Skip to main content
x

ይበል የሚያሰኘው የአየር መንገዱ ዘመናይነት

እንደ ብሔራዊ ኩራት ከምንጠቅሳቸው አገር በቀል ኩባንያዎች ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀድመን እናነሳለን፡፡ ከ75 ዓመታት በላይ በበጎ አገልግሎቱ ስሙ የሚነሳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከአገር ውስጥ አልፎ በአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪው የአፍሪካ ግንባር ቀደም ለመሆን በቅቷል፡፡ በየጊዜው አዳዲስ አሠራሮችን እያስተዋወቀ በተወዳዳሪነት የዘለቀው አየር መንገዱ፣ በኢንዱስትሪው ትልቃ ስም በማትረፍ በዓለም የሚጠቀስ ተቋም ለመሆን በቅቷል፡፡ በየጊዜው የሚያገኛቸው ሽልማቶችም ለዚህ ምስክር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የቱሪዝም ዘርፉ አኃዞች

በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲኖራቸው ከሚፈለጉ ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ነው፡፡ ዘርፉ እንዲኖረው የሚፈለገው ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንዲሆን ስለተፈለገ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት ለየት ያለ አካሄድ መከተል ጀምሯል፡፡ ይኸውም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራና በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰበሰብ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የሚባል ተቋም ተመሥርቷል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ፣ ዘርፉ በቀጥታም በተጓዳኝም የሚመለከታቸው አገሪቱ ባለሥልጣናት፣ የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ የየክልሉ የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊዎች በምክር ቤቱ አባል ሆነው በየስድስት ወራት እየተገናኙ ይመክሩበታል፡፡