወቃል፡፡ ሳራ ቴሪም የዚህ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ ተቋሙ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ካካሄዳቸው እንቅስቃሴዎች አንዱ ‹‹ሜጋሲቲ ፓርትነርሺፕ›› የሚባለው ፕሮጀክት ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ውስጥ የአየር ብክለት ቁጥጥርን ለማስፈን፣ ብሎም የብክለት ምንጮችን፣ በብክለት ሳቢያ የሚደርሱ የጤና ጠንቆችንና ብክለቱ የፈጠረው የጤና ቀውስ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጫና የሚተነትን ፕሮጀክት ነው፡፡ በዚህ ፕሮጀክት እስካሁን ተጠቃሚ የሆኑት ሁለት ከተሞች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ በዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንድትሆን በመመረጥ ሦስተኛዋ ሆናለች፡፡ በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ የአየር ብክለት መጠንን ጨምሮ፣ ወደፊት ከፕሮጀክቱ አኳያ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንና በሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች አማካይነት ስለሚከናወኑ ሥራዎችና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ በመገኘት ጉብኝት ያደረጉትን ሳራ ቴሪን ብርሃኑ ፈቃደ አነጋግሮ የሚከተለውን አጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ጊዜ ስንነጋገር አዲስ አበባ ከተማ ያላት አየር በመካከለኛ ደረጃ የተበከለ ሊባል እንደሚችል ገልጸው ነበር፡፡ በአሁኑ ጉብኝትዎ ከእርስዎ ጋር የሚሠሩ ባለሙያዎችን አካተው እንደ መምጣትዎ፣ ምን አዲስ ነገር አለ? የታዩ ለውጦችስ ይኖሩ ይሆን?

ሳራ ቴሪ፡- ከዚህ በፊት የነበረው ጉብኝታችን በአዲስ አበባ የቅኝት ጉብኝት በማድረግ ከተማዋ ከጋና ዋና ከተማ አክራ፣ እንዲሁም ከቺሊዋ ሳንቲያጎ ከተማ በመቀጠል የእኛን ድጋፍ ማግኘት የምትችል ሦስተኛዋ ከተማ የመሆን ዕድል ይኖራት እንደሆነ ለማየት ሞክረን ነበር፡፡ አክራ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር በእኛ ፕሮጀክት ሥር የተካተተችው፡፡ ሳንቲያጎ ግን አምና ነው የገባችው፡፡ በመሆኑም ሌላ ሁለተኛ የአፍሪካ ከተማ ለማካተት ምርጫ ስናካሂድ ቆይተናል፡፡ በመሆኑም ባለፈው ጉብኝታችን ወቅት ከአዲስ አበባ በቂ መረጃ ለማግኘት ሞክረን ነበር፡፡ ከጉብኝታችን ባገኘነው መረጃ መሠረትም፣ አዲስ አበባ በፕሮጀክታችን ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል የሚያስችላትን ዕድል አግኝታለች፡፡ የአሁኑ ጉብኝት ግን በጥልቀት ቅኝት የሚደረግበት ወይም በእኛ አጠራር ‹‹ዲፕ ዳይቭ›› የምንለው ዓይነት ዓላማ ያለው ተልዕኮ ነው፡፡

በዚህ ተልዕኮ ሳቢያም ላለፉት ቀናት ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጋር ስንነጋገር ቆይተናል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ በአየር ብክለት ላይ የሚመራመሩ ባለሙያዎችና ፋኩልቲዎች አሏቸው፡፡ በመሆኑም ስለአየር ብክለት ምን ያህል መረጃዎች እንዳሉ ለመገንዘብ ሞክረናል፡፡ የከባቢ አየር የጥራት ደረጃን ወይም የብክለቱን መጠን ብቻም ሳይሆን፣ የሕዝብ ቁጥር ዕድገቱ በጊዜ ምን እንደሚመስል፣ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን የተመለከቱ ስታትስቲካዊ መረጃዎችን፣ በትራንስፖርት ባለሥልጣን ዕውቅና ያላቸው የተሽከርካሪዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ፣ የነዳጅ ጥራትንና የመሳሰሉትን መረጃዎች ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሁሉ ለምናካሂደው የአየር ብክለት ትንተና ሥራ ጠቃሚ መረጃ የሚሰጥ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለመቃኘት የሞከርንበትን ጉብኝት አድርገናል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከእርስዎ ጋር አብረው ስለመጡት ባለሙያዎች ቢነግሩን?

ሳራ ቴሪ፡- ከእኔ ጋር አብረው የመጡት አባላት የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የከባቢ አየር የጥራት ደረጃን የሚለኩ ባለሙያዎች የተካተቱበት የፕሮጀክት ቡድን በአዲስ አበባ ጉብኝት አድርጓል፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ናቸው ከዚህ ቀደም በአክራም ሆነ በሳንቲያጎ ከተሞች ለተሠሩት ሥራዎች እገዛ ሲያደርጉ የቆዩት፡፡ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የአየር ጥራት ቁጥጥር ሥራም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ነው የመጡት፡፡ በጋናም ሆነ በቺሊ የአየር ብክለትና ጥራትን ከመለካት ባሻገር፣ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓትና የመረጃ ትንተና ዘዴዎች እንዴት እንደሚተገበሩ ስናግዝ ቆይተናል፡፡ የብክለት መንስዔ የሆኑ ምንጮችን፣ የብክለት ደረጃን፣ የአየር ብክለቱ የኅብረተሰቡን ጤና የሚጎዳበት መጠንና ስፋት፣ እንዲሁም ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ቀርፆ መተግበር ስለሚቻልባቸው መንገዶችም ስንሠራ ቆይተናል፡፡

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ማለትም እ.ኤ.አ. 2019 መጨረሻ ድረስ ከአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር እየሠራን እንቆያለን፡፡ ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ደንና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር የአቅም ግንባታ የምንሰጥባቸው ሥራዎችም ይኖራሉ፡፡ የአካባቢና የአየር ብክለት ምንነትን ከመገንዘብ ጀምሮ የብክለት ምንጮችን በተመለከተ፣ የብክለት መጠንን ለመቀነስ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች መቅረፅን በተመለከተና ሌሎች ከዚህ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን በዕቅድ በመንደፍ ወደ ተግባር መለወጥ ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች እንሠራለን፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ የመጨረሻው ውጤት እንዲሆን የምንፈልገው፣ ብክለትን በመቀነስ በኅብረተሰብ ጤና ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ማስቀረት ነው፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ስለአየር ብክለትና ስለከባቢ አየር የጥራት ደረጃ እናወራለን፡፡ ነገር ግን የዚህ ሁሉ ዋናው መነሻ የኅብረተሰቡ የጤና ጉዳይ ነው፡፡ ብክለቱ በጤና ላይ የሚደርሰው ጉዳት ነው አሳሳቢው ጉዳይ፡፡ የአየር ብክለት እየተባባሰ ሲመጣ የአስም በሽታ መንስዔ ወደ መሆን ያመራል፡፡ ያለ ጊዜው የሚመጣ የሞት አደጋን ያስከትላል፡፡ የመተንፈሻ አካላትና የልብ ሕመምን  ያመጣል፡፡ በእነዚህ በሽታዎች የሚሰቃዩ ሰዎች ከሥራ ገበታቸውም ሆነ ከትምህርት ቤት ለመቅረት ይገደዳሉ፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሕይወታቸውን እስከማጣት  ይደርሳሉ፡፡ ይህ ሁሉ ከግለሰቦቹ ጉዳት ባሻገር የኢኮኖሚ ቀውስ የሚያስከትል ነው፡፡ ይህ ሁሉ በፕሮጀክቱ የሚካተት ሥራ ነው፡፡ በአየር ብክለት ሳቢያ በሕዝቡና በኢኮኖሚው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና መመርመር ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከባለሥልጣናቱም ሆነ ከባለሙያዎቹ ጋር የነበራችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? ጉዳዩን እንዴት ይቀበሉታል? ወይም የአየር ብክለት በሕዝብ ጤና ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት ያላቸው ግንዛቤ እንዴት ይገለጻል?

ሳራ ቴሪ፡- ባለፈው ጊዜ ስንመጣም በጣም በጥሩ ሁኔታ ነው የተቀበሉን፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ የአየር ብክለት ጉዳይ የሰዎችን ትኩረት መሳብ የጀመረው ገና አሁን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሕዝቡ ለፖሊሲ አውጪዎች ስለብክለት ጉዳይ መናገር የጀመረ ይመስለኛል፡፡ አየሩ በጣም ተበክሏል፡፡ በአካባቢው የሚያስላቸው ሰዎች በዝተዋል የሚሉ ሰዎችን እያየን ነው፡፡ ባለፈው ጉብኝቴ ወቅት እንዲህ ያለውን ነገር መስማቴም ጭምር ነው ዳግመኛ ወደ አዲስ አበባ መምጣትና ነገሮችን በጥልቀት ማየት እንደሚገባን የተገነዘብነው፡፡ በአሁኑ ጉብኝታችን ለዚህ ፕሮጀክት የሚያግዙ መረጃዎችን በመስጠት እንዲተባበሩን ሰዎችን ስንጠይቅ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲ ሰዎች በጣም ፍላጎት አላቸው፡፡ ያሉዋቸውን መረጃዎች አካፍለውናል፡፡ ፕሮጀክቱ ባካተተው የአቅም ግንባታ መስክ ደስተኞች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጥያቄዎችንም ጠይቀውናል፡፡ ለአብነት ያህል የብክለት መጠንና ደረጃውን ለመለካት የሚደረጉ ትንታኔዎችን እንዴት እንደምንሠራ ሲጠይቁን ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ያሉትን የብክለት ምንጮች በሚገባ ለመረዳት እንደሚፈልጉና ይህንንም በምን መንገድ መለካት እንደሚቻል ጠይቀውናል፡፡ የፕሮጀክቱ አንዱ ዓላማ እንዲህ ያለውን ግንኙነት መፍጠር ሲሆን፣ የሚታዩትን የዕውቀት ክፍቶች በመገንዘብ እንዴት ክፍተቶችን መሙላት እንደሚቻል፣ እንዲሁም የአየር ብክለት ቁጥጥር የሚደረግበትን አስተዳደራዊ ዕቅድ መንደፍም ፕሮጀክቱ ትኩረት የሚሰጥበት ሥራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ የአየር ብክለትን ደረጃን ከመከታተል በተጨማሪ የሠራችሁት ጥናትና ትንታኔ ይኖር ይሆን?

ሳራ ቴሪ፡- በአዲስ አበባ የሚታየውን የብክለት መጠን የሚለኩ የአየር ብክለት መከታተያዎች መሣሪዎች በአሜሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ፣ እንዲሁም በኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ በመተከላቸው ከእነሱ የሚሰበሰብ መረጃ አለ፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት መረጃ በመሰብሰብ ሒደት ላይ እንገኛለን፡፡ እርግጥ ባለፈው ጊዜ ስንነጋገር እንዳየኸው፣ መረጃዎቹ አዲስ አበባ በመካከለኛ ደረጃ የሚፈረጅ የአየር ብክለት መጠን እንዳላት ያሳያሉ፡፡ የብክለቱ ደረጃ መካከለኛ ነው ማለት ነው፡፡ በዘርፉ የተካሄዱ አካዴሚያዊ ጥናቶችን ለመመልከት ሞክረናል፡፡ የአጭር ጊዜ የአየር ብክለት ክትትል ውጤትን የሚጠቁሙ ጥናቶችን ዓይተናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 የተደረጉና የታተሙ ጥናቶችንም ዓይተናል፡፡ ከሳተላይት የሚገኙ መረጃዎችም አሉ፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን መረጃዎች ባያመላክቱም፣ ብክለቱ ምን እንደሚመስል የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የሳተላይት መረጃዎች ክፍተት አለባቸው፡፡ ከህዋ ወደ ምድር የሚለቀቀው መረጃ ትክክለኛውን የብክለት ደረጃና መጠን ለማመላከት አዳጋች የመረጃ ሥርጭት ያቀርባል፡፡ የሚያሳዩት አመላካች መረጃ የትኛው ቦታ ላይ የብክለቱ መጠን ከፍተኛ እንደሆነ፣ የትኛው ላይ ዝቅ እንደሚል ለይቶ ለማየት ያስቸግራል፡፡

ይሁንና በመላው ዓለም ያለውን የብክለት ደረጃ ግን በሚገባ ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም ከምድር በሚሰበሰብ መረጃ የብክለት ደረጃውን ማጠናቀርና መተንተን ያስፈልጋል፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃ የሳተላይት መረጃዎች አሉ፡፡ ከአሜሪካ ኤምባሲ የሚሰበሰብ የአየር ብክለት አመላካች መረጃዎች አሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ጥናቶችም አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲም የብክለት ደረጃን የሚከታተልባቸው የመቆጣጠሪያ ጣቢዎች አሉ፡፡ በቅርቡም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕምክና ፋኩልቲም የተከላቸው የብክለት መከታተያ መሣሪዎች (ቢም) የሚያመነጯቸው መረጃዎች በሙሉ ለፕሮጀክቱ ግብዓቶች ናቸው፡፡ እነዚህን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የከተማዋን የአየር ብክለትና የጥራት ደረጃ በሚገባ መለካትና መተንተን ይቻላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የኅብረተሰቡ የጤና ሁኔታ ምን ይመስላል? ከሕዝቡ ቁጥር ውስጥ ምን ያህሉ በብክለት ይጠቃል? የሚሉትን ማወቅ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ የሚታዩት የአየር ብክለት ምንጮች ምን ምን እንደሆኑ ለማየት ሞክራችኋል?

ሳራ ቴሪ፡- የተሰበሰቡትን መረጃዎች በመንተራስ ቴክኒካዊ ትንታኔዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከዚህ በመለስ ግን ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊገልጸው የሚችለው የብክለት ምንጭ አለ፡፡ ማንኛውንም ሰው በየመንገዱ ይህንን ጥያቄ ብትጠይቀው ሊነግርህ ይችላል፡፡ ከመኪና የሚወጣው ጭስ በካይ ነው፡፡ አንዳንዴ በየመንገዱ የሚቃጠሉ ነገሮችን ታያለህ፡፡ ቆሻሻ ይቃጠላል፡፡ ከኢንዱስትሪ የሚለቀቁት በካይ ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ ለማወቅ እየሞከርን ነው፡፡ ከአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር በዚሁ በብክለት ላይ የሠሩት ጥናት ስላለ መረጃዎችን እንዲያካፍሉን ጠይቀናል፡፡ የግሪን ሐውስ ጋዝ ወይም የበካይ ጋዝ ልቀትን በተመለከተ የተሠራ ጥናት አለ፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችና ሌሎችም የሚለቋቸው በካይ ንጥረ ነገሮች ምን ያህል እንደሆኑ የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ፡፡ በመረጃ ማሰባሰብ ሒደት ወቅት እንዲህ ያሉት ጥናቶችን ማየት እንፈልጋለን፡፡

በአዲስ አበባ ስንዘዋወር በርካታ የከሰል መሸጫዎችን ለማየት ችለናል፡፡ ለቤት ውስጥ ማብሰያነት እንደሚውል ተገንዝበናል፡፡ ከሰሉ ሲቃጠል የሚያመነጨው በካይ ጋዝ ለአየር ብክለት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች የሚለቁት በካይ ነገር ምን ያህል ድርሻ እንዳለው በግልጽ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ ከተቋማቱ የሚለቀቀው በካይ ነገር እንዴት እንደሚጓዝና ወደ ከባቢ አየር እንደሚቀላቀል በግልጽ ለይቶ ማስቀመጥም  ይከብዳል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ያሉ የብክለት ምንጮች እንዳሉም ግንዛቤው አለን፡፡ በርካታ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ከከተማዋ ውጪ የሚገኙ በመሆናቸው፣ ወደ ከተማዋ በካይ ጋዞችና ሌሎችም የብክለት መንስዔ የሆኑ ነገሮች እንደሚገቡ ለመረዳት አይከብድም፡፡ ይህ ሁሉ እንዴት እንደሚዛመድና በከተማዋ ብክለትን እንደሚያባብስ ለመረዳት በርካታ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ ሆኖም መኪኖች፣ ቤት ውስጥ ለማብሰያ የምንገለገልባቸው የኃይል ምንጮች፣ በየመንገዱ የሚቃጠለው ነገር፣ ከየቤቱ የሚጣለው ቆሻሻና የኢንዱስትሪ ምንጮች ለብክለት መንስዔ መሆናቸው በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ እንደሰማነው በከተማው ትልቅ የቆሻሻ መጣያ ቦታ ላይ ከፍተኛ ቆሻሻ የማቃጠል ልማድ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ከከተማዋ ኃላፊዎች ጋር ስለአየር ብክለት በምትነጋገሩበት ወቅት የጤና ጠንቅ ስለመሆኑ ጉዳይ ያላቸው ግንዛቤ ምን ያህል ሆኖ አገኛችሁት? ምን ያህል ትኩረት ይሰጡታል?

ሳራ ቴሪ፡- በእርግጥ በብክለትና በኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ረገድ ያለውን ቀጥተኛ ግንኙነት ይገነዘባሉ፡፡ በፕሮጀክቱ ምክንያት የምናመጣቸው የቴክኒክ ጉዳዮች አሉ፡፡ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅና የአየር ብክለት ያላቸውን ግንኙነት ለማመላከት በአሜሪካ የምንጠቀምባቸው ዜዴዎች አሉ፡፡ እነዚህን እዚህ በማምጣትና የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲሁም የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ባለሙያዎችን በእነዚህ ዘዴዎች አተገባበር ላይ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ በዩኒቨርሲቲ ደረጃም በርካታ ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች ስላሉ ሥልጠናውን መስጠታችን የግድ ነው፡፡ በፕሮጀክቱ የሚካተቱት የአየር ብክለት ደረጃ መለኪያ ዘዴዎች የከባቢ አየር ጥራትን ለመለወጥ የሚያግዙ ናቸው፡፡ በብክለትና በጤና ረገድ ያሉ ግንኙነቶችን ለመረዳት የሚያስችሉ ሥልቶች አሉ፡፡ በሁለቱ መካከል ያሉትን ግንኙነቶችንና በአየር ብክለት ላይ ለውጥ ስለመታየቱ የሚጠቁሙ የሶፍትዌር ፕሮግራሞች ስላሉ ለውጦቹ በሕዝብ ጤና ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ብቻም ሳይሆን፣ የሚያስከትሉትን ወጪም መተንተን የሚቻልባቸው ስልቶች ሁሉ በፕሮጀክቱ ተካተዋል፡፡

ማኅበረሰቡ በብክለት ሳቢያ ጤናው ላይ በሚደርስበት እክል ምክንያት ምን ያህል ጫና አለበት የሚለውን ማወቅ የሚቻልባቸው መንገዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ የአስም በሽታ ያለበት ሰው ሆስፒታል ሄዶ ለመታየት ምን ያህል ወጪ ያወጣል? ብለን እንጠይቅ፡፡ ምናልባት ሐኪም ዘንድ ሔዶ ለመታየት 100 ብር ያስፈልገዋል እንበል፡፡ አሁን ባለው የብክለት ደረጃ ምናልባት 100 ሺሕ ሰዎች ወደ ሆስፒታል ይሄዳሉ ብለን ብናስብ፣ ለአንድ ጊዜ የሐኪም ጉብኝት ብቻ አሥር ሚሊዮን ብር ያህል ለማውጣት እንደሚገደዱ ማየት እንችላለን፡፡ የብክለት ጉዳትን በዚህ ቀላል መንገድ ልንገዘነበው እንችላለን፡፡ እንዲህ ያሉ ዘዴዎችን በመከተል ትንታኔዎችን በሳይንሳዊ መንገድ ማውጣት የሚቻልባቸው ዘዴዎች ናቸው የመጡት፡፡

ሰዎች ብክለትን ለመቀነስ የሚረዱ ወጪዎችን ማውጣት አይፈልጉም፡፡ ለምሳሌ መኪናቸውን በየጊዜው በማስፈተሽ፣ ማስተካከል የሚገባቸውን ለማስተካከል የሚጠይቃቸውን ወጪ የሚሸሹ በርካቶች ናቸው፡፡ ይሁንና በዚህ ምክንያት በጤናቸው መጓደል ሳቢያ ከፍተኛ ወጪ ለማውጣት ይገደዳሉ፡፡ የራሳቸውም ሆነ የልጆቻቸው ጤና ሲታወክ ማየት አይፈልጉም፡፡ ግን ይህንን ሊቀንስ በሚችል ነገር ላይ ወጪ ማውጣትንም አይፈልጉም፡፡ ሌላኛው የዚህ ፕሮጀክት ቁልፍ አካል የኮሙዩኒኬሽን ይዘቱ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ፣ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንና ሌሎችም የኅብረተሰቡ ጤና በብክለት ሳቢያ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንደሚያድርበት ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ፕሮግራሞችን በመተግበር ሰዎች ብክለትን በመከላከል በጤናቸው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ ስለሚችሉባቸው መንገዶች የሚያስረዱ ሥራዎችን ማከናወን እንፈልጋለን፡፡  

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የአየር ብክለት ደረጃ መካከለኛ ነው ተብሏል፡፡ አሁን ባለበት ደረጃ ምን መሻሻል ሳይደረግ ቢቆይ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ሊያጋጥም የሚችለው የብክለት መጠን ምን ያህል የከፋ ሊሆን ይችላል?

ሳራ ቴሪ፡- ቁልፉ ነገር አሁን ባለበት ደረጃ ብክለቱ እንደማይቀጥል መገንዘቡ ነው፡፡ አፍሪካ በፍጥነት ወደ ከተሜነት እየተቀረየች ነው፡፡ ኢትዮጵያም እንደዚሁ፡፡ በርካቶች ወደ ከተማ እየጎረፉ ነው፡፡ በመሆኑም ባለበት የሚቆይ ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡ ፈተናውም ይኸው ነው፡፡ ሰዎች እየበዙ፣ መኪኖች እየተበራከቱ፣ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ በመጡ ቁጥር የብክለት መጠኑም እየጨመረ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ የልማት ሥራዎች እየተስፋፉ በመጡ ቁጥር የብክለት ምንጮችም ይበራከታሉ፡፡ ብክለቱ እየበዛ ይመጣል፡፡ ይህንን በበርካታ የእስያ አገሮች ዓይተናል፡፡ የሰዎች የኑሮ ደረጃ እየተሻሻለ ሲመጣ ፍላጎታቸውም እየጨመረ ይመጣል፡፡ በሕዝብ መጓጓዣ ሲጠቀም የነበረው ሰው የራሱን መኪና ማሽከርከር ይጀምራል፡፡ ለየአየር ብክለቱ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮች እየተበራከቱ በመጡ ቁጥር ይህንን ለመቀነስ የሚያግዝ ዕርምጃ ካልተወሰደ በቀር፣ የሰዎችን ጤና ብቻም ሳይሆን የገነቡትን ኢኮኖሚ ጭምር ማቃወሱ አይቀሬ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለው ተፅዕኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያጋጥም እንደሚችል ይታሰባል ማለት ነው?

ሳራ ቴሪ፡- ይህንን ለመናገር ይከብዳል፡፡ መረጃውን ወደ መተንተኑና ሊደርስ ስለሚችለው ጉዳት ገና አላጠናንም፡፡ ሆኖም ለምሳሌ እንደ የውኃ ኃይል ማመንጫ ያሉ ግድቦች ከአየር ብክለት ተፅዕኖ ነፃ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ በከሰል ድንጋይ የሚንቀሳቀሱ ኃይል ማመንጫዎች ግን ከፍተኛ ብክለት ያመነጫሉ፡፡ ከብክለት ነፃ የሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እየተገነቡ ነው፡፡ በዚህ አገር ለአረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማት ትኩረት እንደሚሰጥ እንገነዘባለን፡፡ ይህ ሁሉ ከአየር ንብረት አኳያ የሚያስገኘው ሰፊ ጥቅም አለ፡፡ 

ሪፖርተር፡- በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ስለሚተገበረው ፕሮጀክት ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባ ሦስተኛዋ ከተማ እንድትሆን ተወስኗል ማለት ነው?

ሳራ ቴሪ፡- ፕሮጀክቱ ‹‹ሜጋሲቲ ፓርትነርሺፕ›› የሚል ስያሜ ያለው ነው፡፡ አዲስ አበባ ከአክራ እንዲሁም ከሳንቲያጎ በመከተል ሦስተኛዋ የፕሮጀክቱ አካል እንድትሆን ተወስኗል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ጉብኝትዎ በኋላ የሚሠሩት ምንድነው?

ሳራ ቴሪ፡- የአሁኑ መረጃ ማሰባሰብ ላይ ያተኮረ ጉብኝት ነው፡፡ በፕሮጀክቱ ከሚሳተፉ አካላት ጋር አጋርነትን በመፍጠር ለፕሮጀክቱ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን የማካተት ሥራ ነበር፡፡ ከዚህ በማስከተል የሚሠራው መረጃዎቹን በማጠናቀር ወደ መተንተኑ እንገባለን ማለት ነው፡፡ መረጃዎቹ ስለብክለት ምንጮችና ዓይነቶች ምንነት የሚሰጡንን ውጤት እንገመግማለን፡፡ የአየሩን የጥራት ደረጃ፣ በኅብረተሰቡ ላይ ስላለው የጤና እክልና በዚህም ሳቢያ ስለሚያጋጥመው ጫና ጥናቶች ይካሄዳሉ፡፡ ሆኖም እነዚህን ጥያቄዎች እኛ ሳንሆን የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የሚመልሳቸው ናቸው፡፡ የእኛ ሥራ እነዚህ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ ሥልቶችንና ዘዴዎችን ማስታወቁ ላይ የሚያመዝን ነው፡፡ የአየር ብክለት ደረጃን ለመለካትና ለማስተዳደር የሚያስችለውን ዕቅድ እንዲያወጡም እናግዛቸዋለን፡፡ ፖሊሲዎችን ማመንጨት የሚችሉባቸውን መንገዶች እናመላክታቸዋለን ማለት ነው፡፡ በጥናት የታገዙ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለማሳየት እንጥራለን፡፡ የትኞቹን ፖሊሲዎችና ዕርምጃዎች መተግበር እንዳለባቸው የሚወስኑት እነሱ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡