Skip to main content
x

መመርያ የሚጥሱ የግል ጤና ትምህርት ተቋማት ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የግል የጤና ትምህርት ተቋማት ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ በመደበኛው የቀን ፕሮግራም ብቻ እንዲሰጡ መመርያ ቢያስተላለፍም፣ በርካታ የግል የጤና ትምህርት ተቋማት መመርያውን እየጣሱ እንደሆነ ተገለጸ፡፡ በዚህም ምክንያት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሞታ ሰኞ ግንቦት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ተፈርሞ የወጣ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ መመርያውን የጣሱ በርካታ የግል የጤና ትምህርት ተቋማት በማታ ክፍለ ጊዜ ተማሪዎችን መዝግበው አሁንም እያስተማሩ ናቸው፡፡

በሕገወጥ መንገድ የተማሩ ሦስት ሺሕ የጤና ባለሙያዎች ዕውቅና አግኝተዋል

በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በማታው ክፍለ ጊዜ የጤና ዘርፍ ትምህርቶች እንዳይሰጡ በሕግ ከተከለከለ ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ አሁንም ከመንግሥት ዕውቅና ውጪ ለተማሪዎች አግባብ ባልሆነ መንገድ እየተሰጡ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ብቻ ሦስት ሺሕ ያህል ተማሪዎች በዋናነት በማኅበረሰብ ጤና፣ በነርሲንግ፣ በፋርማሲ፣ በአዋላጅነትና በጥርስ ሕክምና በማታው ክፍለ ጊዜ ተምረው ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መመረቃቸው ታውቋል፡፡ ከምረቃቸውም በኋላም ሕግ መጣሱ እየታወቀ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡