Skip to main content
x

ክቡር ሚኒስትር ጡረታ ከወጡ ሌላ ሚኒስትር ጋር ተገናኙ

የቀድሞ ሚኒስትር ጓደኞቼ ፖስታ ተላላኪ ሆነው ሳይ በጣም ነው የማዝነው፡፡ ሞኝ ነህ እንዴ አንተ? እንዴት ክቡር ሚኒስትር? እነዚህ ሰዎች እኮ በጎን የራሳቸውን ሥራ ስለሚሠሩ በጣም ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የምን ጥቅም ነው? ይኼው ከአገር መውጣት አስቸጋሪ በሆነበት በዚህ ወቅት ፖስታውን እያመላለሱ በጎን የራሳቸውን ሥራ ይሠራሉ፡፡ እኔ ግን ብዙም አልታየኝም፡፡ እኛ እኮ በቅርቡ በሚደረገው የመዋቅር ለውጥ የቀድሞ ሚኒስትሮች የሚታቀፉበት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንዲቋቋም እየገፋፋን ነው፡፡ ምን የሚሉት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት? ተላላኪ ሚኒስቴር!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ እስራት ፈርቶ የተደበቀ ጓደኛቸው ደወለላቸው

ኧረ እኔ የትም መንቀሳቀስ አልችልም፡፡ ራስህን የቁም እስረኛ አድርገሃል ማለት ነው? ምን አማራጭ አለኝ? አማራጩማ መደመር ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትር እኔ ምን እንደሚጠብቀኝ አውቀዋለሁ፡፡ ምንድን ነው የሚጠብቅህ? በቅርቡ ሙዚየም የሆነ ቦታ ነዋ፡፡ የት ነው? ማዕከላዊ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው እያወሩ ነው

- ክቡር ሚኒስትር ጋዜጠኞቹ ተጠርተዋል፡፡ - የምን ጋዜጠኞች? - ባለፈው የምንሠራቸውን ሥራዎች ማሳወቅ ስላለብን ፕሬስ ኮንፈረንስ ይጠራ ብለውኝ ነበር፡፡ - ታዲያ ሳታማክረኝ ነው የምትጠራቸው? - እኔማ አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው ብዬ አስቤ ነበር፡፡ - እንዴት? - ያው ከተሾሙ መቶ ቀናት ስለሞላዎት በዚህ ጊዜ ያከናወኗቸውን ነገሮችን ነዋ ጋዜጠኞቹ የሚጠይቁዎት፡፡ - በእነዚህ በመቶ ቀናትማ ፍቅር፣ መደመርና ይቅርታ ላይ ነዋ የሠራነው፡፡ - እሱ ላይ ታዲያ እርስዎ ምን ሠርተዋል? - እንደምታውቀው የሻይ ቤታችን ሠራተኛና ጥበቃችን ለረዥም ዓመት ተኮራርፈው፣ እኔ ነኝ መካከላቸው ገብቼ ያስታረቅኳቸው፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

አሜሪካ ታዲያ ለምን መሄድ ፈለጉ? መደመሬን በተግባር ለማሳየት አልኩህ እኮ፡፡ አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር? ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላችሁን ዶላር አምጡ አላሉም? አዎን ብለዋል፡፡ ስለዚህ የእሳቸውን ጥሪ ተቀብዬ መደመር ፈልጌ ነው፡፡ ምን እያሉ ነው? አሜሪካ መሄድ የምፈልገው ለዚሁ ነው፡፡ ለምኑ? ላመጣው ነዋ፡፡ ምኑን? ዶላሩን!

ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

ቤታችሁ ያለውን ገንዘብ አውጥታችሁ ባንክ አስቀምጡ እየተባልን ነው፡፡ - ባናስቀምጥስ ምን ሊያደርጉን ነው? - ኦፕሬሽን እንጀምራለን ብለዋል፡፡ - የምን ኦፕሬሽን ነው? - ያው እንግዲህ የቤት ለቤት አሰሳ ሊጀምሩ ይሆናላ፡፡ - ካሰሳው በኋላ ምን ሊያደርጉ? - ካገኙማ ይወርሱናል፣ በዚያ ላይ ሌላ መዘዝ ሊኖረው ይችላል፡፡ - ታዲያ አንተ ምን አሳሰበህ? - እንዴ ክቡር ሚኒስትር ከመንግሥት ኦፕሬሽን በፊት ብሩን ባንክ እንዲያስገቡት ነዋ? - እኔማ ሰሞኑን ይኼንኑ መግለጫ ሰምቼ ብሩን ወደ ሌላ ቦታ ለማሸሽ አስቤ ነበር፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ብቻ በመንግሥት ኦፕሬሽን ጉድ እንዳይሆኑ፡፡ - ከመንግሥት ኦፕሬሽ በፊት በሌላ ኦፕሬሽን ጉድ ተሠርቻለሁ፡፡ - በምን ኦፕሬሽን? በአይጥ ኦፕሬሽን!

ለክቡር ሚኒስትሩ ደላላ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

- ሁለቱ አገሮች ሰላም ከሆኑ እኮ አዳዲስ ቢዝነሶች አቆጠቆጡ ማለት ነው፡፡ - የምን አዳዲስ ቢዝነስ? - ክቡር ሚኒስትር ኢትዮጵያን በ11 በመቶ ስናሳድጋት ምን ያህል እንደተጠቀምን ያውቃሉ አይደል? - እሱማ ልክ ነህ፡፡ - ኤርትራንም በዚሁ ፍጥነት አሳድገን የድርሻችንን መጠቀም አለብን፡፡ - እኔ የኤርትራ ማደግ መቼ አስጨነቀኝ አልኩህ? - ክቡር ሚኒስትር የኤርትራ ዕድገት ያስጨንቅዎታል ብዬ ሳይሆን የእርስዎን ጥቅም አስቤ ነው፡፡ - የእኔ ጥቅም ምንድነው? - እርስዎ እንደ ምንም ብለው የኢትዮጵያ ገንዘብ ኤርትራ ውስጥ እንዲሠራ ያስደርጉ፡፡ - ለምን ተብሎ? - እዚህ በጥሬው የያዝነውን ገንዘብ እዚያ ይዘን ሄደን መሥራት እንችልበታለና፡፡ - እንዴት? እንዴት? - አዩ ቤት ያለው ገንዘባችን ሕገወጥ ነው ሊባል ስለሚችል፣ ኤርትራ ወስደነው ኢንቨስት ልናደርገው እንችላለን፡፡ - ለሚስቴ ጭንቀት መፍትሔ ተገለኘት ነው የምትለኝ? - ክቡር ሚኒትር ቆሻሻው ብራችን እዚያ ታጥቦ ይነፃል፡፡ - የት? - ቀይ ባህር!

የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር አርፍዶ ቤታቸው መጣ

አንጋፋዎቹ እኮ ከውድድሩ የተባረሩት አዳዲሶቹ ላቅ ያለ የእግር ኳስ ችሎ ስላላቸው ነው፡፡ እንዳይመስልህ አትሳሳት፡፡ ታዲያ በምንድን ነው አንጋፋዎቹ የተባረሩት? በአሻጥር፡፡ ክቡር ሚኒስትር ስመለከትዎ እርስዎ ከሚያውቁት ውጪ የሆነ ነገር አይወዱም፡፡ ምን እያልከኝ ነው? ይኸው በአገሪቱ ውስጥ የመጣውን ለውጥ ራሱ መቀበል አይፈልጉም፡፡ አንጋፋዎቹ የሌሉበትን ለውጥ አልቀበለውም፡፡ እንደዚያ ከሆነ የእኔ ምክር አንድ ነው፡፡ ምንድነው ምክርህ? በጊዜ ቢቆርጡ ይሻልዎታል፡፡ ምንድነው የምቆርጠው? ትኬት ነዋ፡፡ የምን ትኬት? የስንብት!

ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው

እሺ ሁሉም ይቅርና እኔን ክብር ያለኝን ሰው አይጥ ብሎ ማዋረድ አይከብድም? - እሱንም እኮ ያገኘኸው በይቅርታ ነው፡፡ - የምን ይቅርታ? - ከጅብነት ወደ አይጥነት የተደረገልህ በይቅርታ መርህ ነው፡፡ - አንቺ ራሱ የምታወሪውን አታውቂም፡፡ - ለማንኛውም እኔንም አንድ የአይጥና የድመት ፊልምን አስታወስከኝ፡፡ - የምን ፊልም? - ፊልሙ ላይ አይጧ ልክ እንደ አንተ ሌባ፣ አጥፊ፣ ተንኮለኛና ሴረኛ ነች፡፡ - ምንድነው የምታወራው? - ስለዚህ እኔም ከዚህ በኋላ አዲስ የቤት ስም አውጥቼልሃለሁ፡፡ - ማን ልትይኝ? - ጄሪ!

ለክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ ከእስር የተፈታ ደላላ ይደውልላቸዋል

ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ብቻዬን ፋብሪካ የዋጥኩ ሰው ነኝ፡፡ - እሱስ ልክ ብለሃል፡፡ - ይኸው አሁን የዋጥኩትን ፋብሪካ እዚሁ አገሬ ላይ እተፋዋለሁ ብዬ ተነቃቅቼ ሳበቃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውኃ ቸለሱብኝ፡፡ - ስማ ዋናው ነገር አንድና አንድ ነው፡፡ - ምንድነው ክቡር ሚኒስትር? - ይህች አገር እንድትለማ ትፈልጋለህ? - ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር? - ማለት? - ይኸው የዋጥሁትን ፋብሪካ ለመትፋት ተዘጋጅቼያለሁ ስልዎት? - በቃ ለልማቱ ይኼን ያህል ተነሳሽነት ካለህ ችግር የለውም፡፡ - እንዴት ማለት ክቡር ሚኒስትር? - አንተ በልማቱ የምትሳተፍበትን ቦታ እኔ አመቻችልሃለሁ፡፡ - የማለማው ቦታ ያገኙልኛል? - በሚገባ፡፡ - የትኛውን ቦታ እንዳለማ ፈልገው ነው? - ማረሚያ ቤቱን!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

- ስማ እንኳን ኢትዮጵያ ዓለም ላይም ስለተነሳ አውሎ ንፋስ ምንም አልሰማሁም፡፡ - ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶዎታል ልበል? - የምን እንቅልፍ? - አውሎ ንፋሱ ያስነሳው ጎርፍ ሲወስድዎት ያኔ ይነቃሉ፡፡ - ሰውዬ የምታወራው ነገር ግራ እያጋባኝ ነው፡፡ - ምን ሆነዋል ክቡር ሚኒስትር? - ምን ሆንኩ? - አገሪቱ ውስጥ የሚነፍሰው የለውጥ አውሎ ንፋስ እየተሰማዎት አይደለም? - እሱን ነው እንዴ የምትለው? - ክቡር ሚኒስትር ፕሮጀክቶቻችን እኮ መና ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ - እንዴት ሆኖ? - ይኸው ለውጡ ብዙ ነገሮችን እየቀያየረ ነው፡፡ - ታዲያ እኛ ምን አገባን? - ክቡር ሚኒስትር ነገሮች እንደ ድሮው ላይቀጥሉ ይችላሉ፡፡ - የምትለው አልገባኝም? - ከፍተኛ ኮሚሽን የምናገኝባቸው ፕሮጀክቶች ላይሳኩ ይችላሉ፡፡ - ለምን ተብሎ? - ይኸው የእኛ ወሳኝ ሰዎች እኮ እየተፐወዙ ነው፡፡ - እ. . . - የውጭ ወዳጆቻችንም ደውለው ግራ ተጋብተናል እያሉኝ ነበር፡፡ - ምንም ሥጋት አይግባችሁ በላቸው፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ሁኔታውማ በጣም አሥጊ ነው፡፡ - እንዴት ሆኖ? - አለቃችሁ እኮ እየተጫወተባችሁ ነው፡፡ - ምን? - ቀዩን ያዬ!